Kuragnaye Film Review

ቁራኛዬ በሲነርጂ አበሻ ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ የቀረበ የደራሲና አዘጋጅ ሞገስ ታፈሰ ፊልም ነው። የፊልሙ መቼት ፲፱፻፲፮ ዓ.ም በንግሥተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘመን እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ የፊልሙ ታሪክም ጎበዜ ደርሶ/ጋሻዬ/ የሚባል አንድ የቆሎ ተማሪ በማህጸን ሳለ በልጅህን ለልጄ ወግ ለትዳር ቃል የተገባችለት አብሮ አደግ ፍቅሩ “ጎንጥ ጥጋቡ” በሚባል የጭቃ ሹም ተጠልፋ ጠፍታበት፤ ከብዙ ዓመታት ፍለጋ በኋላ አግኝቷት እሷን ለማስመለስ የሚሄደውን ርቀት የሚያሳይ ነው።

በፊልሙ ንጉሣውያኑን ይጠቀሙበት የነበረውን “በላ ልበልሃ” በመባል የሚታወቀውን የፍርድ ስርዓት ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በበላ ልበልሃ የፍርድ ስርዓት መሰረት በዳይና ተበዳይ ኩታቸውን ወይ ከላይ የደረቡትን ማንኛውም ቡሉኮ በአንድ እዚያው ባለ ሹም ወይም ባላባት እርስ በእርስ ይታሰራሉ።  እስሩ ሳይፈታ እንዲዳኛቸው ከሚፈልጉት ሸንጎ እንዲደርሱ መሃላ ያደርጋሉ፡፡በዚህ መልኩ ሳይካካዱ ለፍርድ ከሸንጎው የሚደርሱበት መንገድ ሲሆን ይህም ባህል “መቆራኘት” በመባል ይታወቃል፡፡ መቆራኘት ማለት መታሰር ወይም መተሳሰር ማለት ነው፡፡

ፊልሙ በምስል ጥራት ደረጃ በ፲፻፹/HD/ የተቀረፀ ነው፡፡  የካሜራ እንቅስቃሴው በጠቅላላው ማለት በሚቻል መልኩ ካሜራው ሳይንቀሳቀስ/simple shot/ የተወሰደ ሲሆን ተንቀሳቀሰ ከተባለም ለመግቢያ፣ ገጸ ባህሪያትን ለማስተዋወቅ፣ እና ለመውጫ በብዛት የጎንዮሽ እሽክርክሪት/pan/ ለማሳየት  ነው።  ይህም በማድረጋቸው ለማቀናበር/edit/ ከመመቸቱም በተጨማሪ ተመልካች በአላስፈላጊ የካሜራ እንቅስቃሴ/shake/ እንዳይረበሽ ያደርጋል። ብሎም የትረካ ስሜትን ስለሚፈጥር ይበልጥ በስሜት ተመልካች የመያዝ አቅምን ይጨምርለታል።

በብርሃን/light/ ረገድ ስናየው የውጪ/outdoor/ ቀረጻ ላይ የተፈጥሮ ብርሃንን ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ያም በመሆኑ ከተለመደው የፊልም መልክ/cinematic look/ ጠቆር ያለ አድርጎታል። ይህ ደግሞ ደብዘዝ/fade/ ካለው የቀለም ድመቀት/color temperature/ ምርጫቸው ጋር ተዳምሮ ምስሉ ላይ የድሮ ፊልም መልክ አይነት ስሜት ሊያመጣላቸው ችሏል። ይህን በማድረጋቸውም በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ የተለመደው የድሮ ጊዜን ለማመልከት በጥቁርና ነጭ እያረጉ የመስራት ልምድን በመቀየር ከነ”የነገን አልወልድም” ፊልም ተርታ ፈር ቀዳጅ የሆነ ፊልም ነው ለማለት ያስደፍራል።

 የቀለም ድምቀት ምርጫው እራሱ ለተፈጥሯዊው ቀለም የቀረበ በመሆኑ የሚታየው ምስል ለዓይን የማይረብሽ እንዲሆን አድርጎታል። ለቤት ውስጥ/indoor/ ቀረጻው ደግሞ ሰው ሰራሽ ብርሀን/artificial light/ ተጠቅመዋል። የጀርባ መብራቱ/backlight/ “spot light” የምንለውን የመብራት አይነት በመጠቀምና አልፎ አልፎም ከላይ እና ወደ አንድ ጎን በመድረግ ሾልኮ የገባ ብርሃን በማስመሰላቸው የተፈጠረው ምስል የራሱን  ውበት ሊፈጥር ችሏል።

በድምጽ ረገድ በባህላዊ መሳሪያ የራሱን አጃቢ ሙዚቃ ሰርተውለታል። ድምጹም የተመጠነና የማይረብሽ ሆኖ ተዋህዷል። ይህም በስራው ላይ ምን ያህል እንደተጨነቁበት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። የንግግር ድምጹም/dialogue/ ቢሆን ወጥ በሆነ መጠን/pich rate/ የቀረበ በመሆኑ ለጆሮ የሚረብሽ ነገር የለውም። ነገር ግን እንደ እርምጃ እና የእቃ ንክኪ ያሉ በተፈጥሮ የሚገኙ ድምጾች/natural sounds/ የሌሉት በመሆኑ ድምጹ ከቀረጻው በኋላ ለብቻው/off set/ መቅረጫ ክፍል/studio/ ውስጥ መቀረጹን ያሳብቃል።

በገጽ ቅብ/costume and props/ ደረጃ ስናየው የምስሉ ዋና መሠረት ነውና ከእግርና እጅ ጌጥ ጀምሮ እስከ መናንያን ቆብ ድረስ ጠልቀው በመጨነቃቸው የታሪኩን አንኳር ታሪኮችን በትእይንት ላይ በቀላሉ ለመናገር አስችሏቸዋል። ከ፻ ዓመታት በፊት ይለብሱትም ሆነ ይጠቀሙት ከነበረው ከቆሎ ተማሪ ቁርበትና እራፊ ጨርቅ እስከ ነገስታትና ሹማምንት ብሎም ካህናት አለባበስና የሚጠቀሟቸውን ቁሳቁስ ሳይቀር ምን ይመስል እንደነበር ሊሳዩን ሞክረዋል፡፡ በዘመኑ ምን ሲጠቀሙና እንዴት ሲኖሩ እንደነበር በዚህ ዘመን በቀላሉ ለማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ምን ያህል ጥልቅ ምርምር እንዳረጉ ምስክር ይሆናል፡፡ በተለይ በግሌ መናኒዋን ንግሥታችንን የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱን የመመነን ውሳኔ ከመናንያን ቆብ በላይ ዘውድ ስትደፋ በማሳየት ብቻ ንግሥና ከሃይማኖት ጋር ያለውን ትስስር አያሌ ሃሳቦችን ያዘለና ልዩ ስሜት ያለው አይረሴ ትዕይንት ሳላደንቅ ማለፍ አልፈልግም፡፡

በታሪክ አንጻር ስንቃኘው የፍቅር ፊልም ዘውግ ሲሆን የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ወደ ፊልሙ መጨረሻው ክፍል በመውሰዳቸው የጡዘቱ/Climax/ መንስዔ ሆኖ ታሪኩ ሰቅዞ የመያዙ/suspense/ አንዱ ምክንያት ሆኗል ብዬ አስባለሁ። በቋንቋ ረገድ ባህላዊ ጨዋታችንንና  እጣነ ሞገርን ጨምሮ ብዙ ቅኔያዊና ግጥማዊ ዘዬ የታጨቀ ነውና ማራኪነቱ  ‹ወይ ግሩም› ያሰኛል፡፡  በተጨማሪ ያንዳንዶቹ ንግግሮች/dialogue/ በዛ ዘመን ለችሎት ክርክር ይጠቀሙባቸው በነበሩ ቃላት በጥንቃቄ የተቀነበበ በመሆኑ በጊዜው የነበረውን የአነጋገር ዘይቤ ቀለሙን ሊያገኝ ችሏል። ይህም በመሆኑ ምን ያህል እንደተለፋበትና ምን ያህል የአበው ልሂቃን አሻራ እንዳረፈበት አይቻለሁ።

እውነት ለመናገር አፍ የህሊና ማስተንፈሻ ነው እንደሚባለው ይሔን በሚያህል ቅኔያዊና ግጥማዊ ስነቃል በወጥነት ያለመኮለታተፍ ከመናገር አልፎ መከራከር መቻላቸው፣ በእውነት በዘመኑ የሚኖሩ ሰዎች በነገሮች ላይ የነበራቸው የማስተዋል ልህቀትና ስብዕና ብሎም እንደሰው የመብሰል ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል እላለሁ። በዛ ላይ በዳይና ተበዳይን የሚያክሉ ሁለት ተቃራኒ ዋልታዎች በአንዲት “መቆራኘት” በምትባል የኩታ መተሳሰር ሃሳብ ብቻ ተዳድረው ሳይጎዳዱ ቀርቶ ጭራሽ እየተደጋገፋና እርስ በእርስ እንክብካቤ እየተሰጣጡ፣ ከፊታቸው የሚያጋጥማቸውን መከራ በጋራ እየተከላከሉ ባስ ሲልም እርስ በእርስ እየተፃለዩ ለቀናት ብሎም ለወራት በጋራ ፍትህ ለማግኘት መጓዛቸው የልብ ገርነታቸውንና የስብዕናቸውን ግዝፈት በጉልህ ያሳያል፡፡ ከፍ ሲልም ፍትህ ለማግኘት የሚሄዱበት እርቀት ምን ያህል እንደሆነና ለፍትሕ ያላቸውን በቃላት የማይገለጽ ክብርና ቀናኢነት ይመሰክራል፡፡

በፍትሕ በኩል ስናየውም በጊዜው ዓለምን ያስደነቀ እና ከተጻፈ ሕግ በተሻለ ለስብእናና ለስሜት በቀረበ የፍትሕ ስርዓት ስንተዳደር እንደነበር ታሪክ በደንብ ይመሰክራል፡፡ እንደው እንደምሳሌ እንውሰድ እንኳን ብንል ታላቁ ንጉስ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በፍርድ ችሎታቸው ምክንያት የፈረስ ስማቸው “አባ ዳኘው” መባሉን አንስተን መጨዋወት እንችላለን፡፡ ካሰኘንም የነገር ብልት ያውቃሉ ተብለው በእንግሊዞችም ሆነ በጣሊያኖች ብሎም በቀናኢ ፈራጂነታቸው በዓለም ትልቅ ዝና ያላቸውን የጦር ሚኒስትሩን ፊትአውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላ) ጠቅሰን፤ ካስፈለገም ሌሎች እማኝ አድርገን ማውራት እንችላለን፡፡

ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል እንዲሉ ፊልሙን ስመለከት ካስታወስኳቸው ብዙ ከሚደንቁ የአባ መላ ፍርዶች አንዷን አስደናቂ ፍርድ ብቻ መዝዤ ተርኬ ላብቃ፡፡

 እንደሚታወሰው እንግሊዞች ኬንያ በእጃቸው ነበረችና በዛ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ገፍተው መሬት መያዝ ስለሚፈልጉ በግጭት ምክንያት መሬት ለመውረር ምክንያት እየፈጥገሩ ይተነኩሱን ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ሁለት ያልታጠቁ የእንግሊዝ ወታደሮች ያለፈቃድ ገብተው ኖሮ በስህተት በድንበር ጠባቂዎች ይገደላሉ፡፡ የእንግሊዝም ሃገር በቆንጽላው በኩል ከእምዬ ምኒሊክ እልፍኝ አቤቱታውን ያቀርባል፡፡ ጥያቄውም “በሃገራችን ህግ መሰረት ወታደራችን የሞተበት መሬት የእንግሊዝ ይሆናልና የተገደሉበት መሬት ይሰጠን!” ነው፡፡ አፄ ምኒልክም ወይ ወታደሮቹ ይቀጡም ቢሉ አሻፈረኝ ብለው በጥያቄአቸው ይፀናሉ፡፡ ነገሩ የመሬት መቁረስ ጥያቄ እንደሆነ የተረዱት ንጉሱ ትንሽ ካሰቡ በኋላ “ሃብቴ አንተ እየው እስቲ ይህንን ጉዳይ?” ብለው ወደ አባመላ ይመሩታል፡፡ ፊታውራሪም “በእውን በሃገራችሁ ያለው ደንብ እንደሱ ነው?” ሲሏቸው “አዎ” ይላሉ ቆንጽላዎቹ፡፡ ይሄኔ አባ መላ አሰብ ያደርጉና “እንግዲያውስ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዕእለማየሁ እናንተ ሃገር ሄዶ ነው ያረፈውና እናንተም ሎንዶንን ስጡን እና እኛም ይህንን እንሰጣችኋለን፡፡” ብለው ውል አርቅቀው “በሉ ፈርሙ!” ይሏቸዋል፡፡ ይሄኔ እንግሊዞቹ “ልዑል ዓለማየሁ እኮ ታሞ ነው የሞተው፡፡” ብለው ቢመልሱላቸው “እሱን እናንተ አላችሁን እንጂ እኛ ከዚህ በምርኮ ተወስዶ እዛ እንደሞተ ነው ምናውቀው፡፡” ብለው ይመልሱላቸዋል፡፡ ነገሩ ያላማራቸው እንግሊዞችም ታዲያ ውሉን አንፈርምም ብለውና አቤቱታውን አንስተው ይመለሳሉ፡፡ በዚህ ፍርዳቸውም ንግስቲቱና ንጉሱ እጅግ ተደስተው ተነስተው እንደሳሟቸው በታሪክ ተጽፎ ይገኛል፡፡

በመጨረሻም እንደ መጠቅለያ እኛ ሁላችን የዚህ ዘመን ትውልዶች ብሎም በፍትህ ሙያ ውስጥ ያሉ ወገኖች ከበላ ልበልሃም ሆነ ከኦሮሚያው አባገዳ ስርዓት፣ ከደቡቡም ዱቡሻ፣ ከሃመሩ ዶንዛ ሆነ ከጉራጌውም፣ ከአፋሩም የፍትህ ስርዓትም ሆነ ከሽምግልና ስርዓት እጅግ እጅግ ብዙ እምንማረው ይኖረናል። እናም እንደ “የሚመለከተው አካል” እና “መንግስት” አይነት የአፍ ሸጋታ ቃላት ወጥተንና ታሪክን በበዳይና ተበዳይ መነፅር ከማጥናት አልፈን ታሪካችን ውስጥ በምናገኘው ጥበብ ልክ ብንቃኝ እያልሁ፤ ፊልሙ እጅግ መታየት የሚገባው ነውና ፊልሙንም ማንነታችንንም ብናይ እላለሁ አመሠግናለሁ!

(ማስታወሻ:- በዚህ ጽሑፍ ላይ አንዳንድ ሙያዊ ቃላትን ለመተርጎም ተሞክሯል፡፡ ምናልባት የትርጓሜ ግድፈት ካለም ታላቅ ይቅርታ እየጠየኩ ከጎኑ በቅንፍ ዋናው ቃሉ ይገኛል፡፡)

 ኢትዮጵያዊነት ልባምነት!

አስቼ

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *