በወልደሐዋርያት ዘነበ
ሁላችንም በየራሳችን ቀለም ስንሰባሰብ ሀገር ትደምቃለች!
“ሳሮ” ይላል ዶርዜ “..ሰላም ፣እንዴት ናችሁ ፣ጤናችሁ እንዴት ነው “እነዚህን ሁሉ ትርጓሜ የያዘ ቀለል ያለ ግን ብዙ መልዕክት ያለው ቃል ነው።
እኔም “ሳሮ” ብዬ ጽሑፌን እጀምራለሁ።
እንደ ሀገር ብዙ ያልተነኩ ፣ያልታወቁ ፣ያልተዳሰሱ ባህሎች ፣ወጎች ፣እሴቶች ባለቤት ነን :: እሰይ!ተመስገን ነው።ማወቅ ግዴታችንም ነው ።ሌላ ምን እንላለን ማለት የፈለግነውን እያየን እንጨምራለን ።
እንግዲህ “ሳሮ” ወደሚላችሁ፣በደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ሚገኘው፣የሽመና ጥበብ ባለሟል ወደሆነው የዶርዜ ማህበረሰብ ዘንድ በሥነ-ጹሑፍ ሀዲድ አብረን እንጓዝ ዘንድ ወደድሁ ።አማልክቱ ከኛ ጋር ይሁኑ።
ዶርዜ !!….
የስሙ ትርጓሜ ”የተመረጠ”’ እንደማለት ነው። ሐይማኖት ላይ ያለው ቀናኢነት ከእስራኤላዊያን ጋር ያመሳስለዋል። በመላው ኢትዮጵያ የሚገኘው የዶርዜ ህዝብ ብዛት ከ150,000 በላይ እንደሚሆን ይገመታል። በአፄ ምኒልክ ዘመን ንጉሡ የዕደ ጥበብ ስራ የሚሰሩ ሸማኔ ዶርዜዎች እንዳሉ ሲነገራቸው መጥተው አዲስ አበባ ላይ (ሽሮ-ሜዳ) ይከትሙ ዘንድ እንዲሁም ወደ ሰሜኑ ክፍል ሔደው ሽመና ያስተምሩ ዘንድ አዘው እንደነበረ ይነገራል። በዶርዜ ከ13 በላይ ቀበሌያት እንደሚገኙ ይነገራል ። አከባቢው በሽመና ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሙያ ዘርፎችም የምሁራን መፍለቂያ ፣የጠቢባን መገኛ ነው ።
“ሽመናን ያለ ዶርዜ ማሰብ፣ ንጉስን ያለ መንበር እንደማሰብ ነው” እላለሁ። ሽመና ለመጀመሪያ ጊዜ መሸመን የተጀመረው ከዛሬ “500”ዓመታት በፊት በ1590ዎቹ በዶርዜ “ሂርጶ” ቀበሌ ላይ እንደ ሆነ ይነገራል ። በጊዜው የዶርዜ ማህበረሰብ በሽመና ጥበብ የላቀ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።በዚህም የተነሳ የደቡብ ህዝቦች ለንጉሡ የሚያስገቡት ግብር “‘ቡሉኮ”‘ ነበር። ቡሉኮ ማለት የሽመና አንዱ ምርት ነው !!!…
ስለ ዶርዜ ማህበረሰብ ጥቂት እውነታዎች:-
በኢትዮጵያ ብቸኛው ዕለተ ሰኞ ስራ የማይሰራ ህዝብ ዶርዜ ነው። ለምን ቢሉ ቅዳሜ ና እሁድ ላይ በጨዋታም ይሁን በስህተት የተጣላ ቢኖር ሰኞ ነው የሚታረቀው። በዚህም የተነሳ ዕለተ ሰኞን ‘የማርያም ቀን‘ ይሏታል።(እዛ ጥቁር ሰኞ የሚባል የለም ሃሃሃ)
አዲስ አበባን ‘ቱንጋ’ ብለው ይጠራሉ።(ደማቅ ከሚለው ቃል ጋር ይቀራረባል)
ከ800 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የዶርዜ ኤሊ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መገኛ ናት። ከአክሱም ማርያም ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ተመስርቷል ተብሎ የሚነገርለት ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መገኛም ጭምር ናት።
የዶርዜ ማህበረሰብ አዘውትሮ የሚለብሰው የሽመና ውጤት የሆነውን ድንጉዛ ነው።በደስታውም በሀዘኑም ቀን ይህን ልብስ ይለብሰዋል።አብዝቶ ይወደዋል ከሌሎች አልባሳት ለየት ባለ መልኩ።ድንጉዛን በፎጣ ፣በቀሚስ ፣በሱሪ ፣በሽርጥ መልክ እያደረገ ይለብሳል።”ድንጉዛ ምንድነው ? የትስ ተጀመረ ? ማንስ
ጀመረው ?”ለሚሉ ጥያቄዎች ይሄው መልሱ:-
“ድንጉዛ”
ታሪካዊ አመጣጥ
ድንጉዛ ለመጀመሪያ ግዜ የተፈጠረበት ቦታ “ምንድቄ “ይባላል። የድንጉዛ መገኛ ሚንድቄ!
በሀገራችን ኢትዮጵያ ለብሔር ብሔረሰቦች መለያ የሆነው የባህል ልብስ የ“ድንጉዛ” ስራ በዶርዜ ሂርጶ ተወላጆች አማካኝነት ከ 300 ዓመታት በፊት መሸመን መጀመሩን አባቶቻችን በአፈ ታሪክ ይናገራሉ ።
ታሪክ ሲቆይ አፈታሪክ ይሆናል እያለ እያለ ተረት ይሆናል !
ድንጉዛ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዶርዜ ታላላቆች ማለትም “ለአለቃ ፣ለካዎ፣ዳና ፣ቄስ ፣ደሙሳ መለያ እንዲሆን በሚል የሂርጶ ፓንጎ ተወላጅ አባቶቻችን ከአዕምሯቸው አመንጭተው ፈጥረዋል ።እነኚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ስሞች የማዕረግ ስሞች ናቸው። “ፊትአውራሪ ፣ቀኝአዝማች” ወዘተ እንደማለት ! በጦር ሜዳ ስራ ብቻ አይደለም እነኚህ ማዕረጎች የሚሰጡት ለየት የሚያደርገው እርሱ ነው !
የጥለት አጣጣሉም የራሱ የሆነ ታሪካዊ አመጣጥና ትርጉም አለው። የድንጉዛ ባህላዊ ልብስ ዋነኛ ቀለሞች ሶስት አይነት ሲሆኑ እነርሱም:- ቢጫ ፣ቀይ እና ጥቁር ናቸው።
ቢጫው ፦ የዶርዜ ሚንደቄ የተባለው የዱቡሻው አጥር ምሳሌ ነው
ቀዩ ፦በሚንድቄ “ለፍርድ ፣እርቅ ፣ለስብሰባ ፣ለምክክር ፣ለውይይት እና ለንግሥና የሚቀመጡ የዶርዜ ታላላቆች ማለትም የአለቃ ፣የካኦ የደሙሳ ፣የዳና እና እድሜ ጠገብ አዛውንት አባቶቻችን ምሳሌ ነው ።
ጥቁር ፦”ሂርጶ ማጫራ ማጎ”ህዝቡ ለደስታ እና ለሀዘን በጋራ የሚጠቀምበት አደባባይ ትልቅ ሜዳ ምሳሌ ነው ።
አባቶቻችን እንደሚሉት ቀለማቱ በዘመናዊ መልክ ከመዘጋታቸው በፊት:-
1.ቢጫውን ፦ከተለያዩ ተክሎች በመጭመቅ (በተለይ ጋላሎ ከሚባል ተክል እንጨት )
2.ጥቁሩን ፦ከሰል ፈጭቶ በመበጥበጥ
3.ቀዩን ፦ ከእንስሳት ደም ያዘጋጁት እንደነበር ይገለፃል።
ቢጫው- አጥር
ቀዩ- ታላላቆች
ጥቁሩ- ሃዘንና ደስታ
አሰራሩ ደግሞ
ከመሃል ጥቁሩ አለ። ከጥቁሩ አንዳንድ ቦታ ትርፍ ትርፍ እየሆኑ የወጡ አሉ። ያንን ክፍተት ደግሞ በቢጫው ይሞሉታል። ቢጫው የሚጎድለውንም ቀዩ ይሞላዋል። ቀዩ ግን በአንድ ጎኑ ቀጥ ያለ መስመር ይሰራል።
ይተርጎም ቢባል እንዲህ ሊሆን ይችላል:-
ጥቁሩ መደብ ሰፊው የዶርዜን ማህበረሰብ ይወክላል።ሃዘኑም ደስታውም በዚያ አለ። እንደ ጸብ አልያም አለመግባባት ያሉ ነገሮች ሲፈጠሩ ወደ ሚንደቄ ማቅናት ግድ እንደሚል ያሳያል። እንደዚያም ሆኖ ስምምነቱ ላይመጣ ይችላል አንዳንዴ። ይሄ ክፍተት ታድያ በሃገሪቱ ባለ አዋቂ፣ መምህር፣ ሽማግሌ ይሞ’ላል። የቀዩ መደብ በአንድ በኩል ወጣ ገባ የለውም። የዙሩም መደምደሚያ ነው። ከሽማግሌዎችና ከሃገር አዋቂዎች የሚሻገር ጸብም ሆነ ደስታ እንደሌለ ያመለክታል።
ለቅሶ
በሀገራችን በሁሉም አካበቢዎች ዘንድ ራሱን የቻለ የለቅሶ አካሄድ ስርአት አለ ። በዶርዜ ማህበረሰብ ዘንድ ‘ለየት ካሉ ቋሚ ስርዓቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የለቅሶ ስርዓት ነው ።ይህ የለቅሶ ስርዓት ከሌሎች የሀገራችን አከባቢዎች ምን ለየት ያደርገዋል ?
የዶርዜ የለቅሶ ስርዓት “ባሌ “ተብሎ ይጠራል ።ባሌ ሁሉንም ጠቅልሎ የያዘ ቃል ነው። በባሌ ስርዓት ብዙ የሚካሄዱ ሁነቶች አሉ ። ዳንስ ፣የህብረት ዜማ ፣ሙዚቃ ፣የመጠጥ አይነት ፣የምግብ አይነት ፣የትርኢቱ ስፍራ ፣አለባበስ ፣አለቃቀስ ፣ እነዚህን እና መሰል ትርኢቶችን አጠቃሎ የያዘ ነው ።” ባሌ “ቃሉ ዶርዚኛ ሲሆን ማልቀስ ወይም የአልቃሽ ስብስብ እንደ ማለት ነው።
ይህ ስርዓት ለሁሉም የዶርዜ ማህበረሰብ ክፍል ያለ መድሎ እኩል ይደረጋል ። የባሌ ስነ-ስርዓት የማይካሄደው ሟች በገበያ ቀን ና ሰኞ ዕለት ሲሞት ብቻ ነው ።ዕለተ ሰኞ እንደነገርኳችሁ የማርያም ቀን ተብሎ የተሰየመ ዕለት ነው።በዚያን ቀን የሚካሄደው የዕርቅ ስርዓት ብቻ ስለሆነ ወደ አመሻሽ አከባቢ የባሌ ስርዓት እንዲካሄድ ይደረጋል።
ሌላኛው የገበያ ቀን ነው ። በዶርዜ ህዘብ ዘንድ በገበያ ቀን የትኛውም አይነት የለቅሶ ስርዓት እንዲካሄድ አይፈቀድም። ይህም የሆነው ህዝቡ በገበያ ቀን ያለ የሌለውን አቅም አሟጦ ስለሚነግድ የህዝቡ ኢኮኖሚ እንዳይዋዥቅ ፣እንዳይቀዘቅዝ ፣ታስቦ ነው ።ለቅሶ ስርዓት ከተጀመረ በለቅሶ ላይ ከመታደም ውጭ ሌላ ነገር ማድረግ ስለማይፈቀድ ንብረታቸው ለአደጋ ተጋላጭ ስለሚሆንም ጭምር ነው። ቅድሚያ ሟችን እንቅበር የሚል አይነት አመለካከት በማህበረሰቡ ዘንድ አለ። ባሌን የሟች ዘመዶች ሜዳማ በሆነ ስፍራ ላይ በሩጫ ያስጀምሩታል።የሟችን ቤተሰብ ተከትለው የቅርብ ጓደኛ የሆኑ ሰዎች እየሮጡ በመያዝ ያስተዛዝናሉ። ሩጫው የሚሮ’ጠው ሟች እኛን ጥሎ ሄደ ፣አመለጠን የሚል መንፈስ ለመፍጠር ነው ።የቅርብ ጓደኛ ሮጦ ካልያዘ ሩጫው ይቀጥላል።
ለቅሶ ከሶስተኛ ቀን በኋላ ካልሆነ ቤት ውስጥ ተካሂዶ አያውቅም። የሚካሄደው ሜዳ ፣ገበያ ላይ ነው።የባሌ መርሀ-ግብሩን በነፃነት ለማካሄድ ቤት ውስጥ አመቺ ስላልሆነ ብሎም በዶርዜ አከባቢ ለቅሶ መኖሩ ከታወቀ ሁሉም ነዋሪ ይደርሳል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።
በዚህም ምክንያት ስርአቱ ሰፊ ቦታን ስለሚፈልግ ሜዳ ላይ መደረጉ የግድ ነው።
ለቅሶው ያማረ እንዲሆን የሟች ቤተሰብ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።አንድ የዶርዜ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ “የለቅሶ ስርዓቴ ያማረ ይሆን ዘንድ…” ብሎ በማሰብ የቅርብ ዘመዶቹ ጋር ሳንቲም ይቆጥባል ።ሁሉም እርስ በእርሳቸው ተቀማጭ ገንዘብ ይይዛሉ።ያ የሚቀመጠው ገንዘብ ለቀስተኛው የሚጋበዝበት ነው :: በዕለቱ የሚደረጉ የሚወጡ ወጪዎችን በጠቅላላ የሟች ቤተሰብ ይሸፍናል። ምግብ ፣መጠጥ ፣ ሌላው በእድሜ ጠና ያሉ ወይንም ሊሞቱ ጣር ላይ ያሉ ግለሰቦች የተወሰኑ ሰዎችን በቤተሰቡ አማካኝነት ወደ ቤታቸው በመጥራት የተለያዩ የእንስሳት አይነት በማረድ ሰዎችን ያበላሉ ያጠጣሉ ። ቀብድ መሆኑ ነው።የኔ ለቅሶ ቀን በደምብ አድርገህ አልቅስ !!
ከቀብር በፊት የሟች ቤተሰብበች የሟች የቅርብ ጓደኛ በሆኑ ሰዎች አንድ በአንድ እየተጠሩ ምግብ ፣መጠጥ ይጋበዛሉ። ሟች ወጣት ላጤ ከሆነ እንዲህ ብሎ ህዝቡ እየዘፈነ ፣እየጨፈረ ወደ ቀብር ስፍራ ይጓዛል:-
አቤባ ፣ናይቼክ አቤባ (አበባ ነው ልጁ፤በቅርቡ ያብባል ተብሎ ደረቀ )
ናይቼክ ሜቂሬስ ፣ናይቼ ሜቂሬስ (ልጁ ተሰበረ፤ ከሚሄድበት መንገድ ተሰበረ ፤ተቋረጠ )
ጱጱሌክ ናይቼ ፣ናይቼ ጱጱሌክ (ልጁ እንቁላል ነው በቅርቡ ተሰበረ፤ ተቀጨ )
ሟቿ ሴት ልጅ ስትሆን ደግሞ:-
ናያ ሚችዙ ፣ናያ ሚችዙ (ሟች ታሳዝነናለች ፣ሟች አሳዛኝ ነች )
ሎሊዙ ናያ ሎሊዙ ፣(ታምራለች፤ ሟች ቆንጆ ነች )
ባለትዳር የልጆች እናት ፣አባት ሲሞቱ:-
ሀዲርሳ ኦጌ ፣ሀሆ
የሊሪ ዬጎ ፣ሜቶ (የግራ መንገድ ረዥም ነው፤ ወልዶ ጥሎ መሄድ ችግር ነው ፤ማንስ ሊያሳደግ እንዴትስ ሊያድጉ ነው?)
እየተባለ ሴቶቹ አንሶላ በመልበስ ጭናቸው ስር ልብስ ወትፈው እንደ ከበሮ እየተጠቀሙበት፣ እየዘለሉ ፣እየጨፈሩ ወደ ቀብር ስፍራ ይጓዛሉ ። ወንዶች ቡሉኮ ለብሰው ፣ጦር በመያዝ እየጨፈሩ ፣እየዘለሉ ሽለላ እና ቀረርቶ እያሰሙ ይጓዛሉ ። ከቀብር በኋላ ማልቀስ አይፈቀድም።ወደ ሟች ቤተሰብ ቤት ተሂዶ አይዞን ፣በርታ ከማለት ውጪ ማልቀስ አይቻልም ።
መስቀል (ዮዮ ማስቀላ)
ዮዮዮ ዶርዜ ማስቃላ!!
አከባበር ..
ዮ ማስቃላ
ዮ ኡፋይሳ (ደስታ)
በዶርዜ ባህል የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምረው ከ ነሐሴ 16 ጀምሮ ነው።እስከ ጥቅምት አምስትም ይቆያል ።
በእነዚህ ቀናቶች ማህበረሰቡ ልዩ በሆነ መንገድ ሰላምታ ይሰጣጣል ።ከጓደኞቻቸው ጋር ሲገናኙ እየዘለሉ ፣እየጨፈሩ “ዮዮዮ” ይባባላሉ ።ሴት ፣ወንድ፣እናት፣አዛውንት ፣ህፃናት ሁሉም እርስ በእርስ ሲገናኙ ዮዮዮ እያሉ ሰላምታ ይሰጣጣሉ።የመስቀል በዓል በዶርዜ ብሄረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ነው።በመስቀል በዓል ወቅት ያላገቡ ልጃገረዶች በየምሽቱ ወደ አደባባይ በመውጣት እየዘፈኑ ፣ይጨፍራሉ። ሴት ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ አደባባይ ወጥታ እንድትጨፍር ፣ከቤት ውጭ ከጓደኞቿ ጋር እንድታድር የሚፈቀድላት መስቀል ወቅት ላይ ብቻ ነው።
በመስቀል ወቅት አከባቢ ትዳር የመሰረቱ አዲስ ሙሽሮች በተለምዶ አጠራር “ዎዞ” የሚባል የፀጉር አሰራር አይነት ተሰርተው ፀጉራቸው ላይ በትልቁ ለጋ ቂቤ ይቀባሉ። “ጎዝዳ”የሚባል ጨሌ መሳይ ጌጥ አንገታቸው ላይ በማድረግ ከነጭ ነጠላ የተሰራ ቀሚስ መሳይ ልብሳቸውን ለብሰው በዶርዜ ማህበረሰብ ዘንድ ስመ ገናና እና ታዋቂ ወደሆነው “ቦዶ” ገበያ ይወርዳሉ።ገበያው ከተራራው ስር በሚገኝ ወለል ያለ ሜዳ ላይ ይገኛል ።የራስ ቅሏን ቅቤ መቀባቷ የባሏን ጎሳ መቀበሏን በአደባባይ ለህዝቡ ማሳያ መንገድ ነው ።በኋላም በሥነሥርዓቱ ላይ አዛውንት ሴቶች ከልጃገረዶች ጭንቅላት ላይ ያለውን ቅቤ በማንሳት ወደ ሴት ዘመዶቻቸው ያስተላልፋሉ ።ይህም የሚሆነው መንፈሳዊ ቅናትን ለመፍጠር ነው።ላንቺ የሆነው ትዳር ለልጄም ይሁን እንደማለት ነው ።ምኞት ቢጤ…
በኋላም ሙሽሮቹ ወደ ገበያ የሚወጡበት እና ከህብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበት ሰዓት አለ። በተዘጋጀላቸው ባህላዊ ስፍራ ተቀምጠው “ማድሀ ዳና “ወይም ቦርዴ የተባለ የዶርዜ ባህላዊ መጠጥ በጋራ እየተጎነጩ፣ ዮዮዮዮ እያሉ እየተቃቀፉ ድንቅ ማህበራዊ ክዋኔና የአብሮነት ጊዜ ያሳልፋሉ ።ይህም ስነስርዓት “ሶፌ” በመባል ይጠራል።ይህም ስርዓት የሚከበረው ከእርድ ስነስርዓቱ 3 ወይም 4 ቀን ቀደም ብሎ ነው ።
ለበዓሉ አከባበር በጣም አስፈላጊው ነገር የበሬዎች መታረድ ነው። መስቀል ከመድረሱ ከወራት በፊት በዓሉ ሁሉንም ማህበረሰብ ያማከለ እንዲሆን ሁሉም በየፊናው ይተጋገዛል ።ለምሳሌ ገንዘብ ያለው ሰው የተለያዩ ስራዎችን ራሱ መስራት ቢችል ራሱ ሌሎች ገንዘብ የሌላቸውን ሰዎች ለማገዝ ሲል ገንዘብ ከፍሎ ያሰራል። ገንዘቡን ሲከፍል “ለመስቀል በዓል እንዲሆን ቆጥብ ይለዋል”ከዚህ በተጨማሪ እንደየአቅማቸው የተለያዩ ነገሮችን በዕቁብ መልክ ይጥላሉ።ገንዘብ ፣ጥሬ እህል ፣እንቁላል ፣ቅቤ በዕቁብ መልክ የሆነ ሰው ቤት በታማኝነት ይጣላል። ሲጠራቀም የመስቀል ወቅት ላይ ይከፋፈላሉ። በ15ቱም ቀበሌዎች የበሬ ማደሪያ ስፍራ “ቃታ ካብ “እርከን ዙሪያ ወጣቶች እሳት ለኩሰው እያነደዱ እየዘፈኑ ፣እየጨፈሩ ፣ሌሊቱን ሙሉ ያድሩና በጥዋቱ በሬዎችን ይዘው ብዙውን ጊዜ ገበያ በሚካሄድበት ትልቅ ሜዳ ላይ ይወጣሉ።በመስቀል ቀን 2,000 ሺህ እና ከዚያ በላይ በሬዎች ይታረዳሉ።በዓለማችን በአንድ ቦታ ላይ ከ ሁለት ሺህ በላይ በሬ የሚታረድበት ቦታ ከዶርዜ ውጭ እስካሁን አላየሁም ።በአደባባይ በሬዎችን በማረድ ጥሬ ስጋ እየተበላ ቦርዴ ማድሀ፣ጠጅ ፣አረቄ እየተጠጣ ይውላል ።
በዚህን ቀን ስጋ የማይበላ አንድም ሰው የለም ተብሎ ይገመታል ። በዓሉ በአንድነት ስለሚከበር ስጋ ከጤና ጋር ተያይዞ ካልሆነ የማይበላ ማህበረሰብ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም ።
ሌላው የሚገርመው ክረምት እንደ ገባ አንድ ትልቅ ሳር የሚበዛበት ስፍራ ይታጠራል ።ልክ የመስቀል ቀን ያ ሜዳማ ስፍራ ይከፈታል። የተለያዩ የቤት እንስሳት ያለማንም ከልካይ ሳሩን ይመገባሉ ።የዶርዜ መስቀል እንኳን ለሰው ልጅ ለእንስሳትም ጥጋብ ገው ።
መስቀል ለዶርዜዎች ሁለመናቸው ነው። ያላቸውን አቅም አሟጠው የሚያከብሩት ትልቅ በዓል ነው ።
ሀባ ማስቃላ
ዮ ዮ ዮ ሀሹ ጋቲሬስ ።
ሁሉም በየራሱ ቀለም ሀገሩን ያድምቅ!