ሲራክ ወንድሙ
ከመቃብሩ አፋፍ ላይ ነፋስ የሚያወዛውዛት እንቡጥ ፅገሬዳ እያየሁ ቁጭ ብዬ ነበር። በውበቷ ፈዝዤ አፈር ገላዬን እየገፋሁ ወደ እሷ ልንፏቀቅ ባቆበቆብኩት ሽራፊ ቅፅበት በረባሷቸው ዱር ዱር የሚሸት፣ የለበሱት ብጭቅጫቂ ካቦርት ከገፃቸው ጋር ሞት የሚያስበረግግ ሁለት መናጢ ሰዎች መጡና አጠገቤ ቆሙ።
ቀና ብዬ አየኋቸው።
ሸክላ ሰሪዎች ናቸው። ይሄን የመቃብር አፀድ እንደ ደጃቸው ተመላልሰውበታል።
አካፋቸውን ሲመዙ ደነገጥኩ። ከቀናት በፊት ሶስት እነሱን መሳይ መናጢዎች ለአበባ ማስቀመጫነት ሊጠቀሙኝ ሲወያዩ ሰምቻለሁ። እነዚህ ደግሞ ለጀበና ሊያበጃጁኝ ነው።
ቀና ብዬ ዓይን ዓይናቸውን እያየሁ « ተዉ ከቀናት በኃላ ለአበባ ማስቀመጫነት አፈር እኔነቴን ይወስዱታል። ተዉ ለጀበና አታርጉኝ! አትውሰዱኝ !» አልኋቸው።
አልሰሙኝም።
በአካፋው ዝቀው ባነገቱት ኮረጆ ውስጥ ዶሉኝ። የዘላለም የመክሸፍ ቅዝቃዜ ተሰማኝ። በኮሮጇቸው ውስጥ ገብቼ መንደራቸው እስክገባ የማስበው የዚያችን አበባ ዝምታ ነው! የእነዚያ ከመቃብር ሀውልት ላይ የሚፀዳዱ ጥቋቁር አሞራዎችን ፍዘት እና ድንግዘት ነው።
ዋ!
የእንቁራሪቷ ተረት!
ዛሬ ከጎናቸው አለምኞት ፍላጎቴ ስጋዝ ዝም ብሎ ለውድቀት የዳረኝ ልሳን ነገ የራሱን ውድቀት በራሱ የመዳፍ ፊርማ ያረጋግጣል። አበባዋ የመርገፍ ሲሳይ ካልገጠማት በቀር ውበት ያለተመልካቿ አንቡላም ህይወት በመሆኗ፣ ነገ አፈር ዘጋኝ ቢረግጣት እንጂ እንደማይቀጥፋት እሙን ነው።
ለአሞራውም የአዳ’ኝ የደጋን ቀስት በጉረሮው አቀበት እንደሚቀበቀብ እርግጠኛ ነበርሁ።
ሰማዩስ ደምኖ ስለምን ዝም አለ?
እህ! ደከመኝ……..