አስቼ

“ምን አለሽ” በማያ ፊልም ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው። ዳይሬክተርና ተዋናይት እንዲሁም የታዋቂው ገጣሚና ዘፋኝ ቴዎድሮስ ካሳሁን/ቴዲ አፍሮ/ ባለቤት የሆነችው የአምለሰት ሙጬ ፊልም ነው። ፊልሙም በዋናነት አንዲት መርካቶ ውስጥ የምትኖር ሯጭ እንስት በሩጫ ህይወቷ ውስጥ የሚያጋጥማትን ውጣ ውረድ የሚተርክ ነው።

በምስል አኳያ ስናየው ምስሉ የቀለም ውህደት (cinematic look) የሚያምር እና የምስል ጥራቱ እጅግ የሚያረካ ነው። የተቀረፀበት ካሜራ (arri alexa) አሪ አሌክሳ የሚባል ሲሆን ገናና በሚባሉ የፊልም ኢንዱስትዎች ውስጥ ሳይቀር እየተጠቀሙበት ያለ ካሜራ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ እንደነ ኦስካር ያሉ ዓለም አቀፍ የፊልም ውድድሮች ላይ ተቀባይነትና ተመራጭነት ያለው የካሜራ አይነት ነው። ለፊልሙ ስራ ሲባል ከውጭ በመጡ የካሜራ ሙያተኞች የተሰራ ሲሆን አምለሰት አንድ ቃለመጠይቋ ላይ እንደገለጸችው ፊልሙ በጠቅላላ  በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ የተሰራ ነው። በእውነቱ ባላደገው በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ለአንድ ፊልም አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ሰርቶ ማስመረቅ በራሱ ይበል የሚያሰኝ እና በሙያው መስክ ውስጥ ያሉትን ሙያተኞች የሚያበረታታ ጅማሬ ነው።

ነገር ግን ተዋናዩ እንቅስቃሴ በሚያደርግባቸው አንዳንድ ትእይንቶች ላይ ከባድ ጥላ ሲያርፍ ተመልክተናል። ይሄ ደግሞ የምስሉን ጥራት በተወሰነ መንገድ ቀንሶታል። እንደሚመስለኝ ችግሩ ሊፈጠር የቻለው፦ ፊልሙ ከቤት ውጪ(outdoor) ስለተቀረጸ የብርሃን ምንጭ ፀሐይ ትሆናለች። ስለዚህ ተዋናዩ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ አንጸባራቂው(reflector) አብሮ ከተዋናዩ ጋር መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ይሄም  አንጸባራቂውን ትእይንቱ ውስጥ እንዲገባ ያስገድደዋል። ስለዚህም የአንጸባራቂው መቅረት ችግሩን ሊያስከትል እንደቻለ እገምታለሁ።

ከዚህ ውጪ ግን የሚጠቀሙበት የካሜራ አቅጣጫ(angle) እና የካሜራ እንቅስቃሴ ተመልካች የማይረብሽ እና የተዋሃደ በመሆኑ ሳይጎረብጠኝ ተመልክቸዋለሁ።

በድምጽ ረገድ ስንመጣ ደግሞ የፊልሙ ማጀቢያ ዜማ ለጆሮ ተስማሚ እና ከትዕይንቱ የማያናጥብ ነው። ከገበያ ጫጫታና ከመሳሰሉት ተፈጥሮአዊ ድምጾች ጋር እንዲዋሃድ ተደርጎ በአግባቡ የተሰራ በመሆኑ ለምስሉ ውበት እንዲሰጥ እና መቼቱንም በሚገባው ልክ እንዲገልጽ አስችሎታል።

ነገር ግን ፊልሙ የሩጫ እንደመሆኑ የኮቴ ድምጽ መሰማት በሚገባው ልክ መስማት ስላልቻልሁ ትንሽ ግርታ ተፈጥሮብኛል። በተጨማሪም ከንግግር/ጭውውት አንጻርም ስናየው አንዳንድ ቦታዎች ላይ የተዋናዮች ንግግር ድምጹ ለጆሮ ርቆ ለመስማት ያስቸግራል።ይሄንንም እንደ ድክመት ወስጀዋለሁ።

ከገጽ ቅብ አንጻር ስንመለከተው በኑሮ አለመመቸት እና በችግር የተጎሳቆለ ፊት ያላቸውን ገጸ ባህርያት ለመሳል የተጠቀሙት የገጽ ቅብ ከመጋነኑ የተነሳ ተዋንያኑን ሲጠጡ አድረው ወይም ተደባድበው የበለዘ የሚመስል ገጽታ እንዲላበሱ አድርጓቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በዋና ገጸባህሪዋ ላይ ሳይቀር በሚያስታውቅ መልኩ የገጽ ቅቡ ከትእይንት ትእይንት በቀላሉ የሚለያይ አይነት ልዩነት አለው። ይህም በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ የ continuity ችግር በመባል ይታወቃል።

በአልባሳትና በመቼት መረጣ ረገድ ስናየው ቦታውን ጋር የሚሄዱና ቀለል ያሉ ልብሶች በመምረጣቸው በአልባሳት ላይ እንደተጨነቁት በደንብ ያሳብቃል።

አንድ ክፍል ላይ ደግሞ ሰላማዊት እና ቢንያም ስራ ፍለጋ 4 ኪሎ አካባቢ እየተላፉ እየተጓዙ ባለበት ሰዓት ቢንያም መንገድ ዳር የቆመ ሰው ከሚያነበው ጋዜጣ ላይ የቁንጅና ውድድር የሚል ማስታወቂያ እንዳየ ለማድረግ ተሞክሯል። ሃሳቡ መልካም ቢሆንም በማርከር ተሰምሮ የሚታተም ጋዜጣ የለምና ትንሽ ተዓማኒነቱ ላይ ጥያቄ ፈጥሮብኛል። የጋዜጣ አንዱ ቅጠል ምን ያህል እንደሚረዝም የሚታወቅ ነውና ገጹ ቆራጣ እንደነበር በቀላሉ ለማየት ይቻላል።

እስኪ አሁን ደግሞ ከታሪክ አወቃቀርና ተዋናይ መረጣ አንጻር እንየው። ከርእሱ እንደተረዳሁት፦ “ምን አለሽ” አንድም የፊልሙ መቼት መርካቶ ሰፈር ውስጥ የሚገኘውን ምናለሽ ተራ መሆኑን ለማመልከት፣ አልያም ዋና ገጸ ባህሪዋን ምን ማድረግ ትችያለሽ? ምን ማሳካት ትችያለሽ? እያለ ጠይቆ ስለ ታሪኩ ዋና ሃሳብ ፍንጭ ለመስጠት ይመስላል። በመሆኑም ቃሉ ለርዕስነት መመረጡ ጥሩ ምልከታ ነው። ሆኖም ግን “አለሽ” የሚለው ቃል ጠብቆና ላልቶ ሲነበብ የተለያየ ትርጉሞች አሉት። ማለትም ጠብቆ ሲነበብ ከላይ የገለጽኩትን ትርጉም ሲሰጥ ላልቶ ሲነበብ ደግሞ “ምን ተናገረሽ?” የሚል ትርጉም ይኖረዋል። ይህኛው ትርጓሜ ከፊልሙ ሃሳብ ጋር የማይገኘኝ በመሆኑ ርዕሱን ላስተዋለው ሰው ትንሽ አሻሚ ስለሚሆን የርዕሱን ጥራት በመጠኑ ያጎድለዋል እላለሁ።

      ከታሪክ አንጻር ስናየው ጥሩ የሚባል ነገር ቢኖረውም ዲያሎግ በአሳማኝ ሁኔታ ስሜትን መግለጽ ባለመቻሉ በግሌ ይሄን ያህልም ሰቅዞ ልያዘኝም። በፊልሙ ውስጥ የሶስት ብር ሳሙና እና የአንድ ብር ሻይ ቅጠል መኖሩን የተመለከተ ሰው ታሪኩ መቼ እንደተሰራ ለመጠየቅ ይገደዳል። በተጨማሪም አንዳንድ በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ ጥቅም ላይ የማይውሉ ቃላት እና ሃረጋት በየንግግሩ መሃል ሲጠቀስ ይስተዋላል።

ለአብነት ያህል “ሸክም ልንሰራ” የሚለውን ቃል ብንወስድ የአካባቢው ነዋሪ የማይጠቀምበት ቃል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በንግግሩ ማስተላለፍ የሚገባውን ስሜት እንዳያስተላልፍ ምክንያት ይሆናል። ይሄም ተዋንያኑ ስሜታቸውን በነጻነት እንዳይጫወቱ ሲያስራቸው ለማየት ችያለሁ። ለዚህ ምሳሌ እንኳን ብንወስድ ያን ያክል በእሷ ምክንያት የገዛ ሰራተኛውን እስከማባረር የደረሰ ቁጣ የተቆጡት የቢንያም የቀድሞ አሰሪው ጋሼ ሰላማዊት ይቅርታ ብላ እግራቸው ስር ስትወድቅ እየተናገሩ የነበረው ንግግርና እየተበሳጩ የነበሩበት የስሜት ጥልቀት ምንም አለመጣጣም እንደምሳሌ ማንሳት እንችላለን።

በመጨረሻም ስለ ቀጣይነት (continuity) ላንሳና ወደ ማጠቃለሉ ልሂድ። ቀጣይነት(continuity) ማለት አንዱ ትእይንት ባለቀበት ሁናቴ ሌላው ትእይንት መጀመር ማለት ነው። ለምሳሌ ስራ ፍለጋ እየሄዱ ሳለ አንዱ ትእይንት ላይ በቀኝ እጁ በኩል ነበር ያቀፈችው። ወዲያው በተከታዩ ትእይንት ላይ ግን በግራ እጁ ደገፍ እንደማለት ነው ያለችው። እንዲህ አይነት ጥቃቅን የሚመስሉ ስህተቶች በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ተቀባይነት የላቸውም። ነገር ግን የፊልሙን ደረጃ እስከማውረድ ድረስ የሚደርስ ኃይል አላቸው እና አጽንኦት ቢሰጣቸው እና ቢታረሙ መልካም ይሆናል።

በጠቅላላው ፊልሙን ስመለከተው ደራሲዋ ለሃገሯ ያላትን መልካም ምኞት ብዕሯ ፍንትው አድርጎ አሳይቶኛል። ይሄም ደግሞ ይበል የሚያሰኝ እና ሌሎች ደራሲያንን የሚያበረታታ በመሆኑ ለደራሲዋ ያለኝን ታላቅ አክብሮትና አድናቆት ሳልናገር ማለፍ አልፈልግም ።

ሰላሙን ሁሉ ተመኘሁ ከልብ አመሰግናለሁ።

ኢትዮጵያዊነት ልባምነት!

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *