ከዙበይር ኢብራሒም
በቅድሚያ ታላቅ ደራሲ የመሆን ጅማሬ ላይ ነኝ ሊል ሲፈልግ አጥቢያ ብሎ መጣ። ከዚያማ አንዴ በከፈተው ቀዳዳ በኩል ተከታታይ ጥበቦቹን ሲያቀብለን ቆየ። ከጊዜያት በኋላ ትሪሎጂ (Trilogy) ብሎ ደግሞ እንዳከበርነው እንድንኖር በፍቅር እና በእውነት ስም አስማለን። ሶስተኛውን “ይዞብን ይቀር ይሆን?” ብለን ስናስብ “መለያየትማ ሞት ነው” ብሎ ለመደምደሚያው አዘጋጀን። ትሪሎጂውንም በ”ሐሰተኛው” ደመደመ (ምንኛ ያማረ መደምደሚያ!)። ጋሽ አሌክስ ናፈቀን ስንል ደግሞ “ከሀያ ዓመት በፊት ፃፍኩት” ሲለን ባላመንነው ” የተጠላው እንዳልተጠላ” መጣልን። አሁን ደግሞ ቤባንያን ይዞ ተከስቷል። እንግዲህ መሰላሉ እዚህ አድርሶናል።
የእውኑ ዓለማየሁ ገላጋይ አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ በመስክ ስራ ምክንያት በሰላሳ ዓመት እድሜው ለቀቀ። በድርሰቱ ደግሞ ከአዲስ አበባ ለመውጣት ሌላ ሰላሳ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ለመጠበቅ የተገደደ ይመስላል። ያው ወጣ ገባ ብሏል። ነገር ግን በቋሚነት አዲስ አበባን ለቆ ጠቅልሎ የወጣው በዚህ ስራው ይመስለኛል። (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ)
መጽሐፉን እዛው ጋር ገጽ በገጽ እየተመላለስኩ እየደጋገምኩ አብሬ ከረምኩ። ሲያልቅብኝ ደግሞ እንደ አዲስ ጀምሬ ጨረስኩት። አሁን ምን አለፋችሁ ቅርርባችን “ከዘመድ በላይ ሆኗል ሁላ።”
መጽሐፉን እንቶኔ የአፃፃፍ መንገድ ነው፤ እገሌ ኢዝም ነው ብዬ መፈረጅ አልፈልግም። አንብቦ እንዳለ ማጣጣም ሲቻል በሆነ ዘርፍ ውስጥ ለማሳቀፍ ያለ ሩጫ አይገባኝም። አንድ ጊዜ ጋሽ አሌክስ በአንድ መጽሐፉ ላይ ውይይት ለማድረግ እንግዳ ሆኖ መጥቷል። በመሀል ከታዳሚ አንድ ጥያቄ ተነሳ። እንዲህ ይላል
“ይህን መጽሐፍህን በሆነ ዘርፍ ውስጥ ለማካተት ቸገረኝ ። ምን እንበለው? ገላጋይዝም እንበለው?”
“ግራቪቲን ተውና የወደቀውን አፕል አርፈህ ብላ” ነው ያሉት ልጆቹ?(ሃሃሃሃሃሃ)
ኳ ኳ ኳ ወደ ሸኖ! ….
ደራሲው መጽሐፉን ከዘፍጥረት ነው የሚጀምርልን። “የሸኖ ሰማይ ገና መሬትን ያላወቀ አፍላ ነው።መሬት ከጎን አጥንቱ አልተፈለቀቀችም ።” ይለናል። ድንቅ ሜታፎር!
ኳ ኳ ኳ ወደ አሁን! ….
ለማን በገበያውም፣ በጓደኞቹም፣ በዘመዶቹም ህይወት ውስጥ እያመላለስን እንመልከተው እስኪ።
***
ደራሲው በዚህ መጽሐፉ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተንተርሶ ጥበባዊ በሆነ መንገድ ምክር ቢጤ ማስተላለፍ ፈልጓል::ለዚህም እንደ ማሳያ የሚቀርበው አንዱ ገፀ ባህርያቱ የተሳሉበት መንገድ ነው::በጋሽ ይማም በኩል አማራ ገባ፤በአደዬ በኩል ትግራይ ዘለቀ፤በአባ ብሩ በኩል ወደ ኦሮሚያ ጎራ አለ፤በእሞ በኩል ጉራጌ ተሻገረ፤ይሄ አልበቃ ብሎት አስመራ ሁላ ገብቷል፤በቤላ በኩል።
ሸኖ ላይ መከተሙ በራሱ በአጋጣሚ አይመስለኝም። ይቀጥልና አንድ ቦታ ላይ ምንምነታችንን ሊያስታውሰን ይፈልጋል።
በሆሴእ በኩልም የዲዮጋንን የአጥንት ለቀማ ታሪክ ካነሳ በኃላ እንዲህ ብሎ ይዘጋል:-
“ይሄ ያልገባው የሸኖ አፈር ሁሉ በብሔር ተቧድኖ ይለይልን ይላል”
በሌላኛዋ ገፀ ባህሪ እሞ በኩል ደግሞ እንደዚህ ይለናል:- “ተዋደው ያደጉ ተጣልተው እንኳን ተያይዘው ይወድቁ”
በዚህ ሀሳብ በኩል “ተዋደንም ይሁን ተጋምደን አብረን መጥተናል:: ከዚህ በኃላ ያለ’ ጠብ ተያይዞ ለመውደቅ ከሆነ እንጂ አሸናፊ አይኖረውም” እያለን ይሆን?
ከዚህ ጋር ተያይዞ ያሳደጉት ሰዎች ያደገበትን ቤት የተቀባበሉበት ቅደም ተከተል በአጋጣሚ ነው ለማለት ቸግሮኛል:: ጋሽ ይማም አደዬን ተቀበለ።አለማምዶ ጥሎ ሄደ ፤አደዬ አባ ብሩን ተቀበለች። አለማምዳ ጥላ ሄደች…
***
የታሪኩ ማጠንጠኛ የሆነችው ዋና ገፀ-ባህሪዋ ቤባንያን በሁለት አይነት መልኩ ተመልክቻታለሁ::
ቤባ ለእኔ እንግሊዝኛውን ቃል ልጠቀምና Desire(lust) ነች:: ዓለማዊ ፣ጊዜያዊ ደስታን ትወክላለች::”Attachment”ን ትወክላለች:: አብረቅራቂዋን፤ እንካ ግን አትንካ የተባልናትን በለስ(ዓለም) ትመስለኛለች:: የተጣበቅናት ጊዜ የድንጋይ መሰናክል ነች:: መንጭቀን የተላቀቅናት ጊዜ ደግሞ ወደ መንፈሳዊ መገለጥ የምትወስደን መሰላል ነች:: ዋና ገፀ ባህሪው መፍትሔ ከቤተ-ክርስትያን አፀድ በተገኘበት ቅፅበት ቤባንያ ከአእምሮው መዝገብ ስትጠፋ እናያለን:: ቆይታውን ጨርሶ ሊወጣ ባሰበበት ቅፅበት ደግሞ በሀሳብም በአካልም ትከሰታለች::
“ሂድ እያለች እየገፋች ትወስደኛለች”ይላል
“ግንድ አደናቅፎኝ ስወድቅ ደግሞ ቁራጭ ሳቅ ይከተለኛል”ይላል
ይህች ሳቅ በDesire ተገፍተን በዓለማዊ እንቅፋት ተጠልፈን ስንወድቅ ከምትሳቀዋ ቁራጭ ሰይጣናዊ ሳቅ ጋር አትመሳሰልም???
ከዚያስ:-
በተከተልካት ቁጥር ታስደበድብሀለች(ልክ በወንድሞቿ ሲደበደብ እንደነበረው ማለት ነው)። እንዲያም ሆኖ መከተልህን አታቆምም:: የምታቀምስህ ነገር ጊዜያዊ ቢሆንም ውሸት አይደለማ:: ይሰማሀላ:: ታጣጥመዋለሃ::
በአንደኛው ቦታ ላይ መፍትሔ ተደብድቦ በተኛበት ቤባ ትመጣና እቅፍ ታደርገዋለች:: ቀጥላም እንዲህ ትለዋለች:-
“ይህችን ፍለጋ ነው አይደል የምትደበደቢው?”
እርሱም በዚያች ብልጭ በምትል እቅፍ ምክንያት ህመሙን ሲረሳ ይታያል:: ብልጭታ ብትሆንም ትጣፍጣለቻ:: መኖርን ታስመኛለቻ::
ሁለተኛው እይታዬ ሁሉም ሰው ያያት አይነት ቤባንያ ናት:: ያለ ልክ አፍቃሪዋ፤ ዘጠና ዘጠኙን ትታ አንዱን ፍለጋ የምትወጣዋ፤ በድፍረት ከእየሱስ ጋር የተነፃፀረችዋ ናት።
(ይህችኛዋ ፊት ለፊት የቀረበችዋ ስለሆነች ማብራራት አይጠበቅብኝም)
***
በመጽሐፉ ጥቅልል ያሉ ግን ደግሞ እንደ ሸማ መተርተር የሚችሉ አባባል መሳይ አረፍተ ነገሮች መሐል ጥቂቱን ላስቀምጥ
“ከአንድ የጉም ማህፀን ተወለደ ወደ ሌላ የጉም ማህፀን ገባ ትእይንቱ ቅፅበት ብቻ ነበር።”
“ራሳቸውን መግዛት ያቃታቸው መሪዎች ናቸው የመግዛት ጥማቸውን በእኛ በኩል የሚወጡት።”
“አንዴ ሲሰደብ ያብራራ መስሎት አስር ጊዜ ራሱን ይሰድባል።”
“ጫማህን የማሳየት ፍላጎትህ የሰው መጫሚያ ስመህ እንድታድር ያስገድድሀል።”
“የታዘዘው መጣ ስኳር ጨምሬ አማሰልኩ። ሁሉም በታዘዘለት ተጠምዷል።”
“ልጅነቱ አጥብቆ እንዳይዝ ሲያስገድደው ለስላሳውን አንዴ ከጠርሙሱ አንዴ ከብርጭቆው ይቀምሳል።”
“አሁን ይሄ ኑሮ ጠላት የሚያስፈልገው ሆኖ ነው?”(እጅግ በጣም የወደድኳት)
***
መጽሐፉ እንደ አጠቃላይ መንፈሳዊነትን(spirituality ) ይሰብካል። ከመጣበቅ(attachment )፣በቦታ ከመፈረጅ (labeling )መላቀቅን ሊሰብከን ሲፈልግ ዋናው ገፀባህርይ መፍትሔ ከየት እንደመጣ አይነግረንም። እንጀራ አባቶቹና እናቶቹ ሲመጡ ከየት እንደመጡ አይነግረንም። ሲሄዱም ወዴት እንደሚሄዱ አይነግረንም። ልክ ነዋ፤ ወደዚህች ዓለም ስትመጣም ከየት እንደመጣህ አታውቅም (You just exist ) ስትሄድም ወዴት እንደምትሄድ አታውቅም። ከጉዞ መሐል ትገኛለህ፣ ትጓዛለህ፣እየተጓዝክ ትጓዛለህ ይልሀል።
ከዚያ ደግሞ በጋሽ ይማም እንጉርጉሮ በኩል
“እንደው ልንገር እንጂ ታዲያ ለማን ልንገር
ሁሉም ስደተኛ አንቱ ነሁ ባላገር”
ይለናል ።
“እኔና ዱንያ(ይህች ዓለም) ያለን ግንኙነት ረዥም ጉዞ እንደሚጓዝ እና ለማረፍ አንድ ዛፍ ስር እንደተጠለለ መንገደኛ እኮ ነው።” እንዲሉ ነብዩ ሙሀመድ(ሰ.ዐ.ወ)
በመጽሐፉ መጨረሻ አካባቢ ሁለቱም ብልጭልጭ አፍቃሪዎች ቤባንያን(እንቅፋቷን) ካጡ በኋላ ወደ መንፈሳዊ መገለጥ ሲጓዙ እናያለን። አንድ አንድ እያሉ መሰላሉን ይወጣሉ። ጫፉ ላይ ግን አይደርሱም። ምክንያቱም ዓለሙ የመጓዝ ዓለም ነው። ወደ ትክክለኛው መንፈሳዊ ፍቅር የመቅረብ ጉዞ ነው። እየተጓዝክ ታልፋለህ እንጂ አትደርስም ። ነገሩ ከመድረሻው ሳይሆን ከመንገዱ ጋር በፍቅር የሚወደቅበት ነው።
አንድ ቦታ ላይ ገፀ ባህሪው እንደዚህ ይላል:-
“ህይወት ጉዞ ከሆነች አቅጣጫችን ከእርክስና ወደ ብፅዕና መሆን አለበት። ስንፈጠር አልታገዝንም። በራሳችን መፍጨርጨር በውልደት ከተነከርንበት ክፋት በሂደት ወደ ደግነት ማቅናት የህይወታችን ግብ ነው።”
መንፈሳዊ ልህቀትን በተለየ መንገድ ለማሳየት ሲፈልግ ደግሞ አባ ጃርሳ የተባሉትን ገፀ ባህሪ ያመጣል:: እንስሳትን አሳድገው፣ አሰረጅተው ወደ መጡበት የሚሸኙትን አዛውንት ማለት ነው::
ይህችን የአባ ጃርሳ ድርጊት አንዳች መንፈሳዊ ከፍታን የምታሳይ ናት ካለ በኃላ በሌላ ገጽ መጥቶ ደግሞ እንደዚህ ይላል:-
“የተዋለላቸውን የማያውቁ ምስጋናም የማይጠበቅባቸው..” ይላል።
“ህይወትን ያለ አቋራጭ ጠግበው እንዲጠጡ ዓለም ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ ለእነሱ በረከቱ እንደተሰጣቸው ያውቁ ይሆን?”ይልና
“አሁንም በዚህ የሚረካው ህይወታቸውን እያቋረጠ የሚደሰተው ያው ሰው ብቻ ነው” ይለናል::
ውስጥ ወይራ ልንላት እንችላለን? እንበላት ግድ የላችሁም
***
በመጽሐፉ ስለ ፍርሀትና ፍቅር በተደጋጋሚ ተነስቷል:: “ሰውን የሚገዛው ፍቅር አልያም ፍርሀት ነው። ከሁለቱ ውጪ መሆን አይችልም” አይደል የሚባለው?ሁላችንምስ ሁለቱ ውስጥ በመዋለል አይደል ዘመናችንን የምንገፋው ?እሱንም እድለኛ ከሆንን:: የፈጣሪ አልያም የሰይጣን ነህ:: እንደ ፍጡር መሀል ሜዳ የሚባል ነገር አልተሰጠኀም ::ይህንን በገፀ ባህርያቱ በኩል በደንብ አሳይቶናል::
***
አሁን ደግሞ በተራ ምልልሶች መሀል በሽሙጥ ጣል ከሚያደርጋቸው ሀሳቦች ጥቂቱን…
“ለወንበር ያለበስኩትን ኮት ገፍፌ ለበስኩ።”
“አህያ ነው በአህያ እየተመራ ያለው በለኛ።”
“ድንጋይ ድንጋይን እየገጨ ውጤት ሲያስመዘግብ እያየሁ ቆምኩ።”
***
ደራሲው እንደዚህኛው መጽሐፉ በእምነት ነክ ሀሳብ በኩል ሚዛናዊ ለመሆን ሲሞክር ያየሁበት የለም ። እንደውም የኛ አማኝ ነን የምንል ሰዎችን በእምነት እና በክህደት ወይም በእምነት እና በጥያቄ ውስጥ የመዋለልን ኑሮ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። “ዘሀቲ ጥበብ ፈጠረተና”(አንዲት ጥበብ ፈጠረችን) ሲል ይቆይና መልሶ ደግሞ አንዲት ተንኮል በሚል ይቀይራታል። (በዚህ በድህረ ዘመናዊነት ጊዜ የአብዛኛው “አማኝ” መንገድ ይህንን ይመስላል። ዋሸሁ???)
ዋናው ገፀ ባህሪው መፍትሔ ፍጥረት ዓለሙን በአንክሮ ሲያስተውልና በእጅጉ ሲገረም “ዘሀቲ ጥበብ” ይላል። ህይወት የማይለቅ አዙሪት ውስጥ ስትከተው ደግሞ “እውነት አንድ ጥበብ ናት የፈጠረችን? እንዲህ ያለ ተንኮለኛ ማድፈጥ ያለበት ግጥምጥሞሽ የጥበብ ውጤት ነው? አንዲት ተንኮል ማለት አይሻልም?” ይላል።
ከቤተክርስቲያን አፀድ ተቀምጦ ጥያቄው ሁሉ ድራሹ ሲጠፋ “ዘሀቲ ጥበብ” ይላል። ከዚያ ደግሞ ህይወት ዱላዋን ስታሳርፍበት ” ተንኮለኛ ደራሲ እጅ የገባን ይመስለኛል፤ እግዚአብሔርማ ይህን አያደርግም ” ይልና ይሸሻል፤
ማን? ራሱ ደራሲው ዓለማየሁ ። “ከዚያስ?” አትሉም ?
ዓለማየሁ ገላጋይ ደራሲውን ፈጠረ ። ስም ያልተሰጠው ደራሲ ደግሞ ቤባንያን ፈጠረ ይለናል። ደራሲው ራሱ ድርሰቱ ውስጥ አለ። በስም ሳይገለፅ። በድርሰት ውስጥ ሌላ ድርሰት ማለት ነው። በስተመጨረሻም ጋሽ አሌክስ የፈጣሪን መንበር በምናብ ተረክቤያለሁ ብሏል።
“ፈጣሪ ራሱ በዳግም ፈጣሪዎች ተፈጣሪ ሆኗል” ይለናል።
ጉድ በል !
ይሄኔ ነው እንግዲህ አስታርቂኝ ማለት ።
***
ለአንዳንድ ገፀ ባህሪያቱ የሰጣቸው ስሞች ዘና የሚያደርጉ ናቸው
*ሌባው ሰረቀ(ሠረቀ ብዬ ነው ያነበብኩት ሃሃሃ)
*ጉንፋናሙ አባይነህ
*የንጉሱ አጎብዳጅ ጀነራል ይገዙ
*ሰጠኝ በግዱ
ስሞቹ በምክንያት ከወጡ ዘንዳ መፍትሔም ስሙን ይመስል ይሆናል ብዬ ብጠብቅም…
እንዳንጠይቀው ደግሞ በሆሴዕ በኩል ታላላቅ ደራሲዎችን ጠቅሶ “ህዝባቸውን ከመሳደብ ባለፈ መፍትሔ ማምጣት ያልቻሉ የቃላት እማሪዎች ናቸው” ብሎናል። “ብትፈልጉ ከእነዚህ ውስጥ መድቡኝ” እያለን ይሆን???
***
ደራሲው በዋና ገፀ ባህሪው በኩል የክህደት ውጤት የሆነው የወረቀትና የዲጅታል ገንዘብ ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለ ለማሳየት ይሞክራል ።(“ክህደት???”ብላችሁ ከጠየቃችሁ “Nickson shock”ብላችሁ ጉግል ታደርጉ ዘንድ እጠቁማለሁ።)
እንደ ሀገር ጊዜውን ያልጠበቀ መንጠራራት ላይ እንዳለን ለማሳየት ሲፈልግ እንዲህ ይላል።”ሸኖ እቃ በእቃ መለዋወጥ መች አንሷት? ቤታችን የተትረፈረፈውን ይዘን አንዲት መገናኛ ቦታ ላይ መቆም፤ሌላው ቤቱ የተትረፈረፈ ግን እኛ ዘንድ የሌለ ይዞ ሲመጣ መለዋወጥ፤ገንዘብ ባንክ ለሸኖ ምን ያደርግላታል!?”
የገንዘብ ጉዳይ ከኢኮኖሚ አሰተሳሰብም በላይ እንደተሻገረ ሲገልፅ “የደም ዝውውር ማዕከል”፣ “የትንፋሽ መለኪያ” ሆኗል ይለናል። እንዲሁም የዘዋሪዎቹ ዋነኛ እኛን መቆጣጠሪያ መሳሪያ ሆኗል:: ምናልባትም ወደ እቃን በእቃ ልውውጥ ብንመለስ “ከመንግስትና ከጀሌዎቹ ፍፁማዊ ተፅእኖ ነፃ እንሆናለን። ” ይለናል።
ወንድሜ “ቴሌ ብር”፣”እንቶኔ ብር” እየተባለ ጨርሶ ወረቀቱን ገንዘብ ለማስቀረት የሚደረገው ሩጫ ተራ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሀሳብ ከመሰለህ አልተገናኘንም። (ገብቶሀል አላብራራም)
በአንዱ ገፀ -ባህርይ አማካኝነትም ባንክን “የገንዘብ ሱቅ” ወይንም “የአራጣ ሱቅ” ይለዋል። በመጽሐፉ የአራጣ አበዳሪ የሆኑትን አባ ድሪባን አንስቶ “ባንክ ማለት ዘመናዊ አባ ድሪባ ማለት ነው ። ወይም ደግሞ አባ ድሪባን በሺህ አባዝቶ መልቀቅ ማለት ነው”ይለናል።
የገንዘቧን ጉዳይ በዚህች የአንድ ገፀ ባህሪ ንግግር ልጨርስ። በምልልስ መሀል እንደዚህ ይላል:-
“አንድ ቀን ከረባት ባሰረ ጅብ ታስበሉናላችሁ።”
እናስ ከረባት ባሰረ ጅብ ከመበላት የምንድንበት መንገድ ያለ ይመስላችኋል? አላውቅም!
***
መጠነኛ ቅሬታዎቼ
*የመጽሐፉ ቅርፅ አልባ መሆን!
ቁርጥርጥ ያሉ ብዙ ሀሳቦች የታጨቁበት ሆኖ ታይቶኛል።
በእርግጥ ሀሳብ ሀሳቡን ብቻ ለሚፈልግ እንደ እኔ አይነት አንባቢ ተስማሚ ነው:: አብዛኛው አንባቢ ግን የሚይዘው ታሪክ ይፈልጋል፤ ያስፈልገዋልም:: ምሳሌ ፍቅር እስከ መቃብር፤ትኩረትን በሚስብ፣ልከኛ ፍሰት ባለው የፍቅር እና የቤተሰብ ታሪክ ባይታሽ ምን ያህሉ ሰው ያነበው ነበር? በውስጡ የያዘውን ትልቅ ሀሳብ ሳያስተላልፍ መቅረቱም አልነበር? አንባቢ ሰብለ ወንጌልን ፍለጋ ሲመጣ አያይዘህ ሀሳቡን ትግተዋለህ…
*ሸኖ
እያነበብኩ በእርግጥም ጋሽ አሌክስ ለመጀመርያ ጊዜ ከአዲስ አበባ መውጣቱ አስታወቀበት እያልኩ ነበር:: እንግዳ ሆኗል :: ሸኖን ከመረጠ አይቀር ከሸኖ ጋር በስሜት ልንቆራኝ በሚያስችለን መልኩ ቢስልልን መልካም ነበር እላለሁ::
*ሆሴዕ
ጋሽ አሌክስ ራሱን የቻለ ገፀ ባህሪ መፍጠር አቅቶት ነው ዲዮጋን ላይ ያስደገፈው? ወይንስ እግረ መንገድ ዲዮጋንን ለማስተዋወቅ ሲል ያደረገው ነው? የሚለው ጥያቄዬ ነው።
*አላስፈላጊ ገለፃዎች
ይሄ “የሰማዩ ጥልቀት”፣ “ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል” አይነት ገለፃዎች ብዙ ገጽ ይዘዋል:: እንደውም መጀመርያው አካባቢ
“ጋሽ አሌክስ ምን ነካው? ጀማሪ ደራሲ ይመስል አበባው፣ አየሩ፣ ሽታው የሚለን” እያልኩ ሳስብ ነበር::
***
አጠቃላይ የመጽሐፉ ሂደት ለእጣ ፋንታ እጅ በመስጠትና ነፃ ፍቃድን በመጠራጠር ላይ የሚሽከረከር ነው:: ከዘፍጥረትም አይደል የጀመርነው ዞረን ዞረን በበርካታ ነገሮች ውስጥ አልፈን ስናበቃ በዚህች የመጽሐፉ መደምደሚያ በሆነች ሀሳብ ነው::
“አንዲት ጥበብ ሰው ያስመሰለችን ምንም ነን።”
ከዘፍጥረት ወደ ምንምነት! ይህ ነው የሰው ልጅ ጉዞ፤ የሰው ልጅ ብቻ አይደለም የዓለምም ጉዞ ጭምር::
***
እንግዲህ አጻጻፉ፣ ቃላቱ፣ ቅብርጥሴ ብዬ ስለ ጋሽ አሌክስ እንደ አዲስ አላወራም። ብቻ በመጽሐፉ አንድ ቦታ ላይ አፄ ቴዎድሮስ ሼክስፒርን “የእናንተ ዳዊት”እያሉ ነበር የሚጠሩት ይል የለም? ደራሲ ዓለማየሁ በድርሰቱ ዓለም ያለው ቦታ ይህንን ይመስላል:: በእርግጥ ብቸኛው ዳዊታችን አይደለም:: ከዳዊቶቻችን አንዱ መሆኑን ግን መመስከር እችላለሁ::
ሀንቲ ጥበብ ፈጠረትኒ!
ዋሪ ነጋ!
ራራ ነጋ!