ሩት ሃብተማርያም

“እንዲያ ተሞሽሬ፣ አምሮብኝ ተውቤ

አማረብሽ ሲለኝ፣ መላው ቤተሰቤ

ዛሬም በዓይን ‘ባይኔ፣ ይመጣል ትዝታው

እንዴት እንደነበር፣ የሰርጌ ሁኔታው።”

@internet. The Dying Artist A Masterpiece By Zygmunt Andrychiewicz

ይሄ የአስቴር ዘፈን ከወር በፊት አክስቴ ታማ ቤታችን ከመጣች በኋላ የምንሰማው የቤታችን መዝሙር የሆነ ዘፈን ነው። አክስቴ በሳሎናችን ጥግ ላይ ባለ ሶፋ ላይ ተኝታ ቀኑን ሙሉ ይሄን ሙዚቃ አጠገቧ በተቀመጠ የሙዚቃ ማጫወቻ ስታዘፍን ትውላለች።

አስቴር በዘፈኗ ማገባደጃ ላይ “ሰርጌ ትዝታው ዛሬም ህያው ነው” ስትል ምፅፅ እያለች ራሷን ትነቀንቃለች። ከዛ ዘፈኑን ትደግመዋለች። ይሄን ድርጊቷን ለብዙ ጊዜ አይቸዋለሁ። እዝን ትላለች። የለበሰችውን አርበ ሰፊ ጋቢ ጫፍ ጫፉን ጣቶቿ መሃል እያሽከረከረች ትቋጫለች።

የተቋጨውን መላልሳ ትቋጫለች። ከመጣች ጀምሮ የምትደጋግማቸው ተግባራቶቿ፦ ለሰርጓ ድግስ የተቀረጸውን ቪዲዮ ክሊፕ ማየት ፣ የአስቴርን ‘ የሰርጌ ትዝታ’ ዘፈን ማዳመጥ እና ያለማቋረጥ መክሳት ናቸው። በየቀኑ ነበር የምትከሳው። እኛ በየእለቱ የምናደርገውን መብላትና መጠጣት እንኳ እሷ በየቀኑ አታደርገውም ነበር። ምኗን እንዳመማት ግን አልነገሩኝም። የማውቀው ቢኖር ነገር በውበቷ የምትማርከኝ፣ ዘናጯ አክስቴ መታመሟን እና በአስቴር ፍቅር መለከፏን ብቻ ነው።

የቤታችንን በሩን ከፍቼ ሳልጨርሰው እጄ ላይ እንዳለ አንገቴን በስተግራ አስረዝሜ ወደተጫችበት ጥግ አማትራለሁ። እንዲሁ ለማረጋገጥ እና ለምዶብኝ እንጂ ለስለስ ብሎ ሲንቆረቆር በሚሰማው የአስቴር ዘፈን ብቻ እቤት ውስጥ መኖሯንም ሆነ አለመተኛቷን አውቃለሁ። ልክ ስታየኝ ፈገግ እልላታለሁ። ፈገግ የምትልልኝ ይመስለኛል። ቀስ ብላ በእጇ ምልክት ትጠራኛለች። ለምን እንደምትጠራኝ አውቃለሁ። ፈጠን ብዬ በሩን መልሼ የሰርጓ ትዕይንት የተጫነበትን ካሴት ወደ ምስል ማጫወቻው አስገባና ከተኛችበት ሶፋ ስር እቀመጣለሁ። ቀስ ብላ ጸጉሬን ታሻሸኛለች።

“አቡሽ”

“እመት”  ምን እንደምትነግረኝ የማውቀው ይመስለኛል። ሁሌ ይሄን ቪዲዮ ባየን ቁጥር ሰርጓ ላይ ከድንኳኑ ጫፍ እስከ ጫፍ ስላሉ ሰዎች ትነግረኛለች። ሁሉንም ታውቃቸዋለች። ስማቸውን ፣ እንዴት ሰርጉ ላይ እንደተጠሩ እና ያመጡትን ስጦታ ሳይቀር ታስታውሳለች።

“እየው! እዛ የድንኳኑ ምሰሶ ጋ ያለው ሰውዬ ይታይሃል? እየጎረሰ እጁን ሰሃኑ ላይ የሚያራግፈው?”

“አዎ”  ሁለታችንም እኩል እያየነው እሷ ስትነግረኝ በጣም  አተኩራለሁ።

“እሱ ሰውዬ የዓለሜ አለቃ ነው። ዓለሜ ለሱፍ መግዣ ጎሎት ከእሱ ትንሽ ብር ተበድሮ፣ ጨምሮ ነበር የገዛው።”

ዓለሜ የምትለው ባሏ ነው። ቅድም ከነገርኳችሁ ያጎደልኩት የእለት ተእለት ተግባሯ የእሱን ኮቴ በንቃት መከታተሏን ነው። ዓለሜ አክስቴ እኛ ጋር ታማ ከመጣች በኋላ ሁሌ ማታ ማታ ከስራ ሲወጣ እኛ ጋ ይመጣል። ረጅም ፣ ጺሙ የሞላ ፣ ኮስታራ ፣ ጠይም እና ረጋ ያለ ነው። በርግጥ ረጋ የማለቱ ሁኔታ በአክስቴ አጠገቡ መኖር እና አለመኖር ይወሰናል። አሁን ለምሳሌ እኔ ሰፈር ውስጥ ኳስ እየተጫወትኩ እሱ ደሞ ከስራ ሲመለስ ሳየው ረጋ ብሎ የሚራመድ ፤ ኮስታራነቱ እንኳን የማያውቁትን የሚያውቁትን የሚያሸሽ ነው።

ከዚያ ከተል ብዬው ቤት ስገባ አክስቴ የተኛችበት ጋ እኔ እንደምቀመጠው ተቀምጦ ጸጉሩን ስታሻሸው አልያም ሲደንስላት ካልሆነ እንኳ በጣም በፍጥነት በውሎው ያደረገውን ሁሉ ሲናዘዝላት ደግሞ ቅብቅጥብጥ ነው።  እሷ ጋ ረጋ አይልም። እንደሚለያዩ ታውቆት ነው የሚቸኩለው መሰለኝ? ግን በጣም ይዋደዳሉ። ሲገናኙ ከሌላ ሰው ቤት እየኖሩ ያሉ ወይም ሊታዘባቸው የሚችል ሰው ያለ አይመስላቸውም። ጸጉሯንም ገላዋንም የሚያጥባት እሱ ነው። ቀስና ለስለስ አድርጎ ያሻታል፤ ልክ እንደ አስቴር ዘፈን።  ዓይኗን ፣ ጸጉሯን ፣ እግሯን ፣ ጉንጯን እና ሁሉንም ቦታዋን ይስማታል።

እኔም ብሆን ከሚሰራበት የመንግስት እርሻ ጣፋጭ ብርቱካንኖችን ስለሚያመጣልኝ ሲመጣ ደስ ይለኛል። የእሱን መምጣት ቤታችን በር ላይ ቆሜ በሁለት ነገር አውቃለሁ። አንድ በጭቃ የተለወሰ ትልቅ ጫማውን አይቼ ፤ ሌላ ደሞ በአስቴር አለመኖር። አክስቴ እሱን ስታገኝ ነው አስቴርን የምታሰናብታት።

“አቡሽ”

“እመት”

“እየኝ እስኪ! ትንሽ የአይኔ ኩል የተዛነፈ ይመስላል እንዴ?” መዛነፍ ምንድን ነው?

እንጃ እላታለሁ ትከሻዬን ሰብቄ። ‘ህም’ ትልና ከእንደገና ታተኩራለች። አልፎ አልፎ ከሚሰማው ‘ምጽጽጽ’  ከሚለው ድምጿ እና በመጠኑ ከመከፋቷ ውጪ ቪዲዮውን አይታ እስክትጨርስ ተደስታ ነው። አክስቴ ቢደገምላት የምትወደው ሰርጓን ነው። ከባሏ ጋ ያሳለፉት የመዋደድ የእብደት ዘመኗን ነው።

ለስላሳ ጸጉሯ የሚያንሸራትተው ሻሿን ቀስ አድርጋ ወደ ላይ ታስተካክለዋለች። ፊቷን ትኩር ብዬ ሳያት መክሳቷ ካመጣው የተወሰነ ለውጥ ውጪ ፊቷ አልተቀየረም። ግን ደክሟታል። መላ ሰውነቷን ስታንቀሳቅስ በቀስታ ነው። ምንም ያህል ቀስ ብትልም ግን ለሰርጓ ቪዲዮ እና ለአስቴር ዘፈን አትሰንፍም።

የሰርጓ ቀን እኔም አለሁ። ቪዲዮውም ውስጥ ነበርኩ። ረጅም የሱፍ ኮቴን የእጄታ ጫፍ እየበላሁ እናቴን ቀና ብዬ እያየኋት እታያለሁ። ታዲያ ይሄ ትዕይንት መታየት በሚጀምር ግዜ እኔ ሁሌም ስሽኮረመም አክስቴ ደግሞ ትስቃለች። ራሷን አይታ አለማፈሯ ፣ በየቀኑም መድገሟ የሚያስገርመኝ እዛ ቦታ ጋ ስደርስ ነው። ታይቶ እስከሚያልፍ ነፍሴ ልትወጣ ትደርሳለች እኮ።

@Internet. Art History: Where is the death ? — Cercle

አንድ ቀን ግን ከትምህርት ቤት መጥቼ በራችን ላይ ስደርስ ጠቅላላ ሁኔታው ያልተለመደ ነገር ሆነብኝ። የአስቴር ዘፈን የለም። የዓለሜም ጫማ የለም። ቀስ አድርጌ በሩን ከፍቼ  አንገቴን ወደ ግራ አስግጌ ሳማትር አክስቴም የለችም። ግራ እንደገባኝ ቆሜ እያለሁ የቤት ሰራተኛችን ወይንሸት የበሩን መከፈት ሰምታ “ማነው ” እያለች መጣች።

“አክስቴስ?”

“ምፅፅፅ ደከሙና ሆስፒታል ወሰዷቸው። አሁን እቴቴ መጥታ ደህና ናቸው ብላ አጥሚት ወስዳለች። ነገ ከነገ ወዲያ  ይመጣሉ። ና ግባ ምሳ ልስጥህ።”

“እሺ” በሩን ከኋላዬ መልሼ ፤ ከጀርባዬ ቦርሳዬ ወርውሬ ምን እንደመራኝ ሳላስተውል ወደ  ሙዚቃ ማዳመጫው ሄጄ አስቴርን ከፈትኳት።

“አይዞሽ ሙሽሪት፣ አይበልሽ ቅር አይበልሽ ቅር

ትዳር ጥሩ ነው፣ ያሞቃል ፍቅር ያሞቃል ፍቅር።”

እያለች አስቴር ሳትጨርሰው ከየት እንደመጣች ያላስተዋልኳት እናቴ ቤቱን በኡኡታ አደባለቀችው። ብዙ ጩኸት በቤቱ አስተጋባ። ‘የሰርጌ ትዝታ’ በሞት መርዶ ተዋጠ። ቀስ አድርጌ ዘጋሁት። እያለቀስኩ ወጣሁ። ቤቱ ተደባለቀ።  ከዛ በኋላ አስቴርም፣ በጭቃ የቦካው ጫማም፣ የሰርግ ቪዲዮውም፣ ብርቱካኔም እኩል ጠፉ ።

አይዞሽ ሙሽሪት ፤ አይዞሽ አክስቴ…

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *