ልዑልሰገድ አስማማው

ነጋ ደግሞ ሩጫዬን ልጀምር፡፡ ህይወት ሩጫም አይደለች? ናት እንዴ ግን? ማነው ሩጫ ናት ያለው? እንጃ አባቱ። ሩጫነቷን ለማስመስከር ማስረጃ ማቅረብ ባልችልም ግን ሩጫ ትመስለኛለች። ባትሆንም ግድ የለኝም።

ለእንደእኔ አይነቷ ተራ ደንብ አስከባሪ ህይወት እንዲህ ናት እንዲያ ናት ብሎ መፈላሰፍ ምን ሊረባ? ተነስቶ ከላይ እስከታች አንደ ጎመን አረንጓዴ የደንብ ልብስ ለብሶ፣ አረንጓዴ ኮፍያ ተኮፍይቶ፣ አረንጓዴ ጫማ ተጫምቶ፣ ሽመል ዱላ አንግቶ መውጣት… ። አለቆቻችን ህገወጥ ነጋዴዎች ያሏቸውን ከመንገድ መንገድ ማባረር፣ ማሳደድ፤ ድል ቀንቶኝ ነጋዴ ወይም ጥሎት የፈረጠጠውን እቃ ከያዝሁ ለአለቃ ማስረከብ፤ ከዚያ ደሞዝ መብላት።

ታዲያ ህይወት ለእኔ ሩጫ ናት ብል ተሳሳትሁ? ማንን ነው የምጠይቀው? እንጃ አባቱ። አሁን አሁንማ ህይወት በራሷ አስጠልታኛለች። ከእንቅልፌ ስነሳ እንኳን የሆነ አርባ ምናምን ወይም ሰማኒያ ወይም መቶ ምናምን ኪሎሜትሮችን ሮጬ ሮጬ ሮጬ… ከጫፉ የደረስሁ አይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ። ተኝቼ ስነሳ ይደክመኛል። መነሳቱ ሳይሆን ቀጣይ አንድ ቀን ጭማሪ እየኖርሁ እንደሆነ እያሰብሁ ይደክመኛል፤ ስበላ ይደክመኛል፤ ስሄድ ይደክመኛል፣ ስቆምም ሆነ ስቀመጥ ይደክመኛል። ቀኑን ሰድጄ ሳሳድድ ውዬ ወደ ቤቴ ስገባም ይደክመኛል። የሚደክመኝ ግን ሰዶ ማሳደዱ አይደለም። ቀጣይ ሌላቀን እንደሚመጣ ማሰቡ ነው።

ሰው ሲያፈቅር ካፈቀረው ሰው ሃሳብን ብቻ አይደለም ለካ የሚያተርፈው። ኃይሉንም ጭምር ነው የሚጋራው። ያ ኃይል ነበር ለካ ህይወቴን አስደሳች እና አጓጊ የሚያደርጋት። ምክንያቱም ተስፋ ነበረኛ። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ስራ እንደምሄድ ሳይሆን አሱን ለማየት እንደሆነ ነበር የማስበው። ሲስቅ ሳቁን እያየሁ ልደሰት፣ ሌሊት ለህልሜ የሚሆነኝን ቁመናውን ልመረምር፣ ላጤነው እና ልመዘግብ እንደሆነ እያሰብሁ ነበር የምሄደው።

ማታ ከስራ ወደ ቤቴ ስመለስ ደግሞ ናፍቆቴን ታቅፌ ለተጨማሪ ሌላቀን ላየው እንደሆነ እያሰብሁ፣ ተስፋዬን በልቤ ጉያ፣ ምግቤን በፌስታሌ ሸክፌ ነበር የምጓዘው። አስታውሳታለሁ ያቺን ዕለት። አሱን ያየሁባትን፤ ፍቅር እንደ ንብ እዝዝዝ እያለች መጥታ ጣፋጭ መርዞቿን ከልቤ ላይ የተከለችበትን ዕለት።

ትዝ ይለኛል ጎመኔ ለብሼ፣ ጎመኔ ተጫምቼ፣ ጎመኔ ኮፍያ ኮፍይቼ፣ ወደ ተለመደው ሰዶ ማሳደዴ ሳዘግም፤ እሱ እና የስራ አጋሮቹ ደንብ ሽሽት ካርቶኒያቸውን በእጆቻቸው እንደሸከፉ አስፓልቱን ተሻግረው የሁለቱ መንገዱች አካፋይ ላይ ቆሙ። አንዴ ወደኛ ሌላ ጊዜ ወደ አስፓልቱ ውል ውል እያሉ ድንገት አሱም ሲዞር እኔም ወደ እነሱ ስመለከት ዓይኖቼን በዓይኖቹ ገጫቸው። ዓይኖቼም ተስለመለሙ። ይጨፍኑ ይግለጡ ግራ ገባቸው፡፡

ብቻ ቢጫ ቀይ አረንጓዴ ሃምራዊ፣ ሰማያዊ ምናምን የሆኑ ጉራማይሌ ቀለሞች ታዩኝ። ከዚያን ግዜ ጀምሮ ፍቅር መልኩ እንዴት ነው ቢሉኝ እንደዚህ አይነት ነው ብዬ እናገራለሁ እያልሁ አስባለሁ። ከመስለምለሜ በነቃሁበት ቅፅበት አብረውኝ የነበሩት ተራ አስከባሪዎች ተከትለዋቸው ሄደዋል፟፤ እያሳደዷቸው። እኔ ግን ልቤን ለእሱ አስረክቤ ጓደኞቼ እነርሱን ሲያሳድዱ የኔም ልብ ከእሱ ጋር እንድትሳደድ ፈቅጄ ቆሜ ቀረሁ። ጓደኞቼም አሳደው ሲደክማቸው ይሁን ሲደብራቸው ተመልሰው መጡ። እኔ ግን ካለ ልብ ቀረሁ። ልቤን የተሸከመው ካርቶኒ ውስጥ ከልብሶቹ ጋር ያስቀምጣት አልያም ከልቡ ውስጥ ባላውቅም ልቤ ግን ሄዳለች።

ከዚያች ቀን ጀምሮ በፍቅሩ ተለከፍሁ። ቀርቤ እንኳን የማየት እድሉን ማግኘት አልቻልሁም ነበር። ስቀርበው ይሸሸኛል። እኔ ወደ እሱ ስጠጋ የሚያየው አፍቃሪውን ሳይሆን አሳዳጁን፣ የእህል ውሃውን ገመድ የሚበጥስበትን ጠላቱን ነው። እንዴትስ ብሎ እንድጠጋው ይፈቅድልኛል? የተረገመ ስራ። የተረገመ መገጣጠም። አሁን ካልጠፋ ስራ እኔ ደንብ አስከባሪ እሱ ህገወጥ ነጋዴ መሆን ነበረብን? ምናለበት እኔ የሱቅ ነጋዴ እሱ ሸማች ብንሆን? ወይም ደግሞ እኔ አስተናጋጅ እሱ ተስተናጋጅ ብንሆን? ፍልቅልቅ እያልኩ ሳስተናግደው፤ ፈገግታዬን አይቶ ሲማረክ፤ ተማርኮ በአገልግሎቴ ተደስቶ ቲፕ ሲሰጠኝ፤ አትጥፋ ብዬ በፈገግታ ስመልስለት….። እንደዚህ መሆን አንችልም ነበር?

እንዲያም ቢሆን ግን ተስፋ ሳልቆርጥ ያገኘሁትን አጋጣሚ ለመጠቀም መሞከሬን አላቆምሁም። እሱም መሸሹን አልተወም። ታዲያ በአንደኛው ሌሊት ከእርሱ ጋር ስላፋ፣ ስሳሳም እና ስተሻሽ፣ ተሻሽቼም ስተቃቀፍ፣ ተቃቅፌም ደረቱን ተንተርሼ ስተኛ፤ የደረቱ ጸጉር ኮሰኮሰኝ። እና ከእንቅልፌ ባነንሁኝ። ሌሊቱ ነግቶ ነበር። ከእንቅልፌ ስነቃ ትንፋሽ እንደማጠር፣ የልቤም መምታት እንደማቆም አደረገኝ። ከጉንጬም ከጭኖቼ ላይም አንደመቀዝቀዝ አይነት ስሜት ተሰማኝ። ስቅስቅ ብዬ አነባሁ።

ከስራዬ ቀርቼም ቢሆን አሳዳጁን ሳይሆን አፍቃሪውን ሆኜ ላገኘው፣ ፍቅሬንም ልናዘዝለት አሰብሁኝ። ግን ደግሞ ስራዬስ?  ምን ምክንያት ሰጥቼ ከስራዬ ልቅር? “ህገ ወጥ ነጋዴ ስላፈቀርሁ የደንብ ልብሴን ለብሼ ላናግረው ብል ይሸሸኛል። ስለዚህ ከስራ ቀርቼ ላግኘው” ብላቸው ይሰሙኛል? ለነሱ ፍቅር ምናቸው ነው? ቢያንስ የመጀመሪያ ቀን እንደምንም ልሞክር እና ካልሆነ ግን ስራዬንም መስዋዕት አድርጌ አግኝቼው በውስጤ ያመቅሁትን ስሜት እተነፍሳለሁ ብዬ ለራሴ ቃል ገባሁ።

ተነሳሁም አረንጓዴ ለበስሁ፣ አረንጓዴ ተጫማሁ፣ አረንጓዴ ተኮፈየሁም። ከቤቴ ወጥቼ እነርሱ ወደሚሰሩበት ቦታ አመራሁ። ድንገት ልቤ ድው… ድም… ድው… እያለች ስትደልቅ አካባቢዬን ቃኘት ቃኘት አደረግሁ። የማፈቅረው ልጅ ድሬድ ጸጉሩን ወደኋላው አስሮ፣ ጥቁር ሆኖ ፊቱን የሞላው ጺሙን አጎፍሮ፣ ከመንገዱ ዳር ቆሞ ሸሚዞች በእጁ ይዞ የቀረውን ልብስ በካርቶኒው አድርጎ አግሩ ስር አስቀምጦ አየሁት። ለየሁትም።

ቀጥታ ወደእሱ ለማምራት ፈለግሁ። ግን ፊት ለፊቱ ስሄድ ካየኝ ሳልቀርበው በሩቁ ይሸሸኛል ብዬ አሰብሁ። መንገድ ቀይሬ ከኋላው ለመምጣት እንዲመቸኝ አስፓልቱን እነሱ ካሉበት በብዙ እርቄ ተሻገርሁና በሰዎች መሃል እየተከለልሁ አጠገቡ ልደርስ፣ ጥቂት ሜትሮች ምናልባትም አስር የማይሞሉ ያህል ሲቀረኝ ድንገት ዞር አለ። ዓይን ዓአይን ተገጣጠምን። ለማመን በሚቸግር ፍጥነት ከእግሩ ስር ያለው ካርቶኒ አንስቶ አስፓልቱን ለመሻገር ሲፈተለክ፣ የመኪና ፍሬን ሲንሳጠጥ፣ የሰው ኡኡታ ሲቀልጥ፣ እኔም በቆምሁበት ሲጨልምብኝ እኩል ሆነ።

ስነቃ ልብሴ በውሃ ርሷል። አካባቢዬን ስቃኝ የእግረኛ መንገድ ላይ ተኝቻለሁ። የሆነ የማላውቀው ኃይል አስገድዶኝ ዓይኖቼን ወደ አስፓልቱ ወረወርሁ። አስፓልቱ ቀይ ምንጣፍ የተነጠፈበት መስሏል። ከምንጣፉ ጎንም ጸጉሩን ያደረደ፣ ጺሙን ያጎፈረ ወጣት እንደኔው መንገድ ላይ ተኝቷል።

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *