በዙበይር ኢብራሒም

ሄኖክ በቀለ ለማ ይህንንም ድንቅ መጽሐፍ አበረከተ። በመጽሐፉ ታማሚውን ገጸ ባህሪ ጤናው፣ ፍጹም እድለ ቢሱን እድሉ ቀና፣ ዘመኑን ሙሉ በጭንቀት የኖረውን ደስታ ወ.ዘ.ተ… በሚል ሰይሞ ስም ሌላ ማንነት ሌላ ብሎ ቢሞግትም፤ ስምን መልአክ አያወጣውም፣ ቢያወጣውም ሆን ብሎ በዚያ በኩል ሊሳለቅ ሲፈልግ ነው፣ የሚል አይነት ሀሳብ ቢያነሳም፤ ደራሲው ራሱ ግን ስሙን በመጠኑም ቢሆን ከመምሰል አልዳነም( እኔ አልኩ)።

ዓለማዊው የኛ ዘመኑ ሄኖክ እንደ ቅርስ አስቀምጠን በሂደት እየተረተርነው የምንኖረውን ዳጎስ ያለ ሸማ እንካችሁ ብሎናል። ታድያ ይሄኛው ሄኖክ በሀሳብ እንጂ በስጋ ሰማየ ሰማያትን አልፎ አልተጓዘም።

“ሄኖክ ሆይ ቋንቋህ ከበደን ምናለ ቀለል ብታደርገው?” የሚል ጥያቄ ላነሱ አንባቢዎቹ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።

“ራሳችሁን ወደዚያ ደረጃ አሳድጉ እንጂ እኔን እንዴት ውረድ ትሉኛላችሁ”(ቃል በቃል አይደለም ታድያ የደገምኩላችሁ ሀሳቡን ነው)

ስለዚህ የኛ ዘመኗን፣ ደፋሯን፣ ዓለማዊቷን መጽሐፈ-ሄኖክ ለጊዜው ባለንበት ደረጃና በገባን ልክ ዳበስ እናደርጋታለን። ስናድግ ደግሞ እናሳድጋታለና።

አማኙ አብዘርዲስት ሄኖክ በቀለ “ሀገር ያጣ ሞት” በሚል ርእስ በ208 ገጽ በቀነበባት ሁነኛ ሰነዱ ተንፍሶ አስተንፍሶኛል። ለድብርት ጊዜ ቆጥቤ አስቀምጬ እንደ ህመም ማስታገሻ የምወስዳቸው የቃላት ዲጂታል መጽሔት ስራዎቹን ከፍ ባለ ዶዝ ይዞ መጥቷል። መፍትሔ ቢስ የሚመስለውን አዙሪታም ቁስል ሀያሲ ቴዎድሮስ ድንቅ በሆኑ ቃላትና አገላለጾቹ ልሶልናል። “አዎንታዊ አስተሳሰብ አራማጆች ነን” የሚሉ ሰዎች መጽሐፉ ጨለምተኛና “pathos” እንደሚባለው አይነት አካሄድ ያለው ነው ብለው ሊደመድሙ ይችላሉ። ለእኔ ግን “ሀገር ያጣ ሞት” “pathos” አይደለም ከአዳም ስህተት ጀምሮ፣ ሰው የመሆን እጣ ፋንታ ከገጠመን ጊዜ ጀምሮ የታደልነውን ህመም ሲደመር ዘመን አመጣሽ ህመም የምንተነፍስበት ቴራፒ ነው።

በመጽሐፋ ገጽ 189 ላይ እንዲህ ይላል…

“የሀዘንም ቢሆን ኑሮ በስነ ጽሑፍ ውስጥ እንዴት ያባብላል?”

በእነዚህ 208 ገጾች ያልተላሰ ቁስል ጠይቁኝ። ሁሉም ተነክቷል። ፖለቲካው፣ ስነ ልቦናው፣ የማህበረሰብ ምስቅልቅሉ፣ዘመን አይሽሬው የህልውና ቀውስ ህመም፣ ዘርዝሬ አልጨርሰውም። ሁሉም ላይ የሀሳብ ድንጋይ ተወርውሯል። ድንጋዩ ፈጣሪንም አልማረም።በአግባቡ ተሞግቷል ስላችሁ!

         “የዲያቢሎስ ምራቅ የነካት” የተባለችው ምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገርም ራቆቷን ተደርጋ አንድ በአንድ ተበልታለች። በድርሰት ዓለም ስር ማንም ከማንም አይበልጥም በሚል አዋጅ የተነሳው ደሪሲ የፈጣሪን ትርክት ሆምጠጥ ያለ ተረት፣ ዲያቢሎስን ደግሞ የመጀመርያው አብዮተኛ እስከማለት የደረሰ ደፋር መንገድን ተጉዟል።

ከዚህ ሁሉ በፊት ግን በመግቢያው ፈጣሪን

“አይ የልጅ ነገር ብለህ ስለምታልፈኝ” የምትል የፈሪ ቀብድ አስይዞ ነው የጀመረው።

ማን? ከእኛ ከሁላችንም እንደ አንዱ የሆነው አማኙ አብዘርዲስት ሄኖክ በቀለ።

እኛም “አይነኬው” ውስንነታችንን፣ አቅመ ቢስነታችንን ያውቃልና “አይ የልጅ ነገር” ብሎ ችላ እንዲለን በመመኘት ውስጥ ጉዟችንን እንቀጥላለን። ተከተሉኝማ።

  “በምድር ፊት ስላቃችን ማለቂያ አልነበረውም” እንዲል ጥርስ የማታስገልጥ መራር ስላቅ ስለሆነችው ህይወትና ወለፈንዲ ህልውናዋ (ህልውናችን)በሰፊው አንስቷል። እስኪ ለዛሬ ከተነሱት እልፍ ሀሳቦች መካከል የህልውና ቀውሶቻችንን በእጣፋንታ መስኮት በኩል ያስመለከተበትን መንገድ መዘዝ አድርጌ ላስቃኛችሁ።

      በመጽሐፉ በሚያስቀና መልኩ እንደልብ ወደኋላ ወደፊት ሲያስጉዝ (time travel) ፣ ዘለዓለማዊነትን እና ሞትን ሲሰጥ ሲነሳ የተመለከትነው “ሀያሉ ጊዜ” ራሱ የመፈጠር እጣ ፋንታ እንደገጠመው ይነግረናል።

“ፈጣሪም ንጥር ታሪኩን ሳይጀባን ሆምጠጥ ያለ ተረቱን እያሳሳቀ ሳይነግረን አስቀድሞ ያቆመው የመቼ እና የት ቢጋሩን ነበር” ይለናል የመጀመርያው ገጽ ላይ።

ጊዜና ቦታን ተከትሎ የአዳም ዘር ገጽ 65 ላይ በተቀመጠው መልኩ “ለኗሪነት ቀንበር፣ ለህያውነት ጫና ተዳረገ” ይለናል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ለእጣፋንታ እንጂ ለምርጫ አልታደለም። የሰው ልጅ ምርጫ ቢስነት የሚጀምረው እንግዲህ እዚህ ጋር ነው። በነፍስ ወከፍ የእያንዳንድህ ምርጫ ቢስነት ደግሞ ከውልደትህ ይጀምራል ይላል ሄኖክ። ይህንንም ገጽ 68 ላይ ድንቅ በሆነ አገላለጽ እንዲህ ያስቀምጠዋል።

“ሚሊየን የወንድ ሀጢአት ተጋፍቶ ከመካከላቸው አንድ አሸናፊ የተባለ ጎረምሳ ዘር፣ የሴቴ እንቁላል አሽኮርምሞ ሲያፋፋ ተፈጠርሁ። አሸናፊ ምን ስለሆነ አሸነፈ? ባላባት ነው የመኳንንት ዘር? ደጃዝማች ነው ፊታውራሪ? የሰለሞን ዘር ነው የላልይበላ? ከአረብ መጣ ከፋርስ? ከጤግረስ ጠጣ ከጢዮን? ከከሸፈ ትውልድ መሐል እንዴት መከናወን አወቀበት? ከእልፍ ለምን ተመረጠ? የእግዜሩ ነው የእሱ ጥረት? ደቁሶ ካስቀራቸው መሐል እንደው ከእርሱ የተሻለ ጠፍቶ ነው? እንደኔ አይነት ልጅ ለመውለድ ምን እንዲህ አንገበገበው? የቀሩትስ ምን ሆነው መከኑ? የአርባ ቀን እድላቸው ነው ወይስ ከሰባት ትውልድ የተላለፈ እርግማናቸው? ጭሰኛ ናቸው ጥሩራ ባርያ? አሕዛብ ናቸው መናፍቅ? ሀጢእ ናቸው ቅንቅናም? ነጭ ድሀ ናቸው መናጢ?”

 ይህንን ሁሉ አትመርጥም። መጥተህ ነው ራስህን የምታገኘው። ከመጣህ በኋላም ይመስልሀል እንጂ አመለካከትህን አትመርጥም፤ መንገድህን አትመርጥም፤ አመጣጥህ አካሄድህን ይወስናል፤ አካሄድህ አደራረስህን ይወስናል።

 በገጽ 146 መጽሐፈ መክብብን ጠቅሶ እንዲህ ይላል

“ህይወቴ የጀመረው ስወለድ አልነበረም”።

የተጀመረ መጽሐፍ ላይ የመጣህ ቅጣይ መስመር እንጂ ራስህን የቻልክ ጥራዝ አይደለህም። ያንን መስመር እንድታሟላ ተወስኖብህ ከመጣህ ወዲያ መቀየር የምትችለው አንዳች ነገር አይኖርም ነው ሀሳቡ።

“ፍቃዱ አየልኝ” ግርባብ በሚለው መጽሐፉ ብእርን እንዲህ ሲል ያናግራታል

“የማትወጂውምንም ሆነ የምትወጂውን መንገድ እኔ አልሄድም እንድትዪ መብት የለሽም። ምክንያቱም ምን ሊጽፍብሽ እንዳሰበ የሚጽፍብሽ እንጂ ቀድሞውንም አንቺ አላወቅሽም”።

“The value of everything depends on its contribution to a whole of which it can be seen as a part “Nietzsche.

***

  እስኪ ደግሞ ገጽ 93 ላይ በሽማግሌ የተወከለው ጊዜና መልከ የተባለው ገጸ ባህሪ የሚያደርጉትን ምልልስ እንመልከት።

መልከ: -“የተወሰኑ ዓመታት ወደ ኋላ መልሰኝ። ህይወቴ ላይ ማስተካከል ያሉብኝ ነገሮች አሉ።”

ጊዜ: -“ብወስድህም የሰራኸውን ስህተት ደግመህ ትኖረዋለህ ልጄ።”

መልከ: -“አላደርገውም።”

ጊዜ: -“ከእድል ፈንታው ማንም አያመልጥም።”

“If one were to live over again one would want the very life one has already had exactly the same down to its tiniest detail and nothing else”

(Nietzsche)

ካንተ በፊት እየተጻፈ የነበረውን ነገር ለማስቀጠል ብቻ ሳይሆን ካንተ በኋላ ለሚመጣው ገጽ ድልድይ ለመሆንም ጭምር ተወስኖብህ ነው የምትመጣው። ልትቀይራት የምታስባት መስመር ቀጣዩን ገጽ ልታበላሽ ትችላለችና ነው። ክቡን የማሳት አቅም ሊኖራት ስለሚችል ነው። ክቡ ላይ ፍቅር የምትባል ነጥብ ትኖር ዘንድ ዱና ዓይኗን መታመም ነበረባት፤ መልከ ያለ ቅጥ መስከር ነበረበት፤ ተዋቡ የምትባል ነጥብ እንድትሰረዝ ፈጣሪና መፍለጫው ማበር ነበረባቸው።

በአጭሩ

“Not only your past defines your future your future also defines your past.”

(ማንነቱን የረሳሁት ሰው ሀሳብ)

“We could possibly affirm like the untimely death of a loved one or friend or a tragic accident that  kills hundreds of people but perhaps the key were is to zoom out and see such occurrences as essential to the journey we are on as playing unavoidable roles in a beautiful whole”

Nietzsche

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *