ሲራክ ወንድሙ
ማሳሰቢያ
አምላክ በቸርነቱ አኑሮን እስካሁን አድዋን በደመቀ ሁኔታ ስናከብር ኖርን። እኔም እስካሁን በእግዜር ቸርነት ስፅፍ እናንተም ስታነቡ ቆየን ከእንግዲህ ብሞትም ሞት ነውና ልሙት አልልም። መች በላሁ አንባቢ ሆይ ? ደግሞም እግዜር አሳፍሮኝ አያውቅም። ወደ ፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁን ግን ልብ የሚያፀና .. አድዋ አድዋ የሚሸት ፅሁፍ እነሆ በፊትህ ቀርቧል። እኔም የሰውን መሰላቸት አይቼ እንዳላየሁ ባልፍም ብሶበት ፅሁፌን መዝለል ጀምሯል። አሁን ግን በእግዜሩ ቸርነት እጄን አጣጥፌ መቀመጥ አልሆነልኝም።
አንባቢ ሆይ ከአሁን ቀደም እንዲህ አስፈራርቼህ አላውቅም። አንተም አላስፈራራኸኝም። እጄን ልቤን ሳትል ይህቺን ፅሁፍ ታግሰህ አንብብ። ወስልተህ ካለፍካት ግን ትጣላኛለህ። አልምርህም። መሽኛሽ ወርቅ ትሙት ለዚህ አማላጅ የለኝም።
….. በስተመጨረሻም
« አውድማው ይለቅለቅ በሮችም አይራቁ
ቀድሞም ያልሆነ ነው ውትፍትፍ ነው እርቁ¹[1] »ተባለ።

የቁርጥ ቀን ደርሶ..የነፃው ደፍርሶ የውረድ እንውረድ ቅኝቱ ፀናና የማርያምን መሀላ በውስጡ ያነገሰ የንጉስ ክተት ቃል – በአዋጅ ሀገሩን ናኘ።
ጠይም ጦረኞች ፈረሳቸው ላይ በሞገስ እንደተቀመጡ … ጦራቸውን እንዳነገቡ ዱር ጥሻውን ጥሰው በቃላቸው ተገኙ።
አዝማሪ ግጥም ባር ባር እያለው የዜማን ገሳ አልብሶ አበረታለሁ ሲል ማለደ። ድል ሲረገዝ መሸ። ታሪክ ሊፃፍ ቀን ተወለደ።
ነጭ ሸማ የለበሰ ሰራዊት በግራ ንጉሱን በቀኙ ታቦቱን እንዳጀበ በድባብ ደምቆ እንዳቆበቆበ አድዋ ሜዳ ዘመተ።
ጎራዴዎች ሰገባቸውን ጠልተው መመዘዝ ፈለጉ… የናስ ማስር የጠበንጃ ፈሙዞች ሞት እንዳረገዙ ሁላ ቃተቱ። ባንዲራ በሰማይ ንጉስ ከነ ህዝቡ ፤ ከነታቦቱ በመሬት ረጋ።
በቀረርቶ ፉከራና መዝሙር እምቢኝ ሲል የኢትዮጵያ ልጅ በደገሰው ጦርነት ላይ ታደመ። ጎራዴ ከሰገባው ሞት ከአፈሙዝ ሾልከው ወጡ። ነጭ የለበሰው ካለበሰው ጎራ ተቀላቀለ። በረድፍ የተበጀው ሰልፍ ጉራማይሌ ለበሰ። አድዋ ደጇ ጉም መሰለ። ሰማየ ሰማያት የሚደርስ የሚመስል አቧራ እንደማሂጠንት አጥኖ ቀሚሷን እየያዘ ሽቅብ ወደላይ ዳኘ። መድፍ አጓራ… ጎራዴ አፏጨ .. ጠመንጃ እንደጅራፍ ተንጣጣ። ዋይታ ነግሶ ጩኸት በረከተ። ዛፍ ላይ የሰፈሩ ወፍና አሞሮች ጆሯቸውን ይዘው ጠፉ። ሰዓታት ፈጀ።
« ከምን ይልክ ጋራ አብሮ ሲቀድሱ
ምን ይልክ በጦሩ እርሱ በፈረሱ
ጣሊያንን ባረኩት ደም እያፈሰሱ²[2] »
ለዓይን የጋረደው የአቧራ ጭጋግ ከአየሩ ላይ እየሳሳ ሲመጣ ከጉራማይሌው ቀለም ላይ ሲከላወስ የነበረው ግፊያ እየተገታ – ተንቀሳቃሹ አካል በአንድ ወደ መቆም አዘነበለ። ነጩ ሸማ አፈር ቃመ.. በደም ተለውሶ ደከረተ።
ከወደቀው የጠላት አካል ውጪ ያልሸሸ አልነበረም…..
የአሸናፊነት መዲና ባነቀው ዝየራ በሬሳ መሀል ተራምዶ ፎከረ የድሉ ቀን ናትና ነብሱ አርያም እስክትደርስ በደስታ ተሞልቶ ሸማው በነጭ ላቡ እስኪርስ አክላላ።
በማለዳው የኪዳን ቅዳሴው መሀል ከተራሮች መሀል ብቅ ያለችው ጀምበር። አድዋን በድል ሞሽራ ልጠልቅ አቆበቆበች።
የግጥም ዶፍ ዘነበ.. የቀረርቶ መዓት አካፋ…ሄደው የነበሩ አሞሮች መጡ። የአድዋን ሜዳ ሞልተው አንዣበቡ። ነጭ የአሞራ መንጋ የመላዕክት ስብስብ ይመስል አድማሱን ሰንጥቆ ቀረበ።
የአንድ ዘመን ገድል እንዲህ ሆነ።
የጥቁር ደም አምበኞች ተሰብስበው በደማቸው ቀለም አጥንታቸውን ብዕር አድርገው ታላቅ ድርሳን ፃፉ። ልትጠያይም የነበረች ሰማያቸውን በድል ፀሀይ ሞሽረው ቤታቸው ገቡ። ሚስት በባል ጀግንነት ፤ ልጅ በአባቱ ገድል ልቡን ሞልቶ ነገን ናፈቀ።
የብርሃን ልጆች በህብረት ባፀኑት የአንድነት መዝሙር ቀየው ደመቀ አምባው በፍስሃ ሞላ።
ስንቅ የቋጠሩ እጆች … ጦር ጨበጠው ደም የለበሱ … ጠላት አውድመው የተመለሱ ተስፈኛ እግሮች….. የድል ፀሀይ ልቦች …. የሀበሻነት ሞገሳቸውን በፈረስ ላይ ሰቅለው ሰማይ ሲያስጨንቁ ምድርን ቁና አልብሰው ዋሉ።
የጠሪን ትዕዛዝ በአክብሮት የተቀበለ ባለሀገር በደም ፍላት ወደ መጨረሻዋ ሰዓት ወረደ። ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ተማገደ። ማገደም። ፍፃሜው ለየቅል ቢሆንም ነብሱን ለእምነቱ የሰዋ… ግምባሩን በአምላኩ ፊት እንደደፋ ቀና ሲል ከፀሀዩ ታረቀ። በለው ሲል ለፀሎት … ድገም ሲል ለተኩስ ተንበርክኮ ሀገሩን ከሽንፈት አዳናት።
ዓለም እጁን በአፉ እስኪጭን መሀይም የተባለው አፍሪካዊ ፤ ምሁር ነኝ ባዩን አውሮፓዊ ድል ነሳው።
የደም ፀሀይ ባረገዘች የአፍሪካ ሰማይ ስርና በአድዋ መሬት ላይ ተዓምር ከነብር ፈጥኖ ብቅ አለ።የመቻል ወኔ ያስተባበረው ክንድ ሊያውም ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ የቆመን የሰለጠነ ወታደር – ጥሪ ይዞ ቀምበር ፈትቶ.. ሚስቱን ትቶ …በመጣ ባላገር ፤ ታሪክ ሚዛኑን አጋደለ።
ምድር በአባቶች ግዝት ሰማይ በማሪያም መቀነት ታሰረች።
አልቅሰው የሸኙ እናቶች ልባቸው በፍርሃት ተተብትቦ ዝም ያሉ አፎች ለሙሾ ሲዘጋጁ በእልልታ ተበለጡ።
ተማፅኖ ልኮ ያልረጋ ዓይናቸውን ሽቅብ ወደ ጠፈር አሻቅበው ልከው እምባ አቀረሩ። ደረት ሊመቱ የተዘጋጁ እጆች ወደ ሰማይ ከፍ ብለው በምስጋና ቆሙ።
አርያም በሚሰማ የደስታ ሳቅ ቀየው ሰፈሩ ገነነ። በአንፃሩ ትውልድ አመድ ጨብጦ ከመሞት ዳነ።³[3]
ደጀንነት አንዲት ሀገርን ከዘመን ሞት ሊታደጋት ትንፋሹን እፍ ብሎ አነቃት። በቀኙ አቁሞ ዘወራት።
ግጥም በነፋስ ብራና ላይ ተገጠመ። አባት ልጅ አርበኞች በውዳሴ ሆታ ውስጥ ተመሙ።
( ሳቅ ያን እለት አለቀሰ። )
ዜማ ተደርሶ እንጉርጉሮው ቀለጠ። ከሳር ቅጠሉ… ከአህያ ፈረሱ…. ከፊታውራሪ እስከ ባልደራሱ ምስጋና ዘነበ።
( እምባ ሊስቅ መሸበት )
ጣዲቄን አስታወስኩ። እምዬን አስታወስኩ። ጠሀይቱን አስታወስኩ።
( ሞት አቀርቅሮ ሲሄድ አየውት። )
የሰው ሰሞን ናፍቆቴ ጠናብኝ።
ያቺ እለት ፥ ያቺ ቀን የአፍሪካዊ የመቻል ብስራት ዜናው ሆነች።
ሞኝ መስሎ ቢተኛ አላዋቂነቱን ተመርኩዘው ጎራዴያቸውን መዘው መጡበት። የእብሪት ታሪካቸው ሲደመደም በመዘዙት ጎራዴ ወድቀው በአድዋ ሜዳ የአሞራ ሲሳይ ሆኑ።
ባልቻን አስታወስኩ። ሀብተጊዮርጊስ ትዝ አለኝ።
ሉአላዊነትን ማስከበር በየትኛውም መነፅር ራስ ወዳድ አድርጎ አያውቅም።
የሰው ልጅ በጀግንነትና በፍቅር ታንፆ የተፈጠረ ፍጡር ነው።
በፍቅሩ ሰማይ ላይ የጥላቻ ደመና ቢያጠላም በጀግንነት ቀጠናው ላይ ግን የፍርሃት መረዋ አስተጋብቶ አያውቅም።
እንደሁሌው…
.. አድዋ ግዝቶቻችንን መሻሪያ ህያው ቃላችን ነው። በማንነት አንገታችን ላይ አንጠልጥለን በልበ ሙሉነት ቀና የምንልበት ሰንደቅ!
የአለመገዛት ያለመንበርከክና እጅ ያለ መስጠት ብቻ ሳይሆን ያልተቻለን የመቻል የፍጥረትን አብዮት የቀሰቀሰ የአንድ ዘመን ክስተት ነው።
ትውልድ ልክ እንደዶሮ ፊቱ የተበተነውን እየጫረ ከመኖር ይልቅ መርጦ ወዳሻው በመቅረብ የእውቀት ልኩን ያሰመረበት መስመር ነው።
ሀገር የእምቢኝን ጩኸት ወየው ብላ የሰቀለችበት ቆጥና የድሏን ሸማ አርቃ ያገዘፈችበት ችሎት አድዋ ይባላል።
ጀግና የወደቀው ለስሜ ነው። ለዛሬ ማንነትና የክብር ከፍታዬ…!
ስንፍናዬ ጠብ አጭሮ ፥ መዘመን ቅይጥ መልኩን አስፍሮብኝ ፥ በራስ ታሪክ መኩራት ጀርባውን ሳይሰጠኝ የተረከብኩት ስጦታ ነው።
አድዋ የራስ ቃል – የሰው መሆን ግዙፍ ክታብ ፥ የዘመን አሻራን ያዘለ ጠልሰም ነው።
ኢትዮጵያዊ በልቡ ተሸክሞ የሚዞረው እዳና ምንዳው በዚህ የድል ቀን ሲበሰር ከአንድ ቀን ጀምበርነት በላይ ዘመኑን ጌጥ ሆኖ እንደመታያ የሚያገለግል ቀለሙ ነው።
ለእኔም እንደዘመኔ…እንደትውልዴ
የጠይም ጦረኛው ውለታ እግር ሆነኝ። ቆምኩ…! የስጋቴን ትብትብ ፈትቼ ጥዬ በሰላም ጎጆዬ ውስጥ ሞቆኝ ተኛሁ። ነጋ…!
ኑረት ከብዶ ሲገርብኝ የማስበው ያቺን ቀን ነው። የሰው ሰሞን ናፍቆት ሲጠናብኝ የምሰደደው ወደዛ ታላቅ ገድል ነው። ተንበርክከው ላቆሙን ሳይሰለጥኑ ላሰለጠኑን ፤ እየራባቸው ላጠገቡን ሰማዕታት… ሀገርን ያህል ግዙፍ ሸክም በጫንቃቸው ተሸክመው ላሻገሩን ባለውለታዎች …. ጨልመው ላበሩን ልቦች መዝፈን አይበቃም ( ይሆናል )…. መግጠም አይበቃም ( ይሆናል) አዲስ ታሪክ መስራት እራስን በታላቅ ማንነት ውስጥ መውለድ ግን የዜግነትም የልጅነትም ግዴታ ነው። እኔ ስፈተሽ አድዋን እመስላለሁ። ደምና ላብ በውስጤ አለ። ሳቅና እምባ በልቤ አለ።
የዓይኖቼ ቀለማት ውስጥ ፈረሰኛ ይታያል። በአንደበቴ ቃላት ዳር የቀረርቶ ድምፅ ይደመጣል።
ትህትና ዝቅ አድርጎ ፍቅር እንዲዘውረኝ…. ይቅርታ ሸብ አርጎ አንድነት እንዲዋጀኝ ተከፍሎብኛል። በዘመን ገላ ውስጥ አንድ ነን!! በጊዜ ተመን ስር አንድ ነን። ከፆታችን መለያየት ውጪ አንድ የማያደርገን ሀይል አልተፈጠረም! በተረከብኳት ሀገር ላይ መሰልጠን ፣ መከባበር ፣ ፍቅርና መቻቻል መርሆቼ ናቸው።
እኔ ስፈተሽ አድዋን እመስላለሁ። ደምና ላብ በውስጤ አለ። ሳቅና እምባ በልቤ አለ። ጣዲቄን አስታወስኩ። እምዬን አስታወስኩ። ጠሀይቱን አስታወስኩ። ሞት አቀርቅሮ ሲሄድ አየውት። ሳቄ ከፍ ብሎ ሲደመጥ ሰማሁት።በመጀመሪያም በአድዋ ቆምኩ።
[1] አዝማሪት ጣዲቄ
[2] አዝማሪት ጣዲቄ
[3] ገለፃዋ ከፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ አንድ ንግግር የተወሰደ።