ጋሞ ከግሪከ (G VS G)

መሥፍን ዳዊት

የሆነ እውነታ ግሪክን ከጋሞ ጋር እንዳነፃፅር አስገደደኝ፡፡ ለምዕራቡ ስልጣኔ ውልደት ቦታ የሆነችው ግሪክ በምን ሂሳብ፣ ቋንቋቻውን ለመጠቀም ከሚያፍሩ፣ በባህላቸው መድመቅ ከማይፈልጉ፣ ትላንት የት ነበርን ማለት ሐጢኣት ከሚመስላቸው ጋሞዎች ጋር ማነፃፀር ፍትሐዊ ነው? አይ አይደለም፡፡ ግን ነው፡፡ ራስህን ከተቀበልህ፥ በእጅ ያለ ወረቅ እንደ መዳብ ካላልህ፥ሁሉም መነሻው እንደዛው ነው፡፡ ምንም ምን የስልጣኔ ጫፍ አይታወቅም። መነሻው ግን ግልፅ ነው። በእጁ ያለውን ሀብት መጠቀም የስልጣኔ እርሾ ነው፡፡ ከምን ልጀምር?

 ግሪክ እና ዴሞክራሲ፡- እ.ኤ.አ. በ507 ዓ.ዓ. የአቴና መሪ ክሌስቴንስ ዲሞክራትያ ወይም “በሕዝብ የሚመራ” (ከዴሞስ፣“ሕዝብ” እና ክራቶስ፣ ወይም “ሥልጣን”) ብሎ የሰየመውን የፖለቲካ ማሻሻያ ሥርዓት አስተዋወቀ። በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀ ዴሞክራሲ ነበር። ይህ ሥርዓት ሦስት የተለያዩ ተቋማትን ያቀፈ ነበር፡፡[1]

ኤክሌሲያ፣ ሕግን የጻፈ እና የውጭ ፖሊሲን የሚመራ ሉዓላዊ የአስተዳደር አካል፤ ቡሌ ከአሥሩ የአቴና ጎሣዎች እና ዲካስቴሪያ የተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ፣ ዜጎች በዕጣ በተመረጡ ዳኞች ፊት ክርክር ያደረጉባቸው ታዋቂ ፍርድ ቤቶች ነበሩት። ምንም እንኳን ይህ የአቴናውያን ዴሞክራሲ ለሁለት ምዕተ ዓመታት ብቻ የቆየ ቢሆንም፣ የግሪክ ቀጥተኛ ዴሞክራሲ ሥርዓት በዓለም ዙሪያ ላሉ ተወካዮቻቸው የዴሞክራሲ መንገድ አሳይቷል ተብሎ ይገመታል። [2]


[1] Democracy’s Beginning: The Athenian Story by Thomas N. Mitchell, 2015

[2] Ibid

Greek Democracy

ጋሞ እና ዴሞክራሲ፡- ጋሞዎች የራሳቸው ዴሞክራሲ ስርዓት አላቸው። በኢትዮጵያ መንግስት ምስረታ ላይ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የነገስታት የመንግስት ስርዓት ተጠቃሽ ነው። አመራረጣቸው ግን ህዝባዊ ወይም ዴሞክራሲያዊ አይደለም። የስልጣን ምንጫቸው፣ ኃይል፣ ገንዘብ፣ ነገድ፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት ወዘተ ነው፡፡ ያ ማለት ዴሞራሲ የለም ማለት ነው፡፡ጋሞዎች ግን በዱቡሻ ስርዓት ህዝባዊ ምርጫ አድርገው በየአካባቢው መሪ በቀጥተኛ ዴሞክራሲ ይመርጣሉ፡፡ መሪዎች፡- ሀላቃ፣ ሁዱጋ፣ ዳና፣ ሞኒቻ፣ ሙራ ተብለው በስልጣን ተዋረድ ይቀመጣሉ፡፡ በሌላ በኩል በነገስታት ስርዓት ልምምድ ህዝባቸውን የሚመሩት ካዎችም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይም እንደነበሩ ይታመናል፡፡

Gamo Democracy

ቴአትር እና ግሪክ፡- የሰው ልጅ በህብረት ተሰባስቦ በዋሻ ውስጥ ይኖር በነበረበት ዘመን ሁሉም በጎሳ ተከፋፍሎ፥ በስልጣንና በስራ መደብ ተለያይቶ፥ ይኖር አንሰነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ በዚህ የህይወት ስልት ውስጥ ወንዱ አዳኝ ሰቷ ደግሞ በዋሻ አካባቢ እና አልፎ አልፎ እርሻና ፍራፍሬ ለቀማ ላይ ትሰማራ የነበረ መሆኑን ሰምተናል፡፡ ታዲያ ወንድ ለአደንም ሆነ መሰል ተግባራት ተሰማርቶ በዚያ ውሎው ከአውሬዎች ጋር ሲታገል፣ ሲገድል፣ ሲፈራ፣ ሲፎክር፣ ሲጎዳ፣ ሲሞትና መሰል ተግባራት ውስጥ ይውላል። ማታ ወደ መንደር ሲመለስ ለጎሳው መሪ የቀን ገጠመኙን ይተርክ ነበር፡፡ ትረካውም ያን ቀን የነበረውን ሁሉ ምስል ከሳች በሆነ መንገድ የሚያሳይ ነበር   ፡፡

ሰው ሰልጥኖ ከተማ ሰርቶ ቤተመንግስት መስርቶ ሲኖር ጭምር የዚህ አይነቱን ክዋኔ ማቅረቢያ ቦታ እንዲኖረው ተፈልጎ እንዲታነፅ ተደረገ፡፡ በኋላም የሰው ልጅ ይህን ተግባር ለአምልኮ፣ ለሀዘን መግለጫ፣ ለደስታ በዓላት እየተጠቀሙ ያሻሽለው ገባ፡፡ ተውኔት የተጀመረውም ከዚያ ነው፡፡ የተውኔት አላባውያን እያደጉ ስሜትን ሰቅዞ እየያዘ ትልቅ መልዕክትን በጨዋታ እያዋዛ እስከዛሬ እየቀረበ ይገኛል፡፡

ወደ ዋናው ነጥቤ ስገባ የግሪክ ጣሪያ አልባ ወይም አምፌ ቴአትር እስከ 30ሺ ህዝብ ሊያስተናግዱ የሚችሉ በርካታ ቤተ ተውኔቶች ነበሩ፡፡ አሰራራቸውም፣ ለተውኔት ማቅረቢያ፣ ለህብር ዝማሬ ማቅረቢያ፣ ለተመልካች መቀመጫ፣ ለተዋንያን ልብስ መቀየሪያ፣ ለንጉሳውያን፣ ለከፍተኛ ባለስልጣኖችና ሀብታሞች መቀመጫ እና ለፀሎት በቂ ስፍራ እንዲኖረው ተደርገው ነበር።በግሪክ ታሪክ የመጀመሪያ የቴአትር መመሪያ ያዘጋጀው  አርስቶትል እንደነበር ይነገራል፡፡

ጋሞና ቴአትር፡-  በየዕለቱ በሲኒማ ቤት ተዘጋጅቶ የሚቀርብ ትርኢት እና የተፃፈ ቴአትር ባይኖርም፣ እንደ ጥንታዊ ግሪኮች፣ግብፆችና ሮማውያን፣ ጋሞዎችም የራሳቸው ክውን ጥበባት በዘፈቀድም ቢሆን የሚያሳዩበት አምፌ ቴአትር ቦታ አላቸው፡፡

ዱቡሻ ሁለት ትርጉሞች አሉት፡፡ አንደኛው የፍትሕና ዴሞክራሲ ስርዓቱ  ሲሆን ሁለተኛው የስርዓቱ መከወኛ ቦታውም ዱቡሻ ይባል፡፡ አቀማመጡም፡- ወንዶች ለየብቻ፣ ሴቶች ለየብቻ፣ አባቶች ለየብቻ፥ ጎልማሶች ለየብቻ ይቀመጣሉ። የወሊድ ጊዜ ያልጨረሰች ሴት በወንዶች መቀመጫ ላይ መቀመጥ በባህሉ የተከለከለ ነው፡፡ በቦታው ትርኢቶች ለሀዘንም ለደስታም፣ለእርግማንም ለምርቃትም፣ ለጋብቻም ለፍችም፣ ለጦር መኮንኖች ሽኝትም አቀባበልም፣ ለሰርግ ፉከራዎች፣ ለሙሾ ድለቃዎች፣ለመሪዎች ስልጣን ርክርክብ መከወኛ ወዘተ በዚህ አንፌ ቴአትር ነው፡፡

የዱቡሻ መሪዎች ጋያ እያጬሱ በምሽት ጨረቃ ተረትና ምሰሌ ይጫወታሉ። አንዳንዴ ገበጣ እየተጫወቱ ይዝናናሉ። ዲታ ወይም ክራር ሲገረፍ ላባቸው ጠብ እስኪል ድረስ ይጨፍራሉ። ይደንሳሉ። ከበሮም በሴቶች ይደለቃል፡፡ አንዳንዴ ፌጣሪያቸውን ይለምናሉ። ምስጋናም ያመሰግናሉ። የዓመት መለወጫ በዓላቸውንና የእርድ ስነ ስርዓቶችንም እዚያው ያከናውናሉ፡፡[1]


[1] የትዝታ ፈለግ፣ አሰፋ ጫቦ ገጽ 90-92

Debusha Of gamo

ግሪክ እና ፍልስፍና ፡- የግሪክ ጥልቅ አሳቢነትና ፍልስፍና ለምዕራቡ ስልጣኔ የውልደት ቦታ እንደሆነ ይነገራል። በሳይንስ፣በኪነጥበብብ፣ በፖለቲካ አጠቃላይ በአፅናፈ ዓለም ላይ ሁሉ ተመራምረዋል። ተፈላስፈዋል፡፡ ዓለምን ቀይረዋል፡፡ የእይታ አድማሳቸው ሰፋ ያሉ ግሪኮች ጥልቅ አሳቢዎች ከጋሞዎች ጋር በብዙ ይመሳሰላሉ፡፡

ጋሞ እና ፍልስፍና፡- ጋሞዎች በካርማ ፍልስፍና ይታወቃሉ። ለሰው መልካም መስራት መልካም ነገርን ያስገኛል። በራስህ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን ነገር በሰው ላይ አታደርግ ይላሉ፡፡ በረከትም እርግማንም የራስ ስራ ውጤት ነው ብለው ያምናሉ። አብዛኛው ጋሞ ሰው ከሞት በኋላ ባለው ህይወት አያምንም። አሁን ባለው ለተጨባጩ ዓለም መልካምን አድርግ። መልካም ነገር ያጋጥማል ብለው ያምናሉ፡፡፡

ግኝትና ፈጠራ፡- ግሪኮች በዓለም አለ የተባሌ የሳይንስ ፈጠራን አበርክቷል። እያበረከቱም ይገኛሉ። ጋሞዎች በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ልብስን በእጁ ሰርቶ መልበስ የቻሉ ናቸው። ሰዎች ቆዳ እንደ ፋሽን በሚለብሱበት ወቅት ከጥጥ ፈትለው ያውም  በጥበብ ለሴትም ለወንድም፣ ለህፃንም፣ ለአዋቂም የሚሆን ልብስ በእጃቸው የሰሩና እየሰሩም የሚገኙ ህዝቦች ናቸው፡፡[1]

አባይን በማንኪያ ብዬ ለዛሬ እዚህ አበቃሁ


[1] የጋሞ ብሔረሰብ የሸማ ስራ ጥበብ በጋሞ ጎፋ ዞን ማስታወቂያና በህል መምሪያ የተዘጋጀ፣ ታህሳስ 2001 ዓ/ም ገጽ 7-18 https://allafrica.com/stories/201607250586.html

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *