በመንደሪን… መንደሪን…
ውብአረገ አድምጥ
ግጥምና ቀለም ምንና ምን?
ስነ ግጥም መንገዱ ብዙ ነው። ራሱን የሚገልጥበትም ሆነ የሚፈክርበት ሜዳ ሰፊ ነው። ምን ያህል ቢሉ ከልብ ወዲያ ነው መልሳችን።
ገጣሚያን ይዘው የተነሱትን የሃሳብና የውበት ፈርጥ ለልብ ያንቦገቡግ ዘንድ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። በቃላት ተራዳኢነት እየተዋደቁ የምናባቸውን ምስል ግዘፍ ነስቶ እንዲያዩት ይታትራሉ። ከእነዚህ እልፍ መንገዶች ውስጥ አንደኛው ቀለማትን መጠቀም ነው። Colors are the dream-wake state of poetry and creative writing. ትላለች Christina M. Ward ስለ ግጥምና ቀለማት ግንኙነት ባተተችበት መጣጥፏ።
አንዳንዶቹ ደግሞ ከፍ ሲያደርጉት “በየትኛውም ገጣሚ የፈጠራ ስራ ውስጥ ቀለማት የግድ ይገኛሉ” ይላሉ። ቀለማት የከያኒን የመንፈስ መቃተቶች አጭቀው የመያዝ ሃቅም አላቸው። ቀለም የማይዳሰስ የሚመስለውን ረቂቅ ሃሳብ ግዘፍ ነስቶ እንድናይ የሚያግዘን አንዳች መጥበርበርም ነው። ሃሳቦች በቀለም ሲፈከሩ ጉልበታም ይሆናሉ። ለምናብ የቀረበ፣ ለአረዳድም የተመቸ መልክ ይይዛሉ። ስለዚህ አንድ ገጣሚ ቀለማትን በተገቢው ቦታና በተገቢው መንገድ ከተጠቀመ የሚያልምለትን የውስጥ የሃሳብ ውሽንፍር መልክ ሰጥቶ በቃላት ለመሳል ያስችለዋል ብንል ማጋነን አይሆንም።
Color is not simply a decorative element in a poem. Color creates an expanse; a field, a shared formal field, with which to plant more shared components of the material imagination, a poem. Color makes this space bigger, this imaginative space more specific and bigger, gives it weight, makes it solid.
(PROSE FROM POETRY MAGAZINE, What Is Color in Poetry, Or Is It the Wild Wind in the Space of the Word, BY DOROTHEA LASKY)
የመንደሪን መንደሪን ጽይምና
“መንደሪን መንደሪን” በገጣሚ ምግባር ሲራጅ በ2014 ዓ/ም ለአንባቢ የቀረበች የግጥም እስትግቡእ ናት። በ118 ገጾች የተቀነበበችዋ ይህች መጽሐፍ በውስጧ 22 ግጥሞችን ይዛለች። ግጥምን ለመፈከር መንገዱ ብዙ ቢሆንም መንደሪን መንደሪን ይዛው ከተነሳችው ጽይምና አንጻር ለማየት ተሞክሯል። ይሄ ጽይምና በመጽሐፏ አካልና ደም ሆኖ ተዋህዷል። ለምንና እንዴት ይሄን ቀለም እንደያዘች በትንሹም ቢሆን ለማየት እንሞክር።
ጽይምና
በሃገራችን ጸይምነት ለውበት እንደ አንድ መስፈርት ይወሰዳል። አንጎራጓሪው እንዲህ ይላል፦
“ኧረ ጸይም ጸይም ጸይም አትውደዱ
እኔን አታዩም ወይ
የምይዘው ሳጣ ሲጠፋኝ መንገዱ።”
ሌላውም ይቀጥልና
“ከጎድጓዳ ስፍራ ጸይም የሳመ ሰው
እንኳን ሽማግሌ ዳኛም አይመልሰው።” ይላል
ለመሆኑ ይሄን ጽይምና በሃገራችን ለውበት መለኪያ እንዲሆን ያበቃው ምንድን ነው? ብንል አንዳንድ መላ ምቶችን እንደ ምላሽ መውሰድ እንችላለን።
እንደሚታወቀው በሃገራችን ክርስትናና እስልምና ብዙ ተከታይ ያላቸው ሃይማኖቶች ናቸው። በሁሉም ዘንድ የሰው ስነ ፍጥረት መጀመሪያዎቹ አዳምና ሄዋን ናቸው። ታዲያ መተርጉማን አባቶች የመጀመሪያው የአዳም መልክ ምን ይመስል ነበር? ለሚለው ጥያቄ የግል ምልከታቸውን ሰጥተው አልፈዋል። የአዳምን መልክ ሲገልጹም እንዲህ ይሉታል። እንደ ቁራ ያልጠቆረ፣ እንደ ለምጽ ያልተንቦገቦገ፣ ዓይኑ ያላሞጨሞጨ… እያሉ ራሳቸውን የመሰለ ትረክት ይፈጥራሉ። በአጭሩ ጸይም ማለት ነው። በሚያምንት መንገድ የራስን መልክ መሳል ደግሞ በሁሉም የዓለም ህዝቦች ዘንድ የነበረና የሚኖር ነው። ታዲያ ይሄን ጽይምና ወደ መንደሪን መንደሪን ስንወስደው በብዙ መልኮች ተፈክሯል።
ሀ) መካከለኛነት
መካከለኛ ማለት ከሁነት ጽንፎች አማካይ ላይ ቆሞ መገኘት እንደማለት ነው። ትኩስ ወይም በራድ ሳይሆኑ ለብ ብሎ እንደመገኘት ያለም ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። ታዲያ ይሄ መካከለኛነት በመንደሪን መንደሪን ግጥም ውስጥ በብዙ መልኮች ቀርቧል።
አሃዱ፦ ርዕስ
መንደሪን ከፍራፍሬ ውስጥ ይመደባል። በቅርጽም ከብርቱካን አነስ ያለ ከሎሚ ደግሞ ከፍ ያለ ነው። በቅርጽ ከብርቱካን ቢያንስ በጣፋጭነት ግን ብርቱካንንም ሎሚንም ያስከነዳል። የጋራ ጸባያቸው የሆነው መኮምጠጥ በመንደሪን ቤት ኢምንት ነው። ስለዚህ ይሄን በነገሮች ውስጥ መካከል ላይ የመገኘት እጣ ፋንታን ለመግለጽ መንደሪን የሚለውን ከልጅነት ጋር ትዝታ የሚጣባውን ርዕስ መረጠ ብንል የግጥም ነጻነት አይወስነንም። ታዲያ ለምን ብርቱካን አላለውም? ለምንስ ሙዝ አላለውም?
ክልኤቱ፦ የሽፋን ስዕል
የመንደሪን መንደሪን የሽፋን መልክ አረንጓዴነት የተጫነው ነው። ይህ አረንጓዴ ቀለም በስነ ግጥም ውስጥ ብዙ ምልክቶችን symbols ይይዛል። ህያው ተፈጥሮን፣ እድገትን፤ መታደስን ብሎም ስምረትን ይይዛል። Green derived from nature’s lush vegetation, has been a symbol of growth, renewal, and harmony. It is closely associated with landscapes, forests, and the cycle of life. Green signifies fertility, abundance, and vitality. It can also represent hope, rejuvenation, and the beauty of the natural world. (The Symbolic Colors of Poetry- By Tanya M.)
ታላቁ እንግሊዛዊ ገጣሚ ዊሊያም ወርድስወርዝ (William Wordsworth) Lines Written in Early Spring በሚለው ግጥሙ ተፈጥሮን በአረንጓዴ ቀለም ይፈክራል። ለአብነትም ጥቂት ስንኞችን ማየት እንችላለን።
“Through primrose tufts, in that green bower,
The periwinkle trailed its wreaths.
And ’tis my faith that every flower
Enjoys the air it breathes.”
እያለ የተፈጥሮን ስምሙነት ይፈክራል።
ወደ መንደሪን መንደሪን ስንመጣ ይሄ አረንጓዴነት ለብቻው አይደለም። ጥቂት የጥቁር ቀለማት ተጨምረውበት ጸይም አረንጓዴ መልክ ይዟል። ይህ ጽይምና ይዞት ከተነሳው መካከለኛ የህይወት አረዳድ ጋር የተያያዘ ነው ብንል ያስሄደናል። በልምላሜ መካከል የሚያጠላ አንዳች ጽይምና። ታዲያ ይሄ ጽይምናስ ወደ አማካይ የመገስገስ ህይወት አይደለምን?
አንድም ጸይም አረንጓዴ በአበባነትና በፍሬነት መካከል ያለ ጮርቃ ዘመን ነው።መንደሪን ነጭ ያብባል። ሲያፈራ ቢጫ መልክ ይይዛል። ከአበባ ወደ ጎመራ ፍሬ በሚሸጋገርበት ወቅት አማካዩ የጮርቃነት ወቅት ጸይም አረንዴ ነው። ገጣሚው ለምን ይሄንን ቀለም መረጠ? ስለምን ፍሬው በፍቅር የሚገመጠውን ቢጫ መልክ አልተጠቀመም ብለን መጠየቅ ያባት ነው። በህይወትስ ማንም ቢሆን ማፍራቱን ሳያውቅ የሚያልፍባት ለጋ ዘመን አይደለችምን? ህይወትስ ምሉዕ ለመሆን በመጓተት ውስጥ በጊዜ የምትቀነጠስ ጮርቃ አይደለችምን?
ለ) ህይወት
የጥበብ ምንጩም ሆነ ዥረቱ ያው ህይወት ነው። ከምንም ፈልቃ ወደምንም የምትገሰግሰው ህይወት የሰው ልጆች ሁሉ ምስጢር ናት። በተለይ የጥበብ ሰው ዱካዋን እየተከተለ ውሏን ለማግኘት ይባዝናል። ቃልና ሰሌዳ አገናኝቶ፣ ቀለምና ቡርሽ አሰናድቶ፣ በምናቡ መም እየተመመ ይባዝናል። ከአንዱ ጽንፍ ወደ አንዱ ጽንፍ ሁሌም ህይወት አለ። ገጣሚውም ይሄን የህይወት መንገድ ማሰሱን አቁሞ አያውቅም።
የገጣሚው ‘’ተይ አትጓተችኝ ገላሽ ይቀደዳል’’ ከሚለው ግጥሙ ውስጥ እንዲህ የሚሉ ስንኞች አሉ።
“እስከነ ጠይምሽ ፊት ለፊትሽ ቆሜ
ጃዝ ብሉዝ ተስሜ
ልመለስ ባስብም
ተረት ነሽ አይሰምርም።”
(መንደሪን… መንደሪን…ገጽ 31
በእነዚህ ስንኞች ገጣሚው የሚማልልላትን ጸይም ጸዳል ተረት ነሽ እያለ አይጨበጤነቷን ይነግራታል። በታላቁ የተፈጥሮ ኡደት ውስጥ ያለውን ህያው ዜማ እያቀያየርሁ ከፊትሽ ብቆምም ከተረት ባሻገር የሚያዝ ስግው ገላ የለሽም ይላታል። እንደ ተረት በመተረክና ህልው በመሆን መካከል ላይ ያለችን ክፍት ህይወት። ይሄን ሃሳቡን ለማጽናትም ከዚያው ግጥም ላይ ይሄን ያክለናል።
“ጠይሟን ብታወልቅ
በቆዳ በስሯ ምን ይመላለሳል?
ጠይሟን ቢልጡት
ገላ ምን ይመስላለ? …ብዬ ስጠረጥር
መና ቀረሁ መና
በቃል ያለ ጽጌ ስግው ሳላፀና።” ገጽ 32
እውን ያቺ ጸይም አምሳለ ሰብእ ጽይምናዋ ቢገለጥ ምን ይመስላል? ተረትነቷስ ወጥ መልክ ካለመያዝ የሚመነጭ አይደለምን? እንዲህ የመሆን ደርዟን ለማግኘት እየጓጎጠ ሲቃትት ዳናዋ የማይጨበጥ ለምንድን ነው? ይህቺ አይጨበጤ፣ ይህቺ የጸይም ቀዘባ፣ ይህቺ አምሳለ ተረት፣ ይህቺ አምሳለ ኑረት ምንድን ናት? የህይወት መልክስ ከዚህ የተሻገረ ነው ወይ? ገጣሚው ይቀጥላል።
‘’የተከተልኋትን ያህል መንገድ አለማለቁ’’ በሚለው ግጥም ላይ እንዲህ የሚሉ ጸይም ስንኞች ይንቦገቦጋሉ።
“ሕፅን ናት
ሕይወትና ድብርት መሐል
ለሽምግልና ጸጉሯን አሳርራ
የምትጥየመየም ጠይም
(ሞት ግን ጠይም ይገላል?)” —- ገጽ 48
ሕይወትና ድብርት መሐል የምትጠየመየም ጠይም ማናት? ታላቁ ቻይናዊ ፈላስፋና የታኦኢዝም (Taoism) ቀማሪ ላኦዙ (Lao Tzu) በ ታኦ ቴ ቺንግ (Tao Te Ching) መጽሐፉ እንዲህ ይላል።
“The space between heaven and Earth
is like a bellows.
The shape changes but not the form;
The more it moves, the more it yields.”
በመሬትና በገነት መካከል ያለው ክፍት ቦታ እንደ ወናፍ ነው ይለናል። ቅርጹ እንጂ ስሪቱ አይለያይም። ብዙ በተንቀሳቀሰ ቁጥር ርባናውም በዚያው ልክ ይጨምራል እንደማለት።
እዚህ ጋር አለነገር አላመጣሁትም። ይህቺ በድብርትና በህይወት መካከል ያለች ክፍት ቦታ ጸይሟ እድሜ አይደለችምን? ይቀጥላል…
“ግን እላለሁ
(ለምን ነው ጠይም … ዓይናፋር ሞት የሚመስለኝ?)
በቃ?
በቃ ላላገኛት…
በቃ?
ላላያት ነው?” …ገጽ 51
ይህቺን ጽይምና፣ ይህቺን ህልው የመሆን ሁነት ላላያት ነው በቃ ይላል። ሞት እንደሚገላት ራሱ ይጠራጠራል። እውን ሞትስ ሰውን ገደለ ይባላልን?
ታላቁ የቲቤት ቅዱስና ገጣሚ ሚላርፓ (Milarepa) እንደሚለው “My religion is to live—and die—without regret.” የሚለንም ይመስላል። ለዚህ ነው እነዚህ ጸይም ስንኞች ህይወትን መካከል ላይ ባለ ክፍት መንገድ ለመረዳት ይታትራሉ የምንለው።
ሐ) ውበት
ሌላው የገጣሚው ጸይም ምልከታ ውበት ላይ ነው። ደራሲ ያዕቆብ ብርሃኑ ‘’ከባዶ ላይ መዝገን’’ በሚለው መጽሐፉ የውበትን አይፈከሬነትና ከፍ ሲልም ህያው መለኮትነት በሰፊው ያትታል።
እንደ መንደሪን ስንኞች ደግሞ ውበት በየትኛውም የህይወት መልክ ላይ ከመንጸባረቁ ባሻገር በአማካይ የህይወት ውል ላይ የታበተ መቃተት ነው የሚል መልክ አለው። እንዲህ ብቻ ተብሎ ባይቀነበብም በህዋ ቅንፍ ውስጥ ያለ መብከንከን ውበት ነው የሚለን ይመስላል። ታላቁ ላኦ ዙ
“Under heaven all can see beauty as
beauty only because there is ugliness.”
እንዲል። አንድን ውበት ውበት ብለን የምንጠራው ፉንጋም በመኖሩ አይደለምን? የመንደሪን ስንኞች ግን በፉንጋነትና በውበት መካከል ላይ ያለው ክፍት ቦታ ወይም መካከለኛ ቦታ የውበት አድባር ነው የሚሉ ይመስላሉ።
“እስካሁን እስከዚህ ትናንት ነው” ገና በሚል ግጥሙ የሚከተሉት ስንኞች አሉ።
“የተኮሰችልኝ ልጅ ግን
ጠይም እጇ ያተኩስ ነበር
ተንበርክካ
ከንፈሯ…ከጉልበቴ ስንዝር ‘ርቆ ሲጤስ
ያተኮሰኝ ትዝ እያለኝ
ፊቴ ያቀረቀረ የእናቴን ሃዘን ሲያስርሳኝ
(ያን ጊዜ እድሜ አስፈራኝ።)” …ገጽ 72
በዚያ ክቡድ የእናት ሀዘን በዚህ ደግሞ ጸይም ውበት፣ በዚያ የማጣት ህመም፣ በዚህ የእፎይታ ቅመም ይፋንናሉ። በእነዚህ ሁሉ የስሜት ደርዞች መካከል ግን በከያኒው ዓይን ውስጥ የአማካይ ውበት ይገለጣል። በልብ ሰባሪ የመንፈስ ህመምና እፎይ እያለ በሚገኝ የስጋ ህመም መካከል ላይ ያለ የውበት መልክ፣ ያ የውበት መልክ ከሁለቱ የወረሰውን መጎናጸፊያ አጣፍቶ ለከያኒው ጸይም ሆኖ ቢታየው ቃል ገደፈ እንላለን?
መ) ቅርጽ
በመንደሪን የግጥም እስትግቡዕ ውስጥ የሚታይ እንድ ነገር አለ። እሱም ዝርው ጽሑፍና ግጥም ተሰባጥሮ መገኘቱ ነው። አንዳንዶቹ የግጥምን ውበት፣ የግጥምን ምጣኔ፣ የግጥምን ዜማዊነት ይንዳል ሲሉ ይሰማል። አንዳንዶቹ ደግሞ በዚህ ስብጥር ውስጥም ውበት አለ ይላሉ። ቅርጹ እንዲህ ነው ብለን ከመበየናችን በፊት ከመካከለኛነት ወይም ከጽይምና አንጻር ለመመልከት ብንሞክርስ።
“ደብዳቤዎቻችን” በሚለው ግጥም ውስጥ ይሄን መሰል የግጥምና የዝርው ጽሑፍ ውህደት እናያለን።
“ተበጠሰ?
ወይ ረገበ?
የአንቺስ አንጀት ልብ ነው።
የልብሽስ ነገር ከየት ነው?
(እኔን ጥሎብሽ እንጂ አምላክ የመሆን ነበር አይደል ዕጣሽ? አትዋሺም እንጂ እንደሰው ውሸት ብታውቂ የእውነትሽን ንገሪኝ ባልኩሽ ነበር)
እኔን ባይጥልብሽ
እኔን…
አልታከክ የሆድ ቁስል
ስጥልሽ ስሜን ምትጠሪው
ምን ይዞሽ ነው ይሄን ያህል”… ገጽ 37
በተጨማሪም “ገደብ የለሽ ግንኙነት (ምናልባትም) ከአንቺ ጋራ” በሚለው ግጥሙ ተመሳሳይ ዝንቅነት ይታያል።
“አኳኋኗ አይወግንም
ሰውነቷ ለሰው አይሆንም።
ፍቅሯ እስካለሀሞን ይዘልቃል
የተቀጠረችበት ማታ
ለድሆች ራት ይሆናል
(ውዳሴው እንደቀጠለ ነው ለክብሯ ግጥም እንዳዋጣ ተማጸንኳቸው። እሺታቸውን ተሽቀዳድሜ እንዳቅሚቲ አልኩ…)
ሀዘንተኛ ነፍሴን ገላ ከሚያጅባት
ጥላሽን ለብሳለሁ እንደ ፀሐይ ግባት”—-ገጽ 64
እውን ገጣሚው በስንኝ ብቻ ቀለሙን እየመጠነ መጨረስ አልችል ብሎ ነውን? ብለን ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን ከላይ ያሉትን ውብ ስንኞች እያፈለቀ በስንኝ ብቻ መዝለቅን እንደተካነበት አይተናል። ታዲያ ምን አስቦ ነው? ምንስ ለማስተላለፍ ፈልጎ ነው ብሎ ማሰብ ግን የአባት ነው።
የተነሳንበት አውድ ጸይምነት ወይም መካከለኛነት ነውና ከእሱ አንጻር ብቻ ለጊዜው እንመልከተው።
ቀለሙ እየተመጠነ፣ ምቱ እያረገደ፣ ዜማውን እያወረደ፣ ምጣኔውን እያዠጎደጎደ የሚሄደው የግጥም ባህርይ ምሉዕነትን የሚያሳይ ይመስላል። ከምት ሳይጎድሉ፣ እንዳሸበረቁ፣ እንዳቦቀነጡ መጓዝ።
በዝርው የተጻፈው ደግሞ በምናልባትና በቅንፍ ውስጥ የሚገባ የህይወት ተቀጥላ። በሚያረግድ ምትና ውበት መሐል የሚገባ የህይወት አካል። ከምጣኔውና ከስሪቱ እያፈነገጠ ምጣኔ እያደፈረሰ ግን ደግሞ የማይንቁትን እውነት ሹክ እያለ የሚዘልቅ የህይወት መልክ።
ታዲያ ህይወትስ እንዲህ አይደለምን? በመሆንና ባለመሆን መካከል እንዳለ በወናፍ መወጠሪያዎች መካከል ላይ እንደሚገኝ ክፍት የአየር ክልል አይደለምን? በታቀደና በተመጠነ፣ ብሎም በተመተረ ዘወትራዊ አኗኗርና፣ ባልተጠበቀና በድንገቴ የመሆን ብዥታ የተቀነበበ አይደለምን?
ስንሰበስበው
የመንደሪን ስንኞች መልካቸው ብዙ ነው። ግጥም የሚፈከርበት መንገድ ብዙ ነው። ስንኝ የሚተነተንበት ልማድም ግለሰባዊ ነው። ግጥም እንዲሁ ለተራ ትርጓሜ ስንኝ አያነቃም። እንደ ሰዎች ምልከታና ቅምምስ እልፍ ያስብላል።
የመንደሪንን ስንኞች ህይወትን በጸይም የሚመስሉ፣ ህልውናን አማካይ ላይ አስቀምጠው የሚታዘቡ ውብ የቃል መልኮች ናቸው እንላለን።
እናንተም አንብባችሁ የራሳችሁን ምልከታ ትሰጡ ዘንድ እጋብዛለሁ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደራሲው ምግባር ሲራጅ ከ”መንደሪን መንደሪን” በተጨማሪ ሌሎች ሁለት መጻሕፍት አሉት። የመጀመሪያዋ “ዘንባባ” ትሰኛለች። ልብ ወለድና ግጥሞችን አብራ የያዘች የደራሲው የመጀመሪያ መጽሐፉ ናት። እንዲሁም አጫጭር ልብወለዶችን የያዘ “እየዳነ ሄደ” የሚል መጽሐፍም በቅርቡ ለአንባቢ አድርሷል። ባይራ ዲጂታል መጽሔት እነዚህን የደራሲ ምግባር ሲራጅን መጽሐፍ በዚህ እትም ትጋብዛለች።