ተኩ ዣን(ዲ/ን ወ ኢ/ር)
ይሄን አንባቢው ይወስነዋል። ምክንያቱም ማንበብ ሙሉም ሰው ጎደሎም ሰው ያደርጋልና። አነባብን ማወቅ ግን ሙሉ ሰው ያደርጋል። ምክንያቱም ፥ ሰው ከማንበቡና ከሚያነበው ነገር በፊት አነባብን ማወቅ አለበት። ሲቀጥል ፥ የሚያነበውን ነገር ማወቅ አለበት። ካልሆነ ባነበበው ነገር ምክንያት ይጎድላል። ጎደሎም ይሆናል። አነባብን ያወቀ ሰው ብቻ ነው በማንበብ ሙሉ ሰው ሚሆነው። አነባብን ያላወቀ ሰው ግን በሚያጎለውም ሆነ ሙሉ በሚያደርገው ይጎላል። ደግሞም ” ሰው ስላነበበ ብቻ ይቀየራል ብሎ መጠበቅ ስህተት ይሆናል”[1]
ነገር ግን ፦
መጽሐፍ ላይ ያለ ብቻ እውነት የሚመስለው – እንዴት ነው ሙሉ ሰው የሚሆነው? . . . እውነት የሆነ ሁሉም የግድ መጽሐፍ ላይ መስፈር አለበት ብሎ የሚያምን ቂልስ – እንዴት ነው ሙሉ ሰው የሚሆነው? . . . . “ይሄ እውነት ነው” ሲሉት መጽሐፍ ላይ ፈልጎ ሲያጣ “አይ ፥ እውነት ሊሆን አይችልም – እውነት ሊሆን የሚችል ሁሉ እዚህ ላይ ሰፍሯል” ብሎ የሚያምን ቂልስ – እንዴት ነው ሙሉ ሰው የሚሆነው?
መጽሐፍ ላይ ያለ ሁሉንም የሚያምን ቂልስ _ እንዴት ነው ሙሉ ሰው ሚሆነው?
የሆነ የመጽሐፍ ዘውግ ላይ ሙጥኝ የሚልስ – እንዴት ነው ሙሉ ሰው ሚሆነው? . . . ለዚህ ደግሞ የላማንቻው ዶን ኪኾቴ(ኪኻና)[2] ጥሩ ምሳሌ ነው።
ኪኻና ሙሉ ጊዜውን በማንበብ የሚያሳልፍ ገበሬና ጥሩር ለባሽ ነው። ከእጁ መጻሕፍት አይጠፉም። የንባብ መንገዱ ግን የተሳሳተ ነበረ። የሚያነበው በሙሉ በጀብዱ ሥራና በጥሩር ለባሽ ፈረሰኞች ገድሎች የተሞላ ነበረ። እነዚህን መጻሕፍት ደጋግሞ ባነበበ ቁጥር በመጻሕፍቱ ውስጥ ታሪካቸውን እንዳነበባቸው ጀግኖች ጀግና ካልሆንኩ ይል ነበር። እስከመቼ ተራ ገበሬ ሆኜ ከቤት እውላለሁ? . . . እኔስ ጥሩር ለባሽ ፈረሰኛ ለመሆን ምን ይጎድለኛል? . . . ይል ነበር።
በዚህ መሠረት በመጻሕፍቱ ግፊት ወደ ጥሩር ለባሽነት ገብቶ የደረሰበትን ሙሉ ታሪኩን ስናነብ የምናውቀው (የምንረዳው) እውነት ነው። ስለዚህ ንባብ አንድ ዘውግ ላይ ሙጥኝ ከማለት ማዳረስን ይጠይቃል ማለት ነው። መባከን እንዳይበዛም ደግሞ ያለህበትን የሚመስልህን ማስቀደም ይገባል።
ማንበብ አዕምሮን ይገነባል። በአዕምሮ ውስጥ ቋንቋን – የግንዛቤ(cognitive) እድገትን – ማህበራዊ እና emotional እድገትን . . . የሚያበረታቱ ግንኙነቶችን ይፈጥራል።
ማንበብ መሠረትን ይገነባል። በምታምነው እንድትጠነክር – የምታምነውን ብዙ እያወከው እንድትሄድ ያደርጋል።
አለማንበብ ግን ስንፍናን ያበረታታል። የማያነብ ሰው ሰነፍ ነው። ታካችም ነው። የአላማ ጽናት – የእምነት ጽናት – የመንፈስ ጥንካሬ . . . ይጎድለዋል።ጀምሮ ማይጨርሰው ብዙ የህይወት ጎዳናዎች አሉት። የፍቅር ህይወት – ጓደኝነት – የስራ መስክ . . .እነዚህ ሁሉ በአብዛኛው ተጀምረው ይቀራሉ።
የማያነብ ሰው ነገሮችን በአንድ መንገድ ብቻ ነው የሚያየው። “እውነት ነው” ተብሎ የተሰጠው ነገር ሁሉ እውነት ብቻ ነው ለሱ። ወይም እውነት ብቻ መስሎ ይታየዋል። “ውሸት ነው” ተብሎ የተሰጠውም ነገር ሁሉ ውሸት ለሱ። ወይም ውሸት ብቻ መስሎ ይታየዋል።
“እውነት ነው” ተብሎ የተሰጠው ውስጥ ውሸት መኖር አለመኖሩን አያጣራም። “ውሸት ነው” ተብሎ የተሰጠውም ውስጥ እውነት ትኑር አትኑር አይፈትሽም። ይሄ ደግሞ እንደ ክህደት – እንደ ጥርጣሬ ሊታይ አይገባም!
” እውነት ያሉሉት ሁሉ – እውነት ብቻ መስሎ ከታየን
ውሸት ያሉት ሁሉም – ውሸት ብቻ መስሎ ከታየን
ያን ጊዜ ነው – ማየት የተሳነን”[3]
የማያነብ ሰው(ጠንካራ አንባቢ ያልሆነ) የሀሰተኛ ሰባኪዎች እራት ይሆናል። በተሰበከው ልክ ያምናል። የተሰበከውን ሁሉ ያምናል። የተሰበከውን ሁሉ ይከተላል። (ሰባኪዎቹ ምንአልባት ፥ መጻሕፍት – እያንዳንዱ የእምነት ሰው ነኝ ባይ – ወረኛ ጓደኛ – ሚዲያ . . . ወዘተ ሊሆን ይችላል)
ብቻ ፥ ስታነብ ብዙ የምታውቀው እንዳለ እያሰብኽ ትሄዳለህ። አንባቢ ከሆንኽ ደግሞ የማታውቀውን ለማወቅ እየጣርኽ – ሁሉን እየፈተሽኽ ትመጣለህ። “እያወቅኽ ትሄዳለህ” ሲባል ግን የተለየ ነገር አይደለም ምታውቀው። የተለየ ፍልስፍና አይደለም ምታውቀው።
ልታውቅ የሚገባ ብዙ ነገር አለ።
ነገር ግን ስታነብ ፥ የምታውቀው ህይወትን ነው። የምታውቀው የማታውቃቸውን ሌሎች ሰዎችን ፤የምታውቀው ሌሎች አዳዲስ ባህርያትን ነው። የምታውቀው ጥንካሬ ምን እንደሆነ – ፅናት ምን እንደሆነ -ማፍቀር ምን እንደሆነ – ሽንፈት ምን እንደሆነ – ጥላቻ ምን እንደሆነ – ራስ ወዳድነት ምን እንደሆነ . . . ወዘተ ነው ምታውቀው።
የምታውቀው የማታውቀውን ነገር ነው። የምታውቀው ውስጥህ ተቀምጦ ያላስተዋልኸውን/ያላወቅኸውን ነው። ከውጪ የሚጨመርልህ – ውስጥህ ስር የሌለ የተለየ የምታውቀው ነገር የለም።
አዋቂ ውስጠ ላይ ያለውን የሚያውቅ ነው። ማወቅ ደግሞ ወደ ውስጥ ያለውን ማስተዋል ነው። ማንበብ ደግሞ ውስጥ ላይ ያለውን ነገር ማወቂያ መንገድ ነው። አነባብን ማወቅ ደግሞ ትክክለኛለው መንገድ ነው።
[1] ኤፒክቲተስ(ገፅ 106)
[2] ዶን ኪኾቴ(አዘጋጅ ጀመስ ቦልድዊን)
[3] ተኩ ዣን