ተገኑ ጸጋዬ
በዕለተ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ቀጠሮ ስለነበረኝ ወደ ፒያሳ የሚያቀና ታክሲ ውስጥ ተሳፈርሁ። መንገዱ ስለተዘጋጋ መኪናው የሚሄደው በጣም በዝግታ ነው። እግር መንገዴን የጥንቷን ፒያሳ ለማየት አቅጃለሁ። በማህበራዊ ሚዳያው በየዕለቱ ስለሚነገረው የፒያሣ መፍረስ እንደ አንድ የከተማው ነዋሪ ቁጭትና ብስጭት እንዳሳደረብኝ የማልደብቀው ነገር ነው።
እኔን የገረመኝ በየሚዲያው የሚነገረው የከተማ መፍረስ (መናድ የሚለውን ቃል ብጠቀም ይሻላል መሰለኝ) ለማየት ለምን እስካሁን ፒያሳ አልመጣሁም? ንዴቴ እንዳይባባስ ይሆን? ወይንም አየሁ አላየሁ ምንም ጥቅም ስለማይሰጥ? እንጃ ብቻ ወደ ፒያሳ ፍርስራሹን ለማየት አስቤ ብዙጊዜ ሀሳቤን ቀይሬ ቀርቻለሁ።
ፒያሳን ከመውደም ባላድናትም በቀብሯ ላይ መገኘት ነበረብኝ። ከዚያስ? ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ሁሉ አምሮኝ ነበር። የሚቀበረው ሰው ቢሆን ነፍሱ በሰማይ ትረፍ ይባላል። ይህ ግን ተቀባሪው ግዑዝ አካል ስለሆነ ምን ሊባል ይችላል? ዕድለኛ ሆነህ እዚያ አካባቢ ከድሮ ጓደኞችህ ጋር የተነሳኸው ፎቶ፣ አቧራ የጠገበ አልበሞችህ ውስጥ ከተገኘ እሰየው ነው። አለበለዚያ ግን የሚቀሩህ የፒያሳ ትዝታዎች ብቻ ናቸው።
የተሳፈርሁበት ታክሲ ከመሐል ፒያሳ ላይ ጣለኝ። እ-እ-እ ፒያሳ አይደለም። ፒያሳ የነበረችበት ስፍራ ላይ። ፒያሳን ፒያሳ የሚያስብሏት የድሮ ህንፃዎቿ አይደሉ?
አጋነንህ እንዳትሉኝ እንጂ ስለፒያሳ መፍረስ አስቀድሜ ያን ሁሉ ዜና ሰምቼ አሁን እንደ አዲስ ነው ድንግጥ ያልሁት። አፌም የደረቀ መሰለኝ። ምን? ማንን ልጠይቅ? ምንስ ነው የምጠይቀው? ትንሽ ማብራሪያ የሚሰጠኝ ሰው ባገኝ ደስ ይለኛል። ግን ሰለምኑ? መፍረሷን እንደሁ ባይኔ በብረቱ እያየሁ ነው። የተቀባዠርኩኝም መሰለኝ።
በቅርቡ የተሰራውን የአድዋን መታሰቢያ ህንፃ በግራ ትቼ በቀኝ በኩል በቆርቆሮ የታጠረውን የተንጣለለ ግቢ እየቃኘሁ በእርጋታ መጓዝ ጀመርሁ። የአያሌውን ሙዚቃ ቤት (ጥንት የነበረው ነው) አጥሩን ይዤ ወደ ላይ ማቅናት ጀመርሁ። የታጠረውን ቦታ በከፊል እንዳጋመስሁ በር የሚመስል ክፍት ቦታ አገኘሁ። ወደ ውስጥ ለመዝለቅ ጥቂት እንደተራመድሁ አንድ የሻማ ጃኬት መሳይ የደረበ ልጅ፣ “ወዴት ነህ?” አለኝ።
ወደ ውስጥ ለመግባት መፈለጌን ነገርሁት።
ልጁም ኮስተር ብሎ፣ “ሰራተኛ ካልሆንህ መግባት አይቻልም” አለኝ።
ምን ችግር አለው ባየው? አልሁት። የልጁ ድምጽ ጎርነን አለ።
“አይቻልም! አይቻልም!”
እባክህ አጽሟን እንኳን ልየው አልሁት። መልስ አልመለሰልኝም። እኔም ወደ ፊት አቀናሁ። ትንሽ እንደተጓዝሁ የከለከለኝ ወጣት ለሆነ የስራ ባልደረባው ይመስለኛል “ይሄ የፒያሳ ልጅ መሆን አለበት።” ሲል ሰማሁት። ባልደረባውም ቀበል አድርጎ “ያስታውቃል። ይሄ የአዲስ አበባ ልጅ ነው።” አለው።
እኔም በሆዴ “አዎ የመከረኛዋ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ። መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር ባልገዛም ባይነቱ ብትር የሚበዛበት” ብዬ መንገዴን ቀጠልሁ። የቀጠሮ ሰዓት ትንሽ ቢረፍድም ወደ ቀጠሮ ቦታው አቀናሁ።
“ዓለም በየደቂቃውና በየሰዓቱ እየተናደች ነው። አንዱ በልማት ሰበብ ሌላው ደግሞ በነጻነት ሰበብ።”
እውነትም ምድራችን ያለማቋረጥ ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየረች ነው። በመካከለኛው ምስራቅ፣ በኤዢያ፣ በአፍሪካና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት እየተከሰተ ነው።
በአህጉራችን አፍሪካ እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት መቋጫ በማጣቱ አያሌ የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት በጎረቤታችን ሱዳን አሁንም ቀጥሏል። ችግሮቻችንን በውይይት መፍታት የተከለከልን እስኪመስል ድረስ ጦርነትን እንደመፍትሄ ወስደን የንጹሃን ህይወት በየደቂቃው ሲቀጠፍ ዝም ብለን እያየን ነው።
ለመሆኑ የትኛው ነው ትክክለኛው? ለመብቱና ለነጻነቱስ የሚታገለው የትኛው ወገን ነው? ብለን ስንጠይቅ ትክክለኛው መልስ ለማግኘት እንቸገራለን። ምክንያቱም እውነት የአሸናፊና የጉልበተኛ ሆኖ ስለሚቆጠር።
የምዕራባውያንን ሴራ በማጋለጥ የሚታወቁት የቀድሞው የዚምባቡዬ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ንግግር አድርገው ነበር።
(“How do you convince the coming generation that education is the key to success, when we are surrounded by poor graduates and rich criminals”?)
በማን ነው የተከበብነው? ግራ ግብት የሚል ነገር። ይህንን ማለቂያ የሌለው ሃሳብ እያብሰለሰልኩ በእግሬ ስጓዝ የቀጠረኝ ልጅ ስልክ ደወለና “የት ደረስህ?” አለኝ።
እኔም “ጥበብ እድገት ት/ቤት” ጋር እንደደረስሁ ነገርሁት። ጥበብ እድገት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ትምህርቴን የተከታተልሁበት ት/ቤት ነው። ባልንጀራዬም እዚያው ከትምህርት ቤቱ መግቢያ ፊት ለፊት እንድጠብቀው ነገረኝ።
እኔም ከአንድ ሆቴል በረንዳ ላይ ተቀምጬ ሃሳብ እያመነዠክሁ ጓደኛዬ ደርሶ አጠገቤ መቆሙን ልብ አላልሁትም ነበር። ቀና ስል አየሁትና ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ ሰላም አልሁት። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ አተኩሮ አየኝና:-
“ምን ሆነክ? የደበረህ ትመስላለህ” አለኝ።
ኧረ ምንም አልሆንኩም ግን ብዬ ሳልጨርስ “ግን ምን?” አለኝ።
ወደ አንተ ስመጣ እግረ መንገዴን የወደመውን ከተማ አይቼ ገርሞኝ ነው አልኩት።
እሱም “የድሮ ሰፈርህ ስለፈረሰ አዝነህ ነው? ለምን ታዲያ ፍራሽ አውርደህ አትቀመጥም?” ብሎ ሳቀ።
እኔም ኮስተር አልኩና ስለ እሱ አይመለከትህም። ስለ መጣንንበት እናውራ አልኩት። አሁንም ፈገግ አለና በቅጽል ስሜ “ቀዮ” ብሎ ጠርቶ
“ስሜታዊ አትሁን። ዓለም ያለማቋረጥ እየፈረሰች ነው። እኛም የዛው አካል ነን። ሊጤን የሚገባው ነገር ዓለም እየፈረሰች ያለችው አንድም የቀድሞውን ታሪክ ለማጥፋት፣ እንዲሁም የስልጣን ጥምን ለማርካት ነው። ”ጦርነት ያወጅነው ለህዝባችን ጥቅምና ነፃነት ነው።” ይሉሃል። የጥንት ታሪክ የሚያወድሙትን ደግሞ “ለልማት ነው።” ይሉሃል። እውነታው ግን በተቃራኒው ነው። የእኛ ሀገር የችግሩ መነሾ ደግሞ የብሔር ፓርቲና ገዢነት ያመጣው ጣጣ ነው። ለዚህ መፍትሔ የሚሆነው ለጋራ መግባባት የሚበጅ የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨትና ወደ ተግባር መለወጥ ብቻ ነው። መፍትሔው ምንም ይሁን ምን ለህበረተሰቡ የሚበጅ መሆን አለበት። ተግባባን ቀዮ?”
ብሎ የሚታዘዝ አስተናጋጅ ለመጥራት አጨበጨበ። እኔም በሀሳቡ መስማማቴን በጭንቅላቴ ንቅናቄ ገለጽኩለት።
በአሁኑ ዘመን በትህትና መነጋገርና መደማመጥ ዳገት በሆነበት ጊዜ፤ እውነቱና ውሸቱ በተደበለቀበት ወቅት፤ በነጻነት ሀሳብን ለማንሸራሸር የምትደፍረው ወዳጅ ማግኘት ከባድ ነው።
ስለዚህ የዓለማችን ጉዳይ ማይክል ኤልነር የተባለ ፀሐፊ እንዲ ብሎ ትዝብቱን ገልጿል።
“በምድራችን ላይ አሁን ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሏል። ሀኪምች ጤና እያጠፉ ነው፤ የህግ ባለሞያዎችን ህግን እያጠፉ ነው፤ ዩኒቨርሲቲዎች እውቀት እያጠፉ ነው፤ መንፈሳዊ ተቋማት መንፈሳዊነት እያወደሙ ነው፤ ታዲያ እኛ ማንን እንመን? ከአንድዬ ሌላ ማን ይታመናል?”
ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል ትምህርቴን የተከታተልኩት ጥበብ ዕድገት የሚባል ት/ቤት ነው። እኔና ቤተሰቦቼ የምንኖረው ደሞ ሰሜን ሆቴል አካባቢ ናይጄሪያ ኢምባሲ አጠገብ ነበር። በልጅነታችን ሳንቲም ስናገኝ ብስክሌት ለመንዳት ወደ ፒያሳ ወረድ ብለን ስንጫወት ውለን እንመለሳለን። ፒያሳ መዋል ራሱ ደስታን የሚሰጥ ይመስለኛል ለምን እደሆነ አላቅም።
በዚህ መሀል ወላጅ አባቴ ወደ ሀረር ለስራ ጉዳይ ሲሂድ ወደ ሳሪስ የእናቴ ቤተሰቦች ጋራ እንድቀመጥ ተወሰነብኝ። ከአባት እና ከእኩያ ጓደኞቼ ጋራ መለያየቱ ትልቅ ፈተና ቢሆንም ግን ምንም ማድረግ አይቻልም እና ወደ አዲሶቹ ቤተሰቦቼ ቤት መጣሁ።
ከአዲሶቹ ቤተሰቦቼ ለመላመድ ብዙም አልከበደኝም። በትምህርት ጎበዝ መሆኔ እና የአደራ ልጅም በመሆኔ በቤት ውስጥ እንደብርቅ ታየሁ። በእድሜም የቤቱ ትንሽ ልጅ ነበርኩ።
አመታቶች ተቆጠሩ እድሜዬ 13 ሲሞላኝ የአባቴን ወንድም እንድጠይቅ ተፈቀደልኝ። አጎቴ የሚኖረው ሰሜን ማዘጋጃ ገባ ብሎ ላዛሪስት ትምህርት ቤት አከባቢ ነው። ያችን ቀን መቼም አረሳትም። በአጎቴ ጥየቃ ሰበብ ፒያሳን ለማየት ዕድል አገኘሁ። ይህ ነው የማይባል ደስ የሚል ስሜት ነበር የተሰማኝ። በዚህም መሰረት አጎቴን ለመጠየቅ የሚፈቀድልኝ በወር አንዴ በእለተ እሁድ ነበር።
በመሄጃዬ ቀን ቅዳሜ ለሊት ለእሁድ አጥቢያ ሌሊት ነበር የምነሳው። የዛን ቀን ሳቅና ደስታ ይሰማኛል ። ለመሄድ ስጣደፍ የምታየኝ የአክስቴ ልጅ “የት ለመሄድ ነው ይሄ ሁሉ ሽርጉድ?” ትለኛለች። ፒያሳ ነዋ እላታለሁ። “ፒያሳ ደግሞ ምን አለ?” ስትለኝ ደንገጥ እልና አይ አጎቴ ጋር ነው እላታለሁ። “እና አሁን እኩለ ለሊት ነው። እሩቅ ሃገር የምትሄድ ነው እኮ የሚመስለው አነሳስህ።” ትለኛለች እሱማ ነው ግን በጠዋት ለመሄድ ነው። ስላት ዝም ትላለች በዚህ መሃል ለመሄድ በጥፍሬ መቆሜን የምትረዳው አክስቴ የታጠበ ልብስ አልብሳኝ፣ ፊቴ አወዛዝታኝ፣ ሁለት ብርና ብዙ ማስጠንቀቂያ አስታቅፋኝ ትሸኘኛለች። የአክስቴ ልጅም ደበቅ አድርጋ አንድ ብር፣ አለፍ ሲልም ሁለት ብር ትሸጉጥልኛለች። እንዴት እየተንደረደርኩኝ ከቤት እወጣ እንደነበር ሳስበው ይገርመኛል።
ከሰፈራችን የምትነሳ 14 ቁጥር አውቶቢስ ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ታደርሰኛለች። ከባስ እንደወረድሁኝ ቀጥታ ወደ ገ/ትንሳኤ ኬክ ቤት እገባና አንድ ባቕላባዬን አጣጥሜ አፌን እየጠራረኩ ወደ ብስክሌት ተራ እገሰግሳለሁ። ብስክሌት መንዳት አልጠግብም። ለምን እንደሆነ እንጃ ሳንቲሜ ሊያልቅ ሲል ነው የማቆመው። አንዳንዴ እንደውም አጎቴ እንደሚሰጠኝ ስለምተማመን ባለኝ ገንዘብ ሁሉ እነዳበታለሁ። ከዛም በእግሬ ከፒያሳ ወደ ሰሜን ማዘጋጃ አጎቴ ቤት። የልጅነት ነገር ሆኖ ነው መሰለኝ ብስክሌት ስነዳ ልብሴ መቆሸሹን እንኳ ልብ አልለውም። አንዴ እንደውም የአጎቴ ልጅ “በጭነት መኪና ነው እንዴ የመጣኸው?” ብሎ ቀልዶብኝ ያውቃል። በዚህ ምክንያት ነበር ጥንቃቄ ማድረግ የጀመርሁት።
በዚህና በሌሎች በዚህ ጽሑፍ ባልጠቀስኳቸው ምክኒያቶች ነው የፒያሳ ወደ ምድረበዳነት መቀየር ሰላም የሚነሳ የሆነብኝ። እኔ በግሌ የልማት ተቃውሞ የለኝም። ልማትን ማን ይጠላል? ግን ህንጻ ሳይፈርስ ማልማት አይይቻልም ወይ?
ለምን ሃገራችን ላይ ቋሚና ዘላቂ የሆነ፣ ለትውልድ የሚሻገር ግንባታ በጥናት አይገነባም? መንገድ ብዙ ገንዘብ ፈሶበት ይሰራል ይፈርሳል (ለምሳሌ የከተማ ባቡር ግንባታውን ማስታወስ በቂ ነው)፤ እከሌ የሚባል ተቋም፣ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ሌላ ተቋም ይሆናል፤ ጤና ጣቢያ የነበረ ፖሊስ ጣቢያ ይሆናል። በቅርስነት የተመዘገቡ የጥንት ህንጻዎችስ ለምን ይፈርሳሉ? እንዲያውም በአንድ ወቅት አስታውሳለሁ “ከመቶ አመት በላይ የቆዩ ህንጻዎች በቅርስነት እንዲጠበቁ።” የሚል መመሪያ ሁሉ ወጥቶ ነበር።
አሁን ለምን ተሻረ? የጥንቱ አልተፈለገም? ለምን አሁን? ልማታዊ መንግስት ስለሆነ? በአንድ ወቅት አንድ ኢትዮጲያዊ የታሪክ አዋቂ ይመስለኛል በሬዲዮ ቃለ ምልልስ እየተደረገለት ስለ እንግሊዝ ሃገር ተነሳና ምን ያህል የጥንት ቅርሳቸውን እንደሚጠብቁ ለማስረዳት “እንግሊዝ ውስጥ ሼክስፒር ሻይ ሲጠጣበት የነበረ ሻይ ቤት አሁን ምንም ሳይነካ አለ።” ሲል ሰምቼዋለሁ። ምን ያህል ለቅርሳቸው እንደሚጠነቀቁ ማሳያ ነው።
እኛ ሀገር በተቃራኒው የጥንት ቅርስ የሚባል ሲያዩ የሚያቃዣቸው ይመስለኛል። ኢትዮጲያን እነሱ አሁን ጠፍጥፈው የሚሰሯት ነው የሚመስላቸው።
ሁላችሁም እንደምታስታውሱት የዋልድባን ገዳም በልማት ሰበብ ለማፍረስ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። ገዳሙ ሳይፈርስ ለማፍረስ የተነሱት ቀድመው ፈረሱ።የተልዕኮ አስፈፀሚዎችና ተላላኪዎች ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ሰበብ ስለሚፈርሰው ገዳም ቀለል አድርገው “ለልማት ከሆነ እንኳን ዋልደባ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ሊፈርስ ይችላል።” ሲሉ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ከዚህ ነጥቦች ስንነሳ ለእውነተኛ ልማት ከሆነ ከዋልድባ ገዳም የተሻለ ቦታ ማግኘት አይቻልም ነበር ወይ? ለልማት ከሆነ ከፒያሳ ውጪ ሌላ ቦታ ማልማት አይቻልም ወይ? ለሚለው ጥያቄ አፍራሻቹ መልስ የላቸውም። ልማት ልማት ነው በቃ ይሉሀል።
ቀደም ባለው ጊዜ የዘውዳዊውን ስርዓት ጥሎ መንበር ስልጣኑን የተረከበው የደርግ መንግስት መጀመሪያ ከአከናወናቸው ጉዳዮች መካከል በንጉሱ ጊዜ ተገንብተው አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ አያሌ ተቋማትን ሥማቸውን መቀየር ነበር። እና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ፣ ብሔራዊ ቲያትር እና ሌሎችም በርካታ ተቋማት ስማቸው እንዲቀየር አድርጓል። ያልገነባኸውን ስም መቀየር ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?
እና ነገሩን ግልፅ ለማድረግ በዓለማችን ላይ እየተከናወኑ ያሉት ጦርነቶችና ውድመቶች ልማትና ነፃነት የሚል የዳቦ ስም ተሰጥቶአቸው አሁንም ቀጥለዋል ግን እስከመቼ?
እግዚአብሔር ኢትዮጲያን ይባርክ!
ረጅሙ የመከራ ሌሊት ያልፋል።
በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።