ወንድማገኝ ሶሪ

©Artsper (The Hopeless Madhouse by Renjie Gao)
“ስሜን ተውት” አለ የተቸገረው መላኩ ስሙን ቢፈራው። እኔም እንዲያ ማለት ያሻኛል። መጀርፈፌ፥ መኮርፈፌን ያዩ ሁሉ፣ “ደራሲ ወንድማገኝ” እያሉ በየ አረቄ ቤቱ ማጣጫ፥ በየ ቡና መጠጫው ሀሣብ መወርወሪያ፥ ቢያደርጉኝ እራሣቸው ሊሉት ያሠቡት ነገር አለ ማለት ነው። ደራሲው ፥ያ ወንድማገኝ፥ ያ ብቻውን ጥግ ላይ ሚቀመጠው፥ የሚሉኝን እውነት ብዬ ተቀብዬው ይሆንን?
ደግሞም የቀድምው መምህሬ “ተው አንተ ልጅ ቢያንስ አንድ ሥራ ልትሠራ ግድ ነው” ቢለኝ የውስጥ መብከንከኔንና ኩርፊያዬን፣ ብዙ እልበታለሁ ያልሁትን የጽሑፍ ሥራዬን ሰጥቼው ነበር። ዛሬ ላገኘውና በጽሑፌ ልንወያይ ነው ወዲህ የመጣሁት።
አዎን እንደሁልጊዜው ቀድሞኝ ተከስቷል ። የሠጠሁትን ጽሑፍም እያነበበው ነው። ገረመኝ። ደግሞት ነው አልያም ገና አሁን እያነበበው ነው።
“ልቀመጥ ወይስ ሌላ ሚጠብቁት ጥቁር እንግዳ ይኖር ይሆን?” ፕሮፌሰር ። የእኔው ጥያቄ ነበር።
አያይ አንተው ነህ እንግዳዬ ልጅ ወንድምአገኝ።
ጥሩ (ተቀመጥሁ)
ብዙ አወራን———–
ከማን ጋር?
ከስራ ጋር።
እናሣ? (ዓይኔን ወደ ወረቀቱ ጣል አደረግሁት)
ከቤት አየወጣሁ ነው ይላል። ትዝ አለኝ። በዓይነ ኅሊናዬ እንደ ገጣሚዎቹ የጻፍሑትን በቃል ተወጣሁት። ተንስኡ ማለት አሻኝ እንደ ካህኑ። ለማንኛውም ተነሳሁ። ተከተሉኝ። ጽሑፌም እንዲህ የሚል ነበር።
ከቤት እየወጣሁ ነው——–።
(እና ምን አገባን?) ልትሉ እንዳይሆን? ምን አገባንን ምን አመጣው? ፍራቻዬ ከዳር የተነሳው እሳት ከዳር አያበቃም።የሚበላውን በልቶ ወደ መሐል ይተማ’ል እንጂ።
ደግሞ እዚሁ ቅርብ፥ እኛው ከተማ ብዙ ተማሪዎች ከትምህርት ሲመለሱ፣ እናታቸውን ከፍርስራሽ መሐል እንባዋን ጨርሳ፥ እ–እታዋን ተኮራምታ ሲታዜም ያገኙበት ጊዜ ብዙም ሩቅ አይደለም። ትናንት እንጂ! እውነት ይህ የሚረሣ ሆኖ ነው? ወይስ መርሳቱ ተሽሎን አግኝተነው?
ለማንኛውም ከቤት እየወጣሁ ነው ስል አጃኢብ የሚያሠኝ ፈጠራ ሁኖ ሣይሆን፥ አንድም የጊዜ ሚዛኑ ወዲህ ካጋደለ ይህ ቤቴ አመድ ሁኖ ሊጠብቀኝ ይችላል የሚል ፍራቻ፤ ሲቀጥልም ወጥቶ መቅረት ምንም የሆነበት ሀገር ላይ ከመኖሬ አንጻር ስጋት ቢኮፈኩፈኝ ነው።
ዛሬ ላይ የሚደረጉት ነገሮች ያን ያህል ጊዜም፥ ባለሙያም፥ ዕውቀትም አይሹም። (አይሆንንም ትተሽ ይሆናልን ማሠብ ሣይሻል አይቀርም።) የነበረው እንዳልነበር፥ ቁምነገሩ ቅዠት፥ ቅዠቱ ተረት፥ ከአሉ’ ነበሩ ላለመሆን ነው።
እኔ የምለው ሠፈሬ እንዲ የሆነው ከመቼ አንስቶ ነው? (በሀሣብ ብዙ ተጓዝሁኝ መሠለኝ ከሀገር የመውጣት ያህል ነው የደከመኝ አንተዬ።) ሰው ሀገር ያለሁ ይመስል ‘ባር ባር’ የሚለኝስ ነገር በጤናዬ ነው? ለቀዬው ባዳ ሆንሁና የማየው የተፈቀደልኝን ነው። ከምን ተነስተን ምን ላይ ደረስን ጃል?
“ወንድም ራበኝ ” ከሀሣብ ከናወዝሁበት የሚያናጥብ ድምፅ።
ድምፁን ወደሠማሁበት ፊቴን ቀለስኹ “እኔን ከሆነ እንዳልስቅ” በሚመስል ምፀት አየሁት። መልከ ጥፉ ነው። ከናፍሩ በሲጃራ ያረረ፥ የወነቸፈ ወጣት እያጉረጠረጠብኝም መሠለኝ። ቆይ ግን ያ ሠበር የምንለው ነገር፥ ትህትናችን ምን ገባ? አደራውን የበላሁት እንጂ ምፅዋት ጠያቂ አይመስልም ‘ኮ። በእርግጥ አንገቱን ደፍቶም ጠየቀ ተወጣጥሮ ምን አለኝ የተሻለ የምሠጠው? ከሀፍረቴ ውጪ ልስጥስ ብል ምኔን? ይሄኔ አይደል “ከባዶ ላይ መዝገን” የሚባለው?
እሡስ ምን ተዳው ብሎ? “በዊልቸር የሚለምንን ምስኪን ብር እንድሠጥህ መጀመሪያ አስነዳኝ” አይነት ደፋሮች መሀል ሁኖ ስለምን ይልመጥመጥ? አበጀ! ለማንኛውም አራዳ ነው። ዓይኖቼ ስር ኪሴን አወቀው። የሽሙጥ ጥርሱን ፈልቅቆልኝ ሄደ። እእእእእፍ…ፎይ! ለካ የጠያቂዎችን ያህል ሠጪም ይጨነቃል።
አይ ጉዴ! ወገኛ! አሁን እኔ ምኔ ነው ሠጪ? ዱዲ ኪሴ ሣይኖር? ማን ይሙት ፈጣሪ ይክፈላት እንጂ እህቴ ያጠበችልኝን ለብሶ ከመውጣት ባሻገር በኔና “በየኔ ቢጤው” መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? እሱ እውነቱን ተቀብሎ ሲጋፈጥ እኔ ደግሞ በዝምታ ስናውዝ አይደል ጎዳናው ያገናኘን?
“አትሠማም!?” የሆነ ድምፅ ባረቀብኝ። አንደኛውን በመታኝ ሳይሻል ይቀራል? አልሰማም እንዴ? ጆሮዬ እኮ ለወትሮ ማልፈልገውን ሁሉ እየሠማ የሚያናድደኝ አካሌ ነበር። ዛሬ ምን ነካው የሚያሣ’ጣኝ?
“ዎዎዎዎውዎሽሽሽ” ለፉጨት በቀረበ ቃል። ማን ነው? መቼም እኔን አይሆንም። እንዴታ? እሠማለሁ እንጂ። ተናደድኩ ቁጣ ቁጣ አለኝ። ” አህያ? ….” እርፍ! ይለይለት። ምን እንዳደረግሁት እንጃ። በያዘው የጎማ ጅራፍ ቂጤን ዣጥ ቢያደርገኝ ደስታውን አይችለውም። “አህያያያያያያ”
እሡ ምንም ከኔ ቢርቅም የሚነዳት አህያው ከዓይኔ፥ ቃሉ ከአእምሮዬ ሊወጡ አልቻሉም። (ይህ ንግግር የአህያ ነጂው ብቻ ሀሣብ ነው የሚለውን መቀበል ተሣነኝ።) ሁላችንስ ከዚህ አዘቅት ያልወጣን አይደለምንን? የመሪና የተመሪው ሚና ያለ’የበት፥ ተመሪው ከመሪው የቀደመበት ጭምር እንጂ። እሠየው ሰደበኝ። አዎ አህያ ነኝ። አህያ ነን። ዝም ብለህ የምትሸከም፥ ዝም ብለህ የሠጡህን እንክርዳዱንም ግብስባሱንም የምትግፍ ከሆነ የኋላ ኋላ በቁንጣንህ የሚስቁት እነሡ ናቸው ። እነሱን እንደ ብዙ አንተን እንደ ምንም መቁጠር ያላቆምህ ዕለት አዎን አህያ ነህ ። ነን።
እነሱም እንደ ነጂው ስድብ ከምስጋና የተምታታባቸው የቀን ሰካራሞች፥ የተደናበሩ ድንባዣም አይደሉምና ነው? አሁን ይሄን ሁሉ ስዘበዝብ የሆነ የከፋው መምህር፥ አልያም የተቃዋሚ ፖርቲ አባል መስዬ ይሆናል።
እንዳይመስልህ። የወጣልኝ ስራ ፈት ነኝ። መንግስት ኮርቶብኝ እንደ ንብረቱ የቆጠረኝ፡፡ እናታችን ናት እኔና ዘጠኝ እህቶቼን በNGO ፅዳት ሰርታ የምታስተዳድረን። እውን ማስተዳደርስ የእሱ ፋንታ አልነበር? የላይኛው ጌታ። እሡን ተወውና እኔስ እህቴ ያጠበችልኝን አይደል ለብሼ የምወጣው፡፡ ምን ይሉት ስንፍና ነው ግን የተጠናወተን? ቢያንስ ስራ የለኝ፥ ጊዜ አላልቅ ብሎኝ እንደኔም የሚንገላታ የለም፡፡ ታዲያ ምን ነካኝ ቢያንስ ልብሴን ላለማጠብ ለግሜ እሷ ያጠበችልኝን እየለበስሁ የምወጣው?
የት ነው ግን የምሄደው? እንዴት ሰው ቢያንስ ሀገር አይበጠብጥብም? እኔስ ለመበጥበጥ ምንድን ነው የቀረኝ በደል? ጎረቤታችን ሱዳን ሁለት ለመሆን አንገሸገሸኝ ስትል እውነት እንደሚሉት ዳቦ ስሙኒ ገባ የሚል ታሪክ ከሆነ እንደሱዳንም ቄንጠኛ የለ። ኧረ ቀበጠች!
እሺ የእሷስ ይሁን የእኛዋስ ምን ነክቷት ነው? ሆደ ሰፊነቱን ከየት አመጣችው? አንዳንዴ ምርር የሚያደርጉ ነገሮችን ጠፍተው ነው? ስል እራሴን እጠይቃለሁ። ግና ብዙ ብዙ የእናቴ እኛን አስተኝታ፥ ወደ ፈጣሪዋ አንጋጣ፥ ያለቀሰችው እንባ እውን ለፈጣሪዋ መባ ይሆን? ወይንስ ብዙ ድንጋይ የሚያስነሱ ብዙ መፈንቅለዎችኝ በየለቱ ሚያስደርጉ ጉዶች ነበሩ? ግን ካለው ይልቅ የሚመጣውን ፍራቻ፣ የሌሉ ያህል ኦና ውጦን አስፈሪ ዝምታ ውስጥ ገብተናል። በቃ የሙት ልጅ ክብር የለውም ሆነና ነው በሙት አባቴ የማላውቀው ታሪክ እንዲህ አሳሬን የማየው?
የሠፈራችን እድር ግምጃ ቤት ሃላፊ ፊቴ ድቅን ብለው በዓይናቸው በአፍ ጢሜ ከደፉኝ በኋላ፥”እናትህ የእህቷን ሞት ተረድታ ኡ…ኡ…ኡታዋን እያቀለጠች ቁልቁል ዘልቃልሃለች” አሉኝ፡፡
“እናትህ ቁልቁል ዘልቃልሃለች፥ የሚሉት ቃላቶች አቃጨሉብኝ። በፊት በፊት እናቴ የሁሉም ነበረች። የመንደር አለቃ፥ ለሀዘን ለደስታው ፊት አውራሪ፥ የሁሉንም ሀዘን ሀዘኗ ያደረገች አስተዛዛኝ ዛሬ ላይ ግን በሷ የመጣውን የሚጋራት ጠፋ አ? እናታችን እንዳላሏት እናትነቷን ቀሟት። ያንተ ማለቱ አይደል ዘልቃልሃለች ማለቱ፡፡ ያውም ቁልቁል በመሻል እንጂ በማሽቆልቆል የሚገኝ ጥቅም ያለ ይመስል፡፡ ይህ ስለእናት ብቻ እንዳይመስልህ፤ ስለሀገርም እንጂ። ሀዘኗን የሚያስተዛዝናት አጥታ ቁልቁል እንደ እብድ የሚያስጮኋት ወዳጅ አልባ፥ የሙሽራ ላጤዋ ሀገር ናት።

© Pixels PIXELS (Avoiding Problems – PA Painting by Leonardo Digenio)
“አለቀ በቃ?” አለ ፕሮፌሰሩ።
ቢቀጥልስ ምን ሊጨምር እዚህ ላይ? ምንስ ጎድሎ? ብዬ መለስሁለት።
አንተ ጥሩ ጸሐፊ እንደሆንህ አውቃለሁ። ግን ይሄ ጽሑፍ በደንብ አውጠንጥነህ የሠራኸው አይመስለኝም።
እንዴት?
ወንዴ ያነሣኸውን ሀሣብ እንደማንኛውም ተርታው ህዝብ ነው ያወጋኸው፤ እንጂ እንደ ደራሲ አይደለም።
ደራሲስ የተርታው ህዝብ ወላፈን አይነካውም? የራሱ አፋፍ ያለው ይመስል ማሽቀንጠሩ ምን ይሉት ነው? ስትቀነጭርም ስትፋፋም እንደ ህዝቡ ነው።
እሱ ልክ ነህ። ግን ሀሣቡ የተረጋጋ አይደለም። እዛም እዚም ይረግጣል።
እሠየው! አበጀኋ! እውነታው ከዚህ የዘለለ ነው? ትናንት ያመሠገንነው አይደል ምን ይሉኝን ሣይፈራ ዞሮ ሲወጋን ሚከርመው?
ደራሲ የራሡ ትናንት የራሡ ነገ ይታየዋል የታየውን በጽሑፍ ያሣያል።
የት ሁኖ? በአንድ ወቅት ሀያሲ እዝራ አብደላ ከ ዓለማየሁ ገላጋይ ጋ ሲጨዋወቱ እዝራ “ትንሽ ገንዘብ ቢኖረኝ አንድ ቪላ እና የተወሠኑ ሠርቪሶች አድርጌ፥ ደራሢው ለሚበላው ለሚጠጣው ሳይጨነቅ፤ ሲቸገርም የኪስ ሣንቲም እያገኘ በነጻነት እንዲያስብና እንዲጽፍ አደርገዋለሁ” ብሎ ነበር። ሸላይ ሀሣብ! ህዝብ መሐል ያለን ደራሲ የሚያሽሟጥጥ ማህበረሰብ ጋር ስትኖር ታሽሟጥጣለህ። እኔም የዚያ ወገኔ አጥንት ስንጣሪ ነኝ። ወለም ሲለው ወለም ይለኛል።በዚህ ሁሉ ችግር ውጥንቅጥ ውስጥ ያለች ሀገር ላይ ያለ ጸሐፊ አሽሟጣጭ እንጂ ነብይ ሊሆን ትሻለህ?
ቢሆንም ራስን በዚህ ልክ ማየቱ የለብህም ዘመን ያልፋል። የምንጽፈው ግን ከዘመን ይሻገራል።
ይሁና! እውነታው ያ ነው። የኔ ቢጤው፥ ጦርነቱ፥ ስራ አጥነቱ፥ አለመተሣሠቡ፥ አፋፍ ለአፋፍ ተዃኹኖ ግጠመኝ ይዋጣልን ዛቻው፥ የዚህ ዘመን መልካችን ነው።
ፓለቲካው እንዳይጠልፍህ እፈራለሁ።
አሁን ያለው ጸሐፊ ሁሉ የተጠለፈ ይመስለኛል። ደራሲ የስራው ጌታ ነውና በገፀ ባህሪያቱ መብት እንዳለው ሁሉ፣ በህዝብ ላይ የማኖርም ያለማኖርም መብት አለኝ የሚል ንጉስ ያላት ሀገር ነገዋ አጓጊ አይደለም። ከቦኩ አይቀር ብሽቅጥ ነው።
ዘመን መልካምም እኩይም ጎን አለው። ይህ ዘመንም እንደቀድሞዎቹ ሁሉ የሚወደስበትም የሚኮነንበትም ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
ሁሉም እማይባል ሁኖብኝ እንጂ ከሞት ይልቅ ምን ያህል ሚለው ሚያሣስበን፥ የሞት ጅምላና ችርቻሮ የተላመድን፥ ከተራበው ህዝብ ይልቅ ብጣሽ የጣለው መንግስት ሚኩራራበት——–
ታዲያ እሡ መልካም ስራ አይደል? ያለፉት መንግስታት ያላደረጉትን ደሃውን ማገዝ?
አንድ እናት ተፍጨርጭራ ልጇን የምታስተምርበትንና የምታሣድግበትን ጉሊቷን ነጥቀህ ስታበቃ፥ ቅስሟን ከሠበርህ በኋላ ልጇን ብታበላ ብታስተምር ምን ሊፈይድ? ዛሬ አንድ እናት ልጄ ተምሮ ይደርስልኛልን የምታስብ ይመስልሃል? ልጇ የመንግስት የብድር ኩፖን ከሆነ ቆይቷል። ያደጉት አገራት ስንዴውን እንጂ ማረሻውን አይሰጡንም። ለምን አትለኝም? ግልፅ ነው። ለማኝነትን ታቆማለህ፤ ትከሻ ከትከሻ ትለካካለህ፤ ይህ ደግሞ እጅ ለመጠምዘዝ አይሆንም። በደካሞች መሐል የበረቱት ያልፋሉ በሚል አመለካከት ደካሞች ብርቱ የሆኑ ለታ አጻፋው ከባድ ነው። የዘመኑ ማንዴላ የማይፈጠርበት፥ ተያይዞ ገደል የሆነ ነገ ይመጣል።
ስጋትህ ይገባኛል። ይሄን ጽሑፍ ግን በስነ-ጽሑፍ ዓይን ለማየት ነው የሞከርሁት። አምናለሁ በደንብ ታስተካክለዋለህ።
ያ ራስን ማታለል ነው። ቢሆንም እሞክራለሁ።
ድንገት ከተቀመጥሁበት ብድግ ብዬ ፕሮፌሰሩን ተሰናብቼ ጉዞዬን ቀጠልሁ። በመጣሁበት መንገድ ማዝገሙን ተያያዝሁት። ሌላ መንገድ— ሌላ ሃሳብ።