ፍለጋ ና ዝናብ

ብርሃን ደርበው

A man walking in a rain alone. He is in the way of crossing the river.

ይዘንባል…
ይዘንባል…
ስማዩ ያነባል
በእግሮች እርግጫ
በሰማዩ ኩርኩም
አበቦች አልፈኩም

***

ይዘንባል… ይዘንባል…
ስማዩ ያነባል
በሰማይ ነጎድጓድ
ምድር እሪ-ኩም
ፍጥረታት አልረኩም

 ***

ዘነበ… ዘነበ…
በንፋስ ሽውታ እርቃን ተገለበ
ፊታችን፣ ገላችን፣ አፈሩ ረጠበ

 ***

ይዶፋል…ይዶፋል…
ገለባና ፍሬ አንድላይ ይረግፋል
በድፍርስ ጭቃውኃ ጎዳናው ያድፋል
በአፈር ጎደፈ አፈሩ ጎዳና
በጎርፍ ታጠበ
የርምጃ ትዝታ የእግሮቻችን ዳና

 ***

ደሞ ውሽንፍር
ደሞ ወጨፎ
ወደ ጎሬው ይራኮታል
ፍጥረት ግሳንግስ ሸክፎ

 ***

ያካፋል…ያካፋል…
ደመናው ይስፋፋል
ከጨለመ ሰማይ ከሰፋ ደመና
ጠጥሮ ወረደ ውኃ እንደመና
ወረደ…
ወረደ…
የሰፋ ደመና ፀሐይን ጋረደ
ነፈሰ…
ነፈሰ…
በሐኖሱ ሰማይ ውኃ እየነገሠ
ዛፍ ሁሉ ይንሿሿል
ውኃ ለበስ ፍጡር ውኃዉን ይሸሻል
ደሞ ጭጋግ
የዝናብ ሽል የውኃ ልጋግ
ከደመና ወረደ ጠል
ዛፍ ሊታደስ ጣለ ቅጠል


ደሞ አባራ
ፀሐይ ፈካች ምድር በራ
በግፍፍ ደመና በርጥብ ፀሐይ መካከል
ፍጥረት ሁሉ ይጨሳል
ደመና ሊሠራ ፀሐይ ሊከላከል
የፀሐዩን ምሥል
የብርሃን ነጸብራቅ
(የጀንበሩን ቁስል)
በምዕራብ በምሥራቅ
ከልሎት ደመና
ከልክሎት ደመና
ጥላውን ሲነጥቀው
ጥላ ይዘረጋል
በመብረቅ ብልጭታ
በዝናብ ክለላ
አምሳል ይሰንጋል

እኔ…

ለሰማዩ እንባ መሃረብ ይመስል
ሄዳለሁ… በዝናብ
ሄዳለሁ… በምናብ
ዛፉ ሲገነደስ
ፍጡር ሲተራመስ
ፍጥረቱ ሲታደስ
በተራራው መሐል ልፈልግ አንድ አገር
ጎርፍ እከተላለሁ ወንዙን ለመሻገር
እጓዛለሁ………

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *