ሙቼ ነበር አለኝ

ውብአረገ አድምጥ

የእስትንፋሴ ገመድ፥ አላጠረም እንጂ፥ ከአናቱ ተስቦ
የስጋዬ ግዝፈት፥ አልወሸከም እንጂ፥ ከርሴ ተቀርቅቦ
እኔ እኮ ሙቻለሁ፥ መላም የለኝ ከቶ
ገዳይ ቢዘነጋ፥ ሟች እንዴት ረስቶ?

አለኝ—–

አንድ እረምጃ ስቦ፥ ምድሩን ረገጠ
ዓይኑን ቀለስ አድርጎ፥ መልሶ አፈጠጠ፤

አልተጫረም እንጂ፥ ተጋድሎ ዜናዬ፥ መዋዕሌ በቅጡ
ትውልድ ያለብስ ነበር፥ የእውነቴ ደመና፥ ቢመዘዝ ከጭብጡ
የወጣሁት ዳገት፥ የዘለልሁት ጉድባ፥ የሳተኝ አሎሎ
ለሙትም ይከብዳል፥ እንኳን ቀን ለሚያልም፥ ልክ እንደዚህ ውሎ
ሙቼ ነበር እኮ፥ ጠፋ እንጂ ቀባሪው
ሁሉን እንደ መላው፥ ቀንብቦ አሳዳሪው
ሙቼ ነበር እኮ—–

በቀኝ የእጁ ጥፍሮች፥ አናቱን ሞረደ፥ ጎኑንም አከከ
ዓይኑን ክብ አዙሮ፥ ወደ ሰማይ ላከ
ንጥፍ ደመና ነው፥ ምን እንዳረገዘ፥ ድምጹ የሚናገር
ለአንድ አፍታ ዞረና፥ ከፊቱ እሳት ለብሶ፥ ይጮህብኝ ጀመር

አልሰማህም እንዴ፡ አላየህም ከቶ?
ስንቱ ቤት አገኘ፥ ያውም የእድሜ ይፍታሽ፥ እኔን ሙቱን ትቶ
እኔን እኮ ሙቱን?
በአፈር የማጅብው፥ የምንተእፍረት ገንዘብ፥ የስነ ፍጥረቱን፤
እኔን! አዎን እኔን
ቀዬው እያወቀ፥ በጦር ወጋው ጎኔን፤

እጁን ከፍ አድረጎ፥ መናገር ሲዳዳው
አንገቱን አስደፋው፥ የብሶቱ ፍዳው፤

ድምጹን ለሰስ አርጎ

ሙቼ ነበር እኮ!
ሙቼ ነበር እኮ!
ሙቼ ነበር እኮ!

ሌላም ሌላም ቃላት፥ እያግትለተለ
ይሰንደው ጀመር፥ እያከታተለ፤

ድንገት ቀና ብሎ፥ ዙሪያዬን ገርምሞ፥ በነፍሱ ጦር ሳተኝ
በእዝነት ጋሻ አዙሬ፥ በጥያቄ ሃኔ፥ ላናዝዘው ሻተኝ
መዘዘ ግልምጫ፥ በትዝብት ቃፊር፥ ህመሙን አግዞ
ያደባዬኝ ጀመር፥ አግድም ይሰልቀኝ፥ በፌዙ ሰቅዞ
አፉ ጣር አወጣ፥ ሌላም ሞት ደገመ
ሙቼ ነበር ብሎኝ፥ ሄደ እያዘገመ፤

ክው ብዬ ቆሜ፥ ደርቄ እንደ ግራር
ማርከሻ እየፈለግሁ፥ ለተጋትሁት መራር
ስጋ ለብሶ ሳዬው፥ የሙት አንደበቱን
እንደምን ልረዳው፥ የከርታታ ሞቱን።

(ከዘራፊው ማስታዎሻና ሌሎች ግጥሞች ገጽ፣ 72-73)

ከዘራፊው ማስታዎሻ የግጥም መድብል

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *