ውብአረገ አድምጥ

ጌታዬ!
እና በዚህ መንከላወሴ ፥ጠፍቶ የነፍሴ ምርፋቅ
ስጋዬም በነዲድ ጅራፍ ፥ተገርፎ በዓለም ስንፏቀቅ
ማሰነች ነፍሴ ባከነች ፥እንደግዞተኛ ልዑል
መኖር በድጥ ተገፋ ፥መኳተን ሄደ በእንብልብል
መልሰኝ—-
መልሰኝ! ከአንተው ክብር አምባ
ሹመኝ! በሞት ደረባ
ሳበኝ! ወደ ሹም ግብር
እንደሰው፣ እንደልጅ ልኑር
ጌታዬ—
ያጣሁትማ ቦታ አለ፣ በዘመን ትብታብ የታሰረ
የቸገረኝ ፍኖት ሞልቷል፣ ጥንድ አይኔ እየታወረ
ልጥቀስ ክቡር ዳመና፣ ልንሳፈፍ እስከ ወዲያ ሃገር
ልሻገር ሃይቅ ማዕበሉን፣ ልቅዘፈው በጉማጅ በትር
ልውተርተር ተወኝ በእመ አምላክ፣ ላይገታኝ የግዝት ቃሉ
ድምጼ ተንቀለቀለች፣ ፈርሷል ከአንተጋር ውሉ
እባክህ ሳበኝ በእመ አምላክ፣
አክናፍ ከጎኔ ባይበቅል ፥መባርቅት ጀርባ ባይሰጡኝ
አልፋና ኦሜጋው አንተ ወደቀደመ ክብሬ መልሰኝ
አለኝ የከሰመ ዓለም፣ በነፍስም በስጋ መካን
እሱን አትስጠኝ አንድዬ፣ ሞቱን አትሻ የልጅህን
ያጣሁትማ ቦታ አለ!
ብጎርስ የማዕድ ቁልል፣ ብጎነጨ የመጠጥ ጅረት
ስጋዬ አድሮ ከርሃቡ፣ ነፍሴም አድራ ከወረት
የውሻ ጩኸት ገዝፎብኝ፣ ስርድ እያየህ በፍረሃት
የንፋስ መፍጠን ሞት መስሎኝ ፥እንደ አምላክ አልቦ ስርበተበት
አየኸኝ እኮ ትናንትና ፣
ዛሬም አድሬ እንደ አምና፣
የትምከህቴን መንገድ እየው፣
ለኩራቴ ወደር የለው፣
መልሰኝ ለእመ አምላክ ብለህ ፥ደከመኝ የዓለም አለንጋ
መሞትን ለብቻ አየሁት፣ ባይሆን ልኑር አንተ ጋ
ለፍጥረት ስምን ባላድል፣ ከአናብስቱ ባልወዳጅ
እንዴት ለእኔን መሳዩ፣ እኔው ልሁነው አሳዳጅ?
በባዕት ጸሎት እግዚኦታ፣ ለሰው ልጅ መዳን ባልታትር
እንዴት በወንድሜ ደም በሰው ልጅ ስቃይ ልፎክር?
የሳትሁትማ መንገድ አለ ፥ባልፈናጠጥ ከዘንዶ ጀርባ
የዘነጋሁት ክብር አለ፣ ለፍጥረት ስምረት የሚረባ
የት ነው አሠኘን ጌታዬ ፥በየት ነው የእውነት መንገዱ?
በቃኝ ለሞት መሻማት፣ ቀፈፈኝ መተራረዱ
ዘግናኝ ነው መቀራደዱ፣
ጌታዬ—
ደከመኝ የሹም ጋጋታ፣ እፎይ ልበል እባክህ
አስተኛኝ ከአጸዱ ግርጌ፣ ጠልለኝ በሰፊው ክንድህ
አሰብኋት የኪዳን ምድሬን፣ አለቀስሁ ለእሷና ለእኔ
ስትበዘበዝ ታዘብሁ፣ ስትንጓለል አይቷል ዓይኔ
ጌታዬ!
በእናትህ ተለመነኝ ፣ መልሰኝ ካጣሁት ቦታ
ላንተስ ሃዘን አይደልም ወይ፣ የብኩን ልጅህ አውታታ?
ገልጠህልኝ የበኩሬን፣ ሾመኸኝ ከበኩራት ምድር
አክብሬ ባላስከብርህ፣ በላቤ ቁና ባልሰፍር
ልጅህ በዓለሙ ናውዞ፣ የመክሊቱን አንዳች ባይከፍል
ከአባተነት ቅጣት ወዲ፣ያ ይቅር ባህርይህ አይደል?
እናም—– ተመልከት ወደ እኔ
መጥኔ አዬ መጥኔ!
የተገፈፍሁት ግማጃ ጸጸተኝ ፥ያሽቀነጠርሁት እንደ ሰንኮፍ
ሞት ማስነሳት ክብሬ ሆኖ፣ ተከበብሁ በአስከሬን ዝንጥፍ
እመ አምላክ!
የመለኮት እንቁ ሙዳይ፣
ክቡድ እሳት፣ በልብሽ ቻይ
አድምጪኝ የምድር እናት፣ አውጭኝ ከቁልቁለቱ
ለኗሪ እሪታ ምሱ፣ የዓለም ምሽለቅ ግለቱ
እንደ ሌባ፣ ባለ እጅ አመል
ከነፋሻው ብኮበልል፣
ከእምነት ብፈስ ብንፎለፎል፣
እንሰፍስፍ ነው የእናት አንጀት፣ ይላወሳል በልጅ ዳዴ
እኔ እኮ ነኝ ምን ባናውዝ፣ ብንሸራተት ከመንገዴ
አየሽልኝ የጉድ ሃገር?
ሰማሽልኝ የሙት አድባር?
መምዘግዘጉ ከሰገነት ፥አንዳች እውነት ፍክ ላይለው
መልፈስፈሱ ከእምነት አጥር ፥የሞትም ሞት ያልመሰለው
ይሄው በላኝ ቦጫጨቀኝ፣ እኔም ቅርጥፍ ምኔ ሞኙ
ባድማውን መዘበረው፣ ጅል ቢይዘው እንደተኙ
እና በዚህ ተቀየምሽኝ?
ከአስራት ምድርሽ የረሳሽኝ?
ይቅር በይኝ ፣ስለ አባትሽ
ተለመኝኝ፣ በአንድ ልጅሽ
ቆጭቶኛል የሸሸሁት፣ የገፋሁት እንደ ኮሶ
ማዕድ መርገጥ፣ ከእኔም ብሶ
ስልጡን ነኝ ባይ፣ እጥፍ ከስሮ
አዋሻኪ፣ አእዋድ ቆጥሮ
አዬ የጉድ መዝረብረብ ፥እግዚኦ የመአት አንጋዳ
እናት ለልጅ ስትለምን፣ ሃኬትን ሞት እየረዳ
ለምኝልኝ እም አምላክ፣ ጎኔን ጦሩ ነደለው
ስጋዬን ለአሞራ ቀለብ፣ ለጆቢራ ቆርሶ አደለው
ልመለስ ካጣሁት ቦታ፣ አግዥኝ ባክሽ እመ አምላክ
መለኮት ከቃልሽ አይጎድል፣ የሰላም መልአኩን ይላክ
ደከመኝ እኔስ ብኩኑ፣
ከረረ ጅማት ጣመኑ፣
ሳመላምለው በአርምሞ፣ ሳስበው የኑሮን ስሌት
ያጣሁትማ ቦታለ አለ፣ አንዳች የሰው ልጅ ስምረት
የሚጨብጡት አይደል ፥እንደ አሸን ወዲያው ክንፉ የሚረግፍ
የሚጎትቱት አይደለም ፥ከአዞ አረግ ስሩ የሚገዝፍ
የሚታቀፉት አይደል ፥እንደ ዶቃ የአንገት ክታብ
የሚቀምሱት አይደል ፥ሽፍን የምላስ ላይ ቆብ
በራዕይ እንደተሳለ ፣
በምኞት የተንጣለለ፣
ላዩ የእብቅ ተራራ፣
ውስጡ የነፍስ ጎተራ፣
ቃልና ተግባር ተገምደው፣ ያበጁት ከሰንፔር እንቁ
ሞትና ህይወት ተገርተው፣ ያቆሙት እንደ ሰንደቁ
እሱን! አምጡልኝ እሱን!
ስጡኝ የኪዳን ምድሩን፣
እሙ የግዮን ቤቴ፣
እሙ ነይ አመ እምነቴ፣
አድርሱኝ ከቤቴ ደጃፍ፣
አግዙኝ ከሸክሜ ልረፍ፣
ጌታዬ
እና አየኸኝ አይደል?
መቼም ፊቱን ከዞረ፣ ልጅም ከተጸጸተ
ለግብሩ ልጓም አብጅቶ፣ ዳግም ካልወሰለተ
ቃሉስ ለንስሃ ደም፣ ለውሃውስ መች ገደረው
ፍሬው ከጎመራለት፣ ከአሸተ ምን ቸገረው?
ይላልና ህያው ቃልህ፣
የእኔንም ምንዳቤ እየው ፥ስለ እመ አምላክ ስለ እናትህ
መልሰኝ ካየሁት ቦታ፣ አኑረኝ ከእቅፍህ አባ
ስኖር አይትሃልና፣ አልብሰኝ የክብር ካባ
አልብሰኝ ባክህ፣ በእመ አምላክ
ይብቃኝ የደም ዛቻቸው፣ ከልለኝ ከሞትም መልአክ!
ጌታዬ! ዛሬን ሰጋሁ፣
ነገን ፈራሁ ፣
ድንጉጥ ሆንሁ፣ ለዓለም ባይተዋር
የስለት ጩከት እየሰማ ፣ከአራጁ ጉያ እንደሚኖር
አደንደንልኝ ልቦናዬን፣ አደንድሰው ጫንቃዬን
መጋፋት መጎሳሰሙን፣ አልችልምና ብቻዬን
ወረረኝ የሽሽት ዳና፣ ከበበኝ የሽንፈት ተስፋ
እና አንተ እያለህልኝ፣ እንዴት ዳግም ልገፋ?
እንደ ሙተ ከዳ ባድማ፣
እኮ ደግሜ ልድማ?
እኮ ሞቴ ይሰማ?
ቆቻ እየዋልሁ ደነገዘ፣ አቅላላች ጀንበር በሃቅሟ
እሷስ የብርሃን ጎርፍ፣ የንጋት መንገድ ነው ስሟ
እኔ እንጅ የብርሃን ልጅ፣ የጨለማ ግዞተኛ
ስከተልህ እንደኖርሁኝ፣ ይብቃኝ ልረፍ ልተኛ
ይብቃህ በለኝ በእም አምላክ፣ መልሰኝ ካጣሁት ቦታ
ስኖር ነው ይሄ ልመና፣ ስኖር ነው ይሄም ሃሌታ!