ጦሳ (xoossa) እና ለቅሶ በዶርዜ

ወልደሐዋርያት ዘነበ

(የዶርዜ ማህበረሰብ የለቅሶ ስነ-ስርዓት Dorze Community Funural ceremony)

ዶርዜና ውሰጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ስለ ፍጥረታት ማለትም ሰማይ፣ መሬት፣ ውሃ ፣ሰውና እንስሳት አፈጣጠር ያላቸው ዕምነት አንድ ነው። እነዚህ ሁሉ በአንድ መለኮታዊ ሀይል እንደተፈጠሩ ኅብረተሰቡ ያምናል። ይህንንም መለኮታዊ ኃይል ጦሳ(xoossa)ጾሳ በማለት ይጠሩታል። ይህ መለኮታዊ ኃይል የሁሉም ነገር ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ሁሉን ማድረግ የሚችልና በሁሉም ቦታ የሚገኝ መሆኑን ያምናሉ። መኖሪያውም ሰማይ (salo) እንደሆነና ምድርን ለፍጥረታት መኖሪያ ወስኖ የሰጠ መሆኑን ያምናሉ።

          ለዚህ ፈጣሪ አምላካቸው በየጊዜው የዕለት ተግባራቸውን ካከናወኑ በኋላም ሆነ በጥዋት ምስጋና ማቅረብና መለመን የተለመደ ተግባር ነው። ለምሳሌ እግዚአብሔር ወዳለበት ሰማይ አንጋጦ ጥዋት ጥዋት በሰላም ያሳደርከኝ አምላክ በሰላም አውለኝ (Xoosso saron ayssiddayso saro peshsha) ወይም ማታ ማታ በሰላም ያዋልከኝ በሰላም አሳድረኝ (Xoosso saron peshshiraysso saron ayssa) ማለት የተለመደ ነዉ።

        ይህ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለመስራት ያቀዱትን ነገር በ “Xoossa” መልካም ፈቃድ የሚፈጸም መሆኑን ለመግለጽ “ጦስ” ካለ (Xoossi giikko) ስለ አንድ ነገር የእውነትነት ቃላቸውንም ሲሰጡ “ጦስ” ኤሮ’ (Xoossi Ero) በማለት ይምላሉ።

       ከዚህ መለኮታዊ ኃይል የበታች ከሰው ልጅ ግን የበላይ ሆነው ሰውንና መለኮታዊ ኃይልን የሚያገናኙ የተለያዩ መናፍስት(Ayyaana) እንዳሉ ያምናሉ። ፀሎታቸውም ወደ መለኮታዊ ኃይል የሚደርሰው በነዚህ መናፍስት አማካኝነት እንደሆነ ስለሚያምኑ ለመናፍስቱ መስዋዕት ያቀርባሉ።

   በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸው በጎም ሆነ ክፉ ነገር በመለኮታዊ ኃይል መልካም ፈቃድ ወይም ቁጣ እንደሚመጣ ያምናሉ። በሽታ ከክፉ ነገሮች አንዱ ሆኖ አንድ ሰው መለኮታዊ ኃይል የማይፈቅደውን ኅብረተሰቡ ያወገዘውን ነገር “ጎሜ”(ግፍ) በመፈጸም የሚመጣ አድርገው ይመለከታሉ።

 ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት (life after death) ያላቸው እምነት አንድ ሰው አንዴ ከሞተ በኋላ ነፍሱ ወደ ፈጣሪ ትሄዳለች የሚል ሲሆን፤ የሞተ ሰው ነፍሱ በሰማይ እንደምትኖርና ሌላ ዘመድ ሞቶ ወደ ሰማይ ነፍሱ ስትሄድ እዚያ መገናኘት እንደሚቻልም ያምናሉ።

ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው አንድ ሰው ሲሞት የሚባልለት አባባል: – በሰማይ ቤት ነፍሱን ይማረው (Salo keethan shemppo maaro) የሚለው ነው። ይህም በሰማይ ቤት ምህረት እንዳለ እንደሚያምኑ ያሳያል። የሞተን ሰው ስም ጠርተው ከማውራታቸው በፊት “ነፍሱን ይማረውና እከሌ” (Shemppo maaroshin oonakoy) የሚለው አባባል ለዚህ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። የሞተ ሰው መንፈሱ ቤተሰቡንና ቤተዘመዱን በተለያየ ጊዜያት ተመላልሶ እንደሚጎበኝ በሕብረተሰቡ ዘንድ ይታመናል። በመሆኑም የሟች ታላቅ ወንድ ልጅ በየስድስት ወሩ ወይም በየዓመቱ ለአባቱ መንፈስ “ኣዋ (Addee ayyaana)” መስዋዕት ያቀርባል ይህም የሞተ ሰው በአካል ባይሆንም በመንፈስ እንደሚኖር እንደሚያምኑ ያሳያል። 

በአከባቢው አንድ በሽተኛ በሕይወት እንደማይቆይ ሁኔታውን አይተው አዋቂዎችና ሽማግሌዎች የበሽተኛው ቤተሰብ ራሱን እንዲያዘጋጅ ያሳስባሉ። ይህ ማሳሰቢያ እንደተሰጠ የሚቀጥለው ተግባር ቤተሰቡ የለቅሶ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ነው።

      ከሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችም ዋና ዋናዎቹ፦ የምግብ ዝግጅት ለማድረግ እህል መግዛት፥ለጠላ(Dana) የሚሆኑ እህሎችን መውቀጥ፥ማስፈጨት፥እንጨት መፍለጥ፥ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።

      መልዕክት(kita) መላክ፦ ይህ ሩቅ ላሉ ቤተዘመድ የሚላክ መልዕክት ሲሆን ይህ መልዕክት ሲላክ ሰውየው አለመትረፉ ሲታወቅ “እከሌ በጣም ታሟል በነፍስ ድረሱ ራሳችሁን አስባችሁ ኑ” ተብሎ ሰዎች በባህሉ የሚፈፀመውን ለማድረግ ተዘጋጅተው እንዲመጡ ይደረጋል።

   በቤተዘመድ በኩል የሚታረድ ከብት ማዘጋጀት፥መከፈኛ ልብስ ማዘጋጀት ፡ በሽተኛው እንደሞተ ወዲያው ለጎረቤትና ለአካባቢው ሰው የስራ ድርሻ መስጠት የመሳሰሉት ይሆናሉ።

      ከዚህ ቅድመ ዝግጅት ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችለው የበሽታውን የኑዛዜ ቃል  ወይም (Baza) መቀበል ነው። ይህንን አንዳንድ በሽተኛ በራሱ ሽማግሌዎችን አስቀምጦ የሚያደርገው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን በሽተኛው ካልተናገረ ሽማግሌዎች ከዘመዶቹ ከተወከሉት ጋር በመሆን እንዲናዘዝ ይገፋፉታል። በዚህ ጊዜ ሀብቱን ለልጆቹና ለባለቤቱ ያከፋፍላል። የሰው ዕዳ ካለበትም እንዲከፍል ያዛሉ። ለሰው ያበደረው ወይም ያዋሰው ገንዘብና ንብረት ካለም ይገልጻል። እንደዚሁም ለራሱ ለቅሶ ማድመቂያ እንዲሆን ገንዘብ ወይም ንብረት ለህዝቡ የኑዛዜ ቃል ይሰጣል። ይህም ወደፊት በውርስ ጉዳይ ላይ ጭቅጭቅ እንዳይነሳና ዕዳ ሳይከፈል ቀርቶ “ጎሜ”(ግፍ) ሆኖ ቤተዘመዱን እንዳይጎዳ በማሰብ የሚደረግ ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት ነው።

   አንድ ሰው ሲሞት ለቅሶ ከመጀመሩ በፊት የሚደረገው በርቀት ያለ ሰውን ስለ ለቅሶው እንዲሰማ ማድረግ ነው። ይህም የሚደረገው በሽተኛው በጠና በታመመበት ወቅት መልዕክት በመላክ ዘመድ አዝማድ እንዲመጣ በማድረግ ሲሆን ይህ ካልተደረገ በሽተኛው ከሞተ በኋላ ቤተሰቦቹና ቤተዘመድ ሩቅ ላለ ዘመድ መልዕክተኛ ይልካሉ። በባህሉ መልዕክተኞች ሁለት ሲሆኑ ከሟች ጋር የደም ዝምድና የሌላቸው መሆን ይገባል።

የለቅሶ አለቃቀስ ሥርዓት ደግሞ እንደሟቹ ሁኔታ ይለያያል።ይህም እንደ እድሜው፡ እንደ የማህበራዊ ከበሬታው ይለያያል። ለምሳሌ ለህጻናት፥ለወጣትና ጎልማሳ የሚደረገው ለቅሶ፤ ለሽማግሌ ወይም ለአረጁ ሰዎች የሚለቀስ ለቅሶና ለጀግና፥ ለባላባት፥ ለአለቃ፥ለካዎና ለደሙሳ የሚለቀስ ለቅሶ አንድ አይነት አይደለም። ይህም ለቅሶው የሚወስደው ቀን፥ የሀዘኑ ክብደትና ቅለት፤ የቅድመ ዝግጅቱ ሁኔታና የመሳሰሉት ይለያያሉ።

        ከታች በምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት በአንድ ወክት በዶርዜ ሐይዞ አካባቢ አንድ ንጉሥ ወይም (Halaka) በሞቱበት ጊዜ የተነሱት ፎቶ ነው።

ከላይ እንደተጠቀሰው በአካባቢው ለጀግና።፥ለሀለቃ ፥ካዎና ለደሙሳ ለቅሶ ሥነሥርዓቱ ይለያል። እናም ለእነዚህ “ኮይሳ” (koysaa) የሚባል የለቅሶ ዜማ እያዜሙ ራቅ ባሉ ቀበሌዎችና አካባቢዎችን በመሄድ የተለያዩ ቅጠላቅጠሎችን፥ሐዴ፥(hade) የነበር ቆዳ፡የአንበሳ ቆዳ፥ የሰጎን ላባ(guchche) ወንዶች ጦርና ጋሻም ይይዛሉ።

    የለቅሶ ዜማዎች ደግሞ፦

ለሴት፦ ችግር ቻይዋ-Dandayee meto dandaye

ታሳዝኝያለሽ-hoo miiggee michees

ታስለቅሻለሽ-hoo miiggee yeessees

ለወንድ ሲሆን፦ የሰማዩ እንቁላል-phuuphulee salo phuuphulee

ታሳዝናለህ-hoo miiggee michees

ታስለቅሳለህ-hoo miiggee yeessees እያሉ ያዜማሉ።

ማሳሰቢያ!

በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች “፣መንግስታዊ “፣መንግስታዊ ባልሆኑ ህጋዊ የሶሻል ሚዲያ ገፆች እንዲሁም በተለያዩ የሀገር ውስጥም ፣ከሀገር ውጭ አስጎብኚ ድርጅቶች። ይህ ሰፊ ማህበረሰብ “መንደር ብሎ “የመጥራት ልማድ አለ። ማህበረሰብ ለመባል ጎሳ ፣አያት ከቅደመ አያት የሚወረስ የዘር ሐርግ ፣የዘር ሀረጉን ከሁለት ወይንም ከዚያ በላይ የሚከፍል መንደር ፣እና የእድሜ እርከን ፣የሚያሟላ ማህበረሰብ እንጂ መንደር አይባልም ። በአከባቢው ከሚገኘው የቱሪስት መዳረሻዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ‘ዶርዜ መንደር ሎጅ እንጂ “አከባቢው ማህበረሰብ ከመንደር በላይ ነው።

ምንጭ ፦ከአከባቢው ሽማግሌዎች ፣

(ፆሲ ኢንጎ ረጅም ዕድሜ ከጤና ጋር “ለዶርዜ ሽማግሌዎች ተመኘሁ )

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *