ዙፋን ክፍሌ

ከአገር አገር ይዞራሉ። ከደብር ደብር ያዳርሳሉ። እኚህ አሮጊት። እኚህ ዓይነ ስውር። ቆላ ይወርዳሉ። ደጋ ይወጣሉ። እኚህ እማማ። ቀን እየቆጠሩ ፥ ቃል እየፈጠሩ ፥ ታቦት እየቀየሩ። ከተሜን በከተሜኛ ፥ ወንዱን ሴቱን በስልት ፥ በስልት ፤ በብልሃት ፥ በብልሃት አርገው ይለምናሉ። በመድኃኔዓለም ፣ በማርያም ፣ በአቦ ፣ በጊዮርጊስ ፣ በተክለሃይማኖት ፣ በሚካኤል ፣ በቅዱሳን እያሉ…። ስለ ፈረሰኛው እያሉ ፣ ስለ አዛኚት እያሉ። እያራሩ። እየፈሩ። እየተቸሩ።
ሲኖሩ… ሲኖሩ…፤
ሲዞሩ… ሲዞሩ…፤
የተጎነጎነች ክር እጃቸው ላይ አስረው መስማትና መናገር የማይችል ልጅ የክሯን ጫፍ ይዞ ይመራቸዋል።
አሁን ካልታጣ አብነት? ካልጠፋ ምሳሌ? በ ዲዳ ልጅ የሚመሩት እግዜርን ወይስ ሕይወትን ለማሳጣት ነው? እንዲዳኝላቸው ነው እንዲዳኝባቸው? ወይስ እነርሱ ናቸው እርሳቸውን ያሳጧቸው?
ልጁ ዓይን አለው ፤ እሳቸው ምላስ። ሁለቱም ሆድ አላቸው። ሁለቱም በአፍንጫቸው ውስጥ ትንፋሽ አለ። እናቱን! ያ ትንፋሽ..። ያ ጉደኛ። ያ ዥል ትንፋሽ። ያ ወርቅ ሕይወት..። ያ ውብ መኖር..። ያ ትንፋሽ.. !
ተዝካር ካለበት ሄደው “ነፍስ ይማር ፣ በአብርሃም እቅፍ ፥ በሱራፊ ክንፍ – ያኑርልኝ..” ፤ ከዝክሩ ደርሰው “ለወሩ ላመቱ ያድርስልኝ ፤ ጣዲቁ ይስጥልኝ ፤ ጽዋችሁ አይጉደል፥ሞሰባችሁ አይነደል..” እያሉ ይመርቃሉ። እንደ አባይ ጠንቋይ ፣ እንደ መለካዊ ካህን ለሰዎቹ ፣ ለመጽዋቾቹ የሚመቸውን ይመርቃሉ። እንዲህ አሞካሽተው ፥ እንዲህ በርጅና ዋሽተው ፤ ከዳቦው እራሪውን ፣ ከጠላው ቅራሪውን ፣ ከንጀራው ትራፊውን ፣ ከሟች ልብስ እራፊውን ይሰጧቸዋል። ለዚህ ለገላ ሲሉ። ለዚህ ለሆድ። ለዚህ ለከርስ ፣ ለዚህ ለፈርስ – ከርሞ ለሚፈርስ። ለዚህ ለትንፋሽ። ለዚህ ለእስትንፋስ – ለ “እፍ..” ፥ ለነፋስ!..ለዚህ…. ለዚህ።
ለዚህችው ወደ ደብር ይወጡና..
“ማነህ..ሰው አለ እዚህ..?” ይላሉ ኮቴ ሲሰሙ።
“አቤት..”
“ጎሽ ልጄ! የማነው ደብር ይሄ?”
“ጸዴንያ ማርያም…”
“እሺ ልጄ። ጸዴንያ ማርያም ትስጥልኝ። በብርሃን ታሰንብትልኝ..”
“ስለ ጸዴንያ ማር..ያያያም ፤ ስለ ብርሃን ወገኖቼ ፤ ስለ ጸዴንያ…”
“ጸዴንያ ማርያም ትስጥልኝ። በብርሃን ታሰንብትልኝ..ስለ ጸዴንያ ማር.. እሺ.. ጸዴንያ ትስጥልኝ..”
ክሽሽ..ክሽሽ…ክሽሽሽ.. ሳንቲሙ እጃቸው ላይ ይዘፍናል። ይዘላል። ምን አገባው ይሄ ብረት ሆድ የለው። ደም የለው። አምላክ የለው። ሳንቲም ይዘፍናል.. ሳንቲም ይሳለቃል። ይስቃል። ጥርስ የለው ምናለበት እሱ። ሰይጣንና እርሱ ጥርስ የላቸውም ግን ይስቃሉ። ሰይጣንና ሆድ ሆድ የላቸውም ግን ይራባሉ። ሰይጣንና ሕይወት እንትን የላቸውም ግን እንትን ያረጋሉ። ትን ያደርጋሉ።
እሱ እቴ ሳይደግስ አይጣላ! ለኮልታፋው ዓይን ፥ ለዓይነ ስውር ልሳን ፤ አይነሳም።
በልጅ ዓይን እያዩ..በአዋቂ ልሳን እየተወያዩ..፤ (የለማኝ ተለማኝ ውይይት!)
ሲኖሩ… ሲኖሩ…፤
ሲዞሩ… ሲዞሩ…፤
በበትራቸው መሬቱን እየቆረቆሩት..እየኮረኮሩት..አፈሩን ፥ ደንጊያውን ፤ ቦይና ግንቡን…
ለበትራቸው የሚያዜሟት ዜማ አለች፦
በትሬ፤እግሬ።
እግሬ፤በትሬ።
ሳላየው አይቶኝ –
ሳይጠልዘኝ በል ቅደም ጠልዘው
እግሬን ግምባሬን ሳያበልዘው
ሳያደባየኝ እንቅፋት ደንጊያ
ዘንጌ ዓይን ማዘንጊያ
ዘንጌ የቀን ሌት ማንጊያ።
ዘንጌ ምራኝ ዳገቱን
ዘንጌ አውጣኝ አቀበት
ዘንጌ አዛኝ ካለበት
ዘንጌ ምሳና ቡና
ዘንጌ መርሐ ዓይነስውር – አንተ አይነ ልቡና!
ከደጋሽ ንፉግ-
እንዳታደርሰኝ እንደበቀደም
ቀኝ፥ቀኙን ይቅናን እንሂድ ቅደም።
ይህንን ካንድ ቦታ ሲያርፉና ሰው የሌለ ሲመስላቸው በአራራይ ዜማ ያዜሙታል። ለዘንግ ባዜሙት ዜማ እግዜርም ሳይቀና አይቀርም። እሰይ! ዓይናቸውን ቢያበራ ለርሱ ያዜሙለት አልነበር? ነገሩ ዜማው ለካ የልበ ብርሃንነት እንጂ የዓይነ ብርሃንነት አይደለም። ወይ ግሩም! አንተ አታደርገው የለ! ሺ አድርገህ በሺውም ልክ መሆን ካንተ በቀር የማነው? ሺ ብታደርግ በሺውም ልክ ነህ ማለቴ ልክ አይደለህም ብል ገሃነም ወደሚባል አገርህ እንዳልጋዝ መፍራቴ አይምሰልህ ፤ እስከ ፀሐይ መግባት ፣ እስከ ኮከብ መውጣት መርምሬ የገባኝ መራራ እውነት ያንተ ልክነትና ፍጽምና ቢሆን ነው እንጂ።
አዎ እየገደልክና እያዳንክ እኩል ልክና ፍጹም መሆንህን ከማወቅና ከማመን እኩል ምን ኮሶ ይመራል?
———
“ማነሽ አንቺዬ..?”
ግራቸው በክር እየተጎተተ ፤ በቀኛቸው ምርኩዝ ይዘው።
“አቤት..” የሰለቸ ድምፅ።
“የኔ ጌታ ጤና ይስጥልኝ። ከዚህ ደብር ነህ እንዴ? “
“አዎ እዚህ ነኝ። እንዳይወድቁ አንተዬ..”
“እሱን ተወው ልጄ። ምላሱ አይፈታም ፤ ጆሮውም እምብዛም… የደብሩ ታቦት ማነው ይልቅስ?”
“ያው እንደናንተው ነዋ…ታቦቱ አንድ ነው!” አላቸው።
ካንጀት ያልሆነ ሳቅ ሳቁና መለሱለት ፤
“እኔ ምን አገር አለኝና እንደኛው ይሆናል ልጄ? እኔኮ ዟሪት ነኝ።”
“ለውጥ የለውም ታቦቱ አንድ ነው አልኩዎት።”
“ስንትስ የሆነ እንደው ስም የለውም ታዲያ?”
“አቡነ ሕይወት ናቸው!” አለ ባጭር፣በምጸት ፣ በምሬት።
“እንዲህ ብሎ ታቦትስ ሰምቼም አላውቅ..ጣዲቅ ናቸው? አቦን ማለትህ ከሆነ እሳቸው አቡነ ገብረ ሕይወት ናቸው።”
“አቦን ማለቴ አይደለም። ጣድቅም ሰማዕትም አይደሉምም።”
“አበስኩ፥ገበርኩ! እንግዲያ አቡነ ተብሎ መልዓክ አይጠራ..!”
“መልዓክም አይደሉማ!”
“የወላዲተ አምላክ! እየቀለድክብክብኝ ነው?”
“የሚቀልዱብዎትስ አማኝ ነኝ ባዩ ነው። ስለ ሰንበት ፥ ስለ ማርያም ብላችሁ ቀንና ዕለቱን ነግራችሁ ቀጠሮውንና ልደቱን ያስታወሳችሁት ዓይናማ ዘበናይ አይደለም እንዴ በስሙኒ ፈንክቷችሁ ፣ ማርያም ዘንድ ሄዶ ‘አየሽልኝ ጽድቄን?’ የሚለው። ቀልደኛስ ያ መንጋና አቡነ ሕይወት ናቸው!”
“አቡነ ሕይወት ይቅር ይበሉህ! ቀልደኛ ናቸው ብሎ ነገር?”
“ኧረ እንደውም ዋዘኛ ናቸው!”
“ዋዘኛስ ክራር ነው አንተ! ጣድቅ ናቸው እሳቸው። መቅሰፍት አትጥራ እንጂ ልጄ።” ተለማመጡት።
“ጣድቅስ ተክልዬ ናቸው ካሉ አይቀር። እኒህ ምንም አይደሉ ብዬዎት ምነው?”
“እንግዲያስ ምንድን ናቸው?”
“እንቆቅልሽ ናቸው!”
“እንቆቅልሽ ብሎ ነገር?”
“እንቁላል ውስጥ እንዳለ ጫጩት።”
“ጫጩቱን ምን አመጣው?”
“በቅርፊት ውስጥ ያለውን ወንድ ይሁን ሴት ማን ያውቃል?”
“የሆነስ ሆነና..?”
“አቡኑም እንዲሁ እንቆቅልሽ ናቸው”
“ጉድ በል አገሬ! ጣድቅ ካልሆኑ.. መልዓክ ካልሆኑ?”
“አዎን ጻድቅም አይደሉ- አይጾሙ፥አይጸልዩ። ሰማዕትም አይደሉም ። ያጋድላሉ እንጂ አይጋደሉም። ያታግላሉ አይታገሉም። መኖር እንቁልልጭ ይሉናል። ለሞት ፣ ለዕድሜ ፣ ለጊዜ እና ለ’ዝጊሔር ያቃጥራሉ። ጻድቅ ሳይሆኑ አቃጣሪ ናቸው። ሞላጫ ናቸው። ሙልጭልጭ ናቸው። ወሽካታ ናቸው…”
አቋረጡትና ፫ ጊዜ ደጋግመው እና በፍጥነት በፍራቻ ሆነው አማተቡ። ለማማተብ ጣታቸውን ሲፈልጉ ምርኩዛቸውን ለቀውት ኖሮ ዝቅ ብለው አንድ ሁለት ቦታ ትቢያውን ካፈሱት በኋላ ምርኩዟን አግኝተው አነሷት።
“በሬድኤታቸው ይሰውሩኝ! ያስፈራሩናል እንዴት ትላለህ..? ተው እንጂ ልጄ..ምነው ባልጠየቅኹህ። ለእንጀራ ብዬ ጣድቅ ቆሜ ማስሰደብ ለኔስ ኩነኔ አይደለም?”
“ስለሚያስፈራሩን ነዋ! ‘ለርሃብ ባልናገር ፣ ለጭንቅ ባልጠቁምህ መቸ አቡነ ሕይወት ሆኜው?’ ይሉናል እያልኩዎት እኮ ነው። ይኸው እርሶን አስፈራርተው በስማቸው ‘ስለ አቡነ ሕይወት’ እያሉ ይመጸወታሉ እርሶም። እኚሁ ናቸው አቡኑ..ይበሉ..” አለ።
ድምጹ የጉዞ መሆኑን ሰሙና፤
“ታዲያ ከመቅደሱ ደርሻለሁ ወይስ ሩቅ ነው?” አሉ ጮክ ብለው።
“ሩቅም ቅርብም አይደለም። ይልቅ ጻድቅ ወይስ ሰማዕት ናቸው ላሉኝ መናኒ ናቸው። ከየትኛው ዋሻ እንደዘጉ አይታወቅም። ይበሉ መቅደሱን ያገኙለት በጸሎት አይርሱኝ!” ብሎ ዕንባ ያጋቱ ዓይኖቹን እየጨመቀ ሲራመድ ፤
“ክርስትና ስምህ ማነውና?”
“ያው እንደርስዎ ነው። ገብረ ሕይወት ይበሉኝ -የሕይወት ባርያ።”
ሴትየዋ ተገርመው፤
“እንደርስዎ? የእኔ ማነው?” አሉ።
“አመተ ሕይወት ነዎት – የሕይወት ገረድ።”
አለና የራሱን ሦስት ስሞች እያስታወሰ አዘገመ። የመሰንበት ስም -ገብረ ሕይወት ፤ የሰንበት ስም – ገብረ እግዚአብሔር ፤ የስንብት ስም – አስክሬን።
ከራቀ በኋላ ወደ ዓይነስውሯ በሩቅ ሲገላመጥ ቁጭ ብለዋል።
የዛሬው ውሏቸው ከከሐዲና ችኮ ሰው ጋር ሆኖ እንጀራ ቢጠይቁ ፤ ስለእንጀራ ተነግሯቸው ባቡና ቁጭ አሉ። ቁጭ አሉና አዜሙ። ያቺን ዘንጌን። ያቺን ዘፈን ብትሆን ትዝታ ፣ ያቺን መዝሙር ብትሆን አራራይዋን – ያቺን ዘንጌን….
ዘንጌ ዓይን ማዘንጊያ።
ዘንጌ ‘የቀን ሌት’ ማንጊያ።
ሳያደባየኝ እንቅፋት ደንጊያ ፤
ሳይጠልዘኝ በል ቅደም ጠልዘው
እግሬን ግምባሬን ሳያበልዘው
ብዬህ አልነበር..?
ዘንጌ ፣ ዓይነ ልቡና
ወዳጅስ ነበርን አምና፣
እንግዲህስ.. እንግዲህ.. ይቅር
እንቅፋት ለምኔ ላፍር
ተነቃቀለ የጣቴ ጥፍር
አሁንማ ተው – አሁንስ ይቅር..።
ዘንጌ ዓይን ማዘንጊያ።
ዘንጌ ‘የቀን ሌት’ ማንጊያ።
ቦዩን ፥ ኮረቱን – ስትዳብስ
የስውር እንባ ስታብስ
ተወው ደከመህ አንተም
እኔም እዚሁ ልቆይ – አንተም ከዱርህ ክተም!
ዘነበ። የማን መሆኑ ነው? የምርኩዟ የስንብት እንባ ወይስ አራራዩ እግዚአብሔርን አስነባው? ሁለቱም ይሆኑ ይሆናል – ላይሆንም።