ሮሃ ናትናኤል
ምንታዌነት ምንድነው?! ቢሉ
ዓለ’ም “a doctrine that the universe is under the dominion of two opposing principles, one of which is good and the other evil”. ይህቺ ጣጠኛ ዓለማችን፥ ብኩኗም ህይወታችን በሁለት ሀይላት መካከል የምትባዝን መከረኛ ናት እንደማለት ነው፡፡
ጥሩ የሆነው አለ፤ መጥፎም ብርሃን አለ፤ እንዲሁም ፅልመት ውበት አለ’ም አይደል? ስለዚህ አስቀያሚነቱም አለ፡፡ ሰማይና ምድር፣ ሴትና ወንድ፣ ጠቢብና ደደብ፣ ግራና ቀኝ፣ እውነትና ውሸት የመሳሰሉትን ሁለት መልኮችን እናገኛለን፡፡ ሀይማኖትም የሚለን ይሄንኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር አለ፡፡ እሱም መልካም አባት ነው፡፡ ሰይጣንም እንዲሁ አለ፡፡ እሱም አሳሳችና ከሳሻችን የሆነው፥ የክፋት ሁሉ ስር ነው፡፡
ሀይማኖት ይህንን ጎራ ከፍሎ ለቅዱሱ ጦርነት ከእግዚአብሔር ወገን እንድንሰለፍ ይጋብዘናል። ሀይማኖት ግን ከመሰረታዊ የምንታዌነት ሀሳብ ትንሽ ማፈንገጥ አለው፡፡ እሱም መልካም የተባለው እግዚአብሔር ሁሉን ቻይና፣ መጥፎ በተባለው ሰይጣን ላይ የበለጠ ሀይል እንዳለው ይነግሩናል፡፡ እግዚአብሔር መጥፎውን ከምድር ነቅሎ በመጣል ለምን አባታዊ ፍቅሩን እንደማያሳየን ሀይማኖት የምትለን ነገር የላትም፡፡
ግና በምንታዊነት የትኛው ትክክል፣ የቱስ ስህተት እንደሆን አናወቅ ነገር፡፡ ጥሩ(መልካም) የምንለው ከሚስማማን የስሜት መሰረት ተስተን የምንበየነው ነገር ነውና፡፡ ጥሩና መጥፎ የሚባል ነገር የለም፡፡ ያሉት ሁለት ተቃራኒ ሀይላት ብቻ ናቸው፡፡ እሳት እና ውሃ ቀርቦልሃል፤ ወደ ወደድኸው እጅህን ትሰዳለህ፡፡ ወደ ወደድኸው ሲል የስሜታችንን መሻት ማመላከቱ ነው፡፡
እንዲሁም እሳቱን መጥፎ፣ ውሃውን መልካም አይልህም፡፡ The Metrix ን አይተኸው እንደሆነ ነገሩ እንደዛ ነው፡፡ bule pile እና red pile እንደማለት ነው፡፡ the two possible lines of life. ወይ ደሞ the two possible line of reality ብንለው? እውነት እውነት እላችኋለሁ በዚህ የህይወት ኡደት ውስጥ ትክክልና ስህተት የሚባሉ ነገሮች የሉም፡፡ ያለው ሁለት መሆኖች ብቻ ነው “መሆን x ና ተራቃራኒው መሆን y”. ቀባጠርክ አትበሉኝና ህይወትን እንዲህ ነች ባይ ነኝ፡፡

የምንታዌነት (dualism) ቀኝት በስነጽሑፍ ውስጥ
- Conceptual Dualism. ማለትም ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች በጽሑፉ ውስጥ እንደዋና ጭብጥ ሲነሱ እንደማለት ነው፡፡ የታሪኩ ፍሰት፣ ተቃራኒ ሀሳቦቹ በሚፈጥሩት ውጥረትና ግጭት ውስጥ የሚዘልቅ ነው። እውነትና ውሸት፣ ታማኝነትና ክህደት ፣ ፍቅርና ጥላቻ ፣ ርህራሄና በቀል ወዘተ እና መሳሰሉት ሀሳባዊ ተቃርኖዎች ላይ የተመሰረተ ጭብጥ ያለው ነው፡፡
- Character Dualism. ሌላው ምንታዊነት በስነጽሑፍ ውስጥ የሚንፀባረቅበት ስልት character dualism ይባላል። ማለትም ገፅባህሪያት በገዛ ህሊናቸው ውስጥ የሚከሰት desire conflict እና moral dilemma (internal conflict) ይዘግብልናል። በዚህ ቅኝት ከተቀመሙ ዐቢይ ስራዎች ውስጥ crime and punishment by Fyodor Dostoyevsky የሚጠቀስ ስራ ነው።
crime and punishment ውስጥ ያለው ዋና ገፀባህርይ ራስኮልኒኮቭ ለፈፀመው የግድያ ወንጀል ባስቀመጠው የምሁራዊ ትንተናና፣ ወንጀሉን ከፈፀመ በኃላ በሚኖረው የፀፀትና የጥፋትኝነት ስሜት መካከል ሲዋልል እንታዘብ ዘንድ ዴስቶቭስኪ ይህንን በሚገባ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል፡፡ የራስኮልኒኮቭ internal conflict የ character duality ሁነኛ ማሳያ ሆኖ መቅረብ ይችላል።
- Cultural and social Dualism. የባህልና የእምነት ተቃርኖዎችን የድርሰቱ ዋና ጭብጥ አድርጎ የሚተርክልን የስነጽሑፍ ዝንባሌ ነው፡፡
- symbolic dualism. ይህ ማለት እንግዲህ ሁለት መሰረታዊ ተቃርኖ ያላቸውን ሀሳቦች ወይ እውነቶች በወካይ ነገሮች የማቅረብ ስልት ልንለው እንችላለን። በዚህ ስልት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ስራዎች መካከል የቻርለስ ዲከንስ “the tale of two cities” እና የኦስካር ዋይልድ “the picture of Dorian gray” ናቸው።
ዲከንስ “the tale of two cities” በሚለው ስራ ውስጥ duality’ን በቀጣዩ ቃል ጥሩ አድርጎ አንፀባርቋል
“It was the best of times, it was the worst of times, it was the age of wisdom, it was the age of foolishness, it was the epoch of belief, it was the epoch of incredulity, it was the spring of hope, it was the winter of despair, we had everything before us, we had nothing before us, we were all going direct to Heaven, we were all going direct the other way-in short, the period was so far like the present period, that some of its noisiest authorities insisted on its being received, for good or for evil, in the superlative degree of comparison only…(Dickens 5)”.
እዚሁ ስራው ላይ order and chaos ን በሁለት ከተሞች ወክሎ ይተርክልናል፡፡ ሎንዶን የሰላም የመረጋጋት እና ተስፋ ተምሳሌታዊ ውካይ ስትሆን አንፃሩን ፓሪስ የመረባበሽ እና የችግር ተመሳሌታዊ ፍቺነትን ትሸከም ዘንድ በደራሲው ተመርጣለች፡፡
ሌላው የ symbolic dualism ማሳያ የኦስካር ዋይልድ “the picture of Dorian gray” ነው፡፡ ዋና ገፀባህርይ በሆነው Dorian grey በኩል ውበትን ከሞራል ልዕልና ጋር አሰናኝቶ ይተርክልናል። ዋይልድ በዚህ ስራው መዋብንና ማስቀየምን የመልካም ተግባርና የመጥፎ ምግባር ተምሳሌትን እንዲወክሉልን አድርጎ አቅርቦልናል።
እቴሜቴ ሎሚ ሽታ እና ምንታዌነት
አዳም ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሚያደርገው እቴሜቴ የሎሚ ሽታ የሚል የልጆችን ጨዋታ(?) ነው፡፡
እቴሜቴ የሎሚ ሽታ
ያ ሰውዬ ምን አለሽ ማታ?
ምንም ምንም ምንም አላለኝ
ትዳሩን ፈቶ ልውሰድሽ አለኝ:;
አይወስድሽም ትዳሩን ፈቶ
ምሎልሻል ጋሻ ጦር መትቶ
ከቤቴ በላይ ቁራ ሰፍሮ ቁራ ሰፍሮ
የለችም ብሎ ሄዶ በሮ ሄዶ በሮ
እኔን ያብረኝ ያክንፈኝ ያክንፈኝ
የዝሆን ሀሞት ያስጠጣኝ ያስጠጣኝ
የዝሆን ሀሞት መራራ ነው መራራ ነው
የጎበዝ ልቡ ተራራ ነው ተራራ ነው
ተራራ ሄጄ ስመለስ ስመለስ
ቁንጫ ቆማ ስትቀድስ ስትቀድስ
እባብ አንገቱን ሲነቀስ ሲነቀስ
አህያ ሞታ ጅብ ሲያለቀስ ሲያለቀስ፡፡
ለጨዋታው ልቦለዳዊ ስጋና ደሞ ፈጥሮለት ህያው ይሆን ዘንድ የተዋበ የቃል እስትንፋስ እፍፍፍ ይልበታል፡፡ የተጠቀመው ቅርፅ ደሞ character dualism የሚሉትን ነው፡፡ ይህ character duality በሁለት መልክ ቀርቦ እናገኘዋለን፡፡ አንድም አንዷ ገፀባህርይ ከሌላዋ ገፀባህርይ ጋር በሚኖራቸው የባህሪ የአስተሳሰብ ና የድርጊት ተቃርኖን የሚያንፀባርቅ ሲሆን፤ አንድም ደሞ በአንዷ ገፀባህርይ ጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠር የሀሳብ ተቃርኖ ወይም መረባበሽ ነው(internal conflict)፡፡
1. ሎሚ ሽታ እና ሁሉአገርሽ (external conflict)
በአዳም ሁሉአገርሽ እና ሎሚ ሽታ በሚባሉ ገፀባህርያት በኩል ሁለት አይነት የህይወት ፅንፍን ያስቃኘናል፡፡ ወንድ አውልነትና እመቤትነት፣ መታመንንና ክህደትን፣ ክብርና ውርደትን ኳኩሎ ያቀርብልናል፡፡ እዚህ ተቃርኖ ውስጥ አዳም ጥዶን ይጠፋል፡፡ ማንኛዋ ልክ ማንኛዋ ስህተት እንደሆነች በራሳችሁ ውስኑ ብሎ፡፡ ይህችኛዋ ልክ ያቺኛዋ ስህተት ብሎ አያመላክትም፡፡ ደራሲው የራሱን የስነምግባር ብያኔ ተደራሲ ላይ ሊጭን አይቃጣውም፡፡ አዳም እንደፈጣሪም ይሰራራዋል፡፡ እሳትና ውሃ አቅርቢያለሁ ወደ ወደዳችሁን እጃችሁን ላኩ ምናምን እንደሚል፡፡ ይህ ለተደራሲው እዳም በረከትም ነው፡፡ ነፃነትም ሀላፊነትም እንደማለት፡፡
ሁሉአገርሽና ሎሚ ሽታ ከአንዱ ፅንፍ ወዳንዱ ፅንፍ ሲሰደዱ መንገድ ላይ የተገናኙ ነፍሶች ይመስሉናል፡፡ ሁሉአገርሽ ከወንድ አውልነት ከብልግናና ከድንቁርና አጠቃላዩን ቢባል ፅልመት ከሆነ (ከመሰላት) ህይወት ለመላቀቅ ስትጋጋጥ እንዲህ ትላለች:- “በዚህች አይነት ቀላል የአጃቢነት ስራ ትንሽ ሳንቲም የማግኘት ነገር ደቃቃም ብትሆን የመኖር ሞራሌን አነሳስታዋለች [አዳም: ገፅ 80] “፡፡
አንፃሩን ደሞ ሎሚ ሽታ ተቻኩላ በማግባቷ ያስመለጣት የወጣትነት ቡረቃን፣ የኮረዳነት ቁሌትን በመናፈቅ ስልት ስትብከነከን በአዳም የቃላት ሙዚቃ ውስጥ እዬዬዋን እናደምጣለን፡፡ እንዲህ ስትል:- “አንድ ቀን ጠዋት ስነቃ ብዙ ያላሳለፍኳቸው ያልኖርኳቸው መልካም ነገሮች እንዳሉ ሊያሳየኝ ነው መሰለኝ እግዜር አስናቀን አምጥቶ ፊቴ ገተረው። [አዳም: ገፅ 84]”
አያውቁትም እንጂ ማሊያ እየተቀያየሩ ነው። ሸርሙጣዋ የሽርሙጥና ካባውን ጥላ ባልገባት መልኩ ጨዋና ክብር ያለት እመቤት ለመሆን ስትሞክር ፤ የአስሪዋን ቦታ ስትመኝም እንዲህ ባይ ነች፡፡”ጋሼ ታደሰ ለሎሚሽታ ያደርግ እንደነበረው” አንብብልኝ?” ብለው እሺ ብሎ ያነብልኛል [አዳም: ገፅ 98]”
እመቤት የተባለችው ባለትዳሯ ደሞ ክብሬ ምን ሊበጀኝ፣ ክብር የሚሉት፣ ባል የሚሉት ነገር የህይወትን ደስታን እንዲሁም ፍስሃን እንዳላጣጥም ጠፍረው ይዘውኛል ብላ የክብር ማእረጓን ስትገፍ እንታዘባለን ስትል እዩልኝ:- “አስናቀ ጋር እንዳልሄድ ባል ሆኖ እዚህ ስለገተረኝ ውስጤ እየተበሳጨ ነው። ምቀኛ ስለሆነብኝ ነው። [አደም :ገፅ 86]” በክሌቱ ገፀባህርያት የኑረት ስንጥቃት ውስጥ ህይወትን አጮልቀን ስንቃኝ የምናገኘው ነገር የህይወትን ሁለት መልክ ነው፡፡
2. የሚፋጅ ሀምሌ (internal conflict)
ሌላው አዳም በሎሚ ሽታ አእምሮ ውስጥ ትናንት እና ዛሬን፣ ፍቅርና ትዝታን በጣምራ ገምዶ ያስደምመናል፡፡ እንደ ማብሪያ ማጥፊያ፣ አንዴ በፍቅር ብርሃን አንዴ በትዝታ ብርድ፣ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ሲለው ወዲህ፣ ሲለው ወዲያህ እያለ እያንገላታን፡፡ የሚፋጅ የፍቅር ሙቀትን እና እንደ ሀምሌ የሚሰራራውን ብርዳም ትዝታ እንደ አንድ የሚሰፋበት መራቀቅ አጃኢብ ያስብላል፡፡ ይህ ሁሉ በሎሚ ሽታ አንጎል ውስጥ ነው፡፡ ትዝታና አስናቀ(ፍቅር) እየነዷት፡፡ [አዳም: ገፅ 96]
የጽሑፉ ልብ የሆነው አንቀፅ ጠቅሼ ላብቃ፡፡. በዚህ አንቀፅ ሁለትነትን ፣ ምንታዊነትን በተዋበና እንደ ማር ጥፍጥፍናው አፍ ላይ በሚሰማ ስልት በአዳም ቃላዊ ውበት እንሰክራለን፡፡
ይኸው:-
መምሸት እንደጀመረ አስናቀ ቤት በረንዳ ላይ ሆኜ ታደሰ በፔጆው እየተሳበ ቤቱ ሲገባ እየሁት (ሀምሌ ትዝታ):: አሰናቀ ጎኔ መጥቶ ተቀምጦ ወደ ታች ያያል:: የቀኝ እጁ መዳፍ በውስጥ ልብሴ ስር ጡቴ ላይ እንደ ሙቅ ጎጆ ያርፋል (የሚፋጅ ፍቅር):: ከተከፈተ አፌ የሚወጣው ማንንም የማረከ ሞዛርት ነው።(ማብራት ፣ ብርሃን ፣ የሚፈጅ ፍቅር)፡፡ ታደሰ እቤቱ ገብቶ ምን እንደሚያደርግ በሃሳቤ አወጣለሁ አወርዳለሁ:: ማድቤት ነው:: ያቺ የብረትድስት፣ ጠዋት እሱ ፊቱን ሲታጠብ የምጭራት የክብሪት ሳጥን ድምፅ። ሳላቋርጥ የምተኛባት ሶፋ:: የመኝታ ቤቴ ትልቅ መስታወት።(ማጥፊያ ፣ ፅልመት ፣ ሐምሌአዊ ትዝታ)…. አስናቀ አንገቴን ይልሳል:: በጆሮዬ የወንድ ቀረርቶውን ይሰዳል። ውስጤ የሚፋጅ ሐምሌ ነው:: ምላሱ ቅባት የነካ መቀነት ነው ታጥቄው የማድር። እንደ ሚወደኝ ይነግረኛል :: የማንሾካሾኩ ግለት ሊገለኝ ነው:: ሁለመናዬ ይከፈታል። (ማብሪያ ፣ ብርሃንና የሚፋጅ ፍቅር)፡፡ ጠበቃው ባሌ ደንገዝገዝ ባለው ምሽት ያቺ ልጅ ቤት ሲሄድ አየዋለሁ:: ተንከራፎአል። የደከመው ይመስላል። የምንኖረው አንዴ ነው:: ነገ ሞት ይመጣ ይሆናል፡።የሚሞትበትን የሚያውቅ አለ? የለም:: (ማጥፊያ ፅልመት እና ሀምሌ መሳይ ትዝታ)፡፡ በጭኖቼ መሃል ግለቴን የሚቀናቀን ቅዝቃዜ ይፈሳል፡፡ የአስናቀ አውራጣትና አመልካች ጣት ጡቴን ይቆነጥጣሉ። በቦዙ ዓይኖቼ (የቦዙ ይመስለኛል) ወደ ቤቴ ሄጄ ተመለስኩ። ወደ አስናቀም መጥቼ ወደ ቤቴም ሄድኩ። ተመላለሰኩ። ትዝታና አስናቀ እየነዱኝ። አስናቀ እየነዳኝ። (አብረናት እንደ ሸማኔ መሪወሪ አንዴ ወደ ሚፋጅ ፍቅር አንዴ ወደ የሚበርድ ትዝታ ተንገላታን) [አደም: ገፅ 96]
የአዳም ስራዎች ቢታለቡ የሚወጣቸው የማያልቅ በፍስሃው ሁሉን ኡኡ የሚያስብል ቃላዊ መረቅ ነው፡፡ እኔ ከበረከቱ ፉት ያልኩት ይሄን ነበር፡፡
ተጨረሰ
