እፉዬ ገላ… የአፍታ ዳሰሳ

በዙበይር ኢብራሒም

Maሙሽ

Myክል አዝመራው

Mamush. A Novel By Michael Azmeraw. The book reviewd By Zuber Ibrahim.

“አንድ ልጅ እፉዬ ገላ ያሳድዳል። እየሮጠ ይከተላታል። ይወድቃል ይነሳል። ወደ ላይ ይዘላል። ከንፋስ ላይ ነጥቆ፣ ታግሎ ታግሎ ታግሎ እንደምንም ብሎ ከእጁ ያስገባታል።ወድቆ መጎዳቱ፣ ሮጦ መድከሙ፣ ሲያገኛት መሳቁ፣ የእውነት መሆኑ የነገሩን ጨዋታነት አይቀይረውም። ምናልባት በቁምነገር ወስደን ያሳደድነው ህይወት በስተመጨረሻ ጨዋታ ይሆናል።”

ይለናል ወጣቱ ጸሐፊ እሱባለው አበራ ንጉሴ

ሁላችንም የየራሳችን እፉዬ ገላ አለን። ያንተ እፉዬ ገላ ምንድነው? ያንቺስ? ወደዛ ከመሄዳችን በፊት ግን “ሲጀመር እፉዬ ገላው ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት፣ አያይዘን ሌሎች ጉዳዮችንም ለማውጋት ከደራሲ ማይክል አዝመራው ጋር እንጓዝ።”በየት በኩል?” ካላችሁ በ207 ገጽ ቁልጭ አድርጎ ጽፎ “ማሙሽ”ብሎ በሰየማት መጽሐፉ በኩል።

ስሟ ብቻ ነው ታድያ ማሙሽ፤ በሁሉም ማእዘን  “ጋሼ” የሚያስብላትን አቅም ይዛ ነው የተከሰተችው።

እፉዬ ገላችሁ ንባበ ንባብ፣ ጽሑፋ ጽሑፍ፣ ሀሳበ ሀሳብ፣ ምናበ ምናብ የሆነ ሰዎች ተከተሉኝና ዳሰስ፣በስሱ ዳበስ እያደረግናት እንደሰት እስኪ።

 ማሙሽን በእኔ ዓይን በኩል ትመለከቷት ዘንድ በአክብሮት አዛ’ለሁ ማነው… እጋብዛለሁ። መጽሐፉ ሁልጊዜም አቅም ኖሮኝ ብጽፍ ልጽፍበት በምፈልግበት መንገድ ነው የተዘጋጀው ። የሆነን ግዙፍ ሀሳብ ትንፋሽ ሰጥቶ በታሪክ ውስጥ  ማሳየት።  ሀሳቦቹን “Academic” በሆነ መንገድ ተጽፈው አይቻቸዋለሁ። በዚህ ልክ ግን አልገዙኝም። በአጭሩ እዚህ ጋር ነፍስ ተዘርቶባቸው ነው ያገኘኋቸው።

   ይዘቱ ሽፋኑ ላይ ትwisted ፊiction ብሎ ያስቀመጠው አይነት ነው። ወደ አማርኛ ለመመለስ ያህል twisted fiction ማለት የሰው ልጅን በስቃይ የተሞላ  የህይወት አዙሪት ብሎም ያንን ታግሎ በህይወት ለመቆየት የሚሄድበትን ርቀት በታሪክ ውስጥ የምናሳይበት መንገድ ነው። አፃፃፉ ደግሞ plot twist የሚባለው አይነት ነው። እንደ ስሙ አተራረኩ ላይ እጥፋት የሚበዛው ፤ባልተጠበቁ አጀማመርና አጨራረሶች የተሞላ የአተራረክ መንገድ ነው።

የተፃፈበትን መንገድም ሆነ አጠቃላይ የመጽሐፉን ሀሳብ ቁልጭ አድርጋ የምታሳይ አንቀጽ ከራሱ ከመጽሐፉ ላይ ላውጣላችሁ።ገፅ 149 ላይ እንዲህ ይላል፡-

“ለኔ ህይወት በአጫጭር ልብ ወለድ የተሰራች ረጅም ልብ ወለድ ነች። ከአጭር ልብ ወለድ አንፃር ካየኸው ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩህ ይችላሉ፤ ዳኛና ፍትህ የሌለ ይመስላል።ከረጅም ልብ ወለድ አንፃር ካየኸው ግን ለሁሉም ጥያቄ መልስ አለ። ለሁሉም በደል ፍትህ አለ። ያ ረጅም ልብወለድ ደግሞ ለሌላ  ትልቅ ረጅም ልብ ወለድ ግብአት የሚሆን አጭር ልብ ወለድ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ማንንም በምንም የምንዳኝበት ቦታ ላይ ያለን አይመስለኝም። የኛ መወራጨት ያለው አጭር ልብ ወለድ ውስጥ ነው። ከረጅም ልብ ወለድ አንፃር ሲታይ ደስታና ሀዘናችን ሁሉ ከምናስበው የተለየ መልክ ይኖረዋል። ለዛ ነው መጽሐፌ ላይ ‘ከዮኒቨርስ አሰራር ጋር እርቅ አውርዶ መኖር ያስፈልጋል’ያልኩት። ጥያቄዎች እንዳሉ ጠፍቶኝ ሳይሆን የሆነ ቦታ በሆነ አሰራር ይመልሳሉ በሚል ተስፋ ነው።”

ማስተላለፍ የፈለገውን መልዕክት በአፃፃፍ ስልቱ በኩል መግለፅ መቻል አይገርምም!?

******

 እነዚህ በቀጣይ የማነሳቸው  ሀሳቦች ላይ አረፍ ብለን እንቀጥል እስኪ ደግሞ። በመጽሐፉ ሁለት ቦታዎች ላይ ተመሳሳይ አይነት ሀሳቦችን አግኝቼ ጥያቄ ሆኖብኝ ነበር። እንደሚከተለው አቀርባቸዋለሁ:-

አንድ – “ይሄ አሳሳም ከታስፈልጊኛለሽም ይበልጣል፤ ይሄ? ይሄማ የአምልኮ ነው አለች”ይላል። ያዙልኝ!

ሁለት – ” አይቼዋለሁ አስተቃቀፍህን ፤ ከእወድሻለሁም ይበልጣል፤ ታስፈልጊኛለሽ ነው ያልካት፤ ለዛ ነው በፍጥነት የወለደችልህ ” ይላል።

ውድ እንስት አንባቢዎቼ ሆይ እንዲህ አይነት አሳሳምና አስተቃቀፍ በእውኑ ዓለም አለን?ካለም ምን አይነት እንደሆነ ብታስረዱኝ ውለታችሁን አልረሳም።

    **************

 ደራሲው በገፀ-ባህሪያቱ በኩል የሰው ልጅን አንድነትና ሶስትነት ያሳየናል። ቆይ! ድንጋዩን ቁጭ አድርጉና  ተከተሉኝ ፤ እንድንግባባ።

   በመጀመሪያ በዚህ መጽሐፍ የተነሳው ትልቁ ሀሳብ የሰው ልጅ አንድ የሚኖርለትም፤ የሚያኖረውም ሱስ(ዕፅ) አለውም ያስፈልገዋልም የሚለው ነው። ሱሱ መጥፎም ይምሰል ጥሩ ፤ ከፍ ያለም ይምሰል ዝቅ በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ መኖሩ አይቀሬ ነው።

   በእኔ አረዳድ የዓለምን ትርጉም የለሽነት የሚያስረሳን(የሚያዘናጋን) ሱስ ያስፈልገናልም አለንም። የትኛውም ዓለማዊ ሩጫ ከዚህ ዕፅ ይመደባል።ከየትኛውም ወጥቶ መግባት፤ መገፋፋት፣ መሯሯጥ፣መራወጥ ወዘተ ጀርባ ያለው ይህ ዕፅ ነው። አብዛኛው የሰው ልጅ በዚህ ተራ በሚመስል የህይወት ምልልስ የተጠመደ ነው። ከአንዱ መሰናክል ወደ አንዱ፤ ከአንዱ ምኞት ወደ ሌላው፤ከአንዱ አላማ ወደ ሌላ አላማ እየተሸጋገረ እስትንፋሱ ህቅታ ድረስ ይኖራል።

ገፅ 71 ላይ እንዲህ ይላል:-

“እነዚህ ከእንቅልፋቸው ለምን እንደሚነቁ ያውቃሉ፤ ያዙትም አልያዙትም የሆነ የሚያሯሩጡት ነገር አላቸው። እኔ ግን ህይወት ‘ላንተ የሚሆን ድራማ የለኝም ዝም ብለህ የሌሎቹን ኑሮ መመልከት ትችላለህ’ ብላ ያገለለችኝ መስሎ ይሰማኛል” ይላል።

ልክ ነው፤ ህይወት በየጊዜው የተለያዩ ድራማዎችን እየፈጠረች ትርጉም የለሽነቷን ለማስረሳት ዘወትር ትታትራለች። የሰው ልጅም ይህንን ውጣ ውረድ የሚጠላው ይምሰል እንጂ፤ የምሬት ቃላትም ከአፉ ይውጡ እንጂ ነገርየውን ይፈልገዋልም፤ ያስፈልገዋልም።

“ከሸክም ሁሉ ሸክም የሚሸከሙት አለመኖር ነው። “እንዲል ፈላስፋው ባዶነትን መሸከም የምንችልበት ጫንቃ አብዛኞቻችን ጋር የለም።

 ገፅ 169 ላይ እንዲህ ይላል:-

“በየጊዜው ራሱን እየሸወደ የሚኖርበት አንድ ተጨማሪ ውሸት እስካገኘ ድረስ ሌላ ነገር አይፈልግም”

የአብዛኞቻችን ኑሮ ይህንን ይመስላል፤ ነገር ግን ከውሸት ዓለም መንቃቱም ደግሞ የራሱ የሆነ ከባድ ሸክም አለው።  በመጽሐፉ ገፅ 70 ላይ

“ከነቃሁ መጋፈጥ የማልችላቸው እውነቶች ያሳድዱኛል” እንዲል ካለንበት የውሸት ዕፅ ተላቀን ወደ እውነት መንቃት የሚያስከትለውን ማለቂያ የለሽ የጥያቄ ውርጅብኝ ያለ መልስ ለመሸከም የሚያስችል ጫንቃ እስክናበጅ ድረስ ውሸታችንን እያደስን መኖር ተመራጭ ይመስለኛል። 

Review on the novel Mamush.
© Greg Howard fine art studio. (A Bit of Solitude. by U.K professional artist Greg Howard.)

እንግዲህ የኑሮ ውጣ ውረዱ የአብዛኛው ሱስ ነው ካልን ስለተቀረው ጥቂት ሱሰኛ ደግሞ እናውራ።

 የአንዳንዱ ዕፅ ፍቅር ፣የሌላው  ፖለቲካ የአንዳንዱ ስዕል፣ ሙዚቃ፣ ጽሑፍ ብቻ ጥበብ ነክ ነገር ነው ይለናል። አንዳንዱ ደግሞ የማይረቡ በሚመስሉ ሱሶች ይደበቃል። ለምሳሌ ገፅ 71 ላይ እንዲህ ይላል:-

” እርግጥ ነው ሴሰኛ ባልሆን እራሴን አጠፋ ነበር። እርግጥ እስካሁን የቆየሁት በእሱ ምክንያት ነው”

የዕፁ ተራ ወይ ከፍ ያለ መምሰል የነገርየውን ድራማነት አይሽረውም። 

የእኛስ ሱስ ምን ይሆን???  እሱን በተነጠቅንበት ቅፅበት መኖራችን ትርጉም አልባ የሚሆንበት ነገር ምንድን ነው?

የእኔ አንደኛው ሱስ እምነት ይባላል። የማምነው ወደ ፊት ያለን እሳት ፍራቻ ብቻ አይደለም። ይልቁንም እዚህ ምድር ላይ ያለን ከባዶነት ስሜት የሚነሳ ወላፈንን ፍራቻ ጭምር እንጂ። የማይመለሱ፣ ለራሴም የሚያስፈሩኝ፣ ባዶነት የወለዳቸው ጥያቄዎቼ እንዳልነበሩ የሚሆኑት ይህንን ሱሴን አጥብቄ በያዝኩበት ሰሞን ነው። በመጽሐፉ አንድ ቦታ ላይ እንዲህ ይላል፡-

“ይኀው የህልሜ ፍቺ፤ በመንታ መንገድ የሚፈሰው ወንዝ መንታዎቹ ዳግሞች ናቸው። እንደ ወንዞቹ ሁለቱም አንድ አይነት ናቸው። ሲጠጧቸው ግን ጥቅማቸው  ይለያያል። አንደኛዋ ጥም ትቆርጣለች አንደኛዋ ቁስል ትፈውሳለች። ውኃና ፀበል ናቸው።”

ስለዚህ የእኔ ሱስ ፀበሉ ነው ልንል እንችላለን ?ታድያ ሱሰኛ መሆን ካልቀረ ፀበሉ አይሻልምን?

*           *            *             *

ከመሰጡኝ አረፍተ ነገርና ሀረጎች መካከል ጥቂቱን:-

“በጊዜ ራስህን አለመግደል አንዱ ክፋቱ ይሄ ነው ። ዓይንህ እያየ የምትፅየፈውን ሰው ትሆናለህ “

“ከመሸነፍ በላይ ጎትጎተው ያስጀመሩትን ጦርነት መሸነፍ የከፋ ነው”

“የምተኛበት አልጋ እንጂ የማየው ህልም የለኝም”

“ምንም እውነት አንተ ጋር ብትሆን እንባህ ሲበዛ ግን ለመታመን እየጣርክ ይመስላል”

“አሸናፊ እንደመሆን ምን ትዕግስተኛ የሚያደርግ ነገር አለ”

“የሚያስገርማትን ማወቅ የበለጠ እሷን እንዲያውቅ አደረገው”

“እንደው ሲመቻቸው ጎረበጣቸው”

“በተኩላ ለምድ የሚደበቅ በግ እንዴት አያሳዝን”

“ሌሎች በፍቅር ስም ሲጠሉኝ እሱ በጥላቻ ስም ወደደኝ”

“ዙሮ ተዟዝሮ የሚችሉትን አድርገው የቀረውን ደግሞ “የጀንበር አመል ነው” እያሉ ማለፍ ነው እንጂ በነጋ ቁጥር ለሌለው መሸበት ተብሎ እየታዘነማ እንዴት ተብሎ ይዘለቃል”

“ከፈጠርኩት በኋላ መልሶ የሚፈጥረኝን ነገር  እፈጥራለሁ”

“ታሪክ ራሱን አይደግምም፤ እኛ ነን ስህተታችንን የምንደግመው”

“ጥሩ የውሸት ታሪክ እንድነግራችሁ  ከፈለጋችሁ ትንሽ እውነት  ስጡኝ”

“ወሲብ ወሲብ ትልና መልሰህ አምላክ አምላክ ትላለህ። የሆነ ወንጌላዊ ለመሆን ተፈጥሮ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር የጠለፈው ዲያቆን ነው የምትመስለኝ “

“ተራ ህይወት በሌለበት ተአምር ምን ይሰራልኛል?”

“እዚህ ዓለም ላይ ሊቆጣጠርህ ነው እንጂ ሊወድህ የሚፈልግ የለም። አንተም ከኩራትህ ፍርሃትህ ስለሚበልጥ ትንበረከክላቸዋለህ”

********

እንቀጥላለን

  የአንዳንዱ ሱስ ደግሞ (እኔ የአብዛኛው የምለው)በሚያስገርም ሁኔታ ህመም ነው ይለናል። የሚያኖረው እየጎዳው ያለው ህመሙ ነው። ዘወትር የሚያማርርበት፤ የሚያለቅስበት ህመም የመኖሩ ምክንያት ነው ይለናል። ሽፋኑም ላይ ሲick addiction ብሎ አስቀምጦታል።

ከገፅ 34-35 እንዲህ ይላል:-

” ሱሰኛ ነው እንጂ ደስተኛ ነው ያለ የለም። ሱስ የሚያስፈልገን ደስተኛ ሁነን ለመኖር ሳይሆን ለመኖር ነው። ደስተኛ ሆን’ም አልሆን’ም ጠዋት የምንነቃበት ምክንያት ይሰጠናል። አንዳንዶች እንዲህ ናቸው። ከስቃያቸው ጋር ሱስ ይይዛቸዋል ።”

 ይህንን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩት “Adlerian psychology ስለሚባል ነገር ያነበበኩ ጊዜ ነው። ስለሱም ራሱን የቻለ ዳሰሳ እሰራለሁ ኢንሻአላህ። ለአሁኑ ግን ብዙም ያልተወራለት Alferd Adler የሚለውን እንስማ።

“ሰዎች የማይቀየሩት ፍሮይድ እንደሚለው ጠባሳቸው(Trauma) ለመቀየር ስለማያስችላቸው ሳይሆን ከጠባሳቸው ጋር መኖር ስለሚፈልጉ፤ መቀ’የር ስለማይፈልጉ ነው” ይለናል።

የደህንነት ስሜት የሚሰጣቸው ህመማቸው ነው። ምቾታቸው ህመማቸው ነው። አብሯቸው ከኖረው ስቃይ ጋር ተፋተው ብቻቸውን እንዴት መኖር እንደሚችሉ አያውቁም። ህመም-አልቦ ኑሮ ፍፁም ወደማያውቁት አዲስ ዓለም ይወስዳቸዋል። ዓለምንም እንደ አዲስ ለመተዋወቅ ይገደዳሉ። በዚህም ምክንያት ለውጡን አይፈልጉትም ነው ሀሳቡ( በሚገባ መንገድ ገልጬው እንደሆነ አላውቅም)።

ስለዚህ ብዙ ሰው ችግሩን፣ ስር የሰደደ ህመሙን የሚያወራልህ እንድታድነው ላይሆን ይችላል። ከህመሙ ሱስ የያዘው ሊሆን ይችላል።

ገፅ 35 ላይ እንዲህ ይላል..

“እንዲህ አይነት ሰዎች ሲገጥሙሽ ልታድኛቸው አትሞክሪ። ልታስጥይው ከሞከርሽ ከሱሱ ነጥለሽ ያለ ጊዜው ትገድይዋለሽ። ዝም ብለሽ”ኧረ እንዴት አድርጎ ረገመህ!?” ብለሽ ከንፈርሽን ምጠጭለትና ቀጥይ።”

አንዳንዱ መፍትሔ ሳይሆን “ኧረ እንዴት አድርጎ ረገመህ!?” መባልን ፈልጎ ነው የሚመጣው እያለን ነው።

ውስብስብ ነው አይደል?ስንኖረው ያልከበደን ወስብስብነት ስንገልፀው ከበደን

“people have a hard time letting go of their suffering. Out of fear of unknown, they prefer suffering that is familiar” (Thich Nhat Hanh)

*         *     *       *      *

 ሁላችንም የሆንነውን የሆንነው በሆናቸው ነገሮች ምክንያት ነው ይለናል።

The girl who is afraid to be

She speaks to me fondly of passions and talents,

      Guitars and stars,

       Then stops short

And apologizes for speaking at all.

All because somewhere in her life,

Someone she loved broke her heart

By ignoring her beautiful words

     and telling her to shut up,

           Keep it down,

nobody cares.

   People aren’t born sad

   We make them that way.”

Nikita Gill

*       *        *         *

ሀ ብለህ በለቅሶ ከመጣህባት ቅፅበት ጀምሮ የምታልፍባት እያንዳንዷ ሁነት ሰርታሃለች ፣ እየሰራችህ ነው፣ ትሰራሀለችም።  ይህንን ገፅ 197 ላይ እንዲህ ባለ ውብ አገላለፅ ያስቀምጠዋል:-

“ደግሞ እኮ ስም ሲያወጡልን ለያዩን እንጂ መጀመሪያ ላይ ሞክሼ ነበርን። ስንገናኝ ስም፣ ቤተሰብ፣ ሳቅ የሌለን ማሙሾች ብቻ ነበርን። “

 የታከምነው ስንቀር እያንዳንዷን የዛሬ ድክመትም ሆነ ጥንካሬያችንን የተነቀስነው በዚህ በማሙሽነት ጊዜያችን ነው። “Inner child” ይሉታል ነጮቹ። “ሁላችንም በትልቅ ሰው ገላ ውስጥ ያለን ህፃናት ነን” ይባል የለ።

******

“In another universe

 I meet my mother

When she is a child

We go for a walk on the seaside

and she tells me all the things

 she loves about the world.

We share a hundred jokes

and she loves so easily,

without a single worry.

I want to meet that version of her

Wide eyed and full of joy

Easily laughter and care free

Before the same world

she loved so deeply

broke her heart”

Nikita Gill

***

  ከላይ የጠቀስናቸውንም ይሁን ማንኛውም አይነት ጠባሳ የምናስተናግደው በአብዛኛው በዚህ የማሙሽነት ጊዜ ነው። አደራረግህ፣ አኳኋንህ፣አካሄድህ ሁሉ ከዚህ ጠባሳ ይነሳል። ሁልጊዜም እንዲህ እላለሁ፡-

” ጠንቅቄ እንዳውቅህ ጠባሳህን አሳየኝ”

 ሁሉም ከዚህ ምሽግ ተነስቶ እየተኮሰ ነው መግባባት ያቃተን። ምሽጉ ያለበትን ካወቅህ፣ ከደረስክበት ሰብረህ ወይ ገልጠህ አየኀው ማለት አይደል። ያኔ ሁልህም አንድ አይነት ነገር ውስጥ የምትዳክር ተመሳሳይ ፍጥረት መሆንህ ይገለጥልሀል። መፈራረዱ ቀርቶ መተዛዘኑ ይከተላል።

****

“from a young age

I always felt the need to stay quite

      shush

they’d say you talk too much

Why are you being so loud?

My inner child’s voices were silenced,

when all it wanted was to be heard.”

*          *      *      *    *

ይህንን ሁሉ መንገድ የመጣሁት በእርግጥም አንድም ሶስትም መሆንሽን ለማስረዳት ነው። ዛሬሽ ላይ ትላንት አለ ፤ ነገሽ ላይ ዛሬ አለ። ስለዚህ የሰው ልጅ ትላንቱን ብቻ አይደለም ዛሬውን ብቻም አይደለም። ነገውን ብቻም አይደለም ። ትላንት የሆነ አይነት ሰው ነበር፤ ዛሬ ወደ ሆነ አይነትነት ተቀይሯል፤ ነገ ደግሞ ወደ ሌላ አይነትነት ይሸጋገራል። በእያንዳንዱ ሽግግር ውስጥ ግን ሶስቱም ቦታ ቦታቸውን ይዘው አሉ። መሻገሩን ትሻገራለህ ረግጠኸው ያለፍከው ጎዳና ግን ሸክምህ ሆኖ አብሮህ ይዘልቃል።

አንተ ትላንት ዛሬም ነገም ነህ!

ታድያ አንድም ሶስትም ሆንክ ማለት አይደል!

*****

“I wish someone

 had warned me,

 when I was younger,

Now i stay up all night and weep

The ghosts of everything

You have loved and lost

Come back up to haunt you in your sleep”

Nikita gill

*****

” አየህ በህይወት ያሉ ስሜቶች ሁሉ ከሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ አያልፉም ። ከዛ በላይ ልግፋቸው ካልክ ብጥስ ብለው ወደ ዜሮ ይመለሳሉ። ልክ እንደ ወሲብ። በውስጣችን ያለው ማሙሽ ግን ያቺን ሶስት መቶ ስልሳ አንደኛ ዲግሪ ላይ ያለች ስሜት ለማግኘት የማያስፈነቅለን ድንጋይ የለም ” ይልሀል ማይክል። ሁላችንም እንደየ ደረጃችን ከፀሀይ በታች አዲስ ነገር ፍለጋ ነው ሩጫችን ። ማሙሽ አያርፍም ፤ አይጠግብም ፣ያራውጠናል።

*      *        *       *     *     *    *

 ስጠቀልለው ማሙሽ ለእኔ “Inner child” ነው፤ የማይጠረቃው የሰው ልጅ ፍላጎት ነው። ቁስላችንን እየላስን አንድንኖር የሚፈልገውና በየቦታው እየተገኘ sabotage የሚሰራብን ጠላት ነው። በአጠቃላይ እስካላከምነው ድረስ ከኋላ ሆኖ የሚዘውረን ግለሰባዊ “Elite force። የማይታይ ሪሞታችን እንደሆነም ይቀጥላል። ያንተን ፊት ያስመታል ፤ እየኖረ ያለው ግን እሱ ነው። አልፎ አልፎ ራስህን ገዝተህ እየኖርክ እንዲመስልህ እንደሌለ  ደበቅ ይልልሀል። ዋና ዋና ማርሽ ቀያሪ የህይወት አጋጣሚዎችህ ላይ ግን እየተገኘ አቅጣጫ ያስቀይራል፣ ይወስናል ፣ይመራል።

ስለዚህ የድህነትን ጎዳና መምረጥ ግድ ይልሃል።ውሃውን ትተህ ፀበሉን መጠጣት ግድ ይላል።

“እንዴት” ነው ያልከው?

“ነፃ እንዳይወጣ ከፈለግህ ቀድሞውኑ  መታሰሩን እንዳያውቅ አድርግ” አይደል የሚባለው ?

ቢያንስ አሁን መታሰርህን አውቀሃል። ግማሽ ሄደሃል ማለት ነው።

“ከልብ ካለቀሱ ደግሞ እንባ አይገድም”

****

“In another universe

 I meet my father

When he was a child.

We play catch in the woods

and as we play, he tells me

he isn’t allowed to cry

but sometimes the world

hurts him and he doesn’t know

what to do with all that pain.

so, I give him the shoulder

he needs to cry on.

 and he does. he does

until the tears has done.

after wards, I buy him ice cream

and I listen to his laugh,

the glowing warm laugh

of a child who knows he is safe.

I wish someone could have done that for him

been a kind, safe place

for the child he used to be.

Would it have made a difference?

Would it have made a difference?”

Nikita Gill

*         *        *          *         *       *

  ጨረስን! ሳይሆን ጀመርን። መጽሐፉ ገና አልተነካም። ትሁን ለመሆን አይደለም፤ከልቤ ነው፤ ለሶስተኛ ጊዜ ደግሜ ባነበው በተለየ መልኩ እንደማየው እርግጠኛ ነኝ። ያላነበባችሁት ማንበብ ግዴታችሁ ነው። ያነበባችሁት ደግሞ ድገሙት። የተፃፈበት መንገድ ግሩም ነው ።ቃላት አጣጣሉ Forced አይደለም። ቀላል ቋንቋ ነው የተጠቀመው፤ በነፃነት የተፃፈ ነው። ለራሱ ብቻ የፃፈው ሁሉ ይመስለኛል መጀመሪያ ። ብቻ ይነበብ !

ጥሩ ኅያሲዎች ደግሞ ይህንን እንደመነሻ ወስዳችሁ፣ አንብባቹ ፍትፍት ብታደርጉልኝ ውለታችሁን አልረሳም።

 ቅሬታ

ሚዛን ለመጠበቅ ስል በግድ ስህተት ስፈልግ ራሴን አገኘሁትና “ምነው! በቃ ወድጄዋለሁ (ሙሉ በሙሉ)ማለት መብቴ አይደል እንዴ?” ብዬ ብእሬን አስቀመጥኩ።

ምንም አልጎረበጠኝም (ጥሞኛል)

*******

እኔ ጨረስኩ ብያለሁ እንግዲህ

እናንተ የምትሉትን በሉኝ

ከተቻችሁኝም ታድያ አደራ ቀለል አድርጋቹህ

“ለምን?” ለሚለው ጥያቄያችሁ

መልሱ ገፅ 25 ላይ  አለላችሁ(አቤት ግጥም ሃሃሃ)

“ቆይ አንተ የሰው አስተያየት ለምን ይህንን ያህል ግድ ይሰጥሀል?”

 “እኔ ያደግኩበት አካባቢ በቀላሉ ስለማይገኝ የቫይታሚን ላቭ እጥረት አለብኝ”

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *