ሳምራዊት ንጉሤ

ጊዜ ቢወስድም ልክ አለ! …. የወደድነውም ሁሉ ልክ አይደለም!

አንድ አባት ለልጁ ጫማ ለመግዛት ወደ መሸጫ ሱቅ ይገባል። ከዛም ለልጁ ይሆናል ያለውን እያስለካ ያስሞክረዋል። አንዱ ሲሰፋ እንዱ ሲጠብ በመጨረሻ ልጁ ዓይኑ ከአንድ ቆንጆ ጫማ ላይ አረፈ። “አባ ያ ይሁን?” አለ ለአባቱ ወደ ጫማው እያመለከተ።

አባቱም “እስኪ አምጣው ይሞክረው” አለ ለሻጩ። ጫማው መጣ ሞከረው።

ልጁ ጫማውን በጣም ስለወደደው አባቱ “እ ይዞሀል?” ሲለው “አይይይ አልያዘኝም ሆኖኛል” አለው። አባቱ “ግን እስኪ ተነስ እና ሄድ ሄድ በልበት” አለው። የልጁ ፊት ላይ ምቾት የለም ይሄን ያየው አባት በእጁ ጫማውን ነካ ነካ ሲያደርገው እንደያዘው አወቀ “ልጄ” አለው ቀና ብሎ እያየው….

“ልጄ ጫማ ከሚጠብህ ሀገር ቢጠብህ ይሻላል”

እውነት ነው።

ልክ ጥሩ ነው!

ስለወደድነው ብቻ ብዙ ልክ ያልሆኑ ህይወቶች ውስጥ ያለን አንጠፋም እኮ…. ሲጠብ ቆይ እየቆየ ይለቃል፤ ሲሰፋ ሳድግ ይሆነኛል አይነት ተስፋ።

ለመቼ ነው የፈለግነው ለአሁን ነው ለወደፊት?

ጊዜ ቢፈጅም ዋጋ ቢያስከፍልም የሚሆን መፈለግ አይሻልም?

ልጁ ይሁን ያለው አንድም ጫማውን ስለወደደው ሁለትም የሚሆነው ከጠፋ አባቱ የሚሆንህ ጠፋ እኮ ብለው መግዛቱን እንዳይተውበት ነው።

አባቱ ግን ጫማህ ከሚጠብህ ሀገር ይጥበብህ ነው ያለው። ካልሆነው የሚሆነውን የውስጥ ህመም ቀድሞ ተረድቶታል።

አንዳንዴ ደግሞ  እኛ ያላየነውን ከውጪ ሰዎች ያዩልናል።ልክ የአይናችንን ጉድፍ ለማየት መስታወት እንደሚያስፈልገን አይነት ማለት ነው።

“ይሄ ነገር ልክህ አይደለም” እንዳለው አባት።

ሀገር ቢጠብ ተጠጋግቶ ይኖራል፤ጫማ ቢጠብ መፈናፈኛ የለም።

ሀገር ቢጠብ ይጥበባ የት አባቱ ኧረ ወገን እንተጋገዝ እና ወደዛ እናስፋው ይባላል ፤ጫማ ቢጠብ ህመሙን ለማን ያጋሩታል?

ልክ ጥሩ ነው።በቃ ልክ ሆኗል በቂ ነው!

የወር ሰው ይበለን!

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *