ገጣሚ ታዲዎስ አዲሱ
ሆድ ይመስል _ የማለዳውን ዕርስት
እርስት!
አድርጎት!
ልክ እንደ ቀላዋጭ _ ምንይሉኝ ሳይፈራ
ሲጠራ!
በመለኮት!
“ምሽት አምጡ!” ለሚል አንገቱን ቆልምሞ
ልክ እንደ ከዘራ
ክፉ ባለንጀራ
ሃቅሽን ለቀላል ለምን አሳየሽው?
ወንፊት ውሃ ይዞ የት ሲደርስ አየሽው?
አልልሽ እንዳ’ገር
አልልሽ እንደ-ሰው
ከነገረ-ቀደም _ ማሪያም ስትዋሰው፤
ጭሮ አዳሪ ሆዴ
ከሆነው በስተቀር _ የለም የተዋሰው።
[ይሄንን ታውቂያለሽ…]
ምናምኒት እብለት የለም ለ’ኔ ማረ’ግ፤
የጉሎ-ዘንግ
“ደንበኛ ነው”
ባለው ጥፍር ሲሞሻለቅ _በሃረግ ግንድ
እንዳልነድድ!
ቀለም እና ቀንዱን
ገለባ እና ግርዱን
ለይቼ እንድለየው _ አውቄ እንዳውቅበት
በሆዴ አለሽበት።
ስዟዟረው ፀዳልሽን
ስላዬሁሽ ስትከፊ
እንደ _ ነቢ ትንቢት ባይቀርልኝ ጥፊ
ጥርሶቼን ነክሼ እንደ’ማዬ ወንፊት
ዳግም እስክትስቂ…
እዞራለሁ እንጂ አልሸሽም ካንቺ ፊት።
[ይሄንን ታውቂያለሽ..!]
ግን ደሞ ወርቄዋ…
‘ራስ የቻልኩብሽ መወከል አንገቴ
የኔ ዘንፋላ እናት መሞት አትታክቴ
እኔም ልክ እንደ-ሰው
ማርያም ብትዋሰው
ጭሮ አዳሪ ሆዴ
እጅ አይደርሴ ቦታ፣ ጫንቃውን ሲያሳከው
ከወደደው ሌላ፣ ገልጦ እንደማይሰጠው
ለአበጋር ብቻ፣ ለሰባት _ ከዘራ
የልቤን ገልጬ _ ክስ አለ ምከሰው።
[ ፩ ]
አውቃለሁ…
ሳታረጂ!
ሳታስረጂ!
“ለሂያጅ _ የለውም ወዳጅ”
እያለ ልቡ ድስቅ ይመታል
ያቀፍሽው ሁሉ ዘመን ይረታል።
አውቃለሁ…
በታጠቅ ጌታ በካሳ መንፈስ
ከዘመን መሳ-መሳ ለመፍሰስ፤
መንገድ የሚሰጥ
እንደ ሳለ _ አይሰጥ
ማንም እንዳሻው እንደ ነየተ
ቆርሶ እንዳይበላሽ እየመከተ
ላይመቸው የሱ ገላ
ላይታጠብ እንደጥላ
አንጀት ሲርቀው ፣ ተስፋ እየበላ
መቀነት የፈታች፣ ጉብል አይነት ጉዞ
ነበረውን ብቻ፣ ልጅነቱን ይዞ
መንገድ ሲገባ…
እንዳመጣጡ ወደ ‘ሚያዝበት
‘ካ’ቤት… ወዴት ሌላ…
ጉምቱ ሃጃ ያለበት
አንዲት ወንድ የለሽም!
ከዋጠሽ ማጥ ስቦ ከጉድ የሚያወጣሽ
አ’ደይ! አደይ! ሳይል… ልክ እንደ እንቁጣጣሽ
ፈክቶ የሚያፈካሽ፤
አንዲት ወንድ የለሽም!
ግን እንዴት ቢቸግር?
ምን ያህል ቢጠናሽ?
የምትመጭበትን ወቅትሽን ጠብቆ፤
ከሚሰብር እና… ከሚቀጥፍ ሌላ
የሚጠብቅ አጣሽ!?
[ ፪ ]
አውቃለሁ…
“ሳማ ነው ይበላል
እሬት ነው ይመራል
እውነት ሳይኖርበት፣ ያለ-እምነት ዘመኔ
እንኳን ለሚመጣው፣ ለተረሳው ቀኔ።
አውቃለሁ…
ቢሞላም እንኳን፣ ክብደት ሳይጨምር
ፀሎት መልሶ፣ ስለት ሊያሰምር
ካንድ አምላክ በቀረ…
አለ ቢባል ባለም፣ ዘመን የሚያስጠልል
ይቆረጥ ምላሱ…
ቅቤ _ አንጉቶ ቆርጦ፣ ዳግመኛ እንዳይቀጥል።”
ብለሽ ነው ምታምኝው፣ ዛሬም እንደ-ድሮ
‘ልፋ ያለው በሬ ቆዳው ለከበሮ’
(ቢሆንብሽ እንጂ…)
ወልዶ እንዳልወለደ
እንደ መሃን
ካንቺ ይልቅ መካን
ከነዐንን የወደደ
መኖሩን ነው እንጂ ማኖሩን የካደ…
ሆዱን ወዶ
ክፋት ለምዶ
ሁሉም ለየ’ራሱ
ሁሉም ለ’የነፍሱ
ፀንቶ ባይቆም እንኳን፣ ችሎ ልክ እንደ አክሱም
ዳቦ እንደቆረሰ እንደደረበ ስም፤
አውቃለሁ!
አታውቂም
ግን እንዴት አትነቂም!?
እንደ ላሊበላ
ቅዱስም ንጉስም፣ መሆን ሲጠናበት
ልጅሽን ባ’ንደዜ
አሽከርም እርኩስም፣ መሆን ሲፈርድበት
ለዛውም ያመንሽው
“መንገድ ምራኝ” ያልሽው፣ የባዕድ አሽክላ
እንዴት ትተኛለሽ?
የልጅሽን ዘመን…
እንደ ዘኬ ቆሎ፣ ጋፍፎት ሲበላ?
[ ፫ ]
“መማር ማስተማር” በሚሉት ፈሊጥ
አስረው፣ ተብትበው፣ ባንድ እጅ እንደ ሊጥ
እንደ_ገና ዳቦ
ከላይም
ከ
ታ
ች
ም
ልክ እንደ ተስቦ
ሊለበልቡን!
ሊያንገበግቡን!
እንደ ንስሃ አባት፣ እንደ ሼህ እንደ አቡን
ጧት ማታ ሲሰብኩ፣ በቃላቸው ሲያልቡን
ምንጭሩ እንደ-ነቃ
እንደ ሽንቁር ሳንቃ
ልክ እንደ ብርሌ፣ ሆነን ላንሆን እቃ
ስንጣል እያየሽ
ዝም የምትይበት፣ አንጀት ግን ማ ሰጠሽ?
[ አንቺ’ማ የለሽም! ]
አንችማ የለሽም!
አውቃለሁ ሆድሽን
ተሸክሞ ሟች ነሽ፣ ‘ራስ በራስሽን።
እንጂ’ማ እንዳሉት
አንቺ እንደሰበኩት
“መማር ማስተማር…
የሚሉት ፈሊጥ፣ የተቀሰመው፣ ከሆን ከአበባ
የታለ ጣዕሙ፣ ማሩስ የት ገባ?
ቀፎ’ማ ሞልቷል!” ትያለሽ እንጅ…
ሻጭም ገዢ ሆኖ
ባወቀው ነውና፣ ዋጋ ሚ’ያሸምተው።
ዝም መች ትያለሽ፣ ችለሽ አንቺ እንደ ሰው?
[ ፬ ]
‘እሬቱን ምሬቱን፣ ጨቅጭቄ ብጠጣው
እኔስ እንደማጣት፣ የሚመረኝ አጣሁ።’
እንዳለው አዝማሪ…
አንድ ካላቢው
አንድም ከጥጃሽ
መርጦ መምረጡ
ሰግቶ ሲያሰጋሽ
ለኔ ለምስኪኑ፣ የማላውቀው ሃገር
ለሆዴ ጥሬ፣ ለቤቴ ማገር፤
ጧት-ማታ እያሳየው፣
እንደ ሄዋን በለስ…
ለመጣፍ ለጣፈው ሆደ ባሻ ሆዴ፤
ግንባር አስመትቶ፣
መኖሩን አስንቆት፣
መንገድ ቢያስጀምረው ትፈርጃለሽ እንዴ?
ወይስ ምህረት አለሽ?
ሳይኖሩ በመኖር፤
አንችን ጥሎ ሄዶ፣ አንችኑ ላከለሽ?