ሳምራዊት ንጉሤ

አባት ልጁን ይዞ እየሄደ እያለ፥ በመንገዳቸው ዛፎችን ያያሉ። ከዚያም ልጁ አባቱን “አባቴ ይሄንን ዛፍ አነቃንቄ ቅጠሎቹን ማንቀሳቀስ እችላለሁ?”ብሎ ጠየቀው።
አባቱም “አዎ! ሙሉ አቅምህን ከተጠቀምህ በደንብ ትችላለህ” አለው። ልጁ አባቱ እንዳለው ወደ ዛፉ ይሄድና ዛፉን መነቅነቅ ይጀምራል።
ቆይቶ ወደ አባቱ እያየ “አባቴ አልቻልሁም” አለው።
አሁንም አባቱ “ሙሉ አቅምህን ተጠቀም ትችላለህ” አለው።
ልጁም እንደገና ሞከረ አልቻለም። አባቱንም “አባቴ ሙሉ አቅሜን ተጠቀምሁ ግን አልቻልሁም” አለው እያዘነ።
“ሙሉ አቅምህን አልተጠቀምህም”። እኔ አብሬህ አለሁ። እንዳግዝህ ግን አልጠየቅኸኝም!”አለው አባትየው።
እርዳታ መጠየቅ ክብራችንን የሚቀንስብን የሚመስለን ስንቶቻችን ነን? “አግዘኝ” ማለት ሞት የሆነብን። “እሱን እርዳኝ ከምል ብሞት ይሻለኛል” ብለን እናውቃለን እኮ።
አቅም እናድርጋቸው። አንዳንዶች “በእኔ ነው እኮ እዚህ የደረሰው እንጂ እሱ ምኑን ችሎት”ይላሉ። ይበሉ! ለእኛ መወጣጫ አድርጎ ካዘጋጃቸውስ? እሱን ፈርተን አይደል “እርዱኝ”፥ “አግዙኝ” የማንለው። “ኧረ በኋላ ጉራውንም አልችለው”እያልን ስንቱ አመለጠን?
አንዳንዶቻችን ለመርዳት፤አንዳንዶቻችን ለመረዳት የተፈጠርን ቢሆንስ? ግን ደግሞ “ይሄ አለኝ ይሄን ጨምርልኝ፤እስከእዚህ መጣሁ የቀረውን አግዘኝ”፥ ለማለትም ትንሽም ይኑረን። ሰዎች ጥረታችንን ሲያዩ ደስ እያላቸው ይረዱናልና።
የወር ሰው ይበለን።