ሩት ሃብተማርያም
ከመኝታዬ ተነስቼ ስንደረደር የሄድኩት ወደ ውሃ መቅጃው ጉድጓዱ ነበር። ደጅ ለመውጫዬ እና ገላዬን ለቅለቅ ለማለት የሚያስፈልገኝ ውሃ በቂውን ያህል የቤታችንን ግድግዳ ተደግፎ በቆመው ገበቴ ሞላሁ። በትንሽ የቅል መጥለቂያዬ ከገበቴው ቀድቼ ወደ ጓሮ ዞሬ ጉዳዬን ፈጻጽሜ ስመለስ ሳስብ የነበረው የጉድጓድ ውሃ ለምን ለብ እንደሚል ነው። ለምንድነው ግን? መሬት ቆፍረን ከማህጸኗ ስለምንጠልቅ ነው? ወይስ እኛ የማናውቀው እሳት አለ? ሲገርም።
በጠዋት የነቃሁ መስሎኝ ነበር። ግን ከብቶች ወጥተዋል። ሊረፍድ ነው እንዴ? አይ ሀዊ ሳትመጣ ቢያንስ ገላዬን ታጥቤ መጨረስ አለብኝ ብዬ እያሰብኩ ቅሏን እንደነገሩ ጣል አድርጌ የገበቴ ውሃዬን ይዤ ወደ ተከለለች ቦታዬ ሄድኩ። ትላንት የገዛሁትን ሳሙና የት እንዳረኩት ሳሰላስል አድራሻው ጠፋብኝ። ጉጉቴ ትውስታዬን ሁሉ ፈተነው። ብቻዬን እያጉተመተምኩ ሳጥኔን ስከፍት ሳሙናዬ አድራሻዬን ሲፈልግ እንደነበረ ሁሉ ከልብሶቼ አናት ላይ ጉብ ብሎ ተገናኘን። ልብሴን ይዤ ተመለስኩ።
ገላዬ ላይ የመጀመርያውን ውሃ ሳፈስ እንደነገሩ ጣል ያደረኩት የደጅ መውጫ ቅል በእናቴ ሲያሰድበኝ አንድ ሆነ። እቃ ፈልጋ ያለማግኘት አመሏን እያወቅኹ ማድረግ የሌለብኝን ነው የሰራሁት እያልኩ ገላዬን ከሳሙናው አዋድዳለሁ። በሀሳቤ ‘ቶሎ ቶሎ ልበል ሀዊ ትመጣለች እኮ’ እያልኩ ግን ደሞ ከጉድጓድ ከወጣው ለብ ያለ ውሃ ጋ አካሌን ቀስ እያልኩ እያስደነስኩ ሳይታወቀኝ ብዙ ቆየሁ።
ብትት ብዬ የነቃሁት ሀዊ ከእናቴ ጋ ሰላም ስትባባል ሰምቼ ነው። ቶሎ ቶሎ ውሃውን ገላዬ ላይ ደፋሁና ልብሴን ለበስኩት። ሻማ ቀሚሴ በእርጥበቴ ራሰ። ተንደርድሬ ወጣሁ። ገበቴውን ሳሙናዬን እና የቀየርኳቸውን ልብሶች እኔ እንዳላመጣኋቸው ሁሉ ትቻቸው ሮጥኩ። ሀዊ በማታየኝ በር ቤት ገብቼ ለጥምቀቴ ብዬ ያዘጋጀሁትን አበሻ ቀሚስ ለበስኩ። ቫዝሊን ፊቴን አበስ አደረኩ። ሹሩባዬም ቆንጆ ነው። ሀዊ ወዳለችበት ስገባ ሩጫው እንዳልሞከረኝ ሁሉ ምነው ዘገየሽ በሚል የኩራት ፊት ነበር።
እናቴ ያዳፈነችውን እሳት እየገለጠች በዓይኗ ቂጥ ነገረ ስራዬን ታያለች።
ዞር ትልና ሀዊን “ልጄ እሷን ተያት ዛሬ ከቀልቧም አይደለች። አንቺ ስሚኝና ቁርስ ብላችሁ አቦል ጠጥታችሁ ሂዱ ትደርሳላችሁ እኮ” ትላታለች።
” አይ እትዬ አስካለ ሌሎችም ልጆች ወንዙን ተሻግረው እየጠበቁን ነው። እንሂድ” ብላ መለሰች። ምልልሳቸው እኔ እንደሌለሁ የቆጠረ ነበር። ብዙም አልከፋኝም። እንሂድ ብቻ።
ዛሬ ከሌላው የተለየ ምን ኖሮ እንደጓጓሁ ባላውቅም በእናቴ አባባል ‹ ልቤ ጠፍቷል›፡፡ ሁሉንም ነገር በችኮላ እና በጉጉት ነበር የማደርገው፡፡ የጤና መሆኑ ያጠራጠራት እናቴ ብቻ ሳትሆን ሀዊም እንደሆነች ከአስተያየቷ ገብቶኛል፡፡ ምን ቸገረኝ! ነጠላዬን እያስተካከልኩ ቀደም ብያት እራመዳለሁ፡፡ በግማሽ ልብ አወራታለሁ፡፡ አሁን ለነገሩ እንዲህ ያቅበጠበጠሸ ምንድን ነው ብባል ማስረዳት አልችልም፡፡ ለወትሮው ቢሆን ጓደኛዬ ለምናኝ ፣ የእሷ ልመና አሳዝኗት እናቴ ገፍታኝ ነበር የምሄደው፡፡ ዘንድሮ ምን ልዩ ነገር ኖረው አላውቅም፡፡
እንደው ለነገሩ ውለታ ቢስ እና እፍረት የማያውቀኝ ሁኜ ነው እንጂ እንዲህ መሆኔ ጥምቀት መሄድ ከጀመርኩ ጀምሮ ነጠላዋን በነጠላዬ አያይዛ ጥምቀት የምትወሰወደኝ ጓደኛዬ ከሞተች ገና ሁለት ወሯ ነው፡፡ ለትንሽ ደቂቃ እፍረት ሸነቆጠኝ፡፡ ዓለም ትባላለች፡፡ ከእኛ ቤት ወንዝ ተሻግሮ ነው ቤቷ፡፡ ትምህርት ቤት ነው የማውቃት፡፡ ጠይም ፣ ረዥም ፣ በመሰልከክ እና በመደፍጠጥ ( ያስቃል ቃሌ) መሃል ያለች ቆንጆ ፣ ባለ ሹሩባ ደስ የምትል ልጅ ነበረች፡፡ ታመመችና ሞተች፡፡ ዘመድ ነው በመድሀኒት የገደላት ይላሉ አላውቅም እኔ ምክንያቱን ብቻ ሞተች፡፡ ትንሽ ሰው ይሞታል ብዬ ስለማላስብ መሞቷ በጣም አስደግጦኝ ነበር፡፡ ለራሴ ፈርቼ ነበር፡፡
ከትምህርት ቤት ስንመጣ የማናወራው ነገር አልነበረም፡፡ ስለ ቤተሰቦቿ ስትነግረኝ ደስ ይላት ነበር፡፡ በተለይ ወሊሶ ስለሚኖር ወንድሟ፡፡ እንዴት ነበር የምትወደው፡፡ ስለሚያመጣለት ብእርና ደብተር ስለማሸጊያቸው ታወራኝ ነበር፡፡ ከተማ የገባ የቅርብ ዘመድ የለኝምና እያንዳንዱን ጉዳይ በትኩረት እከታተላት ነበር፡፡ አንድ ቀን ስናወራ ወንድምሽን አልወደውም አልኳት፡፡ ቀልቧ ተገፈፈ፡፡ ድንጋጤዋን አይቼ አይ አይ እሱን አይደለም ያኛውን ነው .. አክስታችሁ ጋር ስመጣ መንገዱ እያለለት የኛን አጥር ዘሎ የሚያልፈውን ነው፡፡ ደሞ ጥቁረቱ ሲያስፈራ፡፡ እንዳንቺ ቆንጆ አይደለም አልኳት፡፡ እናቴ እንዲህ ማለቴን ብትሰማ ትገለኝ ነበር፡፡ ግን ለጓደኛዬ ነው ያወራሁት፡፡ምስጢሬ የተጠበቀ ነው፡፡እና ሞተች፡፡ ብቻ ሞተች፡፡ አዘንኩ፡፡ ወይ ያዘንኩ መሰለኝ፡፡ ሁለት ወር ሳይሞላት ነጠላዬን እየነሰነስኩ እሷ ወደ መራችኝ ጥምቀት እየተራመድኩ ነው፡፡እናቴ ያመረረ ሀዘንተኛ ስታይ ‹‹ Namni du’e waliin awwaalame hin jiru>> ከሞተው ጋር የተቀበረ የለም የምትለው አስታውሼ ትከሻዬን ነቅንቄ ዝቅ ብዬ ጫማዬን አይቼ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡
በሀሳብ ስወዘወዝ ሀዊን እንደረሳኋት ትዝ ያለኝ ትከሻዬን ስትነቀንቀኝ ነው፡፡
‹‹ዛሬ ምን ሆነሻል ልጅቷ?›› አለች ሀዊ ከዓይኖቼ የሆንኩት ታገኝ ይመስል ትኩር አድርጋ እያየችኝ፡፡
ምን ሆንኩ?
‹‹የሆንሽዉንማ አንቺ ታውቂያለሽ፡፡›› ብላ ቁንጥር እያለች ቀደመችኝ፡፡ እነዛ ትንንሽ ከንፈሮቿ በኩርፊያ አሞጥሙጠው ሰው ለመሳም የተዘጋጀች አስመስሏታል፡፡ ወንዙን ልንሻገር ስናቆለቁል ሳስብ የነበረው ጊዜ ከሃይል ሁሉ ሀያል መሆኑን ነበር፡፡ ዛሬ ውስጡ ገብተን ፤ ኮረቱን ረግጠን የምንሻገረው ወንዝ ከወራት በፊት በማን አለብኝነት የሚደነፋ ፤ በሃይሉ የዘመድ ለቅሶ የሚቀሩለት፤ የደፈረውን ያስበረገገ ጀግና ነበር፡፡ ዛሬ ጭልጭል የሚልና ሀይሉን የሚመሰከርለት አንዳች ምስክር የሌለው ሆኗል፡፡ ጊዜ መጥቶ እስኪያረጋግጥለት፡፡
ዘቅዘቅ ስንል የቀጠርናቸው ልጆች ደርሰዋል፡፡ ቆንጆ ሆነዋል፡፡ ተሳሳምንና ፊታችንን ታቦት ወደ አረፈበት አዙረን መንገዳችንን ቀጠልን፡፡ ስለቀሚሳችን ፣ ስለ ሹሩባችን ፣ ስለ ኮንጎ ሁሉ እያወራን ፤ አንዴ ፈጠን አንዴ ዘግየት እያልን እልልታ ከደመቀበት ቦታ ደረስን፡፡ እስክስታው ፣ ሽብሸባው ተስማምቶ ሳይረባበሽ ይታያል፡፡ ያለመታከት ከአንዱ ወደ አንዱ እየሮጥን እስኪደክመን ድረስ ተወዘወዝን፡፡ በደስታ ፊታችን ወዝቶ ነበር፡፡ ታቦቱን ሸኝተን ወደ ቤት ለመመለስ ስንነሳ ግን በመምሸቱ ልቤ በድንጋጤ እየመታ ነበር፡፡ የእናቴን ፊት ገና በገና ማሰቡ ብቻ በድንጋጤ አደነዘዘኝ፡፡ ያስገባሁትን የማርያም ታቦት ለዛሬ ከዚህ ጉድ እንዲያወጣኝ እያልኩ ከሃዊ ፈጠን ብዬ መራመድ ከፈለኩበት ፍጥነት ግን እየዘገየሁ በሚመስል እርምጃ እፈጥናለሁ፡፡ ነይ እንጂ በሚል አስተያየት ጭፈራው ያደከማትን ሀዊን እገላምጣለሁ፡፡ ጥያት አልሮጥ ነገር ሆኖብኝ ትንሽ እንደመጠበቅ አደርጋለሁ፡፡ ቀሚሷ በአቧራ ተበላሽቷል፡፡
ከፊቴ የሆነ ነገር ውልብ ሲል ሳየው ውሻ መስሎኝ ነበር፡፡ የምናባርርበት ልምጭ ያለመያዛችንን እያሰብኩ እራመዳለሁ፡፡ ግን እንዳሰብኩት አይደለም፡፡ ውሻ ካለመሆኑም በላይ አንድ ብቻ አይደለም፡፡ ጥላው ግዙፍ የሆነው የቀደመ ይመስላል፡፡ ሌሎቹ ተከታይ፡፡ ከፊት ሲከቡኝ ሀዊ ጮኸች፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ የገባኝ እኔ ደንዝዤ አያለሁ፡፡ በደንብ አላውቃቸዉም፡፡ እነሱ ግን የተጠራጠሩ አይመስሉም፡፡ ለመሮጥ እግሬን ሳነሳ እና የቀደመው ጠንካራ እጅ ጨምድዶ ሲይዘኝ አንድ ሆነ፡፡ ለማስለቀቅ ታገልኩ፡፡ ያጠበቀኝ ሳይሆን ሌላኛው አጋዥ በያዘው ዱላ ባቴ ላይ መታኝ፡፡ ህመሙን ዋጥ አድርጌ መታገሌን ቀጠልኩ፡፡ በጣም ታገልኩ፡፡ ሀይል የለኝም፡፡ የቀኑ ፀሐይና ጭፈራ እንዲሁም ርሃቡ አቅሜን አሳንሶብኛል፡፡ ሀዊ ስትጮህ ይሰማኛል፡፡ ያጠበቀኝ ሲሸከመኝ ትከሻዉን ነከስኩት፡፡ በህመም አጓራ፡፡ ግን ተሸክሞኝ ሮጠ፡፡ ሮጠ፡፡ ሮጡ፡፡ እያለቀስኩ ነው፡፡ ራቅን ከተነሳንበት፡፡
ያሰቡት ቦታ ላመጡለት ሰው ሲያስረክቡኝ ዓይኑ መሃል እያየሁት ፤ የራሴ ድምጽ ለራሴ እያቃጨለብኝ ነበር፡፡
‹ ወንድምሽን አልወደውም፡፡