ሩት ሃብተማርያም

ያያታል። ታየዋለች። የመንገዱን ግራ ይዞ ይሄዳል። ቀኟን ይዛ ታዘግማለች። አዘውትሮ ሸሚዝ ይለብሳል። ሁሌም ቀሚስ ትለብሳለች። መነፅር ያደርጋል። የሚያምር ሀብል አላት። ረጅም ነው። አጭር ናት። ጠዋት ድልድይ ስር ላሉት ሽማግሌ ብር ይሰጣል። ማታ ሳንቲም ትሰጣለች።

እሷ

ከመኝታዋ ስትነሳ አታረፍድም። ሳታዘው ትነቃለች። ትታጠባለች። ትለብሳለች። ጸጉሯን በወጉ ታበጥራለች። እጇ ላይ ያለ ሰዓቷን አይታ ፈገግ ብላ ትወጣለች። ታውቃለች። አያረፍድም። እንዳታረፍድ ትጣደፋለች። መንገድ ላይ ከሚተመው ህዝብ ላይ ዓይኖቿ መነፅር ያደረጉ አይኖች ይፈልጋሉ።

እሱ

ህልም ውስጥ ነው። ሲያቅፋት ፤ ሲስማት ፤ የሚያምር ሀብሏን ሲነካ ምናምን ምናምን … ይነቃል። ይደነግጣል። የወንደላጤ ቤቱ ሲያስጠላው። ከሚያምር ህልሙ የትናየት ሩቅ አይነት የሚያስጠላ። ጠዋት ሲነቃ የሚፈልገው ሰዓቱን ነው። ያያል። ያውቃል አታረፍድም። ላለማርፈድ ይጣደፋል። እንደነገሩ ይለብስና ይወጣል። ከሚርመሰመሰው ህዝብ መሃል የሚያምር ሀብል ይፈልጋል።

የሁለቱም ትልቅ ህልም ጎዳናውን መሻገር ነው።

የኔ ህልም ጉዳዩን ለእናንተ መተረክ ነው።  የነገር አጀማመር መጨረሻውን ወስኖ አያውቅምና እኔም የትረካዬን መጨረሻ አላውቅም።

ጎዳና ነኝ እኔ። አልፈውብኛል። ሲዋደዱ ነክተውኛል። ሲደሰቱ ረምርመውኛል። ሲነፋፈቁ ታዛቢ ነኝ። የመዋደዳቸውን ቄጤማ ሲነቅሉ እንግጫው ነበርኩ። ሲበርድ ፣ የመውደዳቸው ትኩስነት በስልባቦት ሲተካ ሁሉን ታዝቤያለሁ።

ዛሬ ያልደረሱ ትንፋሾቻቸውን በእኔ በኩል ትሰማላችሁ።

እሷ

ትናንትና ዛሬ በሚሉ የጊዜ መለኪያዎች መካከል ስንት ልዩነቶች አሉ መሰለህ? እንኳን ትናንትና ዛሬ አሁን እና ቅድም በሚሉት ውስጥ እንኳ ሽራፊ ልዩነት አይጠፋም። እውነት! በሽርፍራፊ ስከንዶች ውስጥ ስንት እንቅፋቶች በእግር ላይ ሰልጥነዋል? ስንት አውሎ ንፋስ ተነስቶ በርዶ ይሆን? ፀሐይ በልጅነት ተወልዳ፥ ለስላሳነቷን ሰጥታ ማቃጠሏን አስከትላለች? በአሁንና በቅድም ልዩነት ውስጥ ስንት ዳኛ ፈርዶ ይሆን? ስንት ትዳር ፈርሶ፥ አንድ መሆን ሁለት ሆኖ ይሆን? ስንት ትንታ በአንድ ጉንጭ ውኃ በርዷል? ስንት ሰው ከመኖር ወደ አለመኖር ነፍሱ ሮጣበታለች? ትናንትና ዛሬ አንድ አይደለም! አሁንና ቅድምም!

🎶

ክረምት አለፈ፥ አደይ ጎመራ

ከልብ ሳንጫወት፥ ፍቅርን ሳናወራ

አብረን እንዋል፥ እንጫወት ፍቅሬ

የፍቅርህ ገዳፊ፥ የጾምኩትን ሽሬ።[1]

“ጊዜ የሁሉም አለቃ ነው። የጥንካሬና የኃያልነት ብቸኛ ገዢ ጊዜ ነው። ጠንካራ የነበረ ሰው ለእርጅና እጁን ይሰጣል። ኃያልነትም ባለበት አይቀጥልም። ጊዜ የራሱ አዲስ ኃያል ይሰራል። በጊዜ ያልተሸነፈ ፍቅር ብቻ ነው።” ትለኛለች አያቴ። በነገሮች ተፈትኖ ቢወይብም ፍቅር ሁሌም የዘገየ አሸናፊ ነው። ለዛ ነው አሁን ረስቼሃለሁ፥ ዘንግቼዋለሁ ካልሁበት ሳብ አድርጌ፣ በትናንት እና በመቀየም አቧራ የተሸፈነ ፍቅራችንን ‘እፍፍፍ’ ስለው እንደ ተዳፈነ እሳት፥ እንደቆሰቆሱት ልቤ ላይ የሚነደው።

አሁን የትናንትናዋ ባለአበባ ቀሚሷ ወጣት አይደለሁም። ጸጉሬ መሃል ያ የምትወደው ጠረን የለም። እየበታተነ የሚጫወትበት የለም። ትናንት ከሰዓት አንተ ስትገፋኝ ምሽቱን ሌላ የትዳር እቅፍፍ ውስጥ ወደቅሁ። አሁን የምትወዳቸው ጡቶቼን ልጅ እያሳደግሁበት ነው። አንተን የሚስሙ ከንፈሮቼ ትዳሬን አሰማምርበታለሁ። ቤተሰቤን እስምበታለሁ። ልዩነቱ እንዳንተ ዓይኔን ከድኜ ቦታ ሳ’ለይ አልስመውም። እዚህ በቀመር ነው ሁሉም ነገር። ከመስመር አያልፍም። አልሳሳትም። ዓይኔን ከፍቼ መስመሬን አስምሬ እስመዋለሁ። ታዲያ አንዳንዴ በፍቅር ጨዋታ መሃል ትዝ ትለኛለህ። ልሰጠው የጀመርኩት ሙቀቴ ተሰብስቦ የሄደበት ይጠፋኛል። እንደዚህ ሲሆን ገላዬን ከገላህ በአካል ባላዋህድም ታማኝነቴን ያፈረስኩ እየመሰለኝ እሸማቀቃለሁ። እባክህ ይሄኛው ህመሙ ኃያል ነውና እንደዚህ አታድርግ እሺ!

እና ግን ደህና ነህ? አገባህ? ወለድህ? ሚስትህን እንደ እኔ ጸጉሯን እየበታተንክ ትጫወታለህ? መንገድ መሃል ትዘፍንላታለህ? የሸሚዝህን ቁልፍ አሁንም ታዛንፋለህ? መነፅርህን አውልቀህ ዓይንህን ከድነህ በጥልቅ ትስማታለህ? ድንገት ስራ መሃል ደውለህ ግጥም ታነብላታለህ? ደስ የሚል እብደትህን ስርአት እና ማደግ የሚሉት ነገር ሸረሸረብህ? አሁንም ጆሮዋ ላይ ፅጌሬዳ ያደረገች ሴት ትወዳለህ? የሰው አጥር ላይ አበባ ለመቅጠፍ ብለህ ውሻ ያሳደደህ ትዝ ይልሃል? ሃሃሃ

አሁን ድረስ ግርማ በየነን እኮ አልሰማውም። ከሰማሁት ለሳምንት እደነዝዛለሁ። ‘ፅጌሬዳ’ን እንዴት ልርሳው? እና ይሄ ሁሉ ማያያዣ እያለን ግን ተለያይተናል? ረስተኸኛል? ረስቼሃለሁ? ጸደይ መሃል ፈክተን ጸደይ መሃል ጠወለግን። እኛ ተለያየን እንጂ ሁሉም ከመስመሩ አልተዛነፈም። እና እጆችህ ከእጆቼ መላቀቃቸው አይቆጭም? ፍቅር ማለት እንደ እነሱ ነው እንዳልተባልን ስስታችንን ምን ወስዶት፣ የፍቅራችን ክረምት ደረሰ? እና ትናንት እንደ ዛሬ አይደለም። ዛሬም ትናንትን አያክልም። ከጊዜ ትበልጣለህ። አላይህም ፣ አታየኝም ግን አብረኸኝ አለህ። ይሄ ልክ ነው ልክ አይደለም? ከትዳር ፆሜ መሃል የምታስፈስከኝ ሀጢያቴ ነህ!!


[1]ፍሬሕይወት ለማ “አብረን እንዋል”።

post on under glass window
© Pinterest

እሱ…

“ነገሮችን አልፌ ሳያቸው የምቆጭ አይነት ሰው አይደለሁም። ታውቂ የለ? ትናንት ያደረግሁት ነገር በጊዜው ልክ ነበር ከሚሉት መሃል ነኝ። ይሄ አቋሜን ልክነት የነሳሽው አንቺ ነሽ። ከትናንት የሚጎድል ወደዛሬ የማይሻገር ነገር ሁሉ በግዴለሽነት የሚታለፍ ነገር እንዳልሆነ ያስተማርሽኝ አንቺ ነሽ። ሃሃ ቢማሩት ምን ይሰራል? ማርፈድ እንደሚያቆስል ከቆሰሉ በኋላ መረዳት ምን ያደርጋል?

የመጀመሪያ ቀን ሳይሽ አበባ በጆሮ ግንድሽና በለስላሳ ጸጉርሽ መሃል አስቀምጠሽ ነበር። ደስ አልሽኝ። ለአበባ አበባ ምን ይሰራለታል እያልሁ ንብ ሆኜ ልቀስምሽ ተጠጋሁ። ስቀርብሽ ደስ አልሽኝ። ታሳሺ ነበር። ባለቀለም ቀሚስሽን ለብሰሽ እንደ እንቦሳ እየዘለልሽ ስትመጪ ሳይሽ መልአክ ትመስይኝ ነበር። ጸጉርሽ መሃል ያለ ጠረንሽን ዓይኔን ከድኜ ሳጣጥም ሲንደሬላን ያጨሁ ልዑል የሆንሁኝ ይመስለኝ ነበር። የነፍስሽ ንፅህና ከሀጫ በረዶም ያስንቃል። ነገሮቼ ሁሉ በነበር ጫፋቸው ተዘምዝሟል። ልክ ቁጫጭ መሸፈኛ ውስጥ እንዳለ በልቶ እንደጨረሰው ከረሜላ አለሁ እያልሁ ነው የሄድሁብሽ።

አንድ ቀን የጻፍሽልኝን አስታወስሽ? ወረቀቱ አርጅቶም ኪሴ ውስጥ ተቀምጧል። ላንብብልሽ? እንደ ዱሮው “ጌትዬ አንብብልኝ!” ብለሽ እጅሽን ጉንጮችሽ ላይ አድርገሽ ዓይንሽን ባታንከራትችብኝም ላንብብልሽ።
 
” … እጆቼን አጥብቀህ ያዘኝ። ጣቶችህ ህይወቴን ማስቀጠያ ክሮቼ ናቸው። ከልቤ ኩልል እያለ የሚሰማው የፍቅር ዜማ ለሌላ ሰው ትርጉም አልባ ሹክሹክታ ነው። አንተን ካልሳሙ እንዴት ሊገባቸው ይችላል? ትንፋሽህ በአንገታቸው ዙሪያ ካልዋለ እንዴት ሊሰማቸው ይችላል??
 
… ዓይኖችህን ሳይ የሚሰማኝ ምትሃት ልዩ ነው። እ— አለ አይደል? ፈጣሪ አሰልፎ ዓይን ሲያድል አንተን ሲያይ ቆይ ላንተ ሌላ አለ። ና ተከተለኝ ብሎ ያዳላልህ ይመስለኛል። ሁሌም እደነግጣለሁ። ሃሃ አያስቅም ሀሳቤ? ፈጣሪ ሲያዳላ ሃሃ–
 
… በጸጉሬ መሃል እጅህ ሲርመሰመስ የት እንዳለሁ እዘነጋለሁ። ጣቶችህ ነገር ይፈልጉኛል። መንሳፈፍ ስጀምር ትሄዳለህ። ትሸሸኛለህ። ለምን ሩቅ ትሄዳለህ? ለምን ዝም ብለህ አትስመኝም?
 
… አንተ የተረት ከተማዬ ልዑል ነህ። የተረት ከተማ ነዋሪዎች ደግሞ እ– ልክ እንደ መልአክ አይታዩም ፤ አይዳሰሱም ፤ … አይሳሙም። ሁሌም እወድሃለሁ።” እንደዚህ ያልሽን እያነበብኩ ነው የምተነፍሰው።”
 
🎶
ፀሐይ ጨረቃም፥ ምንም ናቸው
ካንቺ ጋር ቀረ፥ ውበታቸው
ባንቺ ያልተገራ፥ ምን ተገኘ
ፍቅርሽ ሲነካው፥ ያልተቃኘ።[1]
 
ነገሮች በአሉበት ይቀጥላሉ። ንፅህና ስርዓት በሚሉት ኩል ይኳላል እንጂ ነገር ሁሉ መስመሩን ሳይለቅ ይከናወናል። አገባሁ። ወለድሁ። ልጄን በስምሽ ሰይሜ ዓይኖቿ መሃል ንፅህናሽን የምፈልግ ብኩን ሆኛለሁ እንጂ ደህና ነህ ወይ? ካልሽኝ በሰዎች መለኪያ ደህና ነኝ። ትናፍቂኛለሽ። ጸጉርሽ መሃል ያለው፥ ዓይኔን ከድኜ የማጣጥመው ጠረንሽ ሌላ ቦታ ላገኘው አልቻልሁምና ይናፍቀኛል። አፍ አውጥቼ አልናገር እንጂ የነገሮች ሁሉ ሚዛኔ አንቺ ነሽ። ልክ ነህ እንዲሉኝ የምፈልገው ባንቺ ተመዝኜ ነው።
ደህና ነኝ…!


[1] ጎሳዬ ተስፋዬ  “ይታየኛል”።

Separation by Edvard Munch Hand-painted Oil Painting blonde

©Etsy Australia (Separation by Edvard Munch Hand-painted Oil Painting blonde)
 
ፍቅር መልኩ እንዴት ነው?  የሄደው የመጣው መነካቱን የሚለካው በምን ሚዛን ነው? የፍቅር ልክነት የት ጋ ነው መስቀሉ? የነካን ፣ የወደደን ፣ የተወን ሄዷልን ያልነው ሁሉ የትኛው ሰውነታችን ጋር የሚደበቀው? አብሮን ለሚነፍሰው ንፋስ አብረነው ብንሮጥም ግን የልባችን እሽክርክሮሽ አብራን የለችምና ለሌሎች የሚታየው መውለብለብ ብቻ ይታያል።
 
እኔ መንገድ ነኝ። እናንተ ደሞ የትንፋሻቸው ፣ የእርምጃቸው ፣ የነበረ መልካቸው መዳረሻዎች ናችሁ። በእኔም አልተጀመረምና በእናንተም አይቆምና ላያችሁት እና ለሰማችሁት እውነታቸው ሁሉ መንገድ ሁኑላቸው።
እናም መንገድ ስላጡ ትንፋሾች እንማልዳለን!

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *