ዶርዜና የቀርከሃ ቁርኝት

ዳኪዪ ኦሊሴ

ቀርከሃ የሣር ቤተሰብ ዝርያ የሆነ በተፈጥሮ ወይም በሰው ሰራሽነት ሊለማ የሚችል የደን ዓይነት ነው። ቀርከሃ በቁመቱ እስከ ስድስት ሜትር ሊደርስ የሚችል ሲሆን ያለቅርንጫፍ እስከ አራት ሜትር ሊረዝም ይችላል። ቅርንጫፎቹ ቀጫጭን ቅጠሎች ያሉት ሆኖ በስብጥር የሚያድግ ፤ ቅጠሎችም ቀጫጭን ሆነው ለእንሰሳት መኖነት የሚያገለግሉ ናቸው። ቀርከሃ ብዙ ዓይነት ዝርያዎች ሲኖሩት ጻርዞ፣ ላሌ እና ሶልኬ በዋናነት ይጠቀሳሉ። ጻርዞ የሚባለው የቀርከሃ ዓይነት ከሁሉም ዓይነቶች የበለጠ ጠንካራና ለቤት ሥራ የሚመረጥ ነው።

ቀርከሃ ለዶርዜ ብሔረሰብ ሁለንተናዊ ነገሩ ነው። ቀርከሃ በዶርዜ ማህበረሰብ እለት ተዕለት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል። በዶርዜዎች ከመግቢያ በር እስከ ማጀት ቀርከሃ ያልገባበት ምንም ነገር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከመግቢያው ስንጀምር የእያንዳንዱ የዶርዜ ሰው መኖርያ ቤቱ በአጥር የተከለለ ነው። ይህ አጥር የሚሰራው ከቀርከሃና ከቀርከሃ ብቻ ነው። የአንድ አባወራ ቤት አጥር ርዝመቱና ስፋቱ እንደ አባወራው የይዞታ መጠን ሊለያይ ይችላል። የአጥር መለኪያው “ሶሜ” ይባላል። አንድ ሶሜ ማለት የአንድ ቀርከሃ ሙሉ ርዝመት ነው። የአጥር ቀርከሃ ሲቆረጥም መለኪያው ሶሜ ነው።  የተወሰነ ቀርከሃ በቁመቱ እንዳለ ይሰነጠቅና ሌላው ደግሞ እንደአስፈላጊነቱ በሁለት ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ወይም ባነሰ ቁመት ተቆራርጦ ይሰራበታል። በሌላ አባባል ሶሜ ሲባል የአንድ ቀርከሃ ርዝመት መሸፈን የሚያስችል የተቆራረጠ ቀርከሃ መጠን እንደማለት ነው። በርዝመቱ መጠን የሚሰነጠቀው ቀርከሃ “ኢቄ” ይባላል ይህም ወደ አግድመት የሚዘረጋው ነው። የኢቄ ቁጥር እንደ አጥሩ ከፍታ ይለያያል ዝቅተኛው የኢቄ ቁጥር አምስት ሲሆን ከፍተኛው ሰባት ነው። የአጥሩ ዋና መግቢያው አካባቢ ያለው አጥር ዌንቾ ይባላል።

የዶርዜ ቤት፦ የዶርዜ ቤት ሙሉ በሙሉ የሚሰራው  ከቀርከሃ ውጤት ብቻ ነው። ቋሚው፣ማገሩ፣ ወራጅ የቤቱ ልባስ(ቆርቆሮው) ሚስማሩ ሙሉ በሙሉ የቀርከሃ ውጤቶች ናቸው። እንደ ቆርቆሮ የሚያገለግለው አዲስ የበቀል የቀርከሃ ተክል ነጭ ልባስ ነው፡፡ ይህ ልባስ “ቃታ” ይባላል። አዲስ የበቀለው ቀርከሃ እያደር እየዋለ እየጠነከረ ሲሔድ ነጩ ልባስ ቃታ ከቀርከሃው ይላቀቅና ለቤቱ ልባስ ይሆናል።

መጀመርያ ቀርከሃው ተቆርጦ ተሰነጣጥቆ ለተወሰነ ጊዜ እንዲጠወልግ ይደረጋል። የዶርዜ ቤት በቅርጽ ክብ ሲሆን ለትላልቅ ቤቶች እንደ ሳሎን የሚያገለግለው ‹‹ዞኖ›› ይባላል፡፡ ይህም እንደ ዝሆን ኩምቢ ወጣ የሚለውን ወይም እንደ አፍንጫ ከፍ ያለውን ይይዛል። ቋሚው ከተተከለ በኋላ ዙርያውን ተሰንጥጥቆ የጠወለገው ቀርቀሃ ዙርያውን ተሠባጥሮ ከቋሚዎቹ ወደፊትና ወደኋላ እየተደረገ እስከ ላይኛው ጫፍ ይሰራል።

Dorze cultural House

ይህ ከፍታው እየጨመረ ሲሄድ ከላይ እየጠበበ ይሄድና ጫፍ ከመድረሱ አስቀድሞ ከግራና ቀኝ መስኮት ይሰራለታል። መስኮት ከተሠራ በኋላ ጫፍ ሲደርስ የቤቱ ሥራ ማብቂያ ላይ ሁሉም ቋሚዎች አንድ ላይ ተሰብስቦ የተሰራ ከመካከለኛ ብረት ምጣድ ስፋት የማይበልጥ ባጥ ይሠራና ማሰርያ ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ከፊት ለፊቱ የሚታየው የዝሆን ኩምቢ የሚመስለው “ዞኖ” የተሰኘው የቤቱ ክፍል የሚሠራው። ዞኖ ለትንሽም ሆነ ለትልቅ ቤት ይሰራል፡፡ ነገርግን የትልቅ ቤት በመጠን ሰፋ ብሎ እንደ ሳሎን የሚያገለግል መለስተኛ ክፍለ ይሰራለታል፡፡ ይህ ዞኖ ተብሎ ይጠራል/ ይለያል/። የቤት ሥራው ከፍታው እየጨመረ ሲሔድ እንደ መሰላል የሚያገለግል ድፍን ቀርከሃዎች ተሰባጥረው ግድግዳውን በመብሳት እንደአስፈላጊነቱና እንደቤቱ ከፍታ በሶስት ወይም ከዚያ በበለጠ ደረጃዎች ያሉት ‹‹አጋሌ›› በመባል የሚታወቅ መወጣጫ ይሰራለታል።

ከዚህ በኋላ ነው የቃታ ማልበስ ሥራ የሚጀመረው። ይህ የቤት ልባስ ቃታ ከቤቱ ጋር የሚያይዘው “እያለ” እየተባለ የሚጠራ ከተሰነጠቀ ቀርከሃ የሚሰራ እንደ ሚስማር በሚያገለግል ከአሥራ ከአምስት እስከ ሃያ ሴንቲሜትር ርዝመት ባለው   ሚስማር ይያያዛል። 

የቀርከሃ ልባስ

የዶርዜ ቤት ተሠርቶ ከተጠናቀቀም በኋላ የውስጥ ክፍፍልም ለማድረግ የሚጠቀሙት ቀርከሃ ብቻ ነው። የዶርዜ ትልቁ ቤት “ዎጋ ኬሣ” ይባላል፡፡ ትልቁ ቤት ማለት ነው። ይህ ቤት ከዞኖው ውጪ እንደሁኔታው አራት ወይም አምስት የውስጥ ክፍፍሎች ይኖሩታል። ዋና መግቢያ ላይ ያለው ዞኖ ይባላል፡፡ እንደሳሎን እንግዶች የእንግዳ መቀበያና መቀመጫ ነው። ከዞኖ በኋላ ወደ ውስጥ ሲገባ ‹‹ቆልአ›› ይባላል። ቆልአ ብዙ የውስጥ ክፍፍሎችን ይይዛል፡፡ እነዚህም የእንስሳት ጋጣ “ኦሻ” ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ይህም በቀጭኑ የተሰነጠቀና የሚያምር ጌጠኛ ከቀርከሃ የተሠራ”ቁሩጾ” ይከለላል። ይህ ቁሩጾ ከዞኖ በኩል መግቢያ ወደ መጨረሻው አካባቢ ደግሞ ሌላ በር ይኖረዋል፡፡ ይህም ከኦሻ መውጫነት ያገለግላል። ይኸኛው ቁሩጾ ከዳር እስከ ወድያኛው ዳር ድረስ የጠላ መጠጫ ቅል በየደረጃው ይሰቀልበታል። ለማንጠልጠያነት የሚያገለግሉ የቀርከሃ ስንጥቅጣቂዎች ቁሩጾው ላይ የሚተከሉ ሲሆን ቅሉ የራሱ ማንጠልጠያ ስላለው ይሰቀልበታል። የሚንጠለጠሉ ቅሎች መጠን የእማወራዋን የቤት ውሰጥ እቃ የመያዝና መንከባከብ መቻል እንደአመልካች ያዩታል። ሌላኛው የውስጥ ክፍፍል የአባና እማወራ የማደርያ ክፍል ነው፡፡ የሚቀጥለው የእቃ ቤት “ኡጉራ” የሚባል ሲሆን የሚቀጥለው የልጆች መኝታ ክፍል ነው። ይህ ሁሉ የሚከፋፈለው በቁሩጾ ነው። ሌሎች አነስተኛ ቤቶች እንደ ትልቁ ቤት ክፍፍል ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ቢኖርም እንኳ ከላይ የተገለጹትን የትልቁን ቤት ክፍፍል ያሟሉ ላይሆኑ ይችላሉ።

የአንድ አባወራ ግቢ ከዎጋ ኬሣ (ትልቁ) ቤት ሌላ ትናንሽ ቤቶች ይኖራሉ። “ኤምበሬ ኬሣ” ይህ እንደ ማዕድ ቤት የሚያገለግል ሲሆን እንደሁኔታው የቦርዴ ማስቀመጫነት ያገለግላል። አብዛኛው የአባወራዎች ግቢ የጠላ ማስቀመጫ ቤት ከማድቤቱ የተለየ ይሆናል። ሌላው አባወራው ሸማውን የሚሰራበት ቤት ነው ይህም “ጋባራ” ይባላል።  አሰራሩም ከዋናው ቤት በአጀማመሩ ተመሳሳይነት ሲኖራቸው በአጨራረስ የሚለይ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ከቀርከሃ የሚሰራ ነው ።

በሸማ ሥራ ያለው ሚና፦ ቀርከሃ በሸማ ሥራ ላይ የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የሸማ መስሪያ ሀርፖ (አርብ) መሥሪያነት አገልግሎት ላይ የሚውለው በዋናነት ቀርከሃ ነው። የሀርፖው ጥርስ የሚሰራው ከዚሁ ነው። ጥርስ ማለት ሁለት የድር ክሮች አልፈው ወደ መን መሸጋገርያው ማለት ነው። መን ማለት የሸማ ሥራ ሲከናወን ከፍና ዝቅ የሚለው አካል ነው። ይህም የሚወጠረው አራት ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ሁለቱ በአንደኛው መን ላይ ቀርከሃ ሲሆኑ ሌሎች ሁለቱ በሌላኛው መን ላይ ይሆናሉ።  ሸማ እየተሰራ የሚጠቀለልበት ዎንድራሼ (መጠቅለያ)፣ ሸማ ሲሰራ ድር የሚወጠርበትና አርቡ የሚሰቀልበት ሁሉ ቀርከሃ ነው። ይህ ሲባል ቀርከሃ ካልሆነ ለመስቀያነት አይሆንም ማለት አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተሻሻለው አሰራር የባህር ዛፍ አጣናና ሌሎችም እንጨቶች ይሆናሉ።በጥበብ ሥራ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት ማጾ ሚሣና አሦ የሚሣ ናቸው። ማጾ ሚሣ ማለት ጥበብ ሲሰራ እያንዳንዷን ድር ወደ ላይና ወደ ታች በማድረግ የጥበቡ ዲዛይን መልክና ቅርጽ ይዞ እንዲወጣ የሚያደርገው በዋናነት የሚጠቀስ መሣሪያ ነው። አሦ ሚሣ ግን በማጾ ሚሣ የተሰራውን ዲዛይን ለጥበቡ ግማሽ ምዕራፍ በኋላ ያለውን ዲዛይን ወይም ቅርጽ ይዞ ለማቆያነት የሚያገለግል ከቀጭን የቀርከሃ ሰንጣቂዎች የሚሰራ በጥበብ ስራ ጉልህ ሚና የሚጫወት ጭራሮ መሰል ነው። ይህ ሲሰራ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው። ጭራሮው የሚያርፈው ከመን በኋላ ስለሆነ ድር የመበጠስ ዕድል ሥላለው በደንብ በብርጭቆ ወረቀት መለስለስ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ሲያስወጡትና ሲያስገቡ ድር የመበጠስና ሥራውን የማደናቀፍ እድሉ የሰፋ ስለሚሆን ነው። የድር ማድርያና ድውር ሲደወር ማጉ የሚሰቀልበት ‹‹ ዋጉምቦ ›› የሚሰራው ከቀርከሃ መሆኑን አለመግለጽ የቀርከሃን ውለታ መዘንጋት ይሆናል።

የቤት ውስጥ መገልገያዎች

ኬቼ ሙሉ በሙሉ የሚሰራው ከቀርከሃ ነው። ይህም ቁስ የሚያገለግለው እንሰት ከተፋቀበት ወደ ቤት ወይም ወደ ማከማቻ ስፍራ ለማጓጓዝ ነው።  ሌላው ኬቼ የእንስሳትን እዳሪ ከጋጣ ከወጣ በኋላ ወደ ማሳ የሚያጓጉዙበትም መሣሪያ ነው።

እንዝርት (ልቃቃ) ልቃቃ (እንዝርት) ለዶርዜ ሴቶች አንደ ዋነኛ ማምረቻ መሣሪያ ይቆጠራል። ምክንያቱም አብዛኛው የዶርዜ ሴቶች ፈትልን እንደዋነኛ መደበኛ ሥራ ስለሚቆጥሩ ነው። አንድ ሴት ከአንድ በላይ የመፍተያ እንዝርት ይኖራታል። ሁለት የእንዝርት ዓይነቶች ሲኖሩ በዋነኛት የሚጠቀሰው የመፍተያ እንዝርት ሲሆን ሌላኛው ‹‹ቦጼ›› በመባል ይታወቃል። ይህም የተፈተለውን ልቃቂት ለማዳወርያነት ወይም ለማዳወር ለማመቻቸት ያገለግላል።

ዳቾ፦ የቅርጫት ዓይነት ሲሆን ለፈትልና የፈትል ውጤቶች ማስቀመጫነት የሚያገለግል ነው። ዳቾ ሁለት ዓይነት ሲሆኑ አንደኛው ዕለታዊ የሚፈተል ጥጥንና ተፈትሎ የወጣ ልቃቂት ማስቀመጫ ነው፡፡ ይህም ፑቶ ዳቾ ይባላል፡፡ ይህም ማለት የጥጥ ዳቾ ማለት ነው። ይህች ዳቾ ሴቶች ለቡና ሲሄዱም ቀላል ስለሆነች ይዘዋት ይንቀሳቀሳሉ። በመሰረቱ የዶርዜ ሴቶች ቡና ሲጠጡ ሆነ ሲያወሩ እየፈተሉ ወይንም ጥጥ እየፈለቀቁ ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ቅርጫት ሸሬ ዳቾ ይባላል። ሸሬ ዳቾ በመጠንም ከፑቶ ዳቾ ከፍ የሚል ሲሆን ብዙ ነገሮችን ለመያዝ ያስችላል። ሼሬ ዳቾ እናቶች የፈተሉትን ልቃቂት የሚያጠራቅሙበት ፣ የራሳቸው የሆነ ውድ እቃዎችን እንደ “ዮሻ” ሴቶች ከጫጉላ ቤት ሲወጡ የሚያጌጡበት ጨሌ የሚመስል ውድ ዕቃና ሌሎችንም እንደወርቅ የመሳሰሉትን እንደ ዛሬ ሣጥን በሌለበት ወቅት ለማስቀመጫነት ያገለግላል።

ማይሌና ጋሩማ፦ ለእንሰት መፋቂያነት የሚያገለግሉ ከቀርከሃ የሚሰሩ የቤት ውስጥ መገልገያ ናቸው።ሁለቱም የሚሰሩት የበለጠ ውጤታማ ሆነው እንዲያገለግሉት ጻርዞ ከሚባለው የቀርከሃ ዓይነት ነው።ማይሌ በመጠን አነስ ያለ ሲሆን ለቆጮ መፋቂያነት ያገለግላል።ነገር ግን ጋሩማ  በመጠን ከፍ ያለና የበለጠ ጠንካራ ሲሆን ከቀርከሃ ከታችኛው ክፍል ይሰራል፡፡ ይህም የእንሰቱ ሥር (corm) ጠንካራ ስለሆነ ለመከትከቻነት ያገለግላል።

ሾንቴ፦ ሾንቴ ለማማሳየትና ለማዋሀጃነት የሚያገለግል ሲሆን በአብዛኛው ለገንፎና ቂንጬ መሥርያነትና ቅቤ ከቂንጨው ወይም ከገንፎ ለማዋሀጃነት ያገለግላል።

ኮንጬ፦ ይህ እንደ ሹካ ሶስት ወይም አራት ጣት እጀታ ያለው ለመብያነት የሚያገለግል ቁስ ነው።

ስለዚህ ቀርከሃ በዶርዜዎች ሕይወት የሚጫወተው ሚና ዘርፈ ብዙ ነው።

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *