ተገኑ ጸጋዬ
ስለኢትዮጵያ ሲነሳ ዓለምን የሚያስገርም አንድ ነገር አለ፡፡ ይኸውም የውጭ ጠላት በሀገሪቷ ላይ ሲነሣ የሚያሳዩት ህብረት ነው፡፡ ሪቻርድ ግሪንፊላድ የሚባል ፀሐፊ በጥልቅ መገረም “the mysterious magnetism” ይለዋል፡፡ ሚስጥራዊ ሙጫ እንደማለት ነው፡፡ አንዳንዶቹ እንዲሁም ስውር ስፍ ይሉታል፡፡
በተለያየ ጊዜ የውጭ ጠላት ሀገራችን ለመውረር በወጣበት ጊዜ ህዝቦቿ የሚያሳዩት የትብብር መንፈስ ልዩ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ ምሳሌ የሚሆነን በዓለም የጥቁሮች ሁሉ ድል ሆኖ የተዘመገበው የአድዋ ድል ነው፡፡
የአድዋ ድልን ታሪክ በሁለትና በሶስት ገጽ ለመግለፅ መሞከር ከኩንታል ስኳር ላይ በማንኪያ እንደመቆንጠር ነው፡፡ የአድዋ ድል ዛሬም ድረስ የገዘፈ ፣ የዓለምን ታሪክ የቀየረ ፣ ኢትዮጵያዊያንን ያጋመደ እና ነጮችን ያስደነበረ ተወዳዳሪ የሌለው ታሪክ ነው፡፡
ስለ አድዋ ድል በራሳቸው በነጮቹ አንደበት እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፡፡ ጆርጅ በርክሌይ የሚባል ፀሐፊ እንዲህ ይላል ስለአድዋ ‹‹ከሰፊው የፖለቲካና የታሪክ ትንታኔ አኳያ የአድዋ ጦርነት በአፍሪካ ምድር አዲስ ሀይል መነሳቱን የሚያበስር ይመስላል፡፡ የዚህች አህጉር ተወላጆች የማይናቅ ወታደራዊ ሀይል ሊሆን እንደሚችሉ ልናሰላስል ተገደናል፡፡ እንዲያውም አሁን አስቂኝ ቢመስልም ይህ ሁኔታ /ማለትም አድዋ/ ጨለማይቱ አህጉር በላይዋ ላይ ሥልጣኑን ባንሰራፋው በአውሮፓ ላይ የምታደርገው አመጽ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው›› ብሎ አስቀምጦታል፡፡
እንደገና ደግሞ ከ40 ዓመት በኋላ ፋሺስት ኢጣሊያ ብዙ ዝግጅት አድርጋ ኢትዮጵያን ለመውረር ስትንደረደር ከወልወል ግጭት ጀምሮ ሀገር ፍቅር የሚባል ህብረት በመመስረት ኢትዮጵያዊያን ያሳዩት አንድነት ከዓለም ለየት ያደርጋቸዋል፡፡ እንደሚታወቀው ሊግ ኦፍ ኔሽን ለዚህ ወረራ ወገንተኝነቱን በማሳየቱ የኢጣሊያ ጦር መሀል ከተማ አዲስ አበባ ለመዝለቅ ችሎ ነበር፡፡ በዛን ወቅት ታዲያ ጀግኖች አርበኞች ለጠላት ጦር የእግር እሳት በመሆን በዱር በገደሉ እየተሸሎከለኩ በህብረትና በአንድነት ለ5 ዓመት የአልገዛም ትግል አድርገዋል ፡፡
ሌላው ዳግማዊ አድዋ ተብሎ የሚወራው በ1969 ዓ.ም ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ የተገኘው ድል ነው፡፡ በዚያን ወቅት የሀገሪቱ መሪ የነበሩት ከወታደሩ ክፍል የተገኙት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም የክተት ጥሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲያቀርቡ ገና የሥልጣን ወንበራቸውን በቅጡ አላደላደሉም ነበር፡፡ በዚህ የክተት ጥሪ መሠረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ300 ሺ በላይ የሚሊሻ ጦር በማሰልጠን የሶማሊያን ጦር አይቀጡ ቅጣት ቀጥታለች፡፡
ይህ አስገራሚ የአንድነት መንፈስ እንዴት መጣ ካልን መልሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የተሠራው መንፈሳዊ ልማት፣ የሀገር ፍቅር፣ ዜግነትና ኩራት ህዝቡን በጋራ ጠላት ላይ በአንድነት እንዲነሳና ለድል አድራጊነት እንዲበቃ ስላደረገው ነው፡፡
እንደሚታወቀው የአድዋ ጦርነት ከመደረጉ በፊት ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ላይ ያላደረጉት ደባ ያልማሱት ድንጋይ አልነበረም፡፡ እንደውም ብዙ የታሪክ ፀሐፊዎች በትኩረት ያልዘገቡት በ1884 አካባቢ ተከስቶ ለነበረው ረሀብ የጣሊያኖች እጅ እንደነበረበት ግልጽ መረጃዎች አሉ፡፡ ሆነ ብለው የከብት በሽታ በማስገባት በወቅቱ ከነበረው ከብትና የጋማ ከብት 3/4ኛው እንዲያልቅ መሰሪ ሥራ ሰርተዋል አንዱ የረሀብ መነሻም ይኸው ነበር፡፡
እኔ አሁን ልነግራችሁ የፈለኩት ስለ አንድነት ነውና ልቀጥል
የውጫሌ ውል ፈርሶ ጦርነቱ አይቀሬ ሲሆን አፄ ሚኒሊክ የክተት አዋጅ አወጁ፡፡ በዚያን ጊዜ ታዲያ ሚኒሊክን የሚቃወሙ ደጅአዝማች ጓንጉል የሚባሉ ሽፍታ ነበሩ ጥቂት ተከታዮችም ነበራቸው፡፡ እኚህ ኢትዮጵያዊ አዋጁን እንደሰሙ ከተከታዮቻቸው ጋር ሆነው ስለጥሪው መከሩበት
ደጅአዝማቹ እንዲህ ነበር ያሉት
ይህ ሰው ምን ይላሉ? ጉልበት ያላችሁ በጉልበታችሁ ጉልበት የሌላችሁ በፀሎት እርዱኝ ይላል፡፡ ለመሆኑ የውጭ ጠላት መጥቶ እስኪዋጋን የሚጠብቅ ኢትዮጵያዊ አለ እንዴ? እሱ ኖረም አልኖረም ደፍሮ የሚመጣ ጠላታችንን ማደባየት የሚከለክለን የለም ነበር ያሉት፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የሚኒሊክ የቅርብ የሆኑ ሰዎች ንጉሱን ይቅርታ እንዲጠይቁ ቢመክሯቸው ቅድሚያ ለጦርነቱ ነው ብለው በጦርነቱ ያለምንም ማቅማማት ተሳትፈዋል፡፡
ቆይማ እዚች ላይ አንድ ነገር ልንገራችሁ በዚያን ዘመን የኢጣሊያ መንግስት በኢኮኖሚ አቅሙ ከዓለም አራተኛ ደረጃ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት እንደሚያሸንፍም ከበቂ በላይ እርግጠኛ ሆኖ ነበር፡፡
ወደነጥባችን እንመለስ! ከእነዚህ ድሎች የምንረዳው ነገር ቢኖር ለረጅም ዘመናት አባቶቻችን በትውልዱ አእምሮ ውስጥ የብሔራዊ አንድነት መርሆችን ማስረጽ መቻላቸውን ነው፡፡
የቅርቡን ጊዜ ብናስታውስ እንኳን 1990 ዓ.ም አካባቢ በተከሰተው የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ህዝቡ የቱንም ያህል ከመንግስት ጋር ባይግባባ ለጦርነቱ ያሣየው ዝግጁነትና የከፈለው መስዕዋትነትን እጅግ የሚያስገርም ነበር፡፡ ከማይረባ ሽሮ ይሻላል ሽራሮ እያለ የዘመተው ወጣትና የቀድሞ ሠራዊት ድንበር ለማስከበር ኢትዮጵያዊ አትንኩኝ ባይነቱን ለዓለም አሳይቷል፡፡
ስለዚህ ጦርነት አንድ የቀድሞ ጦር ከፍተኛ መኮንን የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ጦርነት የደገፈው እጅግ ይቃወመው የነበረውን በህገመንገስቱ ላይ የሰፈረውን አንቀፅ 39 ለማስታወስ ይመስላል ብሏል፡፡ ይህ በቂ ጥናት ቢያስፈልገውም አሁንም ወደፊትም በኢትዮጵያውያን ህዝብ ልብ ውስጥ “mysterious magnetism” ሚስጥራዊ ሙጫ ይቀጥላል፡፡ ይህ የአንድነታችን መገለጫ የሆነውን የአድዋንና ሌሎችን የአሸናፊነት ታሪካችንን ለተተከቢው ትውልድ በማስተላለፍ ሊከፋፍሉን የቋመጡትን የባዕዳን ሀይሎች ሥውር ተንኮል መሰባበር ይገባል፡፡
አበቃሁ
አግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ