በሩት ሃብተማርያም
የዛ ማዶ ሰዎች ዘፈን አያምራቸው
አጅሬ ትዝታ አልገባም ቤታቸው
© ONE PAINTING A DAY (6×8 acrylic on canvas board by KELLIE MARIAN HILL)

… ቀያይ ጭኖቼን አጋልጦ የሚያሰጣ ቀሚስ ለብሼ ከባንኮኒው ላይ ተሰይሜአለሁ። በአጭሩ የተቆረጥኩት ፀጉሬ አንገቴን ይኮሰኩሰኛል። ረጅም ነበረ። ምፅፅፅ ከንፁህ ህፃንነቴ ጋር ተቆረጥኩት። አይኖቼ አስቀድቼ በመዳፌ መሃል ከማንከላውሰው ብርጭቆ ላይ ተሰፍቷል። ሴተኛ አዳሪ ነኝ። ጨዋ ሴተኛ አዳሪ ታውቃላችሁ? ሃሃሃ እሺ ፍቅር የያዛት ሴተኛ አዳሪስ ታውቃላችሁ? አታውቁም። ምክንያቱም ሁሉቱንም እንዳትሆን መስመር አበጅታችሁላታል። ፍቅር የእናንተ ግዛት ነው። ጨዋነት ደሴታችሁ ነው።
እዚህ ጎዳናው ላይ ከሚተሻሸው የሰው ጥላ መሃል ያልነካኝ ጥቂቱ ነው። ያልዳበስኩት ፎረፎር ፤ ያልዳሰስኩት ገላ ፤ ያላተናፈገኝ የታመቀ የሰውነት ጠረን ጥቂት ነው። ከገላዬ ተሻሽተህ ስንት ትከፍለኛለህ? ስንት አወጣለሁ? ባንተ ሚዛን ስንት ነኝ? ስል አምሽቼ ዋጋዬ የመሰለውን ከከፈለኝ እና ከቆነጠረልኝ ሰው ጋ ተጋድሜ አድራለሁ። ነገሩ እንዲህ እንደማወራው አይቀልም። ሀብሀብ እንደመቁረጥ፤ የአሃያ ዝንጣፊ ዘንጥፎ ጥርስ መሃል እንደመሰንቀር ፤ ነገሩ ቀላል አይደለም። በእርግጥም ከማያውቁት ሺህ ገላ ጋ መጋደምም ሩቅ ሆነው እንደሚያስቡት ከባድ አይደለም። ቤተሰቡ እጁን አሰፍስፎ ለሚጠብቀው ሰው ፤ በአራስ ልጇ ጉሮሮ ወተት ለማንቆርቆር ለተሳናት እናት፣ ትይዘው ትጨብጠዉ ላጣች ነገሩ እንብዛም ከባድ አይደለም። ያው እንደ መዛኙ ይለያያል።
… ብዙ ወንዶች በህይወቴ መጥተው ሄደዋል። ገላዬ ልክ እንደ ገንዳ ነው። ሁሉም ያሻውን ደፍቶ ይሄዳል። ታዲያ እያንዳንዱ ወንድ የሚለያየው ለገንዳው ያለው እሳቤ ነው። አንዳንዱ ለገንዳው የሚጥለው ቆሻሻ በረከት ሲመስለው በተግባሩ ከገንዳው የተሻለ የሚመስለው ነው። አንዳንዱ ደሞ ገንዳው የጋራ መሆኑን ረስቶ የግሉ እንዲሆን ተመኝቶ የሚቀና ነው። አንዳንዱ እንደ ወንፊት ገንዳውን ካልጠፈጠፈ የማይሆንለት ነው። አንዳንዱ ደሞ ንፅህናውን በገንዳው መቆሸሽ ይለካል። መሄጃ የሌለው ይሄ ገንዳ እኔ ነኝ። ይሄን ገንዳ እንዳሻቸው እንዲሆኑበት የፈቀድኩት እኔው ነኝ።
እንደ ማንኛውም ሴት ነኝ። ሁሉም ሴቶች የሚሰማቸው ሁሉ ይሰማኛል። ሴተኛ አዳሪ ናት ብለው የማይተውኝ ስሜቶች አሉኝ። አፈቅራለሁ ፤ እናፍቃለሁ ፤ በፍቅር መሳም መነካት ያምረኛል ፤ ከልቤ ከት ብዬ እስቃለሁ ፤ እቀናለሁ … ምናምን ብቻ ብዙ። ስለማይተውኝ እንጂ ሁሉም ቢተውኝ እወድ ነበር። እሺ ቆይ በሞቴ ለእኔ ማፍቀርና መናፈቅ ምን ይሰራልኛል? አንድ ቀን ከእንቅልፌ ስነቃ ሁለቱ ስሜቶቼ ከፊቴ ቆመው
“ሰማሽ አንቺ ሴት … እስካሁን አብረን ቆየን። ብዙም የጠቀምንሽ አልመሰለንም። ብንሄድና ብንርቅሽ ሳይሻል አይቀርም። አንቺም እዚህ ስላለን ደስ ያለሽ አትመስይም። ” ብለው ከአጠገቤ እርምጃ ቢጀምሩ እኔ እንጃ ታግዬ ማስቀረቴን። እሰይ! እሰይ! በቸር ግቡ። ‘ማረፊያችሁን ያሳምርላችሁ።’ አለማለቴንም እንጃ።
…
ተማሪ ነበርኩ። መቼ ወደዚህኛዉ ዓለም እንደመጣሁ አላውቅም። ብቻ ግን እየሳቅሁ እጄን ይዞ እያሳሳቀ ወደ ስርቻው እንዳመጣኝ አውቃለሁ። ይሄኛዉ ኑሮ!! መጀመሪያ አካባቢ ይሞቅ ነበር። ልክ እንደአዲስ ፍራሽና ብርድልብስ በምቾት ነበርኩኝ። ኦህ የልጅነት ሙቀትና ሳቅ!! ሁሉም ከሰፈፌ መቅዳት ሲፈልግ ፤ እዛኛዉ ጥግ ያለው ከዚህኛው ሲጣላብኝ ፤ ሴቶች በእኔ ሲቀኑ ጥሩ እየኖርሁ ልዕልት የሆንሁ መሰለኝ። ጉዱ በኋላ እንደሆነ የትኩስነት ወላፈን የገረፈው አእምሮዬ አላሰበም ነበር። ሁሉም የፈለኩትን እንዳላገኝ ሴተኛ አዳሪነቴ ልክ እንደመታወቂያ እንደሚከተለኝ የተረዳሁት ዘግይቼ ነው። የኛ ሰው መለያ መስጠት አይከብደው። እከሊት እኮ እንዲህ ናት ማለት መች ደክሞት?
ሙዚቃ እወዳለሁ። ብዙ ነገሬን ስለሚያስረሳኝና ከሰዉነቴ ጋር ለመግባባት ትግል ስለማይጠይቀኝ ሙዚቃ ወዳጅ ነኝ። አንዳንድ ማለዳ ድንገት ተነስቼ ክፍሌ ዉስጥ ሁሉን ረስቼ በከፈትኩት ሙዚቃ አቅሌን አጥቼ ስወድቅ ስነሳ ዓለም የሞላልኝ እመስላለሁ። መቼም ለተመልካች አጀበኛ ትርኢት ነው። እንደዚህ የማደርገዉ መንገዱን የቱ ጋ እንዳቆምሁ ሲጠፋኝ ፤ የነገ አቅጣጫዉ ወዴት እንደሆነ ስስት ፤ የቱን አንስቼ የቱን እንደምለቅ ግራ ሲገባኝ እንደሆነ መንገደኛ የት ይገባዋል? መንገደኛ ፈራጅ ነው። በራሱ የሰኞ ማክሰኞ ጨዋታ የሰውን አጨዋወት የሚለካ ግራ የገባው ፍጥረት ነው።
…
እንዴት እንቁም? እንጃ! እንዴት እንውደቅ እንጃ! እንዴት እንሙት? የት እንቀበር? እንጃ! ዓለሙ ሁሉ ለጥያቄዎቹ መልስ የለውም። በርግጥ የረባም ጥያቄ የለንም። ከተውነው ላይ እንጀምራለን።
መጀመሪያ ያየሁት የምሰራበት ቦታ ነው። ጠይም፤ ፂማም ደሞ ባለክምክም ጎፈሬ።
ላስተናግደው ስሄድ ያወጣት “ቢራ አገኝ ይሆን” የምትል ቅላፄውና ትህትናው ሰውነቴን ከፈሉት። ኦህ “ቢራ አገኝ ይሆን?” ጥዑም ሙዚቃን ያስንቅ ነበር። ቀልጠፍ ብዬ አመጣሁለት። ፀጉሬን ቀሚሴን አስተካከልሁ። ኦህ! ያ ሁሉ ወንድ በዓይኑ ሲከተለኝ ኬር የማይሰጠኝ ልጅ መታየት አማረኝ። እንዲያየኝ ፈለግሁ። እሱ እቴ። ያንን ፂሙን እየፈተለ እንኳን ሊያየኝ ራሱንም ረስቷል። ኤጭ!! ሲያምር ግን …
እንጀራ አልፈልግም፣ ምን ያደርግልኛል
ትዝታውን ይዤ፣ ልሂድ ይበቃኛል።
…
በተደጋጋሚ ሲመጣ ተለማመድን። ደሞ የሚቀባው ሽቶ የዝባድ ነው መሠል ከሱ ውጭ ማንም ጋር አጣጥሜው አላውቅም። ኦህ ጠረኑ!! ከጎኑ ቁጭ እላለሁ። እንጀራዬን እረሳለሁ። ራሴን እረሳለሁ። ከንፈሩን እያየሁ ከንፈር የሚመጠጥለት ህይወቴን ረሳለሁ። ስለምደው ባሰብኝ። ለማላውቀው ገላ ገላዬን አስገዝቼ ማንም እንዳይነካኝ ተከላከልሁ። ርሃብ ሲፀናብኝ አንዳንዴ አልፎ አልፎ ብቻ መርጬ እሄዳለሁ። እንደዛም ሆኖ ጠረናቸው ከገላዬ እንዳያድር በውሃ አፀዳለሁ። ህሊናዬን ባያፀዳውም። እሱን ብቻ ቤቴ ወስጃለሁ። ትራሴ ላይ ያለው ጠረን የእሱ ብቻ ነው። እንደንግስት አሰብኩት ራሴን። ጥሩ ለመሆን ጣርኩ።
…
የመጨረሻ ቀን ሲመጣ ደስ ብሎት ነበር። ምነው ስለው ለእሱም ለእኔም ቢራ አዞ ወደ እኔ ዞረ። እ ንገረኛ በሚል ዓይን ሳየው የምወዳት ፍቅረኛዬ የጋብቻ ጥያቄዬን ተቀበለችኝ አለኝ። አልደነገጥኩም። አልቀናሁም። ድንዝዝ አልኩ። እንባዬ ብቻ ታዘዘኝ። አንድ ጠብታ ብቻ የምጠጣው መጠጥ ላይ ገብታ ወደ ሆዴ ገባች። የምወድሽ ጓደኛዬ ነሽ አለኝ። ካንቺ ጋር ያደረግነው ያው ስህተት ቢሆንም ግን ህይወቴ ውስጥ ግን የማልፍቀው ትዝታ ነው አለኝ። ከፍሎ ሄደ። ስንት ሰዓት እንደተቀመጥኩ አላውቅም። ወንበር ሲነሳሳ ገላዬን እየጎተትኩ ወጣሁ።

ዛሬ ሰርጉ ነው!!!
ገላዬን እንደአዲስ እያዘዝኩ ነው።
ፀጉሬ አሁንም ይኮሰኩሰኛል።
ያምራል ብሎኝ ነበር።
ሚስቱ እንዲህ ተቆርጣ ይሆን??
.
አብረን እንደር?