አድኀኖም ምትኩ
ጸጉሯን ጭብርር አድርጋ በቱታና በክፍት ጫማ ትመጣለች፣ ያሻትን ታወራኛለች። በምታወራው የምይዘው አቋም አያስጨንቃትም። ስታወራኝ ፊቴን አታነብም ፣ ነገሬን በቁም ነገረ አትይዘውም። የድሮ ፍቅረኛዋን ኳሊቲ ስትናገር ስለወንድሟ የምታወራ ነው የምትመስለው ። የሰጣትን ስጦታ አይነት ልትነግረኝ ሁላ ትችላለች። እማላቀውን ሰው በቅናቴ ምክንያት እጠላዋለሁ ። ፍሬህይወት ነገሬ ሁሉ ግድ አይሰጣትም።
እኔ …
የአለመወደድን ጠረን አውቀዋለሁ። ያለመጥቀምን ስሜት ከየትኛውም መጥፎ ሁኔታ በላይ አልወደውም። የአልወድህም ምልክት ስታሳየኝ ልቤ ላይ የማልወደው ስሜት ተንከላወሰ። ጠፋሁባት። በሌላ ምክንያት ከሆነ ብዬ፣ እለታዊ ሙድ ከሆነ ብዬ፣ ተናዳብኝ ይሆናል ብዬ፣ እጅግ ብዙ ቆይቼ ከሁለት ቀን በኋላ አግኝቻት ስሜቷን ሰለልሁት።
ከአስር ደቂቃ በኃላ እንደተገናኘን ነበር ሁኔታዋ፣ ዓይኗ ላይ ያለው መሰልቸት በጉልህ የተነበበኝ። ሁኔታዋ ገፈተረኝ። አገፈታተሯ እና አወዳደቄ ሳያዘጋጁ ከድንገተኛ መንጋለል ስሜቱ ይበልጣል። ህመሜ በማዘን አይነት እፊቴ ላይ የሚነበብ ይመስለኛል።
ጠፋሁ!!
ታግሼ ለመወደድ ብጥር፣ እኔነቴን ባሳያት፣ ፍቅሬ የእውነት እንደሆነ፣ በምንም ሁኔታዋ አብሬአት ሆኜ ባሳያት ጥሩ ነበር። አለመወደድን መጋፈጥ አልችልም። አለመወደድን ከምጋፈጠው የምወደውን ነገር ሳጣ የሚሰማኝን ደባሪ ስሜት መቋቋምን እመርጣለሁ። ጉልምስናችን የልጅነታችን ባርያም አይደል?! አለመወደድን እንድታገስ ልጅነቴ አይፈቅድልኝም።
—
አስራ አንድ ዓመት እንደሞላኝ እናቴን መኪና ገጭቶ ገደለብኝ። ጋሽ አበራ የሚባል ዘመዳችን እሳድግሃለሁ ብሎ ወሰደኝ። የእናቴ የነበረው የቀበሌ ቤት በሰባ ብር ተከራየ። እሱ እና ዘመዶቹ ለሁለት ሳምንት ከንፈራቸውን እየመጠጡ እኔን ለመንከባከብ ሞከሩ። ምግብ ብላ፤ እናትህ ኖራ ቢሆን፣ እያሉ በተቻላቸው መጠን አቀማጠሉኝ፤ ተቀማጠልኹ። ጋሽ አበራ የኔ እኩያ ልጆች አሉት። ከእነሱ አንፃር በብስለት እኔ ትልቅዬ ሰውዬ ነበርሁ። እናቴ የቆጥ የባጡን ታወራኝ ስለነበር የማይገባኝ ነገር ያለ አይመስለኝም።
የዘመዴ ቤት ሁለት ዓመት ከሁለት ወር አካባቢ ተቀመጥሁ ። ሁለት ዓመት ተሰቃየሁ። ልጅ ስለምመስላቸው ብልግናቸውን ጥበብ አያለብሱትም ነበር። የሚያደርጉት ነገር ሁሉም ይገባኝ ነበር። አድራጎቱም፣ የድርጊቱ ምክንያትም፣ ስለሚገባኝ እታመማለሁ። ጥጋበኛ ነው፣ የልጅ መርዝ፣ ውለታ ቢስ ይሉኛል። አሁን የአስራ ሶስት የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ እንዲህ ይባላል?! በእርግጥ የሃያ ሶስት ዓመት ልጅ አክል ነበር። በደላቸው አጥንቴ ውስጥ ተቸነከረ። ስንት የማይገባኝ የሚመስላቸው አድሎ ደምስሬ ውስጥ ተተበተበ።
እናቴ ናፈቀቺኝ …ድሃዋ እናቴ፣ ጓደኛዬ፣ ናፈቀቺኝ። ምግብ እንጂ ፍቅር አጉላብኝ የማታቀው እናቴ ናፈቀቺኝ። የዓለም ትልቁ መከራ አለመወደድ ነው! ኖ አይደለም። ነገሬ የሚል ሰው ማጣት ነው። አይደለም። የማትረባ እንደሆንህ ሁሉም ሲስማማብህ ያለው ስሜት ነው። ይሄ ሁሉ አንድ ላይ ሲመጣ ሌላ ሲዖል እንደሌለ ይገለፅልሃል! በመገፋት ብዛት እግዛቤርን አዋርቼው አውቃለሁ …. እሱ ያኔ መልስ አይመለሰልኝም ነበር።
እኩያዬን ቱቦ ውስጥ የወደቀበትን ኳስ ለምን አወጣህ ብለው ይገርፉታል። እኔን ቱቦውን አፅዳ ይሉኛል። በደንብ አላፀዳኸውም ብለውም ይከሱኛል።
በመጨረሻ ወደ ቤቴ ቀጥ ብዬ ሔድሁ። በሰባ ብር የተከራየውን ሰውዬ ውጣልኝ ብዬ ለመንሁት። ከአምስት ቀን በኋላ እወጣለሁ አለኝ። አምስት ቀን በረንዳ አደርሁ። ከአምስት ቀን በኃላ ውጣልኝ ስለው እወጣለሁ እንዳለም እረስቶት ነበር። እኔ አምስት ቀናት እንዲሞላልኝ ሰዓት ስቆጥር እንደከረምሁ አላወቀም። የአንዳንድ ቀጠሮ ግዝፈት ሁኔታችን ላይ የተንጠለጠለ ነው!!
ሁኔታዬን ሲያይ አብረን እንኑር አለኝ። እምቢ አልሁት። ጎረቤቶቼን ሰብስቤ አስለመንሁት። በስንት አማላጅ ወጣልኝ። ብቻዬን መኖር ጀመርሁ። ተሸከምሁ ፣ተላክሁ ……. ሊስትሮ ጠረግሁ። መከራ በላሁ።
የማይወግንልኝ ሳይኖር ብቻዬን የማልችለውን እየተሸከምሁ፤ ሸክሜ ሲወድቅብኝ አሸካሚዬ ሲሰድበኝ፤ ጫማ ስጠርግ የጫማውን ቀለም ካልሲ አስነክቼ ሲመቱኝ፤ ልጅነቴ አሳዝኖቸው እሰጥሃለሁ ካሉኝ በላይ እየሰጡኝ፤ ቀን ቀን አስፋልት ላይ ማታማታ የእናቴ ፍርስርስ ያለች ጓጆ ውስጥ እያደርሁ፤ ሲከፋኝ እያለቀስሁ፥ እግዛቤርን እያናገርሁት አደግሁኝ።
አምላኬ ሁሉን እያየ ነበር ።
ለሁሉም ወሮበላ ሱሰኛ ሌባ ነበርሁ ። ክፉ ነገር ሲከሰት እኔ የመጀመርያ ተጠርጣሪ ነኝ ። መጀመርያ ሰሞን ስጠረጠር ደምስሬ ተገታርትሮ እያለቀስሁ አስረዳ ነበር። እናቴ ስለእውነት እና ስለ እምነት ያሳየችኝን እነሱ የት ያውቃሉ? በቆይታ ብዛት አለመታመን የሚያናድደኝ አልሆን አለ። በጥርጣሬያቸው አለመናደዴ ለሌብነቴ እንደማስረጃ ያጣቅሱታል። የልቤን ጌታ ያውቃል እል ነበር። ክፉ ቀኔን በጌታዬ ድጋፍ ተሻገርሁ ።
ዛሬ
በቂ አለመወደድ እና አለመ’ፈለግ ስላስተናገድሁ አለመወደድን ፊት ለፊት መጋፈጥ አይሆንልኝም ።