ቤዛዊት ዘርይሁን
© Antex Sisay
ይመስለኛል…………
ሶስት አዲስአበባ ሙሉ ብልጭልጭ፥ ሁለት ወሎን ያህል ቁሌት፥ ትግራይን ያህል ውበት፥ ናዝሬትን ያህል ለብ ያለ ስካር የሰሩት የሰመመን ሀሴት ይመስለኛል:: እንደ ፀሐይ ያልበራ፥ እንደጨረቃ ያልደበዘዘ፥ ስስ ብርሃን የተሣለበት ሰፊ ባር፥ የህልም ውስጥ ህልም፥ ቅዠት እና ዱካክ በየአይነት የሚቀርብበት፤ ሁልጊዜም የህልም ውስጥን ህልም አንስቼ በአንድ ትንፋሽ ላጥ አደርጋለሁ። የህልም ቪአይፒ ውስጥ የተመረጠ ህልም አያለሁ። ከሜኑው ላይ እየጨለፍሁ በትንሽ ትንሹ እቀምሳለሁ። ከእናቶቻችን ጥጥ በላይ በነጣ እና በሳሳ ዳመና እየቀዘፍሁ፥ ሩቅ የነበረውን ቅርብ አደርጋለሁ። ያጣሁትን አገኛለሁ። የወደድሁት አጠገብ እሆናለሁ። በሞት የተለየኋቸው እቅፍ መሐል እድር’ እላለሁ:: ደሞ ህልም ምን ምን ይላል? ያልጨረስነውን እንደመቀጠል፥ ሀዘንን እና ልብ ስብራትን እንደ መሻር፥ ልብ መሀል ሙሉ መሆንን፥ ምላስ ላይ መጣፈጥን፥ በደስታ መናወዝን ሁሉ ይላል።
~~
አንድን ነገር ስፈልግ የፍላጎቴ መጠን ልገድበው የማልችለው ኃይለኛ ጉልበት አለው:: የልቤ በርና መስኮቶች አፍነው ለማስቀረት አይችሉትም። ከውስጤ የሚወጣው ኃይል ከፊቴ ያለውን ምንም አይነት ነገር ጥሶ መገኘት ያለበት ቦታ ይገኛል። የፈለግሁትን ብርጭቆም ይሁን ሰው ፊቴ አገኘዋለሁ:: ከዚህ በፊት ይሄ ሁሉ ሆኖ ያውቃል። አያያዙን እና አጨራረሱን ባላውቅበትም የማላሰነብተው ብዙ ከልብ የወጣ ስሜት ያመጣቸው ነገሮች መጥተው ሄደዋል::
ብርጭቆውም ተሰብሯል፤ ሰውም ሄዷል::
እናም በህልሜ ህልም አየሁ።
አስቤው የማላውቀው ሰው፥ በቀን ተቀን ውሎዬ የማላገኘው፥ በአካል የማላውቀው ሰው አጠገቤ ነበር:: እንደፍቅረኛ እጄን ሲይዘኝ፤ ዓይን ዓይኔን እያየ ሲያወራኝ፤ ከንፈሬን ሲስመኝ፤ እጁ ተንሸራቶ ከወገቤ ወደዳሌዬ ሲወርድ፤ በደስታ ስሜት የተወጠረች ነፍሴ ከከንፈሩ መሀል በትንሹ እህህ ብላ ራሷን ስታስተነፍስ፤ የከንፈሩ ሜንት ሜንት የሚል ጣዕም ምላሴ ላይ አየር እየሳበ፥ ኮሌታው ላይ በነሰነሳት ሽቶው ከወንድነቱ ጠረን ጋር ተደባልቆ አውዶኝ ገነት እንዲህ እንዲህ ካላለች እልፀድቅም፥ እስክል ቀይ ፊቱ ላይ በተነሰነሰው ፂሙ አንገቴ ዙሪያ ጉንጮቼ ድረስ በደስታ ሲኮልኩለኝ፤ ትልቅ ሰውነቱ ገና ሳያርፍብኝ ግርማው ከብዶኝ፥ በህልሜ ህልም ውስጥ ሆኜ መንቃትን አልፈልግም ብዬ፥ ፊቴ ላይ መልኩ እንደ ሚጨስ ነገር ሲበታተን እንዳልነቃ ዓይኔን ጭምቅ አድርጌ ጨፍኛለሁ:: አያያዙ ከቃል በላይ ነበር ። ማጥበቅ አለበት። መያዝ ነበረበት። እንክብካቤ እና አለሁ ባይነት አለበት:: እንደሌሎች ህልም እልነበረም። ምናልባት ያን ዕለት ስተኛ የህልምን ኤክስትራ ስፔሻል ህልም አዝዤ ነበር የተኛሁት።
ይሄ ሲሆን አየሁ። ስነቃ ሰውነቴ ተቃጥሏል። ከረሜላው ካፉ ወድቆ አፈር እንደተለወሰበት ህፃን ክፍት ብሎኛል።የእውነት ይመስል ነበር። መነካካታችን እና ስሜታችን ነፍሴ ድረስ ተሰምቶኛል። ስነቃ የእጁ ዳና ከወገቤ እና ዳሌዬ ላይ አልጠፋም። ሽቶው አፍንጫዬ ላይ ነበር። ጉንጮቼ ላይ ፂሙ የፈጠረብኝ መኮስክክስ በስሱ ያሳክከኛል። ተመልሼ ልተኛ ብሞክርም ማስመሰሌ አልሰራ አለ::
እንዲህ አይነት ነገሮች ግራ ያጋቡኛል። አንዳንዴ ህይወት እኛ ባልገባን መንገድ በሚስጥር የምትሰራ ይመስለኛል:: አንዳንዴ ሳይሆን ብዙ ጊዜ:: የቀን ተቀን ድግግሞሻችንን እንደቅዠት በህልም ከማየት ያለፈ እንዲህ አስቤው የማላውቀውን ሰው ከርቀት ጎትቶ በህልም ማስተዋወቅ ምን ሊባል ይችላል? ሁሉንም በዚች ነፍሴ አሳበብሁት።
ነፍሴ ቀልቃላ ናት። እንደማንኛውም አይነት ሰው ኑሮ ለመኖር ስልቹ ነች:: በ”ነው” ወይ “አይሆንም” ለመታጠር አትፈልግም። መሞከር ትወዳለች። መውደቅ ብርቋ አይደለም:: ወይንም ሰውነቴ በድግግሞሽ ዝሎ አእምሮዬ ሲያንቀላፋ ወንደረር ነፍሴ እሺ ብላ አትተኛም። ይመስለኛል……….. ይመስለኛል ያለእውቀቴ ብዙ መንገዶች ሄዳለች። በሌለሁበት ወደኋላ ተመልሳ፥ ሳትጠግብ አደግሽ ተብላ የተከለከለችውን የካሬ ድንጋይ ከጣለችበት ሀሙስ ቤት ላይ አንስታ፥ እስከ ቅዳሜ ተጫውታ አርብን ቤት ገዝታለች:: ማርያምን አታረገውም አይባልም።
ወይንም እናቷ ጋር ተቀምጣ በ”ሳብ በለው ሳብ በለው የሀሙሱን ፈረስ”[1] የወሎ እስክስታዋን አስነክታዋለች። ወይንም ወደፊት ሄዳ ወደፊት የአሁን ምኞቶቿን በድብቅ እየኖረቻቸውና እየተመለሰች ይሆናል። ምናልባት ይሄን ልጅ ቀድማኝ ተዋውቃዋለች። ምናልባት ምንም ባላሰበበት በሌላ ፍቅር መንገድ ላይ ሆኖ ያለፍቃዱ ዓይኑን ስማዋለች:: እጁን ይዛዋለች። ፈገግ ብላ አይታዋለች…
ምናለበት …. ይሄኛውን ልታልፈው ብላ መወጠሪያ ገመዷን አላልታዋለች። ምንም ቀልቃላ ብትሆን ራስወዳድነት የለባትምና የሷን ልብ ልትሞላ የሌላውን አትሰብርም…
ለዛ ይሆናል ቶሎ የቀሰቀሰችኝ።
እንኳን ነቃሁ።
[1] ፍቅራዲስ ነቃጥበብ (ሳብ በለው)