በአስቼ

Yesuf Abeba film review on Bayra digital Magazine.

የሱፍ አበባ ፊልም በለገሰ ገነቱ የፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ የቀረበ የግሩም ኤርሚያስ ፊልም ነው፡፡ታሪኩ ሚያጠነጥነው በአንዲት አምባር የምትባል ልጅ አባቷም፤ ቃል የሚባለው በኋላ የተዋወቀችው ፍቅረኛዋም በካርታ ቁማር ሱስ ውስጥ ሆነውባት እነሱን ከሱስ ለማውጣት የምትከፍለውን መስዋእትነትና የምትጓዘውን ርቀት የሚተርክ ፊልም ነው፡፡

ሁኔታውን የተሻለ እንረዳ ዘንድ በጠቅላላው ሱስ ምን እንደሆነ ለመረዳት ከመሞከር እንጀምር፡፡ ሱስ በማለት የምንጠራው የስነልቦና ህመም ሲሆን አንድን ነገር ከቁጥጥር ውጪ በወጣ ሁኔታ ጎንዮሽ ጉዳቱ እየታወቀ ከአንድ ቁስ ጋር ወይም ክስተት(ክንዋኔ/ድርጊት/) ጋር የሚኖረን ስነልቦናዊ ትስስር ወይም ድግግሞሻዊ ልምምድ ነው፡፡ ከቁስ ጋር ስንል እንደ መጠጥ ፣ ሲጃራ ፣ ሃሺሽ የመሳሰሉት ሲሆኑ የክንዋኔ ሱሶች የምንላቸው ደግሞ እንደ የቁማር ሱስና የወሲብ ፊልም የማየት ሱስ የመሳሰሉት አይነት ልምዶች ናቸው፡፡ 

ጭንቅላታች ከሚተዳደርባቸው ባህሪዎች አንዱ የድግግሞሻዊ ባህሪ ነው፡፡ ማለትም ጭንቅላታችን ነገሮችን ለመቆጣጠር እንዲያስችለው ቅደም ተከተል አስቀምጦ እነሱን በተዋረድ በመጠቀም ድግግሞሽ ይፈጥራል፡፡ በዛም መልኩ ነው እንደ ልብ ምታችን፣ ጨጓራችንን፣ጠዋት የምንነሳበትንም ጊዜ ሁላ ሳይቀር በአጠቃላይ በሰውነታችን የሚፈጠሩ አዳዲስ (stimulus) ክንውኖች ሁሉ የሚቆጣጠረው፡፡ እናም ሱሰኞች ማህበረሰቡ እንደሚስለው ሞራል የጎደላቸው ወይም ስርዓት አልባ እና እራሳቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው አይነት አይደሉም፡፡ የተሳሳተ ድግግሞሽ አእምሮአቸውን ያስተማሩ ሰዎች እንጂ፡፡

ሌላው ሱስ ወይም ሱሰኛ ማህበረሰቡ እንደሚያስበው ከሚጠቀሙት ነገር ጋር አካላቸው አልያም ጭንቅላታቸው ኬሚካላዊ ውህደት ወይም ልምምድ ፈጥሮ አይደለም፡፡ ይልቅ በዚህ ድግግሞሽ ወቅት ጭንቅላታቸው ውስጥ (ዶፓሚን) የተባለ ሌላ ንጥረ ነገር ስለሚመነጭና ያም ንጥረ ነገር ጭንቅላትን የማዝናናትና ጥሩ ስሜት እንዲፈጠር በማድረጉ ነው፡፡ይህንንም ንጥረ ነገር ጭንቅላታችን ላደረገው አዲስ ክንውን እንደ ክፍያ እንደመልስ ስለሚቆጥረው ይህን ንጥረ ነገር በብዛት እንዲገኝ ክንውኑ እንዲደጋገም ጭንቅላት ይገፋፋፋል፡፡ ይህም (reward circuit) ይባላል፡፡ በዚህም ምክንያት ክስተቱ(ክንዋኔው) በሚደጋገም ጊዜ ጭንቅላትን የአሰራር ሂደት ባህሪ ፍፁም ስለሚቀይረው ለማስተካከል ወይም ለመመለስ እጅግ ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ያን ጊዜ ነው ሱስ ወይም የሱስ በሽታ ብለን የምንጠራው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሁኔታው ለከት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ማለትም ለምሳሌ ያክል አንድ ሰው መጀመሪያ ለመስከር አንድ ብርጭቆ አልኮል ይፈጅበት ከነበር በቀጣይ ሰውነቱ ያንን የሚያሰክረውን አልኮል ይለማመድና በቀጣይ በዛው ደረጃ ሰክሮ ዶፓሚን የተባለው ንጥረ ነገር እንዲመነጭ ከአንድ በላይ ብርጭቆ ይጠይቀዋል፡፡

 በዚህም ምክንያት ይበልጥ በሱሱ እየተሳበና እየተዋጠ ይቀጥላል፡፡ እናም እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ያ ማንኛም የተለማመደው ነገር ከራሱ ነጻ ፍቃድ በላይ ሆኖበታልና ከሱ ውጪ ከሌላ አካል ሌላ ተጨማሪ እርዳታ(ህክምና) ያስፈልገዋል፡፡የቁማር ሱስ ወቅትም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፡፡ ዶፓሚን የተባለው ንጥረ ነገር እንዲመነጭ ምክንያት የሚሆነው ሲያሸንፍ የሚኖረው የደስታ ስሜትና አሸንፍ ይሆን ወይስ እሸነፍ ይሆን የሚለው ውጥረት ሲሆን ይበልጥ ስቦ የሚያስቀረው ደግሞ ቀጣይ በተሻለ ስቆምር የተሻለ አሸንፋለሁ የሚለው ሃሳብ ነው፡፡

ፊልሙን ከሲኒማ አውቶግራፊ አንጻር ስናየው ውብ የምስል ቀለም ምጣኔና ታሪኩ በደንብ ሊገልጸው የሚችል መልክ የተላበሰ ሁኔታውን መግለጽ የሚችል ነው፡፡ በተለይ ከቦታ መረጣው ጋር ተዳምሮ እጅግ የመክበድ ስሜት ያለውን የቁማር ቤት ግርማ ቀለም የተላበሰ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን አንዳንድ ቦታዎች ላይ በሚያስታውቅ መልኩ ብሎም በሚረብሽ መልኩ አላስፈላጊ የካሜራ መንቀጥቀጦች ይታዩ ነበር፡፡ ከዛም በተጨማሪ የፀሐይን ብርሃን ውበት በመጠቀም ውበትና ሃሳብ ለመግለጽ የተሞከረ ቢሆንም ትንሽ ለመቀነስ ባለመሞከሩ ወይ ብርሃኑ ቀጥታ ካሜራው ላይ በመብራቱ ትንሽ የሚረብሽ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

ከድምጽ አንፃር ስንመለከተው የራሱ ማጀቢያ ሙዚቃ እስከማዘጋጀት የተደከመበት ሲሆን ከፊልሙ ቀለምና ሃሳብ ጋር የተዋሃደ ፤ ውበትና ሞገስ እንዲኖረው እና እንዳይሰለች አስችሎታል፡፡ ይህም ልምምድ በፊልም ኢንዱስትሪው ላይ ሊለመድ የሚገባው በጣም ግሩምና ይበል የሚያሰኝ ልምድ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ትእይንቶች ላይ በማቀናበር(edit) ስህተት መሰለኝ ድምጽ አልባ ንግግሮች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ትእይንቶች ላይ አጃቢ ድምጾች(folly sounds) ይጎድሉታል፡፡ ያም በመጉደሉ የዛን ትእይንት ሙሉ ስሜት እንዳናገኝ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡

ከድርሰት አንፃር ስንቃኘው ደግሞ ፊልሙ ታሪኩን በጥሩ ሁኔታ የተረከልን ሲሆን የታሪኩን ጡዘት በአግባቡ ገልጾልናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህም ከፊልሙ ደስ ያለኝ ክፍል ነው፡፡ ሌላው ፊልሙ ስለ ትውልድ ተጨንቆ አባቶችን ”ልጅህ እንዳይወድቅ ከፈለግህ አንተ ተጠንቅቀህ ተጓዝ” እያለ ሁለት እርምጃ ቀድሞ ትልቅ ምክር የሚመክር ድንቅ ፊልም ነው፡፡ በተለይ አሁን ላለነው ትውልዶችና ሃገራችን ላለችበት ማንኛውም አይነት ውጥንቅጥ እንደ መድሃኒት የሚወሰድ ትልቅ ሃሳብ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡

 ነገር ግን በአተራረኩ በኩል አንዳንድ ቦታዎች ላይ ጥያቄ የፈጠሩብኝ ሃሳቦች አሉና እነሱን ላንሳ፡፡ትረካው ጥሩ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ግን ተአማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚጥሉ ትእይንቶች ታይተዋል፡፡ ለምሳሌ ለፊልሙ ማማር ብቻ ሲባል የሚገቡ አንዳንድ ትእይንቶች የታሪክ ፍሰቱን ሲያጣርሱ ተስተውለዋል፡፡ ለምሳሌ ታዋቂውና የሚፈራው ቁማርተኛ(አንበርብር) የአንባርን እጮኛ (ቃልን) ቁማር እየተጫወተ ባለበት ሰዓት መጥቶ የአባቱን መኪና ሽጥልኝ ሲለው እምቢ ብሎ ሲወጣ እዛው ቁማር ቤት እንዳለ ንብረቴ በማለት የሚጠራውን ዮናስ የሚባለውን ገጸባህሪና ሌሎች ደብዳቢዎች ሲልክበት አይተን ነበር፡፡ ወዲያው በቀጣዩ ትእይንት አንበርብር የተባለው እኩይ ገጸባህሪ አትክልት ውሃ እያጠጣ እያለ ዮናስ መጥቶ የቃልን መልእክት ሲነግረው ተመለከትን፡፡ ታዲያ አንበርብር በዛ ፍጥነት እንዴት ከቁማር ቤት ወጥቶ ውሃ ማጠጣት ውስጥ ገባ ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን፡፡ ሌላ ጊዜ ነው እንዳንል የሁለቱም ትእይንቶች ጊዜ ምሽት ነው፡፡ በዛ ላይ ዮናስ እየሮጠ ወደ አንበርብር እንደሄደ አይተናል፡፡ በመሆኑም ትንሽ የታሪክ ፍሰቱ ላይ ጥያቄ እንዲፈጠርብን ሆኗል፡፡

ሌላው ቃል ታፍኖ የሚደበደብበት ትእይንት ላይ እጄን ፍቱኝ ብሎ አፋኞቹ ፈተውት ሲወድቅ ከፊቱ ባገኘው ጉማጅ እንጨት ደብድቦ ሲያመልጥ ይታያል፡፡ ነገር ግን ዮናስ ከአፋኞቸሁ አንዱ ሆኖ ሳለ ሲደበደቡ ቆሞ ማየቱ እና ጥቃት አለመፈጸሙ ቃልም እሱን ምንም አለማድረጉ በግሌ ትንሽ ጥያቄ ፈጥሮብኛል፡፡ በተመሳሳይ አንባር እና ቃል ሲተዋወቁ የሚታየው ትእይንት ላይ አንባር የቃልን መኪና (እስፖኪዮ) መስታወት ስትመለከት ይታያል፡፡ ወዲያው ደግሞ አባቷ ከቁማር ቤት ሲወጣ ከቃል ፊት ከቆመው መኪና ውስጥ አስገብታው መኪናውን አስነስታ ስትሄድ ይታያል፡፡ ታዲያ ከፊት የራሷ መኪና ቆሞ ለምን የቃልን መኪና እስፖኪዮ ተመለከተች የሚል ግርታ የሚፈጥር ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

በአጠቃላይ ስናየው ግን የታሪኩ ፍሰት ታሪኩን በአግባቡ የተረከልን ሲሆን አስተማሪነቱም የማይካድ እውነታ ነው፡፡ በመሆኑም የቁማርም ሆነ ሌሎች ሱሶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ትልቅ ከሱሱ ለመውጣት መጀመሪያ ሱሰኞች እንደሆኑ ማመንና በቀጣይ ራሱን የቻለ የስነ ልቦና ህክምናም ሆነ ማገገሚያ ጣቢያ በመግባትና በአግባቡን ህክምናውን ወስደው እራሳቸውንም ቀጣይ ትውልድም ሃገርንም እንዲጠቅሙ እላለሁ፡፡ በመጨረሻም ”ልጅህ እንዳይወድቅ ከፈለክ አንተ ተጠንቅቀህ ተጓዝ” እያልኩ እኔ በዚህ አበቃሁ አመሰግናለሁ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ልባምነት

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *