ውብአረገ አድምጥ

ከሳምንታት በፊት አስቻለው ፈጠነ (አርዲ) “አስቻለ” የሚል መጠሪያ ያለውን የመጀመሪያ አልበሙን ለአድማጭ እንካችሁ ብሏል። ሙዚቃው በአድማጭ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል። በተለይ “እንገር ወሎ” የሚለውና ስለወሎ ታሪካዊና ማህበራዊ ውቅር ብሎም ውበት የሚያትተው ዘፈኑ ብዙዎችን ማስደነቁን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚንሸራሸሩ ጽሑፎች ምስክር ናቸው።
ከዜማና ከቅንብሩ ባለፈ የግጥሙ ሃሳብና ጥራት ለሙዚቃዊ እሴቱ ትልቅ ዋጋ ሰጥቶታል። በተለይ በዘመናችን የግጥም ነገር ችላ እየተባለ ነው የሚል ወቀሳ ይበዛ ነበር። ወቀሳው እውነትም አለው። ይሄ ሙዚቃ ግን እንደ አንድ አብዮት የሚታይ ነው ማለት ይቻላል።
ይሄን “እንገር ወሎ” በሚል ርዕስ በ 6:34 ደቂቃ የተቀነበበውን ዘፈን ግጥሙን ብቻ ለአፍታ ለመዳሰስ ተሞክሯል። ይሄ አተያይም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የግል ምልከታ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ አሳስባለሁ። አብረን እንዝለቅ።
እንገር ወሎ

ድምጻዊ- አስቻለው ፈጠነ (አርዲ)
ዜማ- አስቻለው ፈጠነ (አርዲ)
ሙዚቃ ቅንብር ሚክስ እና ማስተር- ቢንአንዴ (ዜማ አዘዝ)
ግጥም- ኃይለኢየሱስ ደርብ (Hader)፥ አስቻለው ፈጠነ (አርዲ) እና ለመምቴ ሞገዱ
===================================================================
ከመቃብር በላይ፥ ስም ይቀራል ብሎ
ፍቅርና ጀግንነት፥ ያውቅበታል ወሎ
የቀድሞው “ቤተ አምሐራና አንጎት[1]” የአሁኑ ወሎ የባህል፥ የታሪክ፥ የቋንቋ እንዲሁም የማህበራዊ ክዋኔዎች ሁሉ ማሰሮ (Melting pot) ነው ይሉታል። አማራው፣ ትግሬው፣ አፋሩ፣ ኦሮሞው፣ አርጎባው እንዲሁም ሌሎች ህዝቦች ተገምደው የፈጠሩት ልዩ ማንነት ነው። የእስልምና፣ የክርስትና እንዲሁም የዋቂ ፈናው ሽምን ውጤት ነው።
ታዲያ ወሎ ብዝሃነትን የሚያውቅ፣ ስለፍቅርና ስለጀግንነትም ለምስክር የሚጠሩት ህዝብ ነው። ሙዚቀኛው አስቻለው፡ ወሎ ይሄን ፍቅርንና ጀግንነትን አሳምሮ የሚያውቅበት ገፊ ምክንያት “ሰው ቢያልፍም ስም ከመቃብር በላይ ቀሪ ነው ብሎ ስለሚያምን ነው” ይለናል። አባቶቻችንስ ሲተርቱ “ከስብ ስም ይሸታል” አይደል የሚሉት? ወሎም ሰው አላፊ ጠፊ፣ ህይወት ጊዜያዊ፣ ስምና ማንነት ግን ህያው ነው ብሎ የሚያምን አበ ፍቅር ወ ጀግንነት ነው ይለናል።
ወሎ ልቡ ሰፊ፥ መተኛ ድንኳን
አበጋር ይፈራል፥ እንኳን አምላኩን
ልብ የሚለው ቃል “ለበወ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ነው። ለበወ ማለትም ልብ አደረገ፣ አስተዋለ ማለት ነው ይላሉ ሊቃውንቶቻችን።[2]
የወሎ ልብም እንኳን ለማረፊያነት ይቅርና ለመተኛነትም የሚያገለግል እንደ ድንኳን የሰፋ ነው ይለዋል። ለዚህ የልብ ስፋቱ አስረጂ ብዙም መሄድ አይጠበቅብንም፤ እንኳን አምላክን ይቅርና አበጋርንም ይፈራል ይለናል። ለመሆኑ አበጋር ምንድን ነው?
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ በ2006 ዓመተ ምህረት ለ”ፋክት” መጽሔት ካዘጋጀው ቃለመጠይቅ እንዲህ የሚል ጽሑፍ እናገኛለን።
“እንባ የሚደርቀው በፍርድ ሳይሆን በፍቅር ነው” ይላል ቃለ መጠይቁ የተደረገለት በአምባሰል ወረዳ ውስጥ በምትገኝ ጎጥ አበጋር የነበረው አበጋር ይማም እርጋታው።
አበጋር ምን ማለት ነው? የሚል ጥያቄ የቀረበለት አበጋር ይማም እንዲህ ነበር የመለሰው።
“ሽማግሌ ነዋ። የተጣላ ያስታርቃል። ክፉ እንዳይሰራ ተው ይላል። ጅል ነገሩን ዱዓ አድርጎ ያባርራል። እንቅፋት የተባለን ሁላ ያስገልላል። ሰውን አብሮ እንዲበላና እንዲጠጣ ያደርጋል። ይሄ ነው አበጋር ማለት። ያገር ራስ አይነታ ማለት ነው። መሪ ማለት ነው አስታራቂ።”[3]
ከላይ እንዳየነው አበጋር ማለት በሰው ልጆች ዘንድ ሰላማዊ ኑሮ ይሰፍን ዘንድ ከዘሩ በተቀበለው፣ በስብዕናው ባስመሰከረው እውነት ላይ ተመስርቶ ሃይማኖት፥ ባህል ሳይገድበው ለሰው ልጆች ሁሉ የሚኖር ልባም ነው። ከፍርድ ይልቅ ፍትሕንና ፍቅርን የሚያሰፍን ነው። ለዚህ ነው ድምጻዊ አስቻለው አበጋርን ይፈራል እንኳን አምላኩን እያለ የሚመሰክርለት።
የራስ አሊ ሀገር፥ የሴሩ ጓንጉል
ይሾማል ይቀባል፥ አቡን ይመስል
በአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሀገራችንን መልክ የቀየሩ ሁለት አበይት ክስተቶች እንደነበሩ ታሪክ ያስረዳል። እነሱም የግራኝ አህመድ ወረራና የኦሮሞ ህዝብ መስፋፋት ናቸው። በዚህ ምክንያት የቀድሞዋ ቤተ አምሐራ ወደ ወሎ ተቀይራ ቀደምት ኃያልነቷ ተቀዛቅዞ ነበር። ነገር ግን በቀደምት የታሪክ ማዕከልነቷና፥ በዘመነ መሳፍንት ገፊ ምክንያትነት በወሎ አዲስ ስርወ መንግስታት ተመሰረቱ። በዋናነትም የማመዶች ስርወ መንግስትና የወረሴሆች (የየጁዎች) ስርወ መንግስት ናቸው።[4]
አባ ሴሩ ጓንጉልም የየጁ ስርዎ መንግስት ሲመሰረት አካባቢውን ያስተዳድሩ ዘንድ በሽማግሌዎች እንደተመረጡ ታሪክ ይዘግባል።[5] ነገር ግን የየጁ ስርወ መንግስት ከፍተኛ ጉልበት ያገኘው በልጃቸው በአሊ ጓንጉል ነው። “ታላቁ ራስ አሊ” በመባልም ይታወቃሉ። በጠንካራ የጦር አደረጃጀታቸው ቀድመው ይጠራሉ።
አሊ ጓንጉል ብዙ ቦታዎችን ከግዛታቸው በማካተት የጁን ጠንካራ መሰረት ላይ ማቆም ችለዋል። በዘመነ መሳፍንት ከነበሩ አካባቢያዊ መንግስታት ጠንካራውና ተጽእኖ ፈጣሪው እሳቸው ነበሩ።
ብዙ ጦርነቶች ላይ ከመሳተፍ ባሻገር ማዕከላዊ መንግስት ላይ ተጽእኖ ማሳደር ችለዋል። ንጉሰ ነገስቱን አጼ ተክለ ጊዮርጊስን (1779-1784) ሳይቀር ከስልጣኑ በማውረድ አምባሰል ውስጥ በግዞት አኑረዋቸው ነበር። ሳልሳዊ ኢያሱንም ያነገሷቸው እሳቸው መሆናቸውን ታሪክ ዘግቧል።[6]
ወደ አስቻለው ስንመጣ ወሎዬው የጓንጉል ልጅ ራስ አሊ በጉልበታቸው ንጉስን መሻርና መሾም የሚያስችል ብቃት ነበራቸው። ይሄንን ያፈራችም የወሎ ምድር ናት። ስለዚህ የአቡኑን ግብር ሳይቀር መጋራት የቻሉ የሀገራችን ጀግኖች መፍለቂያ ወሎን ታሪኳን እየመዘዘ ይተርክልናል።
ሐሊማ ብላችሁ፥ እስኪ ስሟን ጥሩ
መነን አይደለም ወይ፥ የጁ ስልጣን ክብሩ
እቴጌ መነን በዘመነ መሳፍንት አድራጊ ፈጣሪ የሚያስብል ጉልበት ነበራቸው። እቴጌ መነን ከማመዶች ባላባት ከነበሩት ከሊበን አመዴ ተወለዱ። የመጀመሪያ ስማቸው ሐሊማ ነበር። ክርስትና ተነስተው መነን ተባሉ። ከመጀመሪያ ባላቸው ከየጁው አሉላ ጉግሳ፡ ራሲ አሊን ወለዱ። ትንሹ ራስ አሊን። ትንሹ ራስ አሊም በ13 ዓመታቸው ስልጣን ተረከቡ። ራስ ዓሊም ተዋበችን ወለዱ። እንግዲህ ተዋበች የመይሳው ካሳ (አጼ ቴዎድሮስ) ሚስት ናቸው። የዘመነ መሳፍንት ማክተሚያ የሆኑት “ካሳ ኃይሉ” እቴጌ መነንንና ራስ አሊን አሸንፈው የየጁዎችንና የማምውዶችን ዘመን እንዲያከትም አደረጉ። ራስ አሊን አይሻል ላይ እንደረታቸው ልብ ይሏል።[7]
ለዚህ ነው አስቻለው የቀድሞ ስማቸውን ሳይረሳ እስኪ ለየጁ ስልጣን “ክብር” የነበሩትን እኒያን ገናና እናት እቴጌ መነንን ሐሊማ እያላችሁ ጥሩልኝ የሚለው። ምንም ቢሆን የመይሳውን የልብ ንግስት ተዋበችን በእሳቸው በኩል አላገኘንምን? መይሳውስ ቢሆኑ ተዋበችን የመሰሉ የሴት ልክ ባያገኙ ከህልማቸው ይደርሱ ነበርን? ከተራ ሽፍታነት የተሻገረ ሚና ይኖራቸው ነበርን? ስለዚህም የዚህን ሁሉ ምንጭ ሐሊማን ጥሩልኝ ይላል የዘመናችን አንጎራጓሪ አስቻለው ፈጠነ።
አጀብ
እንዴት ነሽ እንዴት ነሽ፥ የምወድሻዋ
እንዴት ነሽ እንዴት ነሽ ፥ መገን አንገትዋ
እዚህ ላይ አንጀት በሚያባባ ዜማ እንዴት ነሽ እያለ ወደ አሁን የሚወረወር ቃል ይልካል። የምወድሽዋ ከቶ እንደምንድን ነሽ? እያለ ለዚህች የታሪክ ሙዳይ ይንገበገባል። መገን አንገትዋ እንደምን ነሽልኝ ይላል። ለምን አንገት ቢሉ ሚስጥሩ ቢረቅብን እንጂ አይርቅብንምና ነው።
አንገት እኮ ሃይማኖት ነው። አንገት እኮ አዙሮ ማየት የሚያስችል የልብ አካል ነው። አንገት እኮ የቃል መጽኛ የደስታም የመከፋትም ምልክት ነው። አንገት እኮ የድሪው፥ የጌጡ ማረፊያ የንቅሳቱ ማረፊያ ጸዳል ነው። አንገት እኮ የእስትንፋስ ማዕከል ነው። አንገት እኮ ሚስጥር ነው እያለን አይደለም ወይ?
የሀገር ዋርካ ልኩ፥ ሀገረ መንግስት
ጠቅልል ሰውነቱ፥ አማራ ሳይንት
ሰውነት የሚጠቀለልበት ጥላው ለሚያሳርፍ ሀገር ልኩ ወሎ አይደለም ወይ? ሰውነትን የሚጠቀልል፣ መተናነስን ሳይሆን እኩልነትን ባሪያና ገባርነትን፡ አለቃና ምንዝርነትን ሳይሆን የፍቅር ልጅነትን የሚሰብክ፡ ሰውነትን እንደ አርማ ከፍ የሚያስደርግ የሀገር ካስማ ወሎ ነው ይለናል።
አንድም የ”አባ ጠቅል” የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሰውነት አካል፥ የአካላቸው ክፋይ የእቴጌ መነን አስፋው እትብታቸው የተቀበረበትን የወሎዋ አምባሰልን እየጠቀሰልን ነው ብለን ብንደመም ማን ይከለክለናል? ማንም!
አንኮበር ወንዝ ላይ፥ አንዲት ፀሐይ ወጥታ
መቄት ታየች አሉ፥ ብልህ መሪ መርጣ
እናታቸው ከመቄት የምሚመዘዙት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ትልቅ ታሪክ ያላቸው ብልህ መሪ ናቸው። በሁሉም ዘንድ እንደ እናት የሚታዩት ምኒልክ “እምዬ” የሚል ስምም ወጥቶላቸዋል። በዓለም መድረክ ላይ ስላላቸው የዲፕሎማሲ ብቃትም እንደ ሬይመንድ ጆናስ (Raymond Jonas) ያሉ የታሪክ ባለሙያዎች brilliant strategist ሲሉ ያደንቋቸዋል።[8]
ነገረ ውልደታቸውንም ጳውሎስ ኞኞ እንዲህ ይተርክልናል።
“ምኒልክ በ1836 ዓ.ም ነሐሴ 12 ቀን ቅዳሜ ዕለት ተወለዱ። አባታቸው ኃይለ መለኮት ሣህለሥላሴ ሲሆኑ እናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አዲያሞ ይባላሉ።
የምኒልክ እናት ወይዘሮ እጅጋየሁ የንጉስ ሣህለሥላሴ ሚስት የወይዘሮ በዛብሽ ገረድና የልጆች ሞግዚት ነበሩ። እጅጋየሁ የግርድና ሥራ የጀመሩት በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤት አልነበረም። ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤት ከመቀጠራቸው በፊት የአንኮበር ቤተ ክርስቲያን አለቃ የነበሩት የመምህር ምላት ገረድ ነበሩ። በአለቃ ምላት ቤት ግርድና ተቀጥረው ሳለ አንድ ቀን ጧት ለጓደኞቻቸው “….ዛሬ ማታ በሕልሜ ከብልቴ ፀሐይ ስትወጣ አየሁ….” ብለው ተናገሩ። ሥራ ቤቶች የሰሙት ወሬ መዛመቱ አይቀርምና ወሬው ከጌትዮው ከአለቃ ምላት ዘንድ ደረሰ። አለቃ ምላትም “እንግዲያው ይህ ከሆነ ወደላይ ቤት ትሂድ” አሉ። የላይ ቤት የሚባለው የአንኮበሩ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት ከኮረብታ ላይ በመሆኑ አገሬው በተለምዶ “ላይ ቤት” ይለዋል።
እጅጋየሁ እንደተመከሩት ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤት ሔዴው ተቀጠሩ። የእጅጋየሁ የሕልም ወሬ ተዛምቶ ንጉስ ሣህለ ሥላሴም ቤት ገብቶ ስለነበረ የንጉስ ሣህለ ሥላሴ ባለቤት ወይዘሮ በዛብሽ ያ በሕልም የታየው ፀሐይ ከልጃቸው እንዲወለድ ፈለጉ። ወይዘሮ በዛብሽ ከልቻቸው ሁሉ አብልጠው ሰይፉ ሣህለ ሥላሴን ይወዱታል። ስለዚህ ሰይፉ ከእጅጋየሁ ልጅ እንዲወልድ ማታ እጅጋየሁን ወደሰይፉ መኝታ ቤት ልከው ያን ጐረምሳ እንድትጠብቅ አድረጉ።
የልጅ ሰይፉ አሽከሮች የእጅጋየሁን መላክ እንዳወቁ ለጌታቸው ለልጅ ሰይፉ ተናገሩ። ሰይፉ የሚወዳት ሌላ ሴት አለችው የአዲሲቱን የእጅጋየሁን መምጣት እንደሰማ ተናዶ እንዲያባራትም እናቱን ፈርቶ ከወንድሙ ከኃይለ መለኮት ዘንድ ሔዶ “እባክህ ሌላ ሴት ከፈልህ እሜቴ የላኳትን ያቺን ገረድ ውሰድልኝ” አለ። ኃይለመለኮትም እሺ ብሎ ከእጅጋየሁ ጋር ባደረጉት ግንኙነት ልጅ ተፀነሰ”።[9]
የአጼ ምኒልክ እናት ዘራቸው ከመቄት እንደሚመዘዝም አለቃ ለማ ኃይሉ በትዝታ መጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ።
«ያጤ ምኒልክ እናት አባት የላስታ የመቄት ተወላጅ ናቸው አድያሞ ይባላሉ፤ ደጃች አድያሞ።. . . ከዚያ ሸዋ መጣ። እዚህ ሎሌነት ገባ ለሣህለ ሥላሴ አያት። ሲኖር አድያሞ ለማ ከመንዝ ሴት ወልዷት ያጤ ምኒልክን እናት፤. . . እንግዲህ የምኒልክ እናት ባባቷ መቄት ናት።»[10]
በእርግጥ ሌሎች የታሪክ መዛግብት የወይዘሮ እጅጋየሁን ሀገር የተለያየ ቦታ ሲያደርጉት ይስተዋላል። ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው ወይዘሮዋ ከጉራጌ ሀገር የተማረኩ ባሪያ ናቸው የሚሉ እንዳሉ አስፍረዋል።[11] የሚሉ አሉ አሉ እንጂ በማስረጃ የተደገፈ ነገር የለም። በዚያው በአጼ ምኒልክ ዘመን ከተጻፉ የታሪክ ማስረጃዎች ውስጥ የአለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ የታሪክ መዝገብ ወይዘሮ እጅጋየሁን ጎጃም ውስጥ የጎዛምን ወረዳ ተወላጅ ያደርጋቸዋል።[12] ዞሮ ዞሮ ራሳቸው ጳውሎስ ኞኞ እንደሚሉት “ዋናው ቁም ነገር ታሪክ መስራት እንጂ ትውልድ አይደለምና”[13] ወይዘሮ እጅጋየሁ በአንኮበር ሰማይ ላይ ፀሐይ እንድትንጎገቦግ አድርገዋል።
ያቺ አንኮበር አናት ላይ በእጅጋየው አፈ ማህጸን በኩል የወጣች ፀሐይ ማረፊያዋ ከባዶ ላይ አልነበረም ይለናል አስቻለው። ከመሪም መሪ መርጣ ከብልሁ ላይ አረፈች እንጂ። ይሄው ከአገልጋይ ደጅ የተገኘች ፀሐይ ከሀገረ ኢትዮጵያ አልፋ ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ችቦ ሆነች። ለተገፉት መጽናናትን ይዛ ከተፍ አለች። የገረዲቷ የውድቅት ህልምም ተራ ቅዠት አልነበረም። ለሰው ልጆች እኩልነት የሚያበራውን እምዬን ይዞ ከተፍ አለ እንጂ ይለናል።
አገር ክተት ብለው፥ አዋጅ ሲማማሉ
ከቶ ከቶ አደረ፥ ጃማ ወረኢሉ
መጋቢት 5 ቀን 1887 ዓ/ም ንጉስ ምኒልክ አዋጅ አስነገሩ። ከአዋጁ መጨረሻ አካባቢም እንዲህ ይላል።
“ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።” አሉ እምዬ።[14]
የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነት ተመመ። መሰብሰቢያውንም የወሎዋ ታሪካዊ ቦታ ወረኢሉ እንድትሆን ተወሰነ። እንደሚታወቀው ለአድዋ ጦርነት መነሻ የሆነው የውጫሌ ውልም የመዋዋያ ቦታው ወሎ ውስጥ ነው። አድዋ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንና የዓለም ጭቁን ህዝቦች እጣ ፋንታ የተወሰነበት የዓለም ክስተት ነው። ለዚህ ሽርጉድ መሰብሰቢያ ዳስ ወሎ ናት። አቤት መመረጥ!
ታዲያ በወረኢሉ ጥቅምት 18 ቀን 1888 ከሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰበው ጦር ምክሩንና ስምሪቱን ጨርሶ ከወረኢሉ እስከወጣበት ቀን እስከ ህዳር 2 ድረስ እንግዳ ተቀባዩ የወሎ ህዝብ አብሮ ከመዝመት ባሻገር ምግብ በማሰናዳትና በማቅረብ ሀገራዊ ግዴታውን በክብር ተወጥቷል። የህዝቡ አጋርነትም በገሃድ ታይቷል። ወደ መቶ ሺህ የሚጠጋ ሰራዊት ከወረኢሉ እስከ አድዋ ድረስ በወሎ ውስጥ ሲያልፍ ደጀንነቱ አልተለየውም።[15] ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ ለሰንጋው፣ ለበጉ፣ ለጠጁ ልክና መጠን የሌለው ሲሉ የገለጽጹት ከህዳር 8 እስከ 14 በደሴ ለዘማቹ የተደረገውን ከፍተኛ መስተንግዶ ነበር።[16]
ለዚህ ነው የሀገርንና የሰው ልጅን ነጻነት ለማብሰር ቀደምት አባት እናቶቻችን ሲማማሉ የወሎ ምድር የታዘበቸው። በድል ሲመለሱም የቦረቀችው። ይሄን ታሪክ እቅፍ አድርጋ ለያዘች ወሎ ነው ድምጻዊው ከአንቺ ከተው አደሩ ፣ የረሳሁት እንዳይመስልሽ አበባዬ እያለ የሚያሞካሻት። አጃይብ ነው።
[1] አንጎት በጥንት ኢትዮጵያ ታሪክ ከላስታ በስተ መሥራቅ፥ ከትግራይ በስተ ደቡብ፥ ከሐይቅ እስጢፋኖስ በሥተ ምዕራብ የነበረ ግዛት ነው። (ኢትዮጵያዊው ሱራፊ፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሕይወት ታሪክና አስተዋጽኦ። በዲያቆን ዳንኤል ክብረት 2011 ዓ.ም ገጽ 345
[2] መጽሐፈ ግስ ወሰዋስው፥ መርኆ መጻሕፍት፥ እምኅበ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው፤ የቅኔና የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር። ገጽ 233
[3] ደቦ 60 ደራሲያን። ቅጽ 1 አርትኦት እንዳለጌታ ከበደ ገጽ 46-52
[4] ከቤተ አምሐራ እከ ወሎ መንግስት ሃይማኖት እና መስተጋብር። ምስጋናው ታደሰ ዶ/ር ገጽ 155_156።
[5] ዝኒ ከማሁ
[6] ዝኒ ከማሁ
[7] ዝኒ ከማሁ
[8] The Battle of Adwa by Raymond A. Jonas 2011.
[9] አጤ ምኒልክ በጳውሎስ ኞኞ
[10] መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ፣ መንግቱ ለማ እንደጻፈው፣ ገጽ 7-8
[11] አጤ ምኒልክ በጳውሎስ ኞኞ ገጽ 13
[12] የጎጃም ትውልድ ከአባይ እስከ አባይ፣አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ እንደጻፉት ግርማ ጌታኹን እንዳዘጋጀው።
[13] ዝኒ ከማሁ
[14] ዝኒ ከማሁ ገጽ 159
[15] ከቤተ አምሐራ እከ ወሎ መንግስት ሃይማኖት እና መስተጋብር። ምስጋናው ታደሰ ዶ/ር
[16] ገብረሥላሴ ወልደ አረጋይ ፣ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ገጽ 225።

ከልጅ እግሩ ሁሉ፥ የአባ ጤና ባሰ
ሌባ ሻዩን ሁሉ፥ ወርዶ እየመለሰ
“አባ ጤና” የልጅ ኢያሱ የፈረስ ስም ነው። የአድዋው መሪ፣ የአሁኗ ኢትዮጵያ ቅርጽ ሰሪ እምዬ ምኒልክ በጠና ሲታመሙ ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ/ም ልጅ እያሱን አልጋወራሽ አድርገው መሾማቸውን በአዋጅ አስነገሩ። ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደውንም እንደራሴ አድርገው ሾሟቸው። ምክንያቱም ልጅ ኢያሱ እድሜአቸው ትንሽ ነበርና ነው። ንጉስ ምኒልክ ወራሽ የሚሆን ወንድ ልጅ አልነበራቸውም። ልጅ እያሱ ከልጃቸው ከወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክና ከወሎው ንጉስ ሚካኤል ጥር 27 ቀን 1889 ዓ/ም ወሎ ውስጥ መወለዳቸው ይነገራል።[1]
ታዲያ ከሁለት ዓመት በኋላ ሚያዝያ 3 1903 ዓ/ም ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ድንገት አረፉ። ልጅ እያሱም በ14 ዓመታቸው ለብቻቸው ስልጣኑን ያዙት። እስከ ቀይ ባህር ድረስ ታሪካዊ ድንበራችንን ማስመለስ ፍላጎት እንዳላቸውና የዳር ሀገር ህዝቦችንም ለማቀፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸው ታሪካቸው ይናገራል። [2]
የመንግስቱን ስልጣን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠሩ በኋላ ከደነገጓቸው አምስት ህጎች ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ የተጠቀሰው የሌባ ሻይ ጉዳይ ነው።
ህጉም ቃል በቃል እንዲህ ተጠቅሷል።
“ሌባ ሻይ ሲጠጣ በአንዱ ቤት ገብቶ ቢተኛ ባለቤቱ የጠፋውን እቃ ከፍሎ እንደገና እሱው ዋና ሆኖ ሌባ ሻይ ያጠጣና ከሁለተኛው ሰው ቤት ሲተኛ የከፈለውን ያህል ተቀብሎ ሲሄድ፤ ደግሞ ይህ ሁለተኛ ያጠጣና ከሶስተኛው ይቀበል ነበር። በዚሁ አኳኋን እየተከታተለ ሌባ ሻይ እየጠጣ ህዝቡ ያልበላውን እዳ እየከፈለ ተቸግሮ እንግዳም እንዳይቀበል ሌባ ሻይ እፈራለሁ እያለ ከጽድቅ ተነሳስቶ ይኖር ነበር።
ስለዚህም እቃ ጠፋብኝ የሚል ሰው ሌባው እስኪያዝለት ድረስ በሰው ቤትም ቢተኛ በወንዝም ቢታጠብ፣ በራሱ ኪሳራ ሌባ ሻዩን እየጠጣ እደረሰበት ደርሶ ገንዘቡን ይፈልግ እንጂ የባለጸጋ ቤት እያየ ሌባ ሻይ እያሰተኛ ገንዘቡን መክፈሉ የማይገባ ሥርዓት ነውና ከዛሬ ጀምሮ እንዲቀር ወስኛለሁ ብለው አስታወቀ።” [3]ይላል።
በእርግጥ የልጅ እያሱ ዘመን ብዙም ያልተባለለት ነው። በብዛት መጥፎ ገጽታው ይነገራል። በሌላ በኩል ብዙ ለሀገር የሚበጁ ተግባሮች ነበሩት የሚሉም አሉ። ለጊዜው የተነሳንበት ጉዳያችን ስላልሆነ በዚሁ እንለፈው።
ከላይ ድምጻዊው አባጤና ኢያሱን ምን ልጅ ቢሆኑ እንኳን ያንን የሌባ ሻይ አጉል ስርዓት አስወግደዋልና የወሎ ማህጸን ያፈራቸውው እንደመሆኑ መጠን እንደ አምላክ መልካሙን ስራቸውን እያየ ያነሳሳቸዋል።
እንዴት ነሽ እንዴት ነሽ፣ የምወድሻዋ
እንዴት ነሽ እንዴት ነሽ ፡የእኔ ሰለውላዋ
አጀብ
መጣች ሰለውላዋ
አንቺሆዬው ለእኔ ብለሽ ከመጣሽ
በትዝታ አምባሰል ባቲን ቃኝተሽ።
ያቺን የወሎ ፍልቅልቅ የእኔ ሰለውላዋ እያለ ያሞጋግሳታል። ወሎ ታሪኳ ተነግሮ አያልቅም። የዘመናት ሂደቷን እንደ ታሪክ ነጋሪ አለፍ አለፍ እያለ የሚያወሳሳት ሰው የዜማ ምንጭ መሆኗንም አይቶ ሊያልፍ አልፈለገም። አራቱ ቅኝቶችን ከልቦናዋ ዲብ ያፈለቀች ውብ ደብር ናት ወሎ። ባቲና አምባሰል ብላ ደግሞ ከአፈሯ ላይ የቅኝቶቿን ስም ያተመች ሽቅርቅር እኮ ናት፣
ከንፈሯ ሲቀላ፥ እንደ ዶሮ ክንታት
ልክ እንደ ቆቅ አውራ፥ ሂጄ ልመግምጋት
ልክ የቅኝቷን ነገር እያሰበ ያ ህብር ውበቷ ከፊቱ ላይ ድቅን ይልበታል። የሚርበተበተው ውብ ከንፈሯ የዶሮ ክንታት መስሎ ሲቀላ በዓይነ ህሊናው ይሳላል። ሌላ ምንም አያስብም። ልቀኝ ቢል ቅኔ ከወሎ ወዲያ። ላዚም ቢል ዜማ ከወሎ ወዲያ። ነፍስያውን ተከትሎ እንደ ብልጡ የቆቅ አውራ ዘሎ መመግመግ ነው ያማረው። እዚህ ጋር ደረቅ ታሪክ እየነገርኋችሁ ሳይሆን ወሎን በሰው አምሳል ነው ያቀረብሁላችሁ ይለናል።
ከሰዋዊ ስሜቱና ከውበት ምርኮኛነቱ የተሰደደ ማንነት የለውማ ከያኒው። ከእነዚህ ስሜቶች ቢፋታማ ምኑም ከያኒ ሆነው? ምኑን እንስፍስፍ ልብ ታደለው? ምኑን ተመረጠው?
ባለረጅም ሲዋክ፥ ሱናዋን ያሟላች
ጡሐራ ሳዱላ፥ ተገማሽራ አለፈች
በዓይነ ህሊናችን ገምሻራ ልጃገረድ እንድንስል ያደርጋል። መስል ከሳችነቱ ከአንጀት ነው። ገላጭ (descriptive poetry) እንለው ዘንድ ያስገዳድል። ድርጊታዊም ነው። በእንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ ጥርሷን በረጅሙ እየፋቀች እምነቷ የሚያዛትን ቅዱስ ትዕዛዝ አሟልታ፣ በነፍስም በስጋም ውብ ሆና የምታልፍ ገምሻራ ወሎዬ ከች ትላለች።
የሼኾቹ ልጅ ናት፥ የራስ ሚካኤልዋ
እንደበተሐ ጠጅ፥ የተጣለችዋ
ወሎ የሼሆች ማጽጸን ናት ሲባል እንዲሁ ለወጉ አይደለም። እውነት አስገድዶን እንጂ። እንደ አምላክ የከበዱ ሼሆች መፍለቂያ። ስንቱን እናውሳው? የጀማ ንጉሱ መስጂድ መስራች ምሁሩ ሀጂ መሐመድ ሻፊ እንዴት ይረሳሉ? ከ500 መጻሕፍት በላይ በእጃቸው እንደጻፉ የሚነገርላቸው የገታ መስጂድ መስራች ሀጂ ቡሽራ የወሎ ምልክት አይደሉም ወይ? በወረባቦ ወረዳ የሚገኘውን የእስልምና ትምህርት ማዕከል እንደሆነ የሚነገርለትን የጎጃም መስጂድን መስራች፣ ጉልህ አሰላሳይ፣ አንባቢና ደራሲ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሼህ ጎጃም እንዴት ይዘነጋሉ? ሌላም ሌላም ብዙ።[4]
ታዲያ እንደ በተሐ ጠጅ የተጣለችዋ ውብ ልጃገረድ የሼሆቹ ብቻ ሳትሆን የራስ ሚካኤልም ልጅ ናት። ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስም “በተሐ ጠጅ እንደ ተሞላና ሊቀደድ እንደ ቀረበ አቁማዳ፥ ሊፈነዳ እንደማይችል እንደ ወይን ጠጅ አቁማዳ፥ እነሆ፥ አንጀቴ ሆነ”[5] እያለ የሚመሰክረው የለጋ ጠጅን ጣዕምና ጉልበት ቢገነዘብ አይደለምን?
ራስ ሜካኤል የመጀመሪያ ስማቸው መሐመድ አሊ ይባል ነበር።[6] አባታቸው የማመዶች ስርወ መንግስት የወረሒመኖ ባላባትና ገዢ አሊ አባ ቡላ ናቸው። ህጋዊ ሚስታቸውም ንግስት ወርቂት ናቸው። ከህጋዊ ሚስታቸውም አንድ ወንድ ልጅ እሱም አመዴ አሊን ብቻ ወለዱ። በቤታቸውም ከወደ ግንደበረት የመጣች ጌይቲ ገባቤ የምትባል አገልጋይ ነበረች።
አሊ አባ ቡላ ከሚስታቸው ተጨማሪ ልጅ ባለማግኘታቸው እሱን ችግር ለመቅረፍ የወዳጃ ስነ ስርዓት ተደረገ። ንግስት ወርቂቱም በወዳጃው እንግዶችን ከመንከባከብ ይልቅ ሲተኙ አገልጋይ ጌይቲ ሌሊቱን በሙሉ ቡና ስታቀራርብ ስትካድም አደረች።
በነጋም ጊዜ ወዳጃውን የመሩት ሼህ እንዲህ ብለው ጌይቲን መረቋት ይባላል።
ልጅንስ አየን ከገረድ
ስሙንም አልነው ማመድ
የነቢይን ዲን የሚንድ።[7]
አሊ አባ ቡላም ከአገልጋያቸው ከጌይቲ በድብቅ መሐመድ አሊን ወለዱ። የነቢይን ዲን የሚንድ ማለታቸው የንጉስ ሚካኤልን ከእስልምና ወደ ክርስትና መለወጥ በራዕያቸው አይተው ነው ይባላል።
ግንቦት 21 ቀን 1870 ዓ/ም ቦሩሜዳ ሥላሴ ንጉሰ ነገስት አጼ ዮሐንስ ጉባኤ ጠርተው የሃይማኖት ክርክር ተደርጎ ሌሎች ሃይማኖቶች በግድ የኦርቶዶክስ ክርስትናን እንዲቀበሉ አወጁ። ሰኔ 12 ቀን 1870 ኢማም መሐመድ አሊ ሃይማኖታቸውን ወደ ክርስትና ቀይረው በጎቦ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተጠመቁ። ስማቸውን ሚካኢል አሏቸው። አጼ ዮሐንስም የራስነት ማዕረግ ሰጧቸው። ቆይቶ በልጃቸው በልጅ እያሱ ዘመንም ንጉስ ሚካኤል “ንጉሰ ወሎ ወትግሬ” የሚል ማዕረግ ተሰጣቸው። በሸዋና በወሎ ሹማምንት መካከል በተፈጠረው ሽኩቻ ልጃቸውን ልጅ እያሱን ለማገዝ ጦርነት ገጥመው በእነ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (ሃብቴ አባ መላ) በሚመራው የሸዋ ጦር እስከተማረኩበት ድረስ ለወሎም ሆነ ለሀገራችን ብዙ ስራ ሰርተዋል።
ይሄንን ውለታቸውን እያነሳሳ ነው ከሼሆች እኩል ለዚያች ውብ እንስት አባት አድርጎ የሚሰጣት። ይህቺ በውብ ቀዘባ እንስት የምትጠቀሰው የሰው ልክ ራሷ ወሎ አይደለችምን እንድንል ያደርጋል።
ሀገር ሙሉ ሳቋን፥ አቃምሳው ሸጋዋ
እሷ ጋር ያወራ፥ ሐቲማ ነው ፍቅሯ
አደስ ተቀባብታ፥ የእኔ ሰለውላዋ
የተነደፈ ጥጥ፥ እንገር ነው ገላዋ
መገን አንገትዋ፥ የምወድሽዋ
አርሒቡ በይኛ፥ የእኔ ሰለውላዋ
ያቺ እንክብክብ የወሎ ሸጋ ስትስቅ የተመለከተ በፍቅሯ ይወድቅ ዘንድ ግድ አለበት ይላል አንጎራጓሪው። የወሎ ሸንተረር ባበቀለው አደስ የሚዘናፈል ገላዋን ነክራ ሰለውለው ስትል ለሚመለከት የውበት ምርኮኛ፤ “አርሒቡ” ብላ ከፍቅር ጎጆዋ ትጋብዘው ዘንድ አለመመኘት እንደምን ይቻላል? ሰው መሆንና መኖርስ ከዚህ ወዲያ ምንድን ነው? የወሎን ምድር ረግጦስ ከዚህ የውበት ምትሃት ማምለጥ ቀላል ነው ወይ የሚል ድምጸት አለው።
እንገር ወሎ እንገር ወሎ
አርሂቡ መጋሎ
ላይቆርጥልኝ መመለሴ (2)
ባቲና ከሚሴ
ይህቺን የውበትና ሰው የመሆን ድርሳንም እንገር እያለ ይጠራታል። ገጸ ውበቷን ከተነደፈ ጥጥ ጋር አወዳድሮ በእንገር ይመስላታል። ለምን የተነደፈ ጥጥ ቢሉ ኑንጉሩ ተነቅሶ ልስላሴው እንደ ደመና ገላ ነውና እንላለን። እንገር በነጭና በቢጫ መንፈስ ላይ የሚመላለስ ክቡድ የተፈጥሮ መልክ ነው። እንገር ህይወት ነው። እንገር የመጀመሪያ ቅምሻ ነው። እንገር መንገድ ከፋች ነው። እንገር ጣዕሙ ከወተቶች ሁሉ ቁንጮ ነው። አንድም እንገር “የመሆን” መጀመሪያ ነው። የሀገር፥ ሰው የመሆን፥ የአንድነት፥ የቤቴ አምሐራ እሸት፣ የወሎዬነት ውበት ነው።
ይህቺን ቀዘባ የሰው ቁመና ሰጥቶ በእንገር ቢመስላት ቃልን አከበረ እንጂ ገደፈ አንለውም። የነፍስያውን ምህዋር ተከትሎ ከእንገር ቢደርስ እልል እንላለን። ድምጻዊው በዚህ አያቆምም ባቲና ከሚሴን እያሰበ መመለሱ ሊቆርጥለት አይችልም። ወሎ የገባ ወደ ነፍስ ቡጥ ደረሰ ማለት አንችልምን? ከከፍታ አጽናፍ ላይ ቂብ አለ ብንልስ የከያኒው ግጥም አይፈቅድልንም ወይ? ታዲያ ከዚህ መመለስ እንደምን ይቻላል?
እህህ የቦርከናን፥ ውሃ ወልይ የመረቀው
እህህ አንቺን አንቺን አለኝ፥ ቀድቼ ብጠጣው
ከወሎ ኩታበር ማህጸን የሚፈልቀው ቦረከና ደሴና ኮምቦልቻን እየገረመመ ወደ ወንድሙ አዋሽ የሚተምም ወንዝ ነው። እንኳን አንቺን ይቅርና ቦርከናን ብቀምሰው ጣዕሙ አንቺን አንቺን አለኝ ይላል። ከወንዙ ጋር አንድና አቻ ናችሁ እያላት ነው። ድሮስ የወሎ ሊቅ የወሎ ወልይ የመረቀው ውኃ ጣዕሙ ከአንቺ ቢተካከል ትፈርጂብኛለሽ ወይ? እያለ የሚሞግትም ይመስላል።
ፈረንጅ ገባ ደሴ፥ ቁንጂናሽን አይቶ
ላብሽን አንቆርቁሮ፥ ሊያሰራው ነው ሽቶ
እዚህ ላይ ገጣሚው እንዲህ መቀኘቱ ውበትን ለማጉላት ብቻ አስቦ አይመስልም። ይልቅስ ታሪካዊ ዳራ ስላለው እንጂ። እንደሚታወቀው በሀገራችን በ19ኛው ሁለተኛ አጋማሽ ከተመሰረቱ ጥቂት ከተሞች ውስጥ አዲስ አበባን ጨምሮ አንደኛዋ ደሴ ናት። ስለምስረታዋ የተለያዩ መላ ምቶች ቢኖሩም በ1875 በንጉስ ሚካኤል ተመሰረተች የሚለው ሚዛን ይደፋል።[8]
ደሴ ከተመሰረተች በኋላ የአካባቢው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቅሜታ በፍጥነት አደገ። አጼ ምኒልክን ጨምሮ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ጎቢኚዎች ደሴን እየተመላለሱ ጎብኝተዋታል። አንዳንድ በዓላትንም በደሴ ማክበር እየተለመደ መጣ።
ቀስ በቀስ በርካታ ቤቶችና አብያተ ክርስቲያናት መገንባት ጀመሩ።ከአርመን ከግሪክና ከተለያዩ የአረብ ሀገራት የመጡ የዘመናዊ ህንጻ ባለሙያዎች የንጉሱ ሚካኤልን ቤተመንግስትና ሌሎችንም ግንባታዎችን መስራት ጀመሩ።[9]
ከአዲስ አበባ አስመራ በተዘረጋው የመጀመሪያው የስልክ መስመር ከሰባቱ ጣቢያዎች ውስጥ አንደኛዋ ደሴ ነበረች።[10] በ1905 የመጀመሪያው የውሃ ቧንቧ በደሴ ተዘረጋ።[11]
ለዚህ ነው በላብ የተገነባ ውበትሽን ሲያይ ፈረንጅ ወደ አንቺ መትመም ጀመረ የሚለው። ከውበትሽ ላይ የሚፈሰውን ወዝም እየጨለፈ እኒያን የሚያማምሩ ግንባታዎችን መስራቱን ተያያዘው ይለናል። ውበት ከገጽ ቅብ ባሻገር በትጋትም እኮ ይገለጻል። በጥረት ውስጥ በሚንቆረቆር ላብ የውበት መዓት አለ ብንል ማን ቃልን ገደፋችሁ ይለናል?
ኮለምላማ (4)
የራያ ከራማ
አይጠየፍ ሆኖ፥ ይታያል አንገትሽ
ለዳናው ተስዬ፥ እጅሽን ልሳምሽ
አሸዋና ድንጋይ ከቦርከናና ከገራዶ ወንዞች፥ ኖራ ደግሞ ከአምባሰል እየተጋዘ የተሰራ ውብ አዳራሻ። በ2131 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የአምባ ላይ ውበት። 45 ሜትር በ27 ሜትር ስፋት እንዳለውና አንድ አንድ ሜትር ውፍረት ባላቸው ሰባ ምሰሶዎች እንደተዋቀረ ይነገራል። በ1905 ተጀምሮ በ1907 ዓመተምህረት ተጠናቀቀ። የውጭም ዜጎች በግንባታው ላይ ተሳትፈዋል። ታላቁ የንጉስ ሚካኤል አዳራሽም “አይጠየፍ” የሚል ስም ተሰጠው። አይጠየፍ ማለት ዘር፣ ብሄር፣ ቀለም ሳይለይና የመደብ ልዩነት ሳይደረግ ጌታ ከአሽከሩ፥ እመቤት ከአገልጋይዋ፥ ጋር በአንድነት የሚስተናገዱበት አዳራሽ ማለት ነው።[12]
ለዚያ ነው ከፍታና ዝቅታ ሳይገድበን፥ ከዳና መስጅድ ተስዬ እጅሽን ልሳምሽ፤ አንገትሽን፣ የሰውነት የሃይማኖት፣ የማንነት መልክሽን ከአይጠየፍ ሆኖ አይቼዋለሁና ይላታል። ሰውን በሰውነቱ ብቻ ከሚመለከተው የአይጠየፍ አዳራሽ የሰው ልክ አንገታም አለች እያለን ነው።
ጡቷ የራያ ቀንድ፥ ዓይኗ ኮለምላማ
በሌላ አይምጡ፥ እንጂ በይህ በይህማ
ሌላኛ ነው መልኳ፥ ጤነኛ ሚሰብር
የምሬን ወድጃት፥ ሐዋን እስከ እጇ አምባር
ሳልደርስ አላማጣ፥ ሳልረግጠው ደጅሽን
ከወንዙ ጠጥቼ ፥አወቅሁት ጣዕምሽን
መገን ራያዋ(2)
የወሎን ገመገም በሃሳብ ፈረስ ከሰገረበት በኋላ ወደ ራያ ይምዘገዘጋል። ቀንዳቸው ተጀንኖ ያቆበቆቡ የራያ በሬዎችን ምስል በንቁ አእምሮው ያመላልሰዋል። እንደ ክዋክብት የሚያበሩ ዓይኖቿንና የተወደሩ ጡቶቿን በሃሳቡ እያመነዠከ የእሷስ ውበት ሌላ ነው ማለት ያምረዋል። ከዚህ በፊት በሚያውቀው የውበት ቀመር ሊፈታው አልቻለምና። የሐዋ ውበት እንኳን በሽተኛውን ይቅርና ጤነኛውን ሳይቀር እንደ ጓያ ይሰባብራል ይላል። መሰበርን በፍቅር ስንመለከተው እንደምን ያምራል? የራያ ሜዳዎችን እየተነሰነስሁባቸው አላማጣ ካለው ደጅሽ ሳልደርስ ጠረንና ውበትሽን ይዞት ከተሰደደው ወዝሽ ቀምሼ አዎቅሁት እያለ ምስክርነቱን ይሰጣታል። መገን የቆቦ ሰው!
አይይ
አውጉሪሩ(4)
ህምረን አውጉሪሩ
የከያኒው መጻተኛ የውበት ነፍስ በራያ በኩል ወደ ዋግኸምራ ትሻገራለች። መቼስ የወሎ ልብ ሰፊ ነው። የገላዋ ስፋቱም በገመገሙ የተዘረጋ ነው። ከደሴ አላማጣ አልፎ ወደ ዋግ ሲጠጋ ህምረን አውጉሪሩ ማለት ይጀምራል። አንቺ የአገው ኮረዳ ደህና ነሽ ወይ ከቶ? እያለ እንደማትከለክለው እያወቀ ስሟን ያነሳሳል። እንዲህ ነው በውበት የሚጎተት ሰጋሪ መንፈስ አካሄዱ። አንሳውማ አስቻለው!
[1] አባ ጤና ኢያሱ፣ ከጎበዜ ጣፈጠ 2008 ዓ/ም ገጽ 55
[2] አባ ጤና ኢያሱ፣ ከጎበዜ ጣፈጠ 2008 ዓ/ም
[3] ዝኒ ከማሁ ገጽ 77
[4] ከቤተ አምሐራ እከ ወሎ፤ መንግስት ሃይማኖት እና መስተጋብር። ምስጋናው ታደሰ ዶ/ር።
[5] መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 32 በቁጥር 19
[6] ሚካኤል ንጉሰ ወሎ ወትግሬ። ምስጋናው ታደሰ ዶ/ር ገጽ 19
[7] ዝኒ ከማሁ
[8] ከቤተ አምሐራ እከ ወሎ፤ መንግስት ሃይማኖት እና መስተጋብር። ምስጋናው ታደሰ ዶ/ር። ገጽ130
[9] ዝኒ ከማሁ ገጽ 136
[10] ዝኒ ከማሁ ገጽ 146.
[11] ዝኒ ከምሁ ገጽ 150
[12] ዝኒ ከማሁ ገጽ 153

ሐገርን በፍቅር፥ እንዲህ ሲገልጸው
በጦቢያ ታረቁ፥ ጓንጉልና አፄው
እዚህ ላይ ከያኒው ቆም ይልና ከታሪክ ሰበዝ ህያው እውነት መምዘዝ ይጀምራል። እነዚህ ስንኞች ሀገር የሚለውን የወል ስም ለማንጠሪያነት ይጠቅማሉ። ለየትኛውም ሀገር የትርክትን ክቡርነት ማንጸር የስልጣኔ ከፍታ መሆኑን ያበስራሉ። ጓንጉል በዘመኑ ኃያል ነበር። በአመዛኙ ማዕከላዊ መንግስት ደግሞ በጎንደር በከተማው ሳይቀር ጉልበት የቸገረው ተልካሻ ነበር። ከትግሬ፣ ከጎጃም፣ ከሸዋ፣ እንዲሁም ከጎንደር መሳፍንት በተሻለ ወሎዬዎች በዋናነት የጁዎች ወታደራዊ ሃቅም ነበራቸው። የማይመቻቸውን ንጉስ አንስተው የሚመቻቸውን መሾም የሚያስችል ጉልበት ነበራቸው። እሱንም በተደጋጋሚ አድርገው አሳይተዋል።
በሃይማኖት የተለዩ ቢሆኑም እንኳ ከሰለሞን ይመዘዛል የሚለውን የዘመናት ትርክት ለመናድ አልፈለጉም። ከሁሉም ነገር ይቅል ሀገር እንደምትቀድም ገብቷቸዋል። ሀገር ደግሞ ያለ ትርክት በእግሮቿ ለመቆም እንደማትችልም ተረድተዋል። ለዚያም ነው ህዝብን የሚያስማማውን የሰለሞን ዘር ትርክት እያስቀጠሉ በአንድ ሀገር ልጅነት መኖርን የመረጡት።
ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ሰው መሆን አለ? ከዚህ በላይ ሀገርን ማስቀደም ከየት ይመጣል? ዛሬ የጠፋብንን ሀገራዊ አረዳድ ከእነሱ እንማር ዘንድ አይደለም ወይ ከያኒው ለሀገር ሲሉ ግን ታረ’ቁ የሚለን?
ለሀገር ሲባል ጉልበትና ስልጣን መረን አይለቅም። ለሀገር ሲባል ስርዓትና ትርክት አይደመሰስም። ለሀገር ፍቅር ሲባል የግል ዝናና ሃብት ልኩን አያልፍም።
ዋግም ሹም አይጣ፥ የመክሊቱ ሞገስ
ዳና ኸሚስ ታድሮ፥ ሮሐ ይቀደስ
ዋግ ሹም የማዕረግ ስም ነው። በዋናነት ለአገው ተወላጆች ማለትም ለዋግና ለላስታ የመሳፍንት ዝርያዎች ብቻ ይሰጠ የነበረ ማዕረግ ነው። አንዳንዴ ግን በማዕከላዊ መንግስት ጫና የዋግና የላስታ ተወላጅ ላልሆኑትም ይሰጥ ነበር። የትግራዩን ዋግሹ ሰባጋዲስን፣ የሸዋውን ዋግሹም አባተ ቧ ያለውን እንዲሁም የወሎውን ዋግሹም ገብረህይወትን መጥቀስ ይቻላል። እኒህ ከላስታና ከዋግ ውጪ ለሆኑት የሚሰጠውን ማዕረግ ግን ህዝቡ አይቀበለውም ነበር።[1]
በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ከሆነ ዋግሹምነት የተጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው ይባላል። የዳዊት ልጅ፥ የይትረሃም ልጅ አዲል የተባለው የአገዎችች መሪ አገው የሚል ስያሚ ካገኘ በኋላ ነው የሚሉ አሉ።[2]
በሌላ በኩል በ14ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጅር ወሰን በሚባለው የዋግ ተወላጅ ባላባት ዋግሹምነት እንደተጀመረ ይገልጻሉ። የሆነው ሆኖ ዋግሹምነት ከተጀመረበት አንስቶ ከ45 በላይ ቁጥር ያላቸው መሳፍንት በዋግሹነት ማዕረግ እንደተሾሙ ይነገራል።[3]
ለአብነት ያህልም ዋግሹ ጅር ወሰን ፣ ዋግሹም ርቱዕ አምላክ፣ ዋግሹም ጊጋር፣ ዋግሹም ጓንጉል ብሩ፣ ዋግሹም ጎበዜ፣ ዋግሹም ከበደ ተፈሪ እያልን መዘርዘር እንችላለን።[4]
ዛሬ የወሎ አካል የሆነው ዋግኸምራም የዋግነቱን መክሊት ሳያጣ በሞገሱ ይቀጥል እያለን ነው። የሁለቱን የወሎ ክፍሎች አንድነት ለማሳየትም በዳና መስጂድ ታድሮ በሮሐ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ይቀደስ ይላል።
ዳና መስጂድ በሰሜኑ የወሎ ክፍል በሐብሩ አካባቢ ይገኛል። መስራቹም ስመ ጥሩ የእስልምና አስተምህሮ ሊቅ ሼህ አህመድ አደም ናቸው። ምዕመኑን ለሼሁ ያለውን ፍቅር ሲገልጽ “ጌታው ሼህዬ” ይላቸዋል። ሼህ አህመድም በወሎ ከነበሩ ስመጥር ኡላማዎች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ የእስልምና አስተምህሮን ለማስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ይህ የሱፊ እስልምና የትምህርት ማዕከል የሆነው ዳና መስጂድ እንደ ሼህ ዒሳ ሃምዛ፣ የአብሬቱ ሼህ ቡሽራ፥ የወለኔው ሼህ ዑመርና ሌሎችንም ሊቃውንት አፍልቋል።[5]
በሌላ በኩል ሮሐ ወይም ላሊበላ ከአስራ አንዱ ከዛጉዌ ነገስታት ውስጥ አንዱ በሆኑት በንጉስ ላሊበላ (ቅዱስ) (1157-1197) አማካኝነት ከአንድ ወጥ ዓለት የተፈለፈሉ የ11 አብያተ ክርስቲያናት መገኛ ነው።[6]
በአስደናቂነታቸው ዓለም የመሰከረላቸውን ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ገንብቶ ለመጨረስ 23 ዓመታትን እንደፈጀባቸው ገድላቸው ይናገራል። ለግንባታ የሚሆነውን መሬትም “ቀይት” ከምትባል ባላባት በወርቅ ገዝተው እንደሆነም ያትታል።[7]
አብያተ ክርስቲያናቱ በአስደናቂነታቸው ይታወቃሉ። ቅዱስ ላሊበላን ጎብኝተው ከጻፉ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጸሐፍት እንደምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በ1512 ቅዱስ ላሊበላን በመጎብኘት የመጀመሪያው አውሮፓዊ ነው የሚባለው የፖርቱጋል ተወላጅ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ እንዲህ ብሏል።
“It wearied me to write more of these works. because it seems to me that they will not believe me if I write more and because as to what I have already written the truth, the may accuse me of untruth. therefore, I swear by God in whose power that I am all that I have written is the truth… the like of which and so many, cannot as it appear to me, be found in the world. *(F Alvearies the Prester John of indies Vol 1 page 315)[8]
ስማቸው ያልተጠቀሰ ኢትዮጲያዊ ባለቅኔም ስለ ላሊበላ እንዲህ ተቀኝተዋል።
ሞት ሕንጻ ላሊበላ ኩለሄ እንግዳ
ሞትና ህንጻ ላሊበላ ሁልጊዜ አዲስ ናቸው። ማለት ነው።[9]
ታዲያ አስቻለው በዘመናችን ወሎን በገመደበት ስንኞቹ ከዳና መስጂድ አድረን ከሮሐ ብናስቀድስ ሁሉም የእኛ ነውና ይበል ያሰኛል እንጂ መቼም አያስነቅፍ እያለን ነው።
በዚያውም የወሎን የሃይማኖት ህብረት ይፈክራል። እስልምናና ክርስትና አንዱ አንዱን ሳይገፋው በአቻነት እኮ እየሰሙና እየተሰሙ የሚገኙበት የስልጡን ህዝቦች ሀገር ነው እያለን ነው። ይበል እንጂ ምን ይባላል?
ላኮመልዛም ብሔድ፥ አልደርስም ሰቆጣ
የራስ ኃይሉን አንገት፥ ከሮም ሳላመጣ
[1] የአገው ሕዝቦችና የዛጉዌ ሥርወ መንግስት ታሪክ፣ በዶክተር አያሌው ሲሳይ። 2007 ዓ/ም ገጽ 188።
[2] ዝኒ ከማሁ
[3] ዝኒ ከማሁ
[4] ዝኒ ከማሁ ከገጽ 189-237
[5] ከቤተ አምሐራ እከ ወሎ፣ መንግስት ሃይማኖት እና መስተጋብር። ምስጋናው ታደሰ ዶ/ር። ገጽ 128-130.
[6] ገድለ ላሊበላ፣ በቅዱስ ላሊበላ ሰበካ ጉባኤ፣ 4ኛ ዕትም ፣ 2010 ዓ/ም ገጽ ፣ 374
[7] ዝኒ ከማሁ ገጽ 11
[8] ዝኒ ከማሁ ገጽ 12.
[9] ዝኒ ከማሁ ገጽ 14

ሮሐም አስቀደሰን ዳናም ተለማምነን፣ በቱፍታውና በውዳጃውም አደርን ከላኮመንዛ (ደሴ) አልፈን፥ የአላማጣዋን ባለ ጉብጉባ ኮረዳ ተሳልመን ወደ ሰቆጣ ለመሄድ ግን አንድ የታሪክ አደራ አለብን ይላል። እኔ እያለ መቀኘቱ በእሱ ውስጥ እኛም እንዳለን ቢያምን አይደለምን? እሱም የዋግሹም ከበደ ልጅ የሆኑትን የራስ ኃይሉ ከበደን አንገት ከሮም ማምጣት አለብኝ እያለን ነው። ለመሆኑ አንገታቸው ከሮም የደረሰው ራስ ኃይሉ ማናቸው?
ደጃዝማች (በኋላ ሌተናል ጄኔራል) ኃይሉ ከበደ የዋግሹም ከበደ ተፈሪና የየጁ መስፍን የራስ አሊጋዝ የልጅ ልጅ የወይዘሮ ኂሩት ንጉስ ልጅ ናቸው። ፋሽስት ጣሊያን ሀገራችንን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረ ወቅት የዋግን ህዝብ አስተባብረው ከእነ ራስ ካሳ ኃይሉ ጋር ተባብረው ወራሪውን ያስጨነቁ አርበኛ ናቸው።
በአምባላጌ፣ በአክሱም፣ በተንቤን እንዲህም በማይጨው ተዋግተዋል። ንጉሰ ነገስቱ ማይጨው ላይ ተሸንፈው የኢትዮጵያ ጦር ሲፈታ በዋግ ገጠር ገብተው አርበኝነታቸውን ጀመሩ። በሲልዳ፣ በአምደወርቅ፣ እንዲሁም ድግርሻና ሌሎችም ቦታዎች ላይ ጣሊያንንና ባንዳን ረትተዋል። የመርዝ ጋዙንና የአውሮፕላን ድብደባውን ተቋቁመው ተዋድቀዋል። በመጨረሻም በ1930 ዓ/ም ከሰቆጣ 10 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ወለህ ሜዳ ላይ በተደረገው ከባድ ጦርነት ቆስለው ወዲያው ህይወታቸው አልፏል። በዚህ ጦርነት ታላላቅ የጦር መኮንኖና አርበኞች ለእናት ሀገር ክብር ወድቀዋል።
ራስ ኃይሉ በጣሊያኖች ዘንድ ይፈ’ሩ ስለነበር መሞታቸው ሲሰማ ጣሊያኖች አስከሬናቸውን ወደ ሰቆጣ ወሰዱት። አንገታቸውን ቆርጠውም በእንጨት ላይ ሰቀሉት። ለሶስት ቀንም ሰቆጣና ኮረም ላይ አንጠልጥለው አቆዩት። በእናት ምድራቸው እንዳይቀበሩ አስከሬናቸውን ለአውሬና ለአሞራ ቀለብ ይሁን ብለው ክቡሩን የአርበኛ ገላ ወደ ገደል ጣሉት። በመጨረሻም የቆረጡትን አንገቱን ወደ ሮም ላኩት። ለዚህ ተጋድሏቸውም ከተገጠሙላቸው ግጥሞች ውስጥ ጥቂቱን ልጥቀስ።
“አባ መረብ ኃይሉ፥ ኃይሉ አባ ይባስ
አንገቱን የሰጠው፥ እንደ ዮሐንስ
ሥጋ አማረኝ አለች፥ የአባ መረብ ሚስቱ
ወለህ አትሄድም ወይ፥ ከታረደበቱ?
አንቺ ወለህ ማርያም፥ ሲቃጠል ቤትሽ
ዓርብ ተሰቀለ፥ ኃይሉ እንደ ልጅሽ
እሺ ላለው ስጠው፥ እምቢ ላለው ንሳ
አባ መረብ ኃይሉ፥ የተከዜው ነበር፥ የወለሁ አንበሳ”።[1]
ሙዚቀኛው ይሄንን መስዋዕትነት ነው ሊያስታውሰን የፈለገው። የአባ መረብ ኃይሉ አንገት እንዲሁ አንገት ብቻ አይደለም። የማንነታችን ውል ነው እንጂ። የትናንትናችን መልክ፣ የአባቶቻችን ተጋድሎ፣ የተከፈለውን ዋጋ ማንጸሪያም ነው። አንገቱ፣ እምነቱ፣ ጀግንነቱ፣ ሰውነቱ እስካልመጣ ድረስ ወደዚያች ቅዱስ ደብር አልሄድም እያለ ነው። አምባና ገመገሙን ሲያይ ጆቢራ የመነተፈው የአባ መረብ ስጋ ቢሸተው አይደለምን? የተንዠቀዠቀው ደም ሲረግጠው ቢያሳቅቀው አይደለምን? አሁንም እናት ምድሩ የልጇን አንገት መቀበል፣ ማቀፍ፣ መሳም ትፈልጋለች እኮ።
አውጉሪሩ
ህምረን አውጉሪሩ
መገን ቅኔ፥ መገን ዜማ
ጃኖና መንዙማ
በመጨረሻም ታሪክ ነገራና ኩርኮራውን ሲጨርስ አበይት ጉዳዮች አንስቶ ነው። መገን ቅኔ ብሎ ሰፊ ጉዳይ አንስቶ ያቀብለናል። በቅኔ ይሸኘናል። ለመሆኑ ለወሎ ዘፈን ስለቅኔ ማንሳት ምን ይሉታል? ለምንስ አነሳው ብሎ መጠየቅ የአባት ነው። ምክንያቱም ገጣሚ የቃላትን ረቂቅ ጉልበት ጠንቅቆ ያውቃል። እውቁ አሜሪዊ ገጣሚና ድንቅ መምህር ሪቻርድ ሁጎ (Richard Hugo) Triggering town የሚታትን የነፍስ ቡጥ አይስትምና። ለወሎም ቅኔን ሸልሞት እብስ ይላል።
በእርግጥ ቅኔ በኑሮ ይገለጣል ማለት መብታችን ነው። ሚስጥር ባያደላድም ወሎዬነት ቅኔ ነው። እንዲያው ለመሆኑ ከቅኔ ጋር በተያያዘ ስለ ወሎ ምን ይባላል?
ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሺፈራው ስለ ቅኔ እንዲህ ይሉናል። ቅኔ ማለት ቀነየ፡ ገዛ ከሚለው ግስ የተገኘ ጥሬ ዘር ነው። ወይም ቀነየ ፣ ገዛ የሚለውን አንቀጽ ያስገኘ ጥሬ ዘር ነው። ፍቺውም መገዛት ማለት ነው ይላሉ። [2]
ስለቅኔ ሲነሳ የመጀመሪያው ጥያቄ ቅኔን በሀገራችን ማን ጀመረው የሚል ነው። ስለጀማሪው የተለያዩ ታሪኮች አሉ። አንደኛው ቅዱስ ያሬድ ጀመረው ይላል። ሌላው ዮሐንስ ዘገብሎን (ገብላዊ) የተባለ የዋድላ ተወላጅ ነው ይላል። እንዲሁም ቅኔን የጀመረው ተዋነይ ነው የሚሉ አሉ። ደቀ እስጢፋ የሚባል የጎጃም ተወላጅ ነው የሚሉም አሉ።
ለዚህም ነው የዋድላ አገባብ የጎጃም አገባብ፣ የዋድላ ቅኔ የጎጃም ቅኔ እየተባለ እስካሁን የዘለቀው። ድድቅ ወልደማርያምና ሌሎች ስድስት ድድቅ በመባል የሚጠሩ ሊቃውንት በዳውንት የጨረቃ በምትባል ቦታ እየተቀባበሉ ቅኔን አስተምረዋልም አስቀጥለዋልም ይባላል ። ድድቅ ማለት ጀግና ማለት ነው።[3] እውነትም ጀግና። በቅኔ የመዋደቅ ልበ ሙሉነት።
ለዚህ ነው ከላይ መገን ቅኔ ሲል መቀኘቱ።
የዜማውን ጉዳይም ከላይ እንዳየነው ነው። ወሎ ለኢትዮጵያ የዜማ ቅኝቶች ማህጸን ናት። ስለዚህ ወሎ የቅኔም የዜማም መፍለቂያ ናት ይለናል።
የእነ ጃኖ መንዙማም ከዜማና ከግጥም ወገን ነውና ልብ ብለን እናየው ዘንድ በአንክሮ ነግሮናል።
[1] የአገው ሕዝቦችና የዛጉዌ ሥርወ መንግስት ታሪክ ፣በዶክተር አያሌው ሲሳይ። 2007 ዓ/ም። ገጽ 215-235
[2] መጽሐፈ ግስ፣ ወሳሰዋስው መርኆ መጻሕፍት፣ እምኅበ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው፣ የኔና የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር መግቢያ።
[3] ዝኒ ከማሁ
ሲጠቀለል
አስቻለው እንገር ወሎ ሲል ለአድማጭ ያቀረበው ሙዚቃ ከዚህ በላይ መታየት ይችላል ብዬ አምናለሁ። ግጥሞቹ ታሪክን፣ ባህልን፣ ማንነትን፣ ከአሁናዊ መልክና ውበት ጋር የሚፈክሩ ናቸው። በግልብ የምንመለከተውን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተን እናየው ዘንድ እንዲህ ነው እያለ ይነግረናል። ከጥልቅ ንባብ የተገኙ ስንኞቹ ለመረዳት በደንብ መመርመርን የሚጠይቁ ናቸው።
ግጥም ጠጠር ሲል አድማጪን ያርቃል የሚለውን ብሂል የሻረ ሙዚቃም ነው ለማለት ያስደፍራል። በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የሆነ መልክ ይዞ እንደመጣ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በጽኑ ያምናል።
ወደፊትም መሰል ስራዎችን ያቀርብለን ዘንድ እየተመኘሁ በዚሁ ልሰናበት።
ከያኒዎቻችንን ያብዛልን።