ተናዳፊ ትንፋሾች

ውብአረገ አድምጥ

ከትንፋሽ ውበት ረቂቅ የዋሽንት አልበም የተመዘዙ የዘመን መልኮች

ረቂቅ ሙዚቃ ማለት

ረቂቅ ሙዚቃ ማለት በሙዚቃ መሳሪያዎች ብቻ የሚጫዎቱት የሙዚቃ አይነት ነው። ድምጽ (vocals) ሳይገቡበት የሙዚቃ መሳሪያዎች ብቻ ስልት ባለው መልኩ ተዋህደው ይቀርቡበታል። በሃገራችን ረቂቅ ሙዚቃ እንግዳ አይደለም። ከድምጽ ጋር የሚዘፈኑትን ያህል ተደማጭ ባይሆንም ለአድማጭ ግን እንግዳ አይደለም። ለአብነትም እነ ጌታቸው መኩሪያ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ፣ ግርማ ይፍራሽዋ፣ ዳዊት ፍሬው እንዲሁም ሞሰብ ባንዶች ከዚህ ቀደም ረቂቅ ሙዚቃዎችን ለአድማጭ እንዳደረሱ ስራቸው ምስክር ነው። እዚህ ላይ ስማቸው ያልተዘረዘሩ ሌሎች እንዳሉም መዘንጋት የለበትም። በቅርቡም ጣሰው ወንድም የትንፋሽ ውበት የሚሰኝ የዋሽንት አልበሙን ለአድማጭ አድርሷል።

ጥቂት ስለ ጣሰው

ልጁ ከስንጥርጥይ ጋር የነፍስ ቁርኝት አለው። በትንፋሹ ይክምነመናል። የአንጀቱን ብሶት በአየር ሰረገላ እየጫነ ከዘመኑ ጋር ይቆናቋል። ከሸንበቆ አገዳ በራሱ ውብ ጣቶች የተቀረጸችዋ ዋሽንት በገዛ ጣቶቹ የዜማውን ዥረት ታወርደዋለች።

ልጁም ልቡ ለዋሽንት የተሰጠች የዘመን መናኒ ነው። ጣሰው ወንድም ይባላል። በሀገረ ኢትዮጵያ በጎጃም ምድር በጎዛምን ወረዳ ከውብ የገጠር ቀዬ እንደተወለደ በራሱ አንደበት ሲመሰክር የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ሰምቷል። ልጅነቱን በእረኝነትና በቡረቃ ያሳለፈው ጣሰው የዋሽንት ልክፍቱ ከቤተሰብ ይጀምራል።

በአምባውና በቀየው እንደ ቆላ ገራዶ ሲሽሞነሞን እንደ አፋፍ ላይ ገዴ ሲነሰነስ አደገ። ልጅነቱን ከተፈጥሮና ከእንስሳት ጋር ሲተሻሽ ከቆቅና ከጅግራ ጋር ሲተናነቅ ቦርቆበት ከነፈ። የዋሽንትን ነዛሪ ድምጾች በልቡ ቡጥ ስር አስቀምጦ ጣቶቹንና ትንፋሹን ሲያናግር እንደ ዋዛ ተመነደገ።

ድንገት ከአዲስ አበባ ያመጣው እግሩ በለመዳት ዋሽንት ደግሞ ጉርሱንና ነፍሱን ሊያስተሳስሩለት ሲዳዱ አጋጣሚን ብቻ ነበር የጠበቁት።

ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሞሰብ ባህላዊ የሙዚቃ ባንድን ሲመሰርት ጥቂት ትውቂያና ጥረት ነበር የጠየቀው። ሞሰብ ባንድ ከተመሰረተ ከ10 ዓመት በላይ ሆኖታል። በተለያዩ የዓለም ሀገራት እይተዘዋወሩ በጥበብ ነፍስ አውግተው የሃገራቸውንም ስም አስጠርተዋል። ሞሰብ የባህል ማዕከል የሚልም ከፍተው ሰርክ ሙዚቃን ያናግራሉ። ይሄው ባንድ “ጥሞና” እና “ኃይለ ጊዜ” የተሰኙ ሁለት ረቂቅ አልበሞችንም አስደምጦናል።

ጣሰው ከምሽት ቤቶች እስከ ታላላቅ የዓለም የጃዝ መድረኮች ድረስ በእረኝነት ዘመኑ የተዋወቃትን ዋሽንት ይዞ ለጥበብ ተንፍሷል። ከአፍሪካ ጃዝ አባቱ ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር ሳይቀር በዚያች አራት አንጓ ዋሽንት ከሰው ልጅች ነፍስያ ጋር ስለ እውነት ተነጋግሯል። የልቡን፣ የነፍሱን፣ የአንጀቱን ዋይታም ሆነ ሆታ በንጽህና ዘምሯል።

ይሄ የዘመን መንገዱም ከእድሉ ጋር በተጣባችው በዋሽንቱ ላይ አድሮ አልበምን በሌላ ማዕዘን እንድናየው አደረገ። በመጋቢት 17- 2016 ዓ/ም የትንፋሽ ውበት የተሰኘ አዲስ የማሲንቆ አልበሙን አበርክቶልናል። በራሱ የዩቱብ ቻናልም የጀንበርን ማዘቅዘቅ ተከትሎ በዕለተ ሐሙስ ለነፍስ በሚደርስ ቋንቋ ተናገረን።

እኔም ሙያዊ በሆነ መልኩ ሳይሆነ አልበሙን ደጋግሜ ሳዳምጥ የተሰሙኝን አንዳንድ ሰሜቶች እንደ አንድ አድማጭ ለማጋራት ተነሳሳሁ። ሰምቶ ዝም ከሚል ፍርጃ ለመዳን ይመስላል።

የትንፋሽ ውበት አልበም

የትንፋሽ ውበት አልበም 10 የሙዚቃ ትራኮችን የያዘ ነው። በሁሉም ትራኮች ላይ ዋናውን ድምጽ ወክሎ የሚያናግረን ዋሽንት ነው። የሚከተሉት ሰዎችም አብረው ተሳትፈውበታል።

ፒያኖ ቀረጻ እና ሚክሲንግ- ዐቢይ ወልደ ማርያም
ፐርከሽን- ተፈሪ አሰፋ
ክራር- ቢኒያም ዳኛቸው
ቤዝ- እዮስያስ ታመነ
ኤዲቲንግ- ዘመኑ አዳነ

በአስር ትራክ የተከፋፈሉት ረቂቅ ሙዚቃዎች አንዳች የዘመን መልክ የተጎናጸፉ ናቸው። ጥሪአቸውም ወደ አንድ መንገድ ያሰጉዛል። መዳረሻው ከሰው ልጅ ባይሻገርም መንገዱ ግን ግለሰባዊ ነው።

ሁሉንም አንድ በአንድ ማቅረብ ፈታኝ መሆኑ እሙን ነው። የሁሉም የወል ጥሪ የሰው ልጅና የልብ እውነት ቢሆንም መንገዱ ግን ግለሰባዊና ለየቅል ነው። ጣሰውም በቃል የማይቀነበቡትን የስሜት ዜማዎች ስም ለመስጠት ሙከራ አደርጓል። ስም ይመርሆ ለግብር ብሎ ይሆናል። አንድም የወለዱትን በስም መጥራት የአባት ነው ብሎ ይሆናል። እኔም ለነፍሴ በጣም የቀረቡትንና አንዳች ሞጋች ምስል በምናቤ ውስጥ የፈጠሩትን አምስት ትራኮች እኔ ላይ ምን አይነት ስሜት እንዳሳደሩ በገባኝ ልክ ለመግለጽ እሞክራለሁ። በመጨረሻም አመስቱም ትራኮች የሰጡኝን የጋራ ቀለማቸውን ጠቅልዬ ለማስቀመጥ ሞክሬአለሁ። ይሄ ሁሉ መፍጨርጨር እንደ አድማጭ የተሰማኝን ለሌሎችም ለማጋራት ብቻ ነው።

አምባሰል

አምባሰል በፒያኖ ምጥ ጀምሮ ሽቅብ እየተንጠራራ የሚመነደግ የተንፋሽ ውበት ነው።ከሩቅ ከአድባር ወዲያ የከተመን እንቅልፋም የሰው ልጅ ይጣራል። የሚርገበገብ ብላቴና ከቁዘማው እየተላቀቀ ለአንዳች መማለል ከሩቅ የሚጣራ የአልፎ ሂያጅ ሳይሆን የቀዬ ልጅ ጥሪ።

በዋሽንቱ ተወርዋሪ ድምጽ የሚቃትተው የወንዜ ልጅ እኔን የሚጠራኝ ይመስለኛል። እንደ ጉዱ ካሳ በድፍረት የሚወርፍ ስል አንደበት ያለው የጋራ ላይ ንስር ነው። ከአምባሰል ላይ ሆኖ የሚጣራው ድምጽም የተኛን በሙሉ ከድባቴው የሚነቀንቅ የነብይን ድምጽ ይስተካከላል።

ነነዌ

በወፍራም የዋሽንት ጥሪና በቀጭን የዋሽንት ቅጭልጭልታ ድንገት እንደ ብራ መብረቅ በሚወጡ አልቃሽ ዋሽንቶች ይጀምራል። የወዮታ፣ የሃዘን፣ የልመና፣ እንዲሁም የዝማሬ መንፈስ ይታይብታል። በበደልና በስርዬት መካከል ያለች አንዳች ሽንቁር።

ያቺን በቃላት ወይም በንግርት የማይደርሷትን የነፍስ ቡጥ በትንፋሽ እንባ ለመንካት የሚደረግ መንጠራራት። እያንዣበበ በሚገኘው የእሳት ነበልባል መካከል ላይ ቆሞ ለትውልዶቹ የሚገደው ንቁ ሓዋርያ እስትንፋስ። ከላዕላይም ይሁን ከታህታዊ መለኮት ግርጌ እጁን ዘርግቶ የሚማጸን ልባም ዘመነኛ።

አሁንነትን በስንጥርጥይዋ ድምጸት ንቡር ጠቃሽነት ከትናንት ጋር አያይዞ ለማስታረቅ የሚዳዳው የጥበብ ሰው የትንፋሽ ሞገዶች! ሞትና መሰንበትን፣ ሃዘንና ዋይታን ጠንቅቆ በሚያውቅ የሙዚቃ ሰው ትንፋሾች የተገመዱ የድምጽ አለንጋዎች ናቸው። ዳሩ ይሄ ጥሪ ለእኔው ዘመን እንጂ ለማን ነው? መዓትና ምህረቱን ለመለየት ለሚታትር የዘመን ምንደኛ የተወረወሩ ሸንቋጭ ትንፋሾች።

ጉዞ

በወፍ ጫጫታና በሰማይ ወገግታ የሚጀምር የሚመስል መንከብከብ ይፈከርበታል። መንገዱ እንደ አሻል ፈረስ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ የሚከንፉበት አይነት አይደለም። ይልቅስ ጥቅጥቅ ባለ ጫካና የደኖች ውበትና ፍርሃት በሚጥበረበሩበት አይነት ግርማዊ መንገድ ውስጥ የሚደረግ እርምጃ። መራመድ፣ መሮጥ፣ መፍጠን፣ ማናፋት፣ መኳተን፣ ብረክ ብርክ ማለት፣ መንደፋደፍ፣ መደናገጥ፣ መደናበር ሁሉ የተጣቡት የቀበት መንገድ ይመስላል።

በጣሰው ዋሽንት የሚፈከረው ጉዞ ተራ መንከራተት አይደለም። ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ አንድ ቦታ ፈፋውን አቆራርጠው የሚተምሙት መናኛ መንገድ አይደለም። በአእዋፋትና በንፋሳት ሹክሹክታ ታጅበው እየተራወጡ የሚምዘገዘጉት አንዳች መቃተት ብቻ አይደለም።

የሰውን ልጅ ከፍጥረት እስከ ክስመት ድረስ የሚፈክር፤ ከኩኩ መለኮቴ እስከ ሞተ ተጎደጎደ ድረስ የሚያቅፍ ሰው የመሆን መባዘን የተሸከመ ነው እንጂ።  ከመትበስበስ እስከ መነስነስ፤ ከመንከላዎስ እስከ መንፈላሰስ ድረስ በትንፋሽ ተራዳኢነት  የሚራቀቁበት ህያው ሜዳ አይደለምን?

ከላይ እንደተወረወረ ተንከላዋሽ፤ በመንገድ ማጣት ውስጥ አንዳች ቅን መንገድ መሪን የመፈለግ መቀበዝበዝ የሚደመጥባቸው የህይወት አዙሪቶችን ሁሉ የሚያራቅቅ የህይወት ውል ነው።

Life is a journey that must be traveled no matter how bad the roads and accommodations. እንዲል ኦሊቨር ጎልድስሚዝ (Oliver Goldsmith) የጣሰው ተናዳፊ ትንፋኞችም በፍለጋ ውሰጥ እስከ ህይወት ስቅታ ድረስ የሚደርስ አንዳች መብሰክሰክን ያትታሉ።

ታዲያ የዚህ ሁሉ መባከን ውሉ ምንድን ነው? የዚህ ሁሉ የመንገድ ቱማታስ ዳሩ ምን ሊሆን ነው? የዚህ ሁሉ የነፍሳት ህብረ ዝማሬና የመንገደኛ መብከንከንስ እስከ መቼ ነው? የሚል ጥያቄ ቢኖር የትንፋች መልስ ግን ከረቀቀ ሙዚቃ ባሻገር ምንም ነው። ያ የረቀቀ ሙዚቃ ግን ከነፍስ ይደርሳል። በዚያ የነፍስ መጠራት ደግሞ ሰው የመሆንን እውነት እናገኛለን።

ትዝታ

ትዝታ የትናንት ድባብ ነው። ያለፈ ህልማዊ ቅንጥብጣቢ። የሚያመላለስ ደግሞም የሚያስጉዝ፣ ልያዘው ሲሉት እንደ ብናኝ የማይጨበጥ የሚመስል የህይወት ውል ነው። ዛሬን ጠፍጥፎ የሚሰራ እሰኪመስል ድረስ የሚያባባ የትናት ህይወት ቅምምስ ነው።

ጣሰው በትዝታ ትራክ የተነፈሳቸው ነዳፊ ትንፋሾች የአንድ ተራ ሰው ኑባሬ ቅጦች አይደሉም። እንደ ፈላስፋ ልሳን መናገር የሚያምራቸው፣ አተነፋፈሳቸው ሁሉ ለየቅል የሆነ ግን ደግሞ የጋራ ህልውና ያለቸው ህያዋን የጋራ መብሰክሰኮች ናቸው። ዝብቅርቅ የሚመስሉ ግን ደግሞ የወል ወዮታዎች። አንዳች የሳቱት መንገድ እንዳለ የገባቸው፤ ጸጸት የሚጋፋቸው የሚያባቡ ድምጾች ናቸው።

እጣቸው መኖር እንደሆነ የገባቸው፤ በልዩነት ውስጥ የጋራ ሰማይ ሊጎናጸፉ የሚያሰፈስፉ ግን ደግሞ ኩርምት ብለው ተቀምጠው አንዳች የሚያነሱት ጉዳይ ያላቸው ናቸው። ከፍ ብሎ የሚሰማው አብረክራኪ የዋሽንት ድምጽ ከሩቅ ሃገር ሊጠራው ያሰበው አንዳች እውነት እንዳለ የሚያሳብቅበት ሲቃ የሚታገለፍ የትንፋሽ እንፋሎት ነው።

ታዲያ ጣሰው የጋራ እጣችንን፣ ሰው የመሆን ከፍ ሲልም ሃገር የመባል ዘሃችንን ይዞ ከኋላ እየጠራ የሚመልሰን አይደለምን?

ዋሽንቶቹ

የዚህ ትራክ መልክ ደግሞ ሌላ ነው። የተለያየ ቅርጽና ድምጽ ወይም ህልውና ያላቸው ዋሽንቶች የጋራ ዋይታቸውን በሎም ሆታና ቱማታቸውን እያሰሙ ህብርና አንዳች ጥሪ የያዙበት መድረክ ነው። የታፈነ የጋራ ህመም እንዳላቸው ዋይታቸው ይመሰክራል። በአንድ መልካቸው ደግሞ በፈንጠዝያ ህቅታ የሚሰግሩ ይመስላሉ።

ይሄ የሲቃ ድምጻቸው ደግሞ ከከያኒው ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን የራሳቸው ተፈጥሮ ነው። እንዲያ ሆነው ተፈጥረዋልና የከያኒው ሃላፊነት የተሰጠውን መልዕክት ከማቅረብ ላይ ነው።

ታዲያ እኒህ የሚቅበዘበዙ ብሎም የሚያናፉ ህብር ድምጸቶች የእኛው አይደሉምን? የአንተ፣ የአንቺ፣ የእኔ የጋራችን የየግል እሪታዎች ብሎም ሆታዎች አይደሉም ማለት እንዴት እንችላለን። እነዚህ የጋራ ንፍረቃችንና ፍንደቃችን አይደሉም ወይ መኖር የሚባለውን የወል ድንኳን ያላበሱን። ከዚህ የወል ድንኳናችን ውስጥ የሚወረወሩ ተስረቅራቂ ድምጾችን ከያኒው ሰብስቦ እንደ ሰበዝም ሰብዞ ህብር ያለው መልካችንን ከዓይናችን ወደ ጆራችን አመጣው። ይሄ ነው ከያኒ መሆን እንጂ።

የማይጠቀለለው ሲጠቀለል

የጣሰው የትንፋሽ ውበት ሌላም እልፍ ተናዳፊ ትንፋኞችን አምቆ ይዞ ቆይቶ በዜማ መልክ እንደ እንባ የሚያወርድ የዘመናችን ሂስ ነው ብዬ አምናለሁ። ያ እንባ የደስታም የመታመምም ሊሆን ግድ አለበት። ከያኒውም ጋራ ለጋራ እየሮጠ እንደ ለፋፊ አንዳች ሰው የመሆን መንገድን ሊመራር የሚባክን መንደኛ ነው።

ትንፋኞቹ እንዲሁ ለቁዘማና ለዋል ፈሰስ የተተነፈሱ ሳይሆን ድርሳን ሰንደው፣ ከትውልድ ጋር ሊፋረዱ ከአደባባይ የቆሙ አጋፋሪዎች ናቸው። አንዳች ሊናገሩት ያሰቡት ሰዋዊ ብሎም ሃገራዊ ጉዳይ እንዳላቸው ከግብራቸውና ከስማቸው ማዎቅ ይቻላል።

በሃገራችን ብዙም ባልተለመደው በረቂቅ ሙዚቃ መልክ መጥተው ወዮታቸውን የሚያወርዱት ለቃል የለገመን አንደበት የሚወርፉ ሳይሆኑ ይቀራሉን? ተራናገሪ የዘነጋውን የእኛነት ደብር በትንፋሹ ሊያንኳኳልን እንደ ዘመን ጠሪ የተላከ መሲሃችን አይደለም ማለት እንደምን ይቻላል?

ህልው የመሆነ ምልክት የሆኑት እስትንፋሶች በሸንበቆ ጉሮሮ እያለፉ ህይወትን በዚህ ምልዓትና ቁጭት ልክ ማቅረባቸው የእነሱስ ሃገራቸው ልብ ነው አለማለት እንችላለን?

ህይወት አንዳች ህብርን የመፍጠርና የዚያን ህብዝ ትርጓሜ በመፈለግና አንዳች ምሉዕ የምናብ ዓለምን በመፈለግ ውስጥ በሚደረግ መንከራተት የሚገታ አይደለምን? ያን ፍለጋ እኮ ነው ጥበብ የምንለው። የእነዚህ ተናዳፊ ትንፋኞች የመጨረሻ ወደብም መልክን ፍለጋ ነው። ህይወትን እየተናደፉ አንዳች ምልዑነትን ለማግኘት የሚደረግ ኅሰሳ።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ህይወት በመኖር ሃቲት የሚገለጽ መሆኑን ለመናገር የድመጸቶች ውበትና መልክ ምስክር ነው። እንደ ታላቁ ገጣሚ ሮበርት ፍሮስት (Robert Frost)  የህይወትን በይቀጥላል ውስጥ እንደመረዳት ያለ ቀለም አላቸው። በእሱ አባባልም የማያልቀውን ህይወት በማያልቅ ህብር ልዝጋ።

“In three words I can sum up everything I’ve learned about life: It goes on.”

እስኪ የትንፋሽ ውበትን ሰምታችሁ ፍረዱኝ…

ተያያዥ ልጥፎች

2 thoughts on “ተናዳፊ ትንፋሾች”
  1. ይህ አቀራረብ በተጣም የተሻለ ነው፡፡ በቴሌግራም በፒዲኤፍ የሚቀርበው ልክ እንደህትመት እንዲያው በበለጠ በቀለማት ያሸበረቀ በመሆኑ ለማንበብ አስጀጋሪ አድርጎት ነበር፡፡ ይኸኛው እንደ መፀሐፍ አንዳንድ ገላጭ ስዕላት ቢኖሩትም ለማንበብ ቀላል ሆኗል፡፡ እንደ ምርጫችንም የፈለግነውን ለመምረጥና ለማንበብ አመቺ ነው፡፡ በዚሁ ቀጥሉበት፡፡

    1. የባይራ ቤተሰብ ስለሆኑ እና ሃሳብዎን ስላጋሩን እናመሰግናለን።ባይራን ለአንባቢዎቻችን ምቹ ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ፤ ስለአብሮነትዎ እናመሰግናለን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *