በሳምራዊት ንጉሤ
አናፂው ለረጅም ዓመታት ካገለገለበት ድርጅት “ብዙ ዓመታት አገለገልሁ ከዚህ በኋላ ቢበቃኝስ” ይልና መልቀቂያ ያስገባል። አሰሪውም የመልቀቂያ ደብዳቤውን ሲያይ አልተደሰተም። ሀሳቡን ቢቀይር ብሎም ሊያግባባው ሞከረ ……. ግን አልቻለም።
ታዲያ አናፂው በድርጅቱ “አለ” የተባለ ባለሙያ ነበርና የድርጅቱ ባለቤት አንድ ነገር ሊያደርግለት ፈለገ…
ወደ አናፂውም ጋር ሄዶ “መልቀቂያህን ተቀብያለሁ ግን ለመጨረሻ ጊዜ ይችን ቤት ስራልኝና እንለያያለን” አለው። አናጺው ደስተኛ አልነበረም።እንቢ እንዳይልም ይሉኝታ ያዘው። እናም “እሺ” ብሎ ስራውን ጀመረ። “ከአንገት በላይ ስራ” በሚባል አይነት ለጥራቱም ሳይጨነቅ ሰርቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቱን አስረከበ። ቤቱን ሊረከቡት የመጡት የድርጅቱ ባለቤት ቤቱን መጨረሱን ዞረው ካዩት በኋላ እንዲህ አሉት….
“አንተ የድርጅቱ ጎበዝ ሰራተኛ ነህ እና ምን ላድርግለት ብዬ ሳስብ የመጣልኝ ይሄ ነው።ላንተ ቤት ሰርቶ መስጠት።የምሰጥህን ቤት ደግሞ እራስህ ብትሰራው ብዬ አሰብሁ። ስለዚህ ይሄለመጨረሻ ጊዜ የሰራኸው ቤት የአንተ ነው”።
ሰውየው ደነገጠ—- ተቆጨ ።
“ወይኔ” “ወይኔ! ቤቱ ለእኔ መሆኑን ባውቅ ኖሮማ በደንብ የምሰራውን” አለ በውስጡ። የምናወራው ለእኛ፣ የምንፅፈው ለእኛ ፣የምንሰራው ስራ ሁሉ…. ለእኛ ቢሆንስ? ለራሳችን ሲሆን አንሰስትም አይደል?”ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንደሚባለው።
እስከ ዛሬ ስንሰራ የከረምነው ለእኛ ብለን ነው?”ምን አገባኝ እሱ ይጨነቅበት” አላልንም?ለሰዎች ያደረግነው ሁሉ “ለእናንተ እኮ ነው” ስንባል የምንጨምረው ነገር እንዳይኖር አድርገን እንስራ።
የወር ሰው ይበለን