በአስቼ

ጠቦት ፊልም የደራሲና አዘጋጅ ያሬድ ዘለቀ ፊልም ሲሆን በ gorilla films production” ተሰርቶ የቀረበ ነው፡፡ ፊልሙ የሚያጠነጥነው በቤተሰብ ዙሪያ ነው። እናቱ የሞተችበት ኤፍሬም የተባለ ልጅ ሃገራቸው ድርቅ በመግባቱ ከአባቱ ጋር ወደ ዘመዶቹ ይሰደዳል፡፡ አባትየውም ልጁን ዘመድ ቤት በአደራ አስቀምጦ ወደ አዲሰ አበባ ይሄዳል፡፡ ነገር ግን ልጁ በዘመዶቹ አካባቢ እንደ ባዕዳ በመታየቱ ይዟት ከመጣት የበግ ግልገል ጋር አብረው የሚያዩትን ውጣ ውረድና፣ እሷን ለማትረፍ እንዲሁም አባቱን ፍለጋ ለመሄድ የሚያደርገውን ጥረት የሚተርክ ፊልም ነው፡፡
በምስል ደረጃ እንቅስቃሴው በአብዛኛው (እንቅስቃሴ አልባ) ሲሆን በእንቅስቃሴ ደረጃም የተመጠነና የማይረብሽ የካሜራ እንቅስቃሴ ያለው ነው። በአብዛኛውን የሚጠቀመው ካለበት ሳይንቀሳቀስ ጎንዮሽ እሽክርክሪት ብቻ ነው፡፡ ብዙዎቹ dialogues (ቃለ ተውኔቶች) ጊዜ የ shot size (የምስል መጠኑ) long shot (ርቀት ቀረጻ) የምንለው አይነት በመሆኑ ተመልካቹ የትረካ አይነት ስሜት እንዲሰማው አድርጓል። ነገር ግን ከገጸ ባህሪያቱ በመራቁ የተነሳ መልካቸውን በመመልከት ከፊት ገጽታቸው ማግኘት የሚገባንን ስሜቶች እንዳናገኝ አድርጓል፡፡ ይህ በመሆኑም የፊልሙ ስሜት የቀዘቀዘ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል እንደ አንዱ ለመውሰድ ያስደፍራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም shot size (የምስል ቀረጻ ጊዜው) ከአስፈላጊው ጊዜ በላይ በመርዘሙ የፊልሙን ስሜት ፍሰት እጅግ ሊጎትተው ችሏል፡፡ እንደሚታወቀው በቂ ምክንያት ከሌለ በስተቀር የምስል ቀረጻ ጊዜው ከ፭- ፯ ሴኮንድ በላይ መብለጥ እንደሌለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ነገር ግን ፊልሙ የታሪክ ማነስ አይቼበታለውና እሱን ለማካካስ የዘየዱት መላ ሳይሆን እንደማይቅር እገምታለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ፊልሙ በሚረበሽ ሁኔታ ቀስ ያለ ሆኖ ታይቶኛል፡፡
በድምጽ ደረጃ ስንመለከተው ድምጽ ጥራቱ ግሩም ነው። ተፈጥሯዊ ድምጾች ላይ በደንብና በአግባቡ በመኖራቸው እቦታው ያለን ያህል ልዩ ስሜት እንዲሰማን በማድረጉ ምን ያህል እንደተጨነቁበት ያሳያል፡፡ በቃለ ተውኔት ደረጃ ስናነሳ ግን የገጠሩ ቅላጼ/ዘዬ የምንለው/ ፈጽሞ የሌለው ነው። እንዲያውም የተጠና ቃለ ተውኔት እንደሆነ የሚያሳብቅ አይነት ድምጸት አለው። ቃለ ተውኔቱ በጣም ትንሽ በመሆኑ ገጸ ባህሪያቱ ምን ይናገሩ ይሆን እያልን ስንጠብቅ ባግባቡ ሳይናገሩ እና ስሜታቸውም ሳይሰማን እንዲያልፈን ምክንያት ሆኗል።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የፕሮዳክሽን አባላቱ ጠቅላላ በሚባል መልኩ የውጭ ሃገር ዜጋ በመሆናቸው ስሜታቸውን በነጻነት በአማርኛ ቢናገሩ የንግግር ቀለማቸው እንዳያሳብቅ ይመስላል። ይሄንን ለመሸፈን ገጸ ባህሪያቱ ከሚገባው በላይ ዝም ያሉ ሆነዋል፡፡
በታሪክ ደረጃ ጥሩ plot (ግጭቱ)ና sub plot (ደጋፊ ግጭቶቹ) በጡዘቱ ተዋሕደው በአግባቡ በመገንባታቸው ልቀቱ በተሻለ ስሜት እንዲያልቅ ምክንያት ሆነውታል፡፡ ነገር ግን ገጸ ባህሪያቱ በግልጽ አላስተዋወቁንምና ግራ መጋባት ውስጥ የሚከቱ ትእይንቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ብናነሳ በአንድ ትእይንት ላይ ሰለሞን(አጎትየው) ኤፍሬምን “የአጎቴ ልጅ እንዴት አድርጎ ነው ያሳደገህ?” እያለ ሲናገር ይደመጣል፡፡ በሌላ ትእይንት ላይ ደግሞ ጽዮን (የሰለሞን ልጅ) ተሰናብታው ወደ አዲስ አበባ በምትሄድበት ወቅት ”ጥሩ ልጅ ሁን የአጎቴ ልጅ!” ስትለው ይሰማል፡፡ በመሆኑም በእንዲህ ያሉ ብዙ ምክንያቶች በታሪኩ ፍሰት መሰረተት የዝምድና ሃረጋቸው ትንሽ ግራ አጋቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
ጽዮንን ካነሳን ዘንድ አንዳንድ የጎረበጡኝን ሃሳቦች ልሰንዝር፡፡ በመጀመሪያ አዜብ(የሰለሞን ሚስት) የ ጽዮን የእንጀራ እናት መሆኗን የነገሩን ፊልሙ ከግማሽ በላይ ካለፈ በኋላ ፩ሰዓት ከ፭ ደቂቃ ላይ በመሆኑ በቀደሙት ትእይንቶች በሁለቱ በኩል ያለውን የጭቅጭቅ መንስኤም ሆነ እማማ(አያትዋ) ለምን ሁለቱንም ሲመቷቸው እንደነበረ ጭምር ግራ ያጋባ ነበር፡፡
ይሄ በአግባቡ ያለማስተዋወቅ ችግር እንደ ምሳሌ ሊታይ ይችላል፡፡ የጽዮንንና የአዜብን ጉዳይ በተመለከተ ምንም እንኳን የእንጀራ እናትና ልጅ ቢሆኑ የእውነት በገጠሩ ባህል ልጅ ሽቅብ ያን ያህል ትከሻ ገፍቶ እስከማለፍ የደረሰ አፍ ላፍ ይካፈታል ወይ? ባህላችንስ እንዲያ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ፈጥሮብኛል፡፡ ለዚያውም አንዳንዴ አባትየው ባለበት ጭምር፡፡ የዚህን መልስ ለማወቅ አስተዳደጋችንን ማየት በቂ ነውና ብዙ ምርምር የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡ ይህ የልጅ እኩል የመጨቃጨቅ ቀርቶ ተራ ጨዋታ ላይ እንኳን ተሳትፎ የማድረግና የመናገር መብት እስከማቀው ፈረንጆቹ ጋር ያለ ባህል እንጂ በእኛ ባህል ያልጎለመሰና የማይታሰብ ነው፡፡ ይህም የልጅ አስተዳደግ ባህል እውቀት ስለ ደራሲው አስተሳሰብ ፍንትው አድርጎ አሳይቶኛል፡፡
እንዲሁም የኤፍሬም እናት ከመሞቷና ቤታቸው ውስጥ ምግብ የሚያበስል ከማጣታቸው በተጨማሪ እነ ኤፍሬም የተሰደዱበት ምክንያትም ሆነ የእነ ሰለሞን መሰረታዊ ችግር ድርቅ ብቻና ብቻ በመሆኑ ደራሲው ለኢትዮጵያ ያለውን ምስል አሳይቶኛል፡፡ እሚያሳዝነው የእነ ሰለሞን መኖሪያ ብሎ ደመናማ ሰማይና ውብ አረንጓዴ የለበሰ መልከአ ምድር እያሳየ እነ ሰለሞን የተጠየፉትን፣ ጽዮን የተከለችውን፣ በሰው ውጋጅ ያደገ አታክልት እስከ መንከባከብ የደረሰ ድርቅ ለማሳየት መሞከሩ እጅግ ተጋጭቷል፡፡ ይህ ኢትዮጵያን ጠቅልሎ በድርቅ የመመሰል አባዜ መቼና ከየት እንደመጣ የሚታወቅ በመሆኑ ደራሲውን መኮነን አግባብ ባይሆንም እንደው እንደ ባለሙያ ድርቅ ቦታ ነው የስክሪፕቱ መቼት ከተባለ እንኳን location (ቦታ) መረጣ ላይ ለእሱ የሚሆን በረሃ ቦታ መመረጥ ነበረበት፡፡
እንደ ዜጋ ስናየው ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ አረብ ሃገሮች በረሃ ላይ የተመሰረተች ሃገር አደለችም አንጂ እንዲያው ብትሆን እንኳን ሃገራችንን ለማሳየት የምንሰጣት መልክ ላይ እጅግ መጠንቀቅ አለብን እላለሁ፡፡ በዘመናችን እንደሚታየው አንድ ምሳሌ በመስጠት ክፉ ክፉውን እንዲህ ነች ከማለት መቆጠብ ይገባናል፡፡ በአፍ ይሄዳል አይደል ሚባለው? በመሆኑም አንዳንድ ነጠላ ምሳሌዎች ጠቅላላውን አይወክሉምና ተመስገን እያሉ እንደ ኤዢያኖች ስለ ሃገር በጎ በጎውን ማውራት ይበጃል እላለሁ፡፡ ምክንያቱም መጥፎ በማውራት ሳይሆን በመስራት ነውና ሚቀየረው፡፡ በተለይ በፊልሙ ኢንዱስትሪ ያሉ ባለሙያዎች የታየ ይበልጥ ይታመናልና እንደ ሃገር መልካችንን ስንስል ከብዙ አቅጣጫ ብዙ መርምረን እና እጅግ ተጠንቅቀን መሆን አለበት እላለሁ አመሰግናለሁ፡፡
ኢትዮጵያዊነት ልባምነት!