ሩት ሃብትማርያም

ነብይ መኮንን በሩት ሃብተማርያም

ስለ እሱ ብዙ ነገር ማለት ይቻላልና ጽሑፌን ስጀምር ምንም የምቸገር አልመሰለኝም ነበር። ግን ወደ ነገሩ ስገባ ከየት እንደምጀምር ግራ ገብቶኝ ብዙ ቆየሁ። እናም  ስለ ታላቅ ማንነቱ በትንሽ ብዕሬ ለመከተብ እናንተን ዋስ ጠርቼ ጀመርኩ። ከየት እንጀምር? አብዝቶ ከሚያወራላቸው እናቱ እና ናዝሬት? … ወይስ ትልቅ አበርክቶ ስላበረከተበት የእስር ቤት ቆይታው? አልያም ስለ ጣፋጭ ወጎቹ እና መጻሕፍቱ? … ሁሉም የእሱ መልኮች ናቸው እንጀምር። 

ጋሽ ነብይ  ጋዜጠኛ ፣ ጸሐፌ ተውኔት  ፣ ገጣሚ እንዲሁም ተርጓሚም ነው። በእስር ቤት ቆይታው ወቅት ወይም በእስር ቤት በነበረበት ወቅት  የማርጋሬት ሚሼልን ‹ Gone with wind › “ነገም ሌላ ቀን ነው” ብሎ የተረጎመ ሲሆን በቅርብ ጊዜያት ደሞ ‹The Last Lecture› የተሰኘ የአንድ የዓለማችንን እውቅ ሳይንቲስት የሕይወት ታሪክ ‹ የመጨረሻው ንግግር› ብሎ ተርጉሟል።

ጋሽ ነብይ “ስውር ስፌት 1  እና 2” እንዲሁም “ጥቁር ነጭ ግራጫ” የተሰኙ የግጥም መድብሎች አሉት።  በአንድ ወቅትም ፖለቲከኛ ነበር። የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መስራች እና ዋና አዘጋጅም ነው። በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተዟዙሮ ያያቸውን ትዝብቶች በመከተብ በየሳምንቱ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ሲያወጣቸው ቆይቶ በኋላም “የኛ ሰው በአሜሪካ” ብሎ ሰብስቦ  አሳትሟቸዋል።  “ናትናኤል ጠቢቡ” የተሰኘ የመድረክ ተዉኔት እንዲሁም “ባለጉዳይ” የተባለ የቴሌቪዥን ድራማ ተርጓሚና ጸሐፊ ነው። ብዙዎች እንደሚስማሙበት ደግሞ ጨዋታ አዋቂም ነው። እስኪ እሱ አብዝቶ ስለሚናገርላቸው እኛ  ትንሽ ትንሽ እንበል።

ነብይና ናዝሬት

“ኧረ ናዝሬት ናዝሬት ረባዳው መሬት 

ታበቅያለሽ አሉ ሸጋ እንደ ሰንበሌጥ”

ከላይ ያለውን ስንኝ የጻፈው ጋሽ ነብይ “እሱ  አማርኛ ያስተማረው ሰው ጥሩ የተገራ ጸሐፊ ይወጣዋል” ሲል የሚናገርለት መምህር ምጽላለ ሙሉ  ነው። ወይም (ከላይ ያለው ስንኝ ጋሽ ነብይ “እሱ አማርኛ ያስተማረው ሰው ጥሩ የተገራ ጸሐፊ ይወጣዋል” የሚልለት  መምህር ምጽላለ ሙሉ የፃፈው ነው።)  እዚህም ያመጣሁት ጋሽ ነብይ ስለናዝሬት ሲናገር የሚያስቀድማት ስንኝ በመሆኗ ነው። ጋሽ ነብይ በአንድ ቃለ መጠይቁ ላይ “የአንድ ሰው መሀንዲሱ አካባቢው ነው።” ይላል። በትክክልም የአንድን ሰው ባህሪም ሆነ አስተሳሰብ ለመቅረጽ የሚያድግበት ማህበረሰብ የስነልቦና ውቅር ወሳኝነት አለው።  ጋሽ ነብይ ትውልዱ ናዝሬት ነው። በመንሰፍሰፍ የሚጠራት ናዝሬት ለማያውቃት እና ከእሱ አፍ ስለእሷ ለሚሰማ “ምን ቢኖራት ነው?” ብሎ ያስጠይቃል።

 “ይድረስ ከራኬብ ለራኬብ” በሚል ግጥሙ ታዲያ በናዝሬት በኩል አድርጎ ኢትዮጵያን ሲኩላት እናየዋለን። እኔ እንደምረዳው ሰው ትልቁን ምስል የሚያየው እንዲሁም ስለትልቁ ምስል  ግድ ሊለው የሚችለው አጠገቡ ያለውን ሲወድ ነው ብዬ አስባለሁና ነብይም ናዝሬትን በጣም በመውደድ ኢትዮጵያን አፈቀረ። ግጥሙ ራኬብ መኮንን እና ራኬብ ነብይ ለተባሉ ቤተሰቦቹ እንደተጻፈ ይነግረናል።  በእርግጥ ግጥሙ በእነሱ አይቆምም ፤ ለኢትዮጵያውያን  ሁሉ ነው።

 እንዲህ ይላል …

“አየርና ነፋስ፣

ውሃው ሆነ ህዋው፣ የብስና ውቂያኖስ

አያጉዘው የለ፣ አጉዞሽ አጉዞሽ

አሜሪካን ሰፈር፣ የሰው ሀገር ገባሽ

ስመ ሞክሼ እህቴ፣ ዋ ሚስጥሩን ባወቅሽ 

ያን ያህል ሳትሄጂ፣

አሜሪካን ግቢ፣ ናዝሬት ነበረልሽ

ፈረስ የሚያስጋልብ፣ የኳስ ሜዳ ያለው

ዘይቱን ያዘለ፣ ትላልቅ ዛፍ ያለው 

ሽቦ የታጠረ፣ ማንም የማይደፍረው

 ተርኪኒዎች ያሉት፣ ደግሞም ዶሮ ርቢ

ነበር እኮ ናዝሬት፣ አሜሪካን ግቢ” 

…እያለ አያሌ የናዝሬት ትውስታዎቹን እና በረከቶችን ያስዳስሰናል። ይህ “ራኬብ ለራኬብ” የተባለው ግጥሙ በጣም የምወደው ግጥም ነው። ምክንያቱም በአንድም በሌላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያደግን እኛ በዚህ ግጥም ውስጥ የተባሉት ነገሮች ሁሉ ዳስሰውን አልፈዋልና። ታዲያ ያለፈ እንደሆንስ ቢባል “ታላቅ ዘፋኝ የውስጣችንን ዝምታ የሚያዜምልን ነው።” እንዲል ካሕሊል ፤ የውስጣችን ዜማ ተዚሞልን እንላለን።

 እዚህ ጋር ራኬብ ስል አንድ ቀን ጋሽ ነብይ የነገረኝ ወግ ትዝ አለኝ።  ለራኬብ አባቷ ነብይ መኪና ገዛላት። እናም መኪናዋ ቀለም መቀባት ኖረበትና ጓደኛው ቆንጆ አድርጎ ቀባላት። እንድታየው ተጠራች። ከቤታቸው ደረጃ ላይ ወደታች ስታየው ግን ከላይ በደንብ አልተቀባም። ትንሽ መነጫነጭ ነገር … “አባዬ ከላይ እኮ አልተቀባም” ትላለች። ከዛስ የነብይ ጓደኛ ምን አለ? “ራኪዬ ሰው ለሚያየው እንጂ እግዜር ለሚያየው አትጨነቂ!” አላት ብሎ ነግሮኝ ረጅም ሳቅ እንደሳቅሁ ትዝ ይለኛል። ዛሬ ስለ ናዝሬት አይደለም። ስለ ነብይ ነው ።

ነብይና ማዕከላዊ 

“ከዚያ የሚያውቁ የሚያውቁትን እጅግ አቅርቦ በሀሳብ እያጎሉ ማየት … ከዚያ የገዛ ሰፈር ፣ የገዛ ቤት ፣ የገዛ ጓዳ የገዛ ማጀት እናት አባት ልጅ ሚስት ምኑ ቅጡ ዋ! ያጡት ማማሩ?! ማሳሳቱ?!  የታባቱ! ላንድ አፍታ በሀሳብ ቢሸፍቱና በምናብ ቢፈቱ እንዲህ ሀገር መታየቱ ፣ እንዲህ አገር መወሳቱ ደሞ ጣሩ ለሱው ሲሉ መታሰሩ” ይላል “ነገም ሌላ ቀን ነው” የተሰኘ መጽሐፉን ለሁለተኛ ጊዜ ሲያሳትም ባካተተው መግቢያ …።

 ስለ እስር  እና እስረኝነት ሰቀቀን ሲያወሳ። ጋሽ ነብይ “እስር ቤት ላልተማረበት ስቃይ ለተማረበት ደግሞ ት/ቤት ነው!” ይላል። ይሄንንም በተግባር ያስመሰከረ ይመስለኛል። በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት በኢህአፓነት ተጠርጥሮ ለስምንት አመታት እስር ቤት ቆይቷል።  በእስር ቤት ቆይታው 3000 በሚደርሱ የሲጋራ ወረቀቶች ላይ በኋላ “ነገም ሌላ ቀን ነው” ብሎ ስም የሰጠውን የማርጋሬት ሚሼል ‹Gone with the wind> መጽሐፍ ተርጉሟል። ለምን መጽሐፉን “ነገም ሌላ ቀን ነው” ሊለው እንደፈለገ ሲገልፅ “ለመጻፍ የሚያስፈልገኝ ነገር ለማሟላት አራት ጥያቄዎችን መመለስ ነበረብኝ።

1. በምን ልጻፍ — ወረቀት አይገባማ

2. በምን ልጻፍ — እስክሪብቶ ከቤት ተጠሪው እጅ አይወጣማ። 

3. የት ልጻፍ — ቦታ የለማ

4. ጽፌስ — ማውጫ የለማ  በመጨረሻ ግን እንደ   ‹ Gone with the wind> መሪ ገጸ ባህሪዋ እስካርሌት ኦሃራ  አባባል  ነገም ሌላ ቀን ነው! ብዬ ጉዞውን ጀመርኩ።” ይለናል።

እሱ ራሱ እንደሚለው እስርቤቱን ተምሮበታልና ጥሩ ጎኑ ላይ ፣ በረከቱ ላይ እናተኩር ብለን እንጂ ከዓለም ተነጥሎ በአስከፊ ሁኔታ መታሰር ደስ የሚል ቅንጣት ነገር የለውም። እሱም እንዲህ ይላል “ጡር ተናገርክ አትበሉኝ እንጂ ይቺን እስር ለሁሉም የውጪ ዓለም ዜጋ በሾርባ ማንኪያ ማዳረስ ቢቻልና ሦሥት ሦሥት ወር እንኳ ቢቀምሳት ስንት ነገር መማማር በተቻለ!”

በትክክል መረዳዳትን ያሳየ ቆይታ እንደነበረው በተለያዩ ጊዜያት ይናገራል። ምናልባት በትንሹ የመተባበራቸው ውጤት ምስክር አሁን የምንወደው “ነገም ሌላ ቀን ነው” መጽሐፍ ነው። ወይም (አሁን የምንወደው “ነገም ሌላ ቀን ነው” መጽሐፍ የመተባበራቸው ውጤት ነው። ነብይ “አጫሹ ሁሉ አጭሶ አጭሶ ባኮውን ከመወርወሩ  በፊት ለዚያ ተኮራምቶ ለሚጽፍ ዜጋ እንስጠው ማለትን ለመደው “ ይላል።   እንኳንም ተባበራችሁ። ትውልድ ያመሰግናችኋል።  

የኛ ሰው በአሜሪካ በነብይ ዓይን

የእኛ ሰው በአሜሪካ በነብይ መኮንን

“ጋዜጠኝነት ህዝባዊ አገልግሎት ለመስጠት፤ የማሕበረሰብን ህመም ለመታመም እና ተጽዕኖ ለመፍጠር ጥሩ መንገድ ነው።” ይላል አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ቦብ ሺፈር።  ነብይ በትክክል ይሄንን መንገድ የተጠቀመ ይመስላል። ጋሽ ነብይ በአንድ ወቅት  በአንድ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋም በቀረበለት ግብዣ ወደ ሰሜን አሜሪካ አቅንቶ ነበር። የብዙ ሰዎች የሳምንት ጉጉት የሆነችው “የኛ ሰው በአሜሪካ” ጽሑፍ የተጠነሰሰችው እዛ ሄዶ ያየውን በመጻፍ ነው። እዛ በፖለቲካ ትኩሳቱ መሃል ያጣቸውን አልፎም ሞተዋል ብሎ ያሰባቸውን ጓደኞቹን አግኝቷል።

የኛ ሰው አሜሪካ ውስጥ እንዴት እንዴት እንደሚኖር ቁልጭ ባለ ቋንቋ እና ባማረ ለዛ ጽፎልናል። ለዚህም ትጋቱ እናመሰግነው ዘንድ ግድ ይለናል። የሰሜን አሜሪካ ቆይታውን ሲጨርስ ወደ ተለያዩ ሀገራት ተዟዙሮ የዓለሙን ሁሉ አኗኗር አይቷል። ባህልን ባለመረዳት ግራ ተጋብቷል። ይሔንንም በጋዜጠኛ እና ወገኛ ዓይኑ አይቶ አሳይቶናል። ከዚሀም አንዱን እነሆ፡-

ጋሽ  ነብይ መኮንን ጀርመን ሄዶ አንድ ባር ውስጥ ከባለቤቱ እህት ጋር እየጠጡ ነው። ታድያ በጀርመን ባህል የድራፍት ጥራት የሚለካው ሲቀዳ አረፋው በዛ ብሎ ከታየ ነው። እና ጋሽ ነብይ ይሔ ነገራቸው አልጣመውምና የተቀዳለትን ጨልጦ ቀና ብሎ ባሩን ሲገረምም ሰው አፉ በአረፋ ነጭ ሆኖ ያብረቀርቃል።

እነ ጋሽ ነብይ የሚጠጡት ሲያልቅባቸው አስተናጋጅ ለመጥራት ከጎኑ ያለውን ደውል የባለቤቱ እህት ትጫነዋለች። እነሱ ያላወቁት ነገር ቃጭሉ የተዘጋጀው አስተናጋጅ ለመጥራት ሳይሆን ከበር መልስ ቤቱን ሁሉ ለመጋበዝ ነው። መልዕክቱ “በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ነገር ተከናውኖልኛል ወይም ትልቅ ሃብት አግኝቻለሁ። ነፃ ግብዣዬን በመቀበል ደስታዬን ተካፈሉ” ነው። ጀርመኖቹ ነፃ መጠጥ ማግኘታቸውን ለማክበር ቤቱን በሁካታ ሞሉት። ነብይ የጀርመን አፍ አያውቅም፤ የጀርመን ባህል አያውቅም። ምን እንደተፈጠረ አልገባውም። በኋላ የባሩ ባለቤት እነ ነብይን አናግሮ በስህተት መሆኑን ሲሰማ ለደንበኞቹ  የተፈጠረውን ስህተት ካስረዳ በኋላ ይቅርታ ጠየቀ። ጀርመናውያኑ ገንዘባቸውን ከፍለው ወደሚጠጡት ተመለሱ።

እነዚህን እና መሰል ፈገግ የሚያሰኙ ግን ደግሞ መልዕክታቸው ጠንካራነት ያልጎደላቸውን ጽሑፎች ያስኮመኮመን ነብይ ነው። ጥሩ ጋዜጠኛ በቦታው ያልነበረን ሰው እንኳ እንደነበረ እንዲሰማዉ የሚያደርግ ነው እንዲሚባለው እኛም ስራዎቹን አንብበን ለጥሩ ጋዜጠንነቱ እጅ እንነሳለን። 

እናም በመጨረሻ!

ነብይ ሆይ! ለግጥሞችህ እናመሰግናለን!

ለመጻሕፍትህ ወይም ለመጽሐፎችህ እናመሰግናለን!

ለጋዜጠኝነትህ እናመሰግናለን!

ለሰጠኸን  እንዲሁም ለምትሰጠን ሁሉ እናመሰግናለን! 

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *