ስነ ምግባር የራቀው የስነ ጽሑፉችን ቀጠና

ሲራክ ወንድሙ

@Internet. Jonathan Wolstenholme

የዓለም ሁለንተናዊ የኑረት መስተጋብር ጥበብ በነካው መዳፍ ቢዳሰስ የተሻለ ነው ከሚሉት ወገን ነኝ። ጥንት የሰው ልጅ ራሱን በልቦና ሀዲዱ ላይ እስካወቀበት ጊዜ ድረስ በመሰልቸት የተቃኘውን የኑረት ቀለም ጥበብ በመሰሉ ወልጣቀኞች ኩሎ ተግ ማለት የጀመረው እሳትን ካገኘበት … ፣ ረጅም እንጨት ጠርቦ መሬት ከቆፈረበት በዚያ ከድንጋይ ዘመን መለስ ነው።

የቤቱን ጎጆ ሲያቀና ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ለነፍሱ እሴት እፎይታ በሚሰጠው ወሰን ይበለጥ ነበር። በተለይ ባደግሁበት የገጠር ከባቢ የቤቶቻቸውን ግድግዳ በነጭ የኖራ ቀለም ቀብተው የሚያምር የግድግዳ ስዕል፣ ጥቅስና መሰል ምልክቶችን በፊት ለፊቱ ላይ በሚያስውቡ ጥበበኛ እጆች በዝቶ ይጎላ ነበር። ከጎጆ ቤታቸው ከፈፍ ላይም ልክ እንደ ቤተስኪያን ጉልላት የተለያዩ ከጥቅም ውጭ የሆኑ መገልገያዎችን ማስቀመጥ ሌላ የውበት መቸርን ቀለም ይጎዘጉዙበት ነበር። ከጉበኑ ከባቢ ታዛው ላይ የሚሰራው ና በየወቅቱ በስስ እበት የሚለቀለቀው መልኛ መደብ – አባወራው አመሻሹን ተቀምጦበት ውጭ ውጪውን የሚታዘብበት ዓለምን የማያ መድረኩ ነች። ይህን የደቡብ የስነ ውበት ጠልሰማዊ ፍሰት እኔ ከኖርኩበት ዳርቻ ጋር አገናኘሁት እንጂ በሁሉም ከባቢ ይሄን የመሰለ የአኗኗር ጥበባዊ ክዋኔ ያረፈበት ውበታዊ ግዝፈት እንዳለ አለፍ ገደም ስል ያስተዋልሁት ነው። 

ጥበብን እንደቅንጦት ከማይመለከቱት ወገን ነኝ። ጥበብ የአንድን ነገር መነሻ ና መድረሻ እይታው ውበታዊ እውቀታዊ በሆነ መንገድ ለማሳየት የምንጠቀምበት መስመር ሲሆን፤ ቅንጦት ግን ለስሜታዊ ግለት ብቻ በመሸነፍ እጃችን ላይ ያለውን አዱኛ የምንከትበት እመቀ መቃት ነው።

ካለ ጥበብ የነቃ ጎጆ በራድ ነው። የአንድን ቁስ አካልም ይሁን ሌላ ነገር ካለ ጥበብ መስራት የሚቻል ሲሆን ጥበብን አልብሶ ማበጀት ደግሞ ሩቅ እንዲሻገር ያደርገዋል። የሚለው ነጥብ ደግሞ የማያሻማ እውነታ መሆኑን እገነዘባለሁ።

የሰለጠነ ሰው ደጅ እያንዳንዱ እርምጃ የጥበብ ሸማን ይለብሳል። የውበት ቅኔን ይደርሳል። በዘፈቀደ ተሂዶ – በዘበት መመለስ እርም ነው። ትንሽም ቢሆን የጥበብ እጅ መንሻ ያልታከለበት ማንኛውም ነገር አድሮ ከመሻገት አይጎድልም።

በሰው መሻት ውስጥ ስፍር የሌለው ደካ ነው። እውነት የተራራን ያህል የገዘፈ የአለትን ያህል የጠነከረ የፍለጋ ዳርቻ ነው።

ሰው እውነቱን ፍለጋ ሲወጣ መባከን እንዳይስበው፣ የድል ስምረት እንዳይከዳው፣ ከጉዘቱ ጋር የሚያስፈልጉትን ሰንሰለቶች ጤነኝነታቸውን እየመጠነ ዘለበቱን በመልክ በመልክ ያበጀዋል። ያደረጀዋል። የማጣት ፀሀይ እንዳትወጣበት የጥበብ ጀምበሩን ይዋጅበታል። ችክ ያለ ነገር ሁሌም ቢሆን ለቅርብ ምክነት ተጠቂ ነው።

ይህ ከላይ ያነሳነው ሟቹ መንገደኛው ሰው ለመንገድ ስምረትና ህብረት በዘገነው እፍኝ ዳር የሚነሰንሰው ብዙ ነገር አለው።

ኪነ ጥበብም አንዱ ሀሳብን በውበት ገላ ላይ፣ እውነትን በጊዜ ሸራ ላይ የምንከትብባት ሰዋራ መናገሻችን ናት። ሊጠለል የፈለገ ከስሯ ቢያርፍ የጥላነት ወዟን አትነፍገውም። በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ብልጭ ድርግም እያለ የሚያዘግመው የኪነ ጥበብ ምዕራፋችን፣ ብሎም የስነ ጽሑፍ ቀንዲላችን የሚለኩሰውን ደማቅ ጧፍ የተነጠቀ ይመስለኛል።

ይህ ነው የማይባል መሻሻልና ራሱን የቻለ የተስፋ ባለቤት መሆኑ ባይካድም በተለይ ጀማሪ በሆኑና ድክድክ በሚሉት አቅራቢያ የምታዘበው የስነ ምግባር ጉድለት ይሄ አያያዙን ላላወቅንበት ጅምር ጉዞ ሩቅ ያዘልቀዋል የሚል ግምት የለኝም።

የዓይኑን ደጃፍ በሀሜት መሀረብ ጠፍንጎ ኖሬያለሁ የሚል ብዕረኛ በንጋቱ ብስራት ውስጥ ብዙውን ክፍል የማስመሰል እድፍ ባጀለው መልኩ ላይ አባይ ሆኖ መቅረብ ይጠበቅበታል።

@Internet. Jonathan Wolstenholme

ውስጥ ውስጡን ለስብስቡ የሚደረድረውን መሓልየ መሓልይ ብቻውን ሲሆንና ጊዜ ከሁኔታ ጋር ሲያብርበት የደበቃት ማንነቱን (EGO) ጎትቶ በማውጣት የአደባባይ ስሙ ላይ የድንጋጤ ሀውልት እንዲተከል ውለታ ጥሎ ያልፋል። በሌላ ጎኑም “ካልሸበቱ መፅሀፍ አይፃፍም።” ለሚሉ ዋዘኞች ፈጠራና ማስተዋል የግድ አርባና ሀምሳን ዓመት መሻገር አለባቸው። የሚለው እንደሀገር በመርህ ደረጃ የሚጨበጨብለት ሲሆን ማዕረግና የስም ሸክምም ለእዚህ ለእኛ ዘመን ትውልድ ፅህፈት መዝመም አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይታያል።

ሽበተኛ ፀሀፊያንን ጨርሶ የመጥላት ደረጃ ላይ ባልቆምም መሪነት በፀጉር ቀለም ብስለቱ አይገታም።

 ለሽበት ሽበትማ ድንጋይም ይሸብታል። ነገር ግን ከስሩ ሆኖ ሞቱን ከሚደግስለት ብሎም ከሚያበሰብሰው አፈር ሮጦ እንዲድን አቅም አልሰጠውም። ለሽበት ሽበትማ ዛፍም ይሸብታል። ነገር ግን ሽበቱ ከምሳር ጨባጭ ሟርተኛ ፉጨተኞች አላዳነውም። ገዳዩን ቆሞ ከመጠበቅ አልነጠለውም።

ስነ ጽሑፍ የስም ሸክም የማዕረግ ጋጋታ ሳይሆን መሰጠት ነው።  ለአንድ አብዮተኛ የስነ ጽሑፍ ሰው ብሩህ ነፍስና የተፈጥሮ መዘውር ቢመሰክሩለት እንጂ በተሸመደዱና እንደበቀቀን በተደገሙ የአካዳሚ ውጤቶች የሚወሰን አይደለም። ገና መቶኛ ዓመቱን በመድፈን ላይ የሚገኘው የስነ ፅሑፍ ዋርካችን ብዙ ምሳር በጨበጡ ጨካኞች እንደተከበበ ይሰማኛል።

በሌላ ዘርፍ የወር ደመ ወዙን እየተቀራመተ ገና ብር ትር ለሚለው የልቦለድ ህትመት ላይ የሚዘባርቀው መብዛት፤ ደሳሳ ናት ካላት ቤት ጎን ውብ ህንፃ ገንብቶ “ቤት እንዲህ ይሰራል።” ከማለት ይልቅ ታላላቆችን በመዝለፍ ታላቅ ለመሆን የሚውተረተረው እግረኛ ብዛት፤ “የእኔ መፅሐፍ ብቻ ዓለምን ካልለወጠ ሌላው አልፃፈም።” በሚለው እብሪተኛ፤ አንጋፋ ጸሐፊያንን ቅርፅና ሁለንተና እየገለበጡ “መፅሀፍ ፅፈናል” በሚሉ ድርስ ጥራዝ ነጠቆች፤  እነሱ ያሉት ቅርፅ ካልተፃፈ መፅሀፍ ረብ እንደሌለውና እንደ አንድ ስነ ፅሁፋዊ ውጤት እንደማይቆጠር በሚያትቱ ብዕረኞች፤ በመሳሰሉት እና ሌሎች እልፍ ጉዳዮች ስነ ፅሁፋችን የተዛባ እይታ ስር እንዲወድቅ የተገደደ ይመስለኛል።

ቲክቶክና ሌሎች መሰል ማህበራዊ ሚድያዎች አንባቢውን ባመናመነው እንደኛ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ ተቀምጦ በዚህ ልክ እብሪተኛ መሆን ለየትኛውም ፊደል ቆጥሬያለሁ ለሚል ደራሲ ይጠቅማል ብዬ አላስብም። በመተባበር ፈንታ ልዩነት እየመዘዘ የጥላቻ ጅራፉን በሚያኖጋ ስብስብ መሀልም እውቀት ሙና ልጅ ናት።

ለአንድ ጸሐፊ እኮ መፅሀፍትን ማንበብ ለአዳዲስ ቅርፅ፣ ሀሳብ ላለመድገምና መሰል ጥቂት ግልጋሎቶች ካልጠቀመ በቀር ዋነኛ መገለጫው ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው አሁን ባለው የስነ ጽሑፍ ማህበረሰብ ዘንድ ያልተደፈሩ የብዕር ውጤቶች ንባብ ዳዴም ለማለት ከመጀመሩ በፊት የተፃፉና የተደረሱ ናቸው። ስለዚህ አንድ ሰው መፅሀፍትን አላነበምና “እኔ እነ እንቶኔን ስላነበብሁ ሌሎችን መናቅ አለብኝ” የሚለው እርምጃ ሀገርን በብዕሬ ግዝት መልኳን አበጃለሁ ከሚል ሰው የሚጠበቅ አይደለም ከዘመን ወቀሳም ለመሻር ይከብዳል። አውቆ የተከባበረ፣ ለትህትና ዝቅ ያለ እንጂ እውቀትን ድንጋይ አድርጎ ወደ አንድ ወገን የተሰነዘረ ምንዳ የለም።

ንባብ መከባበራችንን ፍቅራችንን ቅንነትና ትህትናችንን የሚያሳጣን ሳይሆን በተቃራኒው የጠፉብንን መልካም እሴቶች መልሶ ሊያቀብለን የሚችል የብርሃን ደጅ ነው። በ16ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን ያነሱት ህዳሴ ወይም የባህል አብዮት መሰረቱ ንባብ ነው። አሁን ላይ ለዓለም የጀርባ አጥንት ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው የትኛውም የስነ ጥበብ፣ የስነ ህንፃ፣ የፍልስፍናና መሰል ነገሮች ምንጩ በጣልያን የተጀመረው የባህል አብዮት ውጤት እንደሆነ ለመመስከር ንቡር መጥቀስ የዛን ያህል አስፈላጊነቱ አይታየኝም። የግምባር ስጋን በአላየንም ቁጡነት ጠባይ ካልሰወሩት በቀር… ይሄም የኛ ዘመን አንብቤያለው፣ አውቄያለሁ እያለ ቡድን መስርቶ የሚናናቀውና የሚሰዳደበው በእነዛ ዘመን ተሰሩ ከተባሉ ውጤቶች ዳር አንድም እርምጃ ፈቅ ማለት ያልቻለ ፉከራን ይዞ ነው።

ማወቅ ስሜት ከወለደው ወገንተኛ የመንጋ ስብስብ ይነጥላል እንጂ ለወደቀ ስብዕና ምላሽ በባትሪ እየተፈላለጉ መርከስን አይፈቅድም። በድፍን ኢትዮጵያ ስነ ፅሁፉን ብሎ የሚጓዝ አንድ ሰው ለአፍታ ፈገግ የምታሰኝ የአብሮነት ገድልን ለማግኘት ይቸገራል። የስነ ፅሁፉ ብቻ ሳይሆን የሀገር ካስማ ይሆናሉ ብለን የምጠብቃቸው በአሁኑ የቄንጥ አጠራር አንጋፋ እድሜ ጠገብ ፀሀፊያን ሳይቀሩ ጥርስ የሚናከሱበት ሰው አያጣቸውም። ያን የተመለከቱ ጀማሪያንም በጎራ እየተከፈሉ ተከታዮቻቸውን በማፍራት መተጋተግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

@Internet. Jonathan Wolstenholme

አንድ ለእዚህ ዘመን የሚሆን መፅሀፍ ጋብዙ ቢባሉ እንኳን ከስብስባቸው ውስጥ የሆነን ጓደኛቸውን መፅሀፍ “ጠርተው ይህ ነው የዘላለም ግብዣዬ” ይላሉ እንጂ የጠሉትን ሰው መፅሀፍ መጠቆም አይወዱም። በአጠቃላይ በጀማሪ ፀሀፊያን አከባቢ ቅንነት የለም። ጀማሪ ደራስያን የመጀመሪያ ሙከራቸውን ባሳተሙ ማግስት ከመፅሀፉ ጋር ተያያዥነት ያለውን ጥያቄ ከመጠየቅ ይልቅ እድሜሽ ስንት ነው ብሎ በሚጠይቀው የሀገራችን ሚዲያ ላይ ይታያሊ። ከዚያማ “ደሀ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት” በሚያሰኝ ኩራትና እብሪት ይጠፈነጋሉ።

የንግግራቸው ቃና አስማታዊ በሆነ መንገድ ይለወጣል። ሸሚዝ መቀየር ሲጀምሩ የአደባባይ ተውኔቱ ይቀጥላል። ደራሲ የሚለው ስምና መፅሀፍ የሚባለው ድጉስ ሰው መሆናቸውን ወዲያ አስጥሎ በጭምብል የሚንቀሳቀሱ አሻንጉሊቶች ያስመስላቸዋል። በየመፅሀፍቶቻችው የሚሰብኩትን አንድ መሆን እነሱ ሲደርሱ ይንዱታል። እግዜር ያሳያችሁ በጦርነትና ሁከት የሞተውን ሳይጨምር ይሁን ጨምሮ  መቶ ሀያ ሚልየን ነን እየተባለ በሚደነቆርባት ኢትዮጵያ አምስት መቶ ኮፒ ሸጥኩ ተብሎ መኩራራትኮ የመጨረሻ የሚያስፈራ በሽታ ነው። የምርቃቶቻቸው ቀን እንኳን ሰላሳው ሰው ከቤተሰብ፣ የቀረው ሀያ ሰው በወዳጅነት፣ አስሩ መሄጃ ሲያጣ የታደመላቸው ዝግጅት ምን ሲል ለመናናቅና ለመገፋፋት ጅማሮ ሆኖ ይመዘገባል? ማወቅ ትህትና ነው ሸብረክ ብሎ ታላቅን ማስቀደም ታናሽን ቦታ መስጠት እንጂ ምንስ ሲሆን ከእኔ በላይ ለሚሉ ጦር አነሳሽ ፉከራ ከትሮ ያስጉዛል?

ከቴውም አዲስ አበባ ታትሞ ክልል ከተሞች ላይ ሳይደርስ አምስትና አስር ዓመት በሚፈጅ የስነ ጽሑፍ ውጤት እንዴት ሀገርን ሊወክል ይችላል? በጣት ከሚቆጠሩ የክልል ከተሞቻችን ውጭ የትኛው ቦታ ላይ የተዳረሰና የገነነ የንባብ ይትባሃል ኖሮን ነው በመከራ ሁለተኛ እትም ለገባች መፅሀፋችን እግር ሰቅለን የምንወራረፈው? ተስፋ መቁረጥ አይበጅ ሆኖ እንጂ አዲስ አበቤውስ ምን ያህሉ ነው መፅሀፍን አንብቦ ለፎቶ መለቃለቅ ከተረፈ ጊዜው የሚረዳህ? ትንሽ የስራዎቻችን ዝግመቱ እና የአመሎቻችን መክፋት ክረቱ የተመጣጠነ አልመሰለኝም። እኛው በእኛው በቀነበብናት ስብስብ የሚጎዘጎዘው አሜኬላ እኮ ተስፋ ያለውን ጀማሪ ደራሲ ብቻ በመጣል የሚመለስ አይደለም። ወደፊት በእሱ እግር ለሚከተሉትም ጭምር ስጋት ነው።

በጥሎ ማለፍ ፉክክር ውስጥ ማንም አይጠቀምም ገዳይም ሟችም። ጀማሪ ፀሀፍያንን ከማበርታት አንፃር

የሬጌው አቀንቃኝ ሀይሌ ሩት ደጃፍ ከዳዊት ተስፋዬ ጋር ባደረገው በአንድ ቃለ መጠይቁ ላይ

በጃማይካ ስላለው የሙዚቃና ሙዚቀኞች ባህል እየተናገረ እንዲህ ብሎ ነበር « አንድ ታዋቂ የጃማይካ ሙዚቀኛ በኮንሰርቱ ላይ አንድ ጀማሪ ሙዚቀኛን መድረክ ላይ ይዞ በመውጣት ከአድናቂዎቹ ጋር ማስተዋወቅና ስራውን ለእሱ በተዘጋጀው ታላቅ ኮንሰርት ላይ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ወዳጅ አድናቂዎቹ ፊት እንዲያቀርብ ማድረግ የተለመደ ነው። » እኛ ሀገር ደግሞ ይህን ሁነት እንተርጉም ብንል ከምንም ነገር ቀድማ ጭንቅላቴ ውስጥ ብቅ የምትለው የአዳም ረታ እቴሜቴ የሎሚ ሽታ መፅሀፍ ውስጥ የስብሐት ጢሞች በሚለው ርዕስ ስር በገፅ 62  ላይ ያለው ንግግር ነው።

« ……

« አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ዓይነት ሰዎች በህይወት ቢኖሩ እላለሁ »

« ለምን? ልንገላቸው ? ጠልፎ ለመጣል ነው ? እሱ ስለቀረብን ቀድሞ ሞት ስለወሰዳቸው ተበሳጭተን ወይ በሞት ቀንተን ይሆናል። የሞት ጓደኞች ነን አብረን ሰንበቴ የምንጠጣ…..ማጭዱን መሸከም ሲከብደው እኛ ቤት ትቶት ይሄዳል እንድንጠብቅለት…..እሱን በጋቢያችን ደብቀን እንወጣለን ደራሲ ልናሳጥርበት አርቲስት ልንቀጥፍበት። ውሸቴን አይደለም። ወጣት ሰዓሊ ይጠላሉ….. ድንገት የማይወዱትን የማይፈልጉትን እንዳያስብ…. እንደ እኔ ዓይነት የበቃው አሮጌ በየቀኑ ይደነቃል፣ ይፃፍለታል። ለምን? ሞቼአለኋ። አላስቀናም ፡ አላስፈራም »

    « በል ስዕሉን መልስለትና እንሂድ። ምን ነካህ አንተ? » አለ ስብሐት።

« አዎ ይመስለኛል ኔክሮፊሊያዎች(ምውት/ሙት/ አፍቃሪ) ነን። ምናልባት። የቆመውን እንገልና የሞተውን እናደንቃለን።

   ወጣቱን እንረሳና ሊሞት የደረሰ ሽማግሌ እናደንቃለን…. ምቀኝነት ከሆነስ? አለ አይደለም ቆሞ ከሰራ ይበልጥሀል፣ስለዚህ ምንም በማይሰራ ሊሰራ በማይችል ሽምትር ለውጠው ። በቀላሉ ያለጭቅጭቅ ያለ ጥይት ያለ እስር ቤት ገለኸው ትገላገላለህ ዐይነት። ተንኮሉ ሁሉ ረቂቅ ነው። በነገር የሚነኩህ እኮ አይታዩም ጃን ። በነኪ ነው የሚጠቀሙት ።….. »

አንፃራዊ በሆነ መንገድ ስንመለከትም  የተወሰኑ ጅማሮች ቢኖሩትም የዚህን ያህል የደራ ስነ ፅሁፋዊ ለውጥ በዚህ በእኛ ዘመን የታደልን አይመስለኝም። ምናልባት ለውጡ ያለው ብዙ የቲፎዞ መልኮች በማሰለፍ እና በየማህበራዊ ሚዲያው ላይ መፅሀፍ ታቅፎ ፎቶ ተነስቶ በመለጠፍ ከሆነ ያስኬዳል እንጂ ጥራቱን የጠበቀ ስራ ማግኘትን ህልም ወርሶታል። እንደፈጠራ ስራ ለመሸጥ መስፈርት የሚያሟላው እምብዛም ነው። ይህ በራሱ የነገውን የስነ ጽሑፍ መንገድ በአሉታ ጎኑ ይሞግታል ብዬ እሰጋለሁ። 

 ኪነት ንፁህና ንጥል ነብስን ትሻለች። ቅንነት በሚያጠቃቸው እንጂ ተንኮል ቀምሮ በሚዋደቁ ግለሰቦች እጅ አትደምቅም። ለዚህም ይመስለኛል ከውጭ በትርጉም የምናስገባቸው እንጂ ተተርጉመው ለዓለም አቀፍ ተደራስያን ሳይደርሱ በሀገር ውስጥ ቀንጭረው የሚቀሩ መፅሀፍት ባለቤት ለመሆን የተገደድነው።

@Internet. Jonathan Wolstenholme

የአንድ ሰው ሩጫ የአንድ ሰው ነው። ምንም ያህል የተሻለ ብንሰራም ሆነ ብናነብ ዓለም የጋራ ናት። ስለዚህ በራስ ወዳድነት ካፖርታችን የደበቅናት ስለት የራሳችንን አንገት ሰልባ ከመጣል እንደማትመለስ ማል ብባል አሻፈረኝ አልልም። በመጪው የስነ ጽሑፍ ዘመናችን አብዬ ፀጋዬና አብዬ መንግስቱ ለማን የሚተካ ስድብ እስኪናፈቅ የሚያባባ ንፁህ ነፍሳዊ ወንድማዊነትን እናፍቃለሁ። እንደስብሐት ነፃ ነብስን የተቸረ አሁን ካሉቱም በተለይ ቅርቤ እንደሆነ እንደሚሰማኝ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ እንደተላበሰው ትህትና እና አክብሮትን በሁሉም ጀማሪ ብዕረኞች ላይ ለማየት እናፍቃለሁ።

በቀደመው ዘመን ግስጋሴያችን ያልተሞከረን ኢትዮጵያዊ ስነ ጽሑፍን ለዓለም ለማስተዋወቅ መትጋት የዚህ ትውልድ ድርሻም እንደሆነ ይሰማኛል። ያ የሚሆነው ግን አንብቤያለሁ ብሎ ለመኮፍስ እጅ ሰጥተን፣ በጥላቻ መበለጥ ስናቆም፣ ወጣትነት ውስጥ ተግ ብላ በእብሪት የምታኩራራ ስሜትን መግደል ስንችል ነው። ከመጠምጠም መማር ይቅደም ቢባልም ለአንድ ታላቅ የስነ ጽሑፍ ውጤትና  ታላቅ ብዕረኛ ሙገሳም ሆነ የማዕረግ ድሪቶ መገለጫው አይደለም። መቻል ፈጠራ እና አዲስ ነገር በምንም ሽፍንፍን ውስጥ የሚቀርብ አይደለምና…!

ችርስ ንቀት ላደራው ዘመናችንም ቢሆን!

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *