ብርሃን ጨልጦ መስከር  (የእሳቱ ሥላሶች)

                                                     -፩-

በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ በደቡብ አፍሪካ ተፈጽሟል ተብሎ ያነበብኩትን የአንድ በዕድሜ ጠና ያለ ቡሽሜን ታሪክ ባስታወስኩት ቁጥር ዘወትር ወደ ጥልቅ ትካዜ ይጎትተኛል፡፡ ይህ ያልታደለ የቡሽሜን አዛውንት ቅኝ ገዥዎች መሬቶቻቸውን በሚያሳድዱ ሰሞን የጎሳዎቹ መሪና ሽምቅ ተዋጊ ነበር፡፡ የሆነ ቀን አካባቢው ላይ በከተሙ የደች ሰፋሪዎች እገዛ አዛውንቱ ኮቦ እና ጥቂት ሌሎች የጎሳዎቹ ሰዎች በድንገት ተያዙ፡፡ እንደተለመደው ፍየል ሰርቀሃል ተብሎ በቅኝ ገዥዎች ፍርደገምድልነት ለአስራ አምስት ዓመታት ዘብጥያ እንዲወርድ ተወሰነበት፡፡

ቡሽሜንን አታስረውም፡፡ ቡሽሜንን እንኳን ለአስራ አምስት ዓመታት ለአስራአምስት ቀናት ካሰርኸው አበቃ የገደልኸው ያህል ነው፡፡ ለምን ብትል ልጅነቱ የንጽህና ነዋ፡፡ ዓለሙ እስከ ከዋክብት ጽንፍ የተዘረጋ፣ ሁሉ ብርቅ ግን ነጻ በሆነበት የበረሃና የዱር ክበብ እንደ ንስር በነጻነት የሚቀዝፍ ገደብን የማያውቅ ነጻ ፍጥረት ነውና፡፡ ቡሽሜንን ስታስረው ያኔ ትሰረብረዋለህ፡፡ ማሰሩን ተወውና በመንደሮች ተወስኖ እንዲኖር ስታስገድደው ያኔ የዘር ማጥፋት አውጀህበታል፡፡ በአሜሪካ ቀደምት ሕዝቦች ቀይ ሕንዶች ላይ የሆነው ይኼው ነበር፡፡

እና በዚያ ዘመን አንድ የጀርመን የስነ ልሳን ተመራማሪ በደቡብ አፍሪካ የቡሽሜን ቋንቋ ለማጥናት የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዘው ሁነኛ የቋንቋው ተናጋሪ ፍለጋ ሲባዝን ከዚሁ ያልታደለ እስረኛ ጋር ተገናኘ፡፡ ጀርመናዊው ቡሽሜኑን በቁም እስረኝነትና በአገልጋይነት ወደ ቤቱ ወሰደው፡፡ ታሪኮቻቸው፣ ተረቶቻቸው፣ አፈታሪኮቻቸው ሁሉ አስራ ሁለት ሺህ (12,000) የእጅ ጽህፈት ገጾች ተመዘገቡ፡፡ ዛሬ ዩኔስኮ ለሰው ልጅ ሁሉ ዋጋ ካላቸው ብርቅ የጽሕፈት ቅርሶች መካከል መዝግቧቸዋል፡፡ ከዓመታት በኋላ አንድ ዕለት ምሽት የጀርመናዊው ረዳት የነበረችው እና የጎሳዎቹን ቋንቋ የምትናገረው ሉሲ ቡሽሜኑን አዛውንት ኮቦን ጠየቀችው፡፡

‹‹ለመሆኑ ከጎሳዎች በመነጠልህ፣ ከመኖሪያ አካባቢህ በመራቅህ የሚናፍቀህ ምንድን ነው?››

ቡሽሜኑ በትካዜ ውስጥ ሆኖ መለሰ፡፡

‹‹የሚናፍቀኝ ምግቡ፣ መሰሎቼ፣ ነጻነቱ፣ ጋራ ሸንተሩ ሊመስልሽ ይችላል፡፡ እኔ ሁልጊዜ የማልመው ግን የጨረቃዋን መውጣት ተከትዬ ወደ ለመድኳቸው ሸንተተሮች ተመልሼ ተረቶቻችን፣ ታሪኮቻችን እንደገና ለመስማት ብቻ  ነው፡፡ ዘወትር የሚናፍቁኝ ተረኮቻችን ብቻ ናቸው፡፡ የማውቃቸውስ ቢሆኑ እንኳን ደጋግሜ ብሰማቸው አልሰለቻቸውም፡፡ ተረቶቻችን እንደ ነፋስ ናቸው፡፡ ምኞቴ ከመሞቴ በፊት አንድ ዕለት እንደገና ተመልሼ እንድሰማቸው ብቻ ነው፡፡ እነሆ አሁን ቁጭ ብዬ ስጠብቃት የነበረችው ጨረቃ ወጥታለች፡፡ ቢፈቅዱልኝ ይህችን ጨረቃ ተከትዬ ወደ ጎጆዬ አዘግማለሁ፡፡  እዚያ ታሪክ አለኝ፡፡ እዚህ እኔ በማይመስለኝ የሴቶች ጓዳ ስንከላወስ እዚያ መሰሎቼ ታሪኮቻችንን እያጣጣሙ ነው፡፡ እዚያ ከተራሮች ጀርባ ልታደመው የሚገባኝ ብዙ ታሪክ አለኝ፡፡››

ታሪኩን እንደተረኩልን ምንጮች ከሆነ ይህ ቡሽሜን ለአንዲት ዕለት እንኳን የናፈቃቸውን ተረቶች ለመስማት ሳይታደል በግዞት ተሸኝቷል፡፡    

.

.

.

መጀመሪያ የሰው ልጅ እሳትን አላመደ፡፡ ምድጃውን ዘረጋ፡፡ በእሳቱ ፍላጻ ነጻ እና ቁጡ መዋነብ፣ በወጋገኑ ትርዒት ሕብር ነፍሱ ማለለች፡፡ በምድጃው ዙሪያ -ብርሃን – ጨልጦ -ሰከረ – ፡፡ እዚያ ተረቱን አደራ፡፡ ደመነፍሱን አነቃ፡፡ ጥንታዊና መሰረታዊ የሆኑ የሰው ልጅን የደመነፍስ ስሪት አንጓዎች በተረቶቹ ቀመረ፡፡ ሸመነ፡፡ የታሪክ ነገራውን አሀዱ የጀመረው እንዲህ ሆነ፡፡

ምናልባት የሰውን ልጅ ከእንሰሳቱ የተለየ፣ በመጠኑ በምክንያታዊ አእምሮ የሚመራ ፍጥረት ያደረገውም ይኼው የታሪክ ነገራ ጥበቡ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምናልባት በቅጡ ልንረዳው ስላልቻልን እንጂ እንደ እኛ የተወሳሰበ ባይሆንስ ስንኳ እንሰሳቱም በራሳቸው አኳኋን የታሪክ ነገራ መንገድ ይኖራቸዋል፡፡ በእርግጥ እነርሱ እንደ እኛ አይጽፉም፡፡ ግን ይዘምራሉ፡፡ ዝማሬያቸው ልዩ ልዩ ዓይነት ሕብር አለው፡፡ ሽብሻቦ፣ ቀዘፋ፣ ማንቋረር፣ ከሁሉ በላይ ስል ደመነፍስ ስሪታቸው ነው፡፡ በትኩረት ለሚያጠናው ነገርየው ተረክ ቀመስ ሳይሆን አይቀርም፡፡  

ምክንያቱም ተረክ ያለው ደግሞ ምናብ (imagination) አለው፡፡ ምናብ ያለው ኅሊና አለው፡፡ ምናብ ያለው እግዚአብሔር ነው፡፡ ተረኮች – የመንፈስ ልምሻ ፈውሶች፣ መጽናኛዎች፣ ቃልኪዳኖች ናቸው፡፡ በእርግጥም ተረክ ያለው ምናብ አለው፡፡ ተረክ ያለው ታሪክ፣ ቀለም፣ ማንነት ይኖረዋል፡፡

ታሪክ ነገራ መጀመሪያ አጀማመሩ ስለተፈጥሮ አመጣጥና አፈጣጠር ከሚያብራሩ ጥንታዊ ሚቶሎጂዎች ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምናልባት ከዚያም ትንሽ ቀደም ይል ይሆናል፡፡ ቀስ በቀስ የሰው ልጅ የታሪክ ነገራ ጥበባትና ጭብጦች የፍቅር፣ የዘለዓለማዊነት፣ የትግል ወዘተ ሀቲቶችን እያሰባጠሩ ከገድል መሰል ኃይማኖታዊ ተረክ፣ ወደ ምክንያታዊ ማሰላሰል (ፍልስፍና) እና ሳይንሳዊ የታሪክ ነገራ መንገዶች እየተለወጡ ዛሬ ያላቸውን ቀለም ለበሱ፡፡ እነሆ የሰው ልጅ የሚሊዮን ዓመታት ሰው የመሆን መቃተት በሁለት ቃላት ሲገለጽ – ‘ታሪክ ነገራ’ (storytelling) – ብ – ቻ – ይሆናል፡፡

ተረት በተለይ የጥንታዊነት ለዛ ያለው ተረክ እንደ ሕይወት ሁሉ ዞሮ የሚገጥም ክብ መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል፡፡  አልፋ እና ዖሜጋ! መቼኑም ‹Dead end› አይኖረውም፡፡

እናም ተረኮቹ ትረካቸው ሳይቋጭ እንዲሁ ቢተውም ካደመጥናቸው ወይ ካነበብናቸው በኋላ ውስጣችን ማደጋቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እናብሰለስላቸዋለን፡፡ ምናባችንን ያነቃን ከሆንን ደግሞ እናስቀጥላቸዋለን፡፡ ምናብ ባይኖረንስ እንኳን ያለማስተዋልም ቢሆን (with out being conscious) ኖረናቸው እናልፋቸዋለን እንጂ ልንቀጫቸውም አቅም የለንም፡፡ ምክንያቱም የምንጽፈው ሁሉ፣ የምናስበው፣ የምንመራመረው … ሕይወታችን ሳይቀር የተረት ቅጣይ ነውና፡፡ መኖር ማለት በላብ እና በደም ታሪክ መጻፍ፣ ታሪክ መንገር አይደለምን?

ነገርግን ዘመናዊም ይሁኑ ጥንታዊ ተረኮች ሁሉ በውስጣቸው የታጨቀ አንዳች ዓይነት ትርጉም እንዲኖር የግድ አይደለም፡፡ የሕይወት ነጸብራቆች ናቸውና ልክ እንደ ሕይወት ሁሉ ትርጉም ሊገኝላቸው የሚችሉ ወይ ትርጉም የሌላቸው (meaningful or meaningless) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴ ትርጉም የንቃተ ኅሊና፣ የሕይወት መንገድ ውጤትም ይሆናልና፡፡

እነሆ በዚህም በእኛ ዘመን ታሪክ ነገራ ተለውጧል አንጂ አልከሰመም፡፡ ደግሞም ይለወጣል እንጂ መቼውንም አይከስምም፡፡ ታሪክ ነገራ የሰው ልጅ ሥነ ሕይወታዊ ሩህ ነው፡፡ ይኸው ሲነማ፣ ዘፈን፣ ልብወለድ፣ ተውኔት፣ ኢንተርኔት የአዲሱ ዘመን የታሪክ መንገሪያ መንገዶች ሆነው ብቅ ብለዋል፡፡ ‹ላሜ ቦራን›፣ ብልጮን፣ ስንዝሮን ‹ቶም ኤንድ ጄሪ› ተክቶታል፡፡ እነ ጦጢት ተረስተው መመሰያዎቹ አኒሜሽኖች (Animations) ሆነዋል፡፡ ሰው ከባቢውን (the natural environment) ረስቶ ወደ ሆነ የማይጨበጥ ኢሊዥንን ዓለም መኮብለል የመረጠ ይመስላል፡፡ እነሆ የአዲሱ ዘመን ታሪክ ነገራ በጥንታዊው ሰው ሥነተረክ ውስጥ ዋናውን ሩህ ንጽህናን (innocence) አጥቶታል፡፡ የታሪክ ነገራ መንገድ መለወጥ የሰውን ልጅ ደመነፍስ፣ የተፈጥሮ ከባቢውን፣ የሚቶሎጂ አረዳዱን ሙሉ በሙሉ እንደለወጠው እሙን ነው፡፡  

     – ልጅነት በሚቶሎጂ ዓይን –

በዚህ ትንታኔ ልጅነት የሚለው አረዳድ ከሰባት እስከ አስራ አራት ወይም አስራ አምስት ዓመት ዕድሜ ያለውን ጊዜ ማለቴ መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡ ይህ ዕድሜ ደግሞ በሚቶሎጂ የሰው ልጅ የመጎልመስ ሂደት በ‹አጸድ› የሚወከለው ጎጆን ተከትሎ የሚመጣው የሁለተኛው እርከን የዕድሜ ደረጃ ነው፡፡ በዚህኛው እርከን ታዳጊዎቹ ተጋዳሊዎች ከጎጇቸው ውጭ ያለውን ተፈጥሯዊ ዓለም እና ሰዋዊ መስተጋብር ቢችሉ ለማሰስ፣ ባይችሉ ለማደፍረስ እና የራሳቸውን ነጻ ቅኝት ለመደንባት ብርሃን ጨልጠውና እሳት ል-ሰ-ው ብቅ ይላሉ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ከራሳቸው መሻት ውጭ የሚያደፋፍራቸው፣ የሚገፋፋቸው ወይ አማራጭ አሳጥቶ ወደዚህ አይቀሬ የሕይወት የንቃት ፈርጅ የሚያንደረድራቸው የሆነ ውጫዊ አካል ይኖራል፡፡ ልጅነት በምስራቅ ጎህ አንጸባራቂ ብርሃን ይመሰላል፡፡ የመፍካት፣ የፍንደቃ፣ የሚጎለምስ ኃይል፣ የመሻት፣ የማድረግ፣ የፍላጎት፣ የሀቀኝነት፣ የንጽህና ጊዜ ነው፡፡ የምሥራቅ ፀሐይ ለምዕራብ ጥላው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

የምሥራቁን ጎህ ብርሃን ጨልጣ የሰከረች አንዲት ተጋፊ ቀበጥ ታዳጊ በሚጎለምስ ወሰንየለሽ ኃይል እየተገፋች ወደ ሕይወት አንገቷን ስታሰግ ግን ልክ የለሽ የማደግ እና የመስፋት ምኞቷን የሚቀፈድድ፣ የማያሰናዝር ሕይወት ይጠብቃታል፡፡ ወይ የልጅነት ደመነፍሷ የሚያሰግራትን ያህል ለመስፈንጠር ነጻነት የሚቸር ከባቢ አይጠብቃትም፡፡ እናም ታምጻለች፡፡ የምሥራቅ ስሪቷን ይዛ የምዕራብ ተጓዦች (የአዋቂዎች ሸንጎ) ላይ በተረክ፣ በስንዝሮ-ኣዊ ተንኮል፣ ለአመጻ፣ ለእነጻ ትሰለፋለች፡፡  

የምሥራቁ ልጅነት እና የምዕራቡ ጉልምስና በሚቶሎጂ እንበለው መሬት በረገጠው የኑረት ቅኝት ዘወትር በሙት ጠላትነት የሚፈላለጉ ተጋፊዎች ናቸው፡፡ እናም የትም እና መቼም ኖረው በሚያልፉ ታዳጊዎችና ጎልማሶች መካከል ለዘለዓለሙ የማይበርድ የትውልድ ፍርርቅ ትግል አለ፡፡ ይሄም ትግል ለዘለዓለሙ ሚቶሎጃዊ ሕይወትን ያበለጸጋል፡፡ ሕይወት ዘወትር የምታብበበውና የምትሰፋው ይሄን በመሰለው የተገራ ፍትጊያ አይደለምን?

እንደሚቶሎጂ እሳቤዎች በልጅነት የዕድሜ ክልል ያሉ ተጋዳሊዎች የሚመላለሱባቸው አጸዶች በፍራፍሬና በአበባ ብቻ ሳይሆን በመናፍስትና አጋንንት የሚያርዱ ተረኮች ጭምር የተሞሉ ናቸው፡፡ ልክ ከእልፍኝ ስትወጣ ተጋዳሊቷን መጀመሪያ ሽብር – ፍርሃት – ጥርጣሬ -ወይ ቢያንስ ለአመጻ የሚገፋፋ ውስንነት ይቀበላታል፡፡ ይሄን ውስንነት ተጋፍጣው ካለፈች ያቺ ሴት የቃቄ ውርደወትን ታክላች፤ ንግሥት ፋራን ትመስላታለች፡፡                                                                             

የውስንነት ቋጠሮው ግን ለዘለዓለሙ የሚፈታ አይደለም፡፡ እዚያም ሌላ ተጋዳላይ ወይ ተጋዳሊትን ለሌላ ጀብደኛ ተልዕኮ ያስነሳ ዘንድ ተቀባበሎ ሊጠብቅ ግድ ነው፡፡ ዘወትር የሚሆነው እንዲያ ነው፡፡ ሁላችንም የየድርጓችንን ያህል የትግል ቋጠሮ ተመጥኖልናል፡፡ ታግለን ብንጠለው የየፊናችን ጀግኖች፣ ብንቀበለው ቂሎች እንሆናለን፡፡

                      

          የኤሮፓ ሰዎች ፍልስፍና ልህቀት ውድቀት?

የሰው ልጅ አጠቃላይ ሁለተናዊ ሥልጣኔ የእሳቱ ሥላሶች ውጤት ብለናል፡፡ የምድጃ፣ የማቅለጫ እና የመሰዊያ… ከፍ ብዬ እንዳተተኹት መጀመሪያ ፍልስፍና የተረት- ተረክ – ቅጣይ ነበር፡፡ ከተረት የተዋሃደ፣ ከዕምነት የተጋመደ… ነበር፡፡ ታሪክ ነገራ እየሰለጠነ፣ እየተቀየጠ፣ እየተለወጠ ሁሉም እንደ ባህሉ እየሸመነው ግብጽ፣ ሜሶፖታሚያ፣ ግሪክን አልፎ፣ ሮምንም ተራምዶ፣ ፍሎረንስ ላይ ደረሰ፡፡ በዚህ ጊዜ በተለይ በምዕራብ ኤሮፓ ከተረት፣ ሥነ አምልኮ እኩል ምናልባት በላይ የአመክዮአዊና (ፍልስፍና) እና የሳይንሳዊ ታሪክ ነገራ መንገዶች መፈርጠም ጀምረዋል፡፡

በአስራ አራተኛው ክፍለዘመን በጣሊያን ፍሎረንስ የኤሮፓ ሰዎች የተሃድሶ ንቅናቄ ሲጀመር ከሦስቱ የእሳት ሥላሶች ሁለቱን አግልሎ ከማቅለጫው ጋር መጣበቅን መረጠ፡፡ የመለኮት ሕልውና ማክተም በአዋጅ እስኪለፈፍበት ድረስ መንፋሳዊነት ዋጋ አጣ፡፡ ባህል፣ ትውፊት፣ ሥነ ተረት በአዲስ መጤው ሳይንሳዊ የቁጥርና ‹የግራፍ› ተረክ ውሽንፍር እንዳይሆን ሆኖ ተሸመደመደ፡፡ በአንድ ወቅት በስፓኝ፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን፣ በኔዘርላንድስ ትልልቅ የአምልኮ ቦታዎች የነበሩ አድባራት በሂደት የምሽት ጭፈራ ቤትነት ተቀየሩ፡፡ ኤሮፓዊያን በዘመናት ሂደት የደረጀውን ሁሉንም የምድጃና የመሰዊያ ቅኝት ለመደምሰስ ከአራት መቶ ዓመታት በላይ ጊዜ አስፈልጓቸዋል፡፡

በዚህ ሁሉ ሂደት ማቅለጫው ብቻውን ደረጀ፡፡ ማቅለጫው አንጥረኛን (Blacksmith) ከመሳሰሉ ጥቃቅን የጎጆ ዕደ ጥበባት ተነስቶ የኢንደስትሪ አብዮትን ወለደ፡፡ ይሄም ሂደት ከተፈጥሮ፣ ከእውነታ፣ ከመለኮትና ከራሱ እውነተኛ ማንነት የተነጠለ ግዑዝ ሸማች ኅብረተሰብን ፈጠረ፡፡ ግብረ ተራክቦ (sexuality)፣ መንፈሳዊነት(spirituality) እና ጾታዊ ማንነትን (Gender) የተመለከተ ምሥጢረ ተፈጥሮን በስምረት መረዳት የተሳነው የተምታታበት አዲስ ቅጥየለሽ ሥርዓተ ማኅበር አቆጠቆጠ፡፡ ስለ ምሥጢረ ግብረተራክቦ፣ ስለወንዴ እና ሴቴ አስተኔነት፣ ስለመንፈሳዊነት ስሙር የሆነውና ያልሆነው ቅጥ አምባሩን አጣ፡፡

ዋናውን አጽመ ነገር ለመጠቆም ያህል እንጂ ይሄን አንድ ምዕተ ዓመት የተጠጋ ጊዜ የፈጀ እጅግ አስደናቂ ግን ለሰብዓዊነት የማይገደው ሽግግር ለመተንተን ሺህ ገፆች አይበቁም፡፡ ሆኖም ሌሎችን ጨምሮ ኤግዚስተንሻሊዝምና አብዘርዲዝም ይሄንንም አዲስ መሳከር የተጫነው፣ ተስፋ ማጣት (despair) የሚያሰግረው የኑባሬ ቅኝት ለመረዳት የኤሮፓ ልሂቃን የሰነዘሯቸው ግብረመልሶች (reactions) እንጂ ልህቀቶች አለመሆናቸውን ለመጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ እንዲያውም ለአፍሪካዊውና ለጥንታዊው የሥነ ተረት ሕዝብ አብዘርድ ራሱ ‹አብዘርድ› የሆነ እሳቤ ነው፡፡ ጥንታዊው ሰው ዘወትር የሚኖረው ከመላው ተፈጥሮ ጋር በተግባቦት ነዋ፡፡ Absurd isn’t a universal phenomenon; it is a ramification of alien European industrialised society.

የኤሮፓ ሰዎች ፍልስፍና በዋናነት በEgo ወይም intellect ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ እንዲያውም የኤሮፓ ሰዎች ፍልስፍና በአንድ ቃል ተቀንብቦ ሲያጥር የሬኔ ዴካርት “I think, Therefore I am.” ግለ ድምዳሜ ይጠቀልለው ይመስለኛል፡፡ እዚህ ውስጥ ‹ናርሲሲዝም› የሚጫነው ‹የእኔነት ግፊት› ጎልቶ፣ ጮሆ ይሰማል አይደል?  

በአንጻሩ የጥንታዊ የስነ ተረት ሕዝቦች ጋርዮሻዊ ፍልስፍና በአፍሪካዊው ‹አቡንቱ› ‹‹እኔ እኔን የሆንኩት እኛ እኛን ስለሆን ነው›› የሚል አስደናቂ ጽንሰ ሃሳብ መቀንበብ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በአፍሪካዊያንና በጥንታዊ የሥነ ተረት ሕዝቦች ዘንድ ከ-intellect ይልቅ ደመነፍስ፣ መንፈስ (spirit) ስል ነው፤ ገዥ ነው፡፡   

የኤሮፓ ሰዎች፣ ሰው የተፈጥሮ የበላይና ገዥ ሊሆን የተገባ ስለመሆኑ ያምናሉ፡፡ ለጥንታዊው የሥነ ተረት ሕዝብ ግን ተፈጥሮ የሚታዘዙት እንጂ የሚዳኙት አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር የተሳሰረ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአሜሪካ ቀደምት ሕዝቦች ቀይ ሕንዶች ቋንቋ ውስጥ ዱር (wild) የሚል ቃል እንኳን እንደሌለ ይነገራል፡፡ ለምን? ምክንያቱም ጫካው፣ ጥሻው፣ አራዊቱ ሁሉ ቤትና ቤተሰባቸው ነዋ! ጎሽማ የተረካቸው ሁሉ ማጠንጠኛ ቅዱስ እንሰሳ ነው፡፡ እናስ እነርሱ ዘንድ ዱር ብሎ ነገር ምን ይሰራል?

በሥነ ተረት ሕዝቦች ዘንድ ከሕግና ቀኖና ይልቅ ንጽህና (innocence) ገዥ ነው፡፡ እግዚአብሔርንስ ቢሆን ልንደርስበት፣ ልንዳስሰው የምንችለው በአመክንዮአዊ ንቅ አዕምሮ (intellect, reasoning) ሳይሆን በንጽህና አይደለምን? በትውፊት ሕጻናትን መላዕክት እንደሚያጫውቷቸው፣ አዛውንትንነት የመላዕክትነት ግርማ ያለው ዕድሜ ስለመሆኑ  የሚነገረን ሁሉ እኮ እንዲያው በአቦ ሰጡኝ የሚነዛ አይደለም!  ሁለቱም፣ ሕጻናትም ሆኑ አረጋዊያን አንድ እግራቸውን በመንፈስ የሚታዘዘው ቀጠና ውስጥ ያሰማራሉ፡፡  

ሆኖም የአፍሪካ ተረቶች ቀለማቸው የሕመም፣ የግፍ፣ የበደል፣ የበቀል፣ የጀግንነት፣ አልፎ አልፎ የፍቅር ሲሆኑ የኤሮፓ ሰዎች ተረቶች ስለምን ድብቅ በብርሃን የተጥለቀለቁ የመናፍስት መንደሮች ቤተመንግስታት ገለጻዎች የሚያሸበርቁ ‹ፌይሪ ቴልስ› (Fairy tales) ሆኑ የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ይመስለኛል? እነዚህ ‹ፌይሪ ቴልስስ› ከሌላው ሕዝብ በተለየ የኤሮፓ ሰዎች ምናብ ‹ለሥልጣኔ› ቀድሞ አንዲነቃ ገፋፊነት፣ አነሳሺነት ነበራቸውን? ‹ተረትህን አሳየኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ› ነውና ነገሩ ራሱን ችሎ መጽሐፍ የሚወጣው ግዙፍ ሀሳብ ይመስለኛል፡፡  እነሆ በሌላ ቋንቋ ቢሆስ ስንኳ አልተውኩትም፤ እየሰራሁበት እገኛለሁ፡፡

                    

                  የተረትን መስዋዕት

ጥንታዊው የሥነ ተረት ሰው ካውካስ፣ ጥቁር አፍሪካዊ፣ ሞንጎላዊ ወይም የየትኛውም ባህል እና አካባቢ ስሪት ቢሆንስ ስንኳ በመሰረታዊ ስነ ባህሪው ልዩነት የለውም፡፡ ቅኝቱ የንጽህና ነዋ፡፡ ለጥንታዊው ሰው መለኮቱ በሙቀጫ ልጅ ርዝመት ልክ የሚደረስበት ያህል ለሁለንተናው ቅርብ ነበር፡፡ በሁሉም የጥንታዊ ሕዝቦች ሥነተረቶች ውስጥ መለኮት በሰው ልጆች ክፋት እና ውትወታ ተማሮ ወደ ሰማይ ርቆ ከመሰወሩ በፊት ለሰው ልጅ ቅርብ እንደነበር የሚተርኩ ሥነተረቶች ማግኘት የሚቻለው ለዚህ ይመስለኛል፡፡

ይሄን ሳስብ ፓውሎ ኮኤልሆ ጽፎት ያነበብኩት በጥንታዊ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ዘንድ የሚነገር አንድ የሚያስደንቀኝን ተረክ እውነት የሆነ ያህል ማመን ያምረኛል፡፡ በእርግጥም እውነት ሳይሆን ይቀራል!

ተረቱ እንደዚህ ነው፡፡

ዘመኑ ጥንት ነው፡፡ የሆነ መንደርን በሀይማኖታዊ መሰጠታቸው የሚያገለግሉ አንድ ራባይ ነበሩ፡፡ መንደሯ ላይ ማንኛውም አደጋ ባጃበበ ጊዜ እኒህ ራባይ ወደ ደን ወጡ፡፡ በዚያ ቅዱሱን እሳት ካያያዙ በኋላ ወደ መለኮት ጸለዩ፡፡ መንደሯም ከፈተና ዳነች፡፡ ያንጃበበውም መቅሰፍት ተመለሰ፡፡

የሆነ ጊዜ ግን ራባዩ በድንገት አለፉ፡፡

እንደገና መንደሯ በአደጋ በተከበበች ጊዜ ተተኪው ራባይ ወደ ደኑ ሄዱ፡፡ አሉም… ‹‹ጌታ ሆይ ጸሎቱን አውቀዋለሁ፡፡ እጸልይልሃለሁም፡፡ ጸሎት የሚደረግበትን ትክክለኛ ቦታ እና የተቀደሰውን እሳት ማያያዙን ግን አላውቅበትም፡፡ ነገርግን አንተ በሁሉም ቦታ አለህ፡፡ ስለዚህ እዚሁ እጸልያለሁ፡፡ ጸሎቴን ስማ መንደሬንም ጠብቅልኝ›› ጸሎታቸውን አድርሰው ተመለሱ፡፡ መንደሯም ከተጋረጠው አደጋ በብዙ ሳትጎዳ ተጠበቀች፡፡

ዘመናት በጸጥታ ተፈራርቀው እኒህኛውም ራባይ አለፉ፡፡ እንደገና መንደሯ ላይ ፈተና በተደቀነ ጊዜ ተተኪው ራባይ ወደ ደኑ ሄዱ፡፡ አሉም…

‹‹ጌታ ሆይ የጸሎት ቦታውንም ሆነ ጸሎቱንም እንዲሁም የተቀደሰውን እሳት ማቀጣጠሉን አላውቅበትም፡፡ ግን ላንተ ምን ይሳንሃል? ስለዚህ እባክህ መንደሬን ከገጠማት አደጋ ጠብቅ፡፡›› አሁንም መንደሯ ፈተናዋን ተሻገረች፡፡

ከዘመናት በኋላ እኒህኛውም ራባይ ባረፉ ጊዜ በእግራቸው የተተካው ልጅ እግር ራባይ ሆነ፡፡ እንደተለመደው መንደሯ ላይ ፈተና በተጋረጠ ጊዜ ከቤቱም ሳይወጣ አለ… 

‹‹ስማኝ ጌታ ሆይ የት፣ ምን እንደሚጸልዩልህ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ግን አንድ የሚገርም ጣፋጭ ተረት አውቃለሁ፡፡ እሱን እነግርሃለሁ፡፡ መንደሯንና ሕዝቦቿን ከችግር እንድትታደጋት እለምንሃለሁ፡፡››

እንደገናም መንደሯ ያንጃበባት ፈተና ተገፈፈላት፡፡

ታሪኩን የተረከልን ፓውሎ ኮኤልሆ ‹ሁሉም ድልድዮች ተሰብረው ሲያልቁ ገደሉን መሻገሪያ የመጨረሻ ድልድዮቻችን ተረኮቻችን ናቸው› ይለናል፡፡ ተረኮች እንደ ከርቤ እና ሽቱ ለመስዋዕት የተገቡ ቅዱስ መነባንቦች ነበሩ፡፡ ዘመናዊው ሰው ግን ተረኩን፣ ጸሎቱን፣  ጸሎት ማድረጉንም፣ የጸሎት ቦታውንም ረሳ፡፡ ልጅነቱን ተነጠቀ፡፡ እናስ ጸሎቱ ሁሉ መቅሰፍት ጠሪ ወይ እሪ በከንቱ የሆነበት እነዚህ ራባዮች የነበራቸውን ንጽህና ቢያጣው አይደለምን? ጸሎቱ፣ ጸሎት የሚደረግበት ቦታ እና ጸሎቱ የሚፈልገው የልብ ንጽህና ቢምታታበት?…

የሰው ልጅ ወደ ምንጩ፣ ወደ ሥነ ተፈጥሮ፣ ወደ ንጽህና (innocence) መመለስ እንዳለበት አስባለሁ፡፡ ሰው ለመላው ስነተፈጥሮ ጠባቂነት መመረጡን ፈጽሞ ቸል ሊለው አይገባም፡፡

ሌላም ነገረ ሀቲታችን የሚያጎላ ግሩም የሕንድ ተረት እነሆ፡፡ ተረኩ እንደዚህ ነው፡፡ ሽቬታቀቱ (shvetaketu) በጥንታዊት ሕንድ ሥነተረት ውስጥ የእውነትን መንገድ ፈላጊው የኡዳላካ (Uddalak) ልጅ ነው፡፡

በዚያ የጥንት ዘመን አባት ኡዳላካ ልጁ ሽቬታቀቱ  አስራ ሁለት ዓመት በሞላው ጊዜ የዕውነትን መንገድ ጠንቅቆ ያውቅ ዘንድ ወደ አንድ የታወቀ መምህር ዘንድ ላከው፡፡ ከአስራ ሁለት ዓመታት በኋላ ልጅ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ አባቱ ተመለሰ፡፡ ሲመለስ እጅግ በርካታ መጻሕፍትን አምጥቷል፡፡

የልጃቸው አኳኋን ያላስደሰታቸው አባትም ልጅን ጠየቁ…

‹‹ልጄ ሆይ ትምህርቱ እንደምን ነበር?›› 

‹‹አባቴ ሆይ በሚገባ ተምሬያለሁ፡፡ በሂሳብ፣ በህክምና፣ በፍልስፍና፣ በሥነመለኮት ዘርፎች ላይ ተራቅቄያለሁ፡፡››

‹‹ነገርግን ልጄ የዕውቀቶች ሁሉ መጀመሪያም መጨረሻ የሆነውን ራስን ማወቅን አውቀሃልን? መንፈሳዊነትንስ ተክነሃልን?››

‹‹አባቴ ሆይ እንደሱ የሚባል ነገር ሲጠራም ሰምቼ አላውቅ፡፡ እንደሱ ያለ ትምህርት ተነስቶም አያውቅ፡፡››

አባት ወዲያውኑ ልጃቸው ራሱን ማወቅን ይማር ዘንድ እንደገና ወደ መምህሩ ዘንድ ላኩት፡፡ መምህሩም የሆነውን በሚገባ ካዳመጡ በኋላ አሉ…

‹‹አሁን ላንተ ያለኝ አንድ ለየት ያለ የማስተማሪያ ዘዴ ብቻ ነው፡፡ አንድ መቶ ከብቶች እሰጥሃለሁ፡፡ እነዚህን እዚያ ራቅ ወዳለው ማንም ወደማይደፍረው ተራራ ይዘሃቸው ትሄዳለህ፡፡ ተራብተው ቁጥራቸው አንድ ሺህ እስኪሞላ ድረስ መመለስ አይፈቀድልህም፡፡››

ነገርየው ግር የሚል ቢሆንበትም ለመምህር መታዘዝ የደቀመዝሙር ደንብ ነውና ትዕዛዙን ተቀበለ፡፡ አንድ መቶ ከብቶቹን እየነዳ ማንም ወደማይደርስበት ተራራ ወጣ፡፡ በዚያ ለዓመታት ከሚያግዳቸው ከብቶች፣ ከአዕዋፍት፣ አንዳንድ የዱር አራዊት በስተቀር ማንንም አላገኘም፡፡ ዓመታት ተፈራረቁ፡፡ ከብቶቹም መራባታቸውን ቀጠሉ፡፡ ትክክለኛ ቁጥሩን የሚያውቅ ባይኖርም ሽቬታቀቱ በተራራ ላይ ያሳለፈው ጊዜ ከሃያ እስከ ከሠላሳ ዓመታት ተገምቷል፡፡

ሽቬታቀቱ ቀስ በቀስ ስሙን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ረሳ፡፡ እንደ ንጹህ ወረቀት ደመነፍሱን አነጻ፡፡ እንደ ሥነተረቱ ትረካ ከሆነ የከብቶቹ ብዛት አንድ ሺህ መሙላቱንስ ስንኳ ያስታወሰችው አንደኛዋ ከብት ነች፡፡

ከዘመናት በኋላ ሽቬታቀቱ ከብቶቹን እየነዳ ወደ መምህሩ ቤት ሲመለስ ያዩ ተማሪዎች እየሮጡ ገብተው ለመምህሩ አንድ ሺህ ከብቶቹ እየመጡ መሆኑን አበሰሯቸው፡፡ በዚህ ጊዜ መምህሩ ከእርጅና የተነሳ ተዳክመዋል፡፡

መምህሩም ተናገሩ… 

‹‹የከብቶቹስ ብዛት አንድ ሺኅ አንድ ነው፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ሽቬታቀቱ ራሱ ከከብቶቹ እንደ አንዱ መሆኑ አይቀርምና፡፡››

በእርግጥም ሽቬታቀቱ ሲመለስ ሁሉንም ዓይነት የተማራቸውን ሰዋሰው፣ ሂሳብ፣ ሕክምና እና መሰል ዕውቀቶች ረስቷል፡፡ በመንፈስ እንደ አዲስ ተወልዶ የንጽህና ልጅነትን ተቀዳጅቷል፡፡ ታላላቆቹ መምህራን ካሰላፏቸው የሚበልጥ ረጅምምም የጽሞና ጊዜን ነበረው፡፡ ሁሉንም ዓይነት ሰውሰራሽ ብልጣብልጥነት ደምስሶ እንደ አዲስ ተወልዷል፡፡ ጸሎቱ ተርታ ነገር ግን ስሙር ሆኗል፡፡ ሲመለስ አዲስ ማንነቱን ያነጸ ፍጹም ቀና፣ ሀቀኛና ንፁህ ሰው ነበር፡፡ በትፊውት ብቻውን የሚኖር እርሱ የእግዜር ጎረቤት ነው እንዲባል እንዲያ ሽቬታቀቱ ለዓመታት የእግዜር ጎረቤት ነበር፡፡ እንደ ነባሩ የጉርብትና ወግ ምናልባት ከእግዜሩ ዘንድ እሳት ተጫጭሮም ይሆናል፡፡ ማንም ጎረቤት እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ማንም ደቀመዝሙር ከመምህሩ ዘንድ የሆነ ትርኳሽ ትንታግ ይዋሳል እንጂ የምድጃውን እሳት እንዳለ አያግዝም፡፡ እንደዚያ ማድረግማ የስንፍና መንገድ ይሆናል፡፡  

እናም እኔም እንደ ካቦ ከማላውቃቸው ተራሮች ጀርባ፣ ከልጅነቴ ወንዞች ባሻገር የተጋረዱ የቅድመ አያቶቼ ተረቶች፣ ታሪኮች፣ ገድላት ይናፈቁኛል፡፡ እንደ ሽቬታቀቱ የአንዱን የዱር አጋዘን ጅራት ወይ የአንዱን ተረት ጫፍ እንደ አስማት ክር ይዤ ጭልጥ ብዬ መጥፋት ያምረኛል፡፡ እግሬ እንዳመጣ ወደ የትም መራመድ ያሰኘኛል፡፡ ሁሉንም መጨበጥ ሁሉንም መጨለጥ ያምረኛል፡፡ ጥሪው ይሰማኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጥልቅ እንቅልፍ መካከል በእንቅልፍ ልቤ ይደርሰኛል፡፡ ጥሪው ከሚሊዮን ዓመታት የጊዜ ርቀት የሚመጣ ይመስላል፡፡ ለእውነታው ዓይኔን መግለጥ ከቻልኩ ወደ የትም ብራመድ እዚህም እዚያም ሕይወት፣ እዚህም እዚያም ምልዓት ነው፡፡

አበቃሁ!

ያዕቆብ ብርሃኑ 

ያዕቆብ ብርሃኑ

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *