(ሙሉጌታ ተስፋዬ- አያ ሙሌ)
በኔው ‘ኔ ጥራና
በኔው ኔ’ ብራና
ባዕሜ ቀሰም ብርዕ – በህይወት ማቅለሚያው
ጠርቤ ስለቁጥ
የኑሮን ሽቁጥቁጥ
የራሴ ጉልቻ…አንገቴ አለ ዘምበል
የደም ወዜ ጠለል…እንባዬ አለ ከምበል
በሞት ሞት ጣረሞት…በልቤ ልብ በል!
ስጋት እንደ ውጋት
ነፍሴን ሲሰንጋት
በቅኔ እንቆቅልሽ…ቁልቁል ተቆልፌ
በእምነት…እምም እመ-እዝነት
በህልም ዓለም ሽምጥ…ግልቢያ ተሰልፌ
ለሥጋ ታርቄ -ለገላ መርቄ
እርቃኔን ወጥቼ-ግብኔን አስጥቼ
የጎኔን ጨረስሁት ሆዴን ስሸነግል
ለነገ ራሴ ስንቅ – ለቋንጣዬ አገልግል
ካምና ከታችአምናው
የጉልበት የጤናው
ቢታይ ሁለንተናው- ሁሉ ሁለመናው
የልቤ ልብ በል – ለልቤ ሲጠናው
ብቻ ላይኔ ብቻ- ላይኔ ለብረቱ- ላይኔ ብቻ ቀናው!
ለታይታ ለዝናው
በሰው ፊት በሸንጎ ለወግ ማ’ረግ ዝናው!
አዎ! በኔው ‘ኔ ጥራና
በኔው ኔ’ ብራና
በብርዔ ስከቁጥ-የኑሮን ሽቁጥቁጥ
ደም እንባ- ደም እንባ- እንበለ እንባ ደም
ሕይወት እንጉርጉሮ- በአታሞ አይታደም
(ለሚንቁኝ ለማያውቁኝ
29/07/1984
(የባለቅኔ ምህላ ገጽ 1)