የተዘነጋው ታሪካችን

(ክፍል አንድ)

ልዑልሠገድ አስማማው

Prometheus, in Greek religion, one of the Titans, the supreme trickster, and a god of fire.

የሰውን ልጅ ታሪክ ስናነሳ በቀደምትነት የሚነሱት የሰው ልጅ ኑሮን ለማሻሻል ስለ ሄደባቸውን መንገዶች፣ ተመራምሮ ስለ ደረሰባቸውን የተፈጥሮ እውነታዎች፣ ፈጥረውኛል እና ይጠብቁኛል ብሎ ስለ ሚያመልካቸው እና መስዋዕት ስለሚያቀርብላቸው አማልክት፣ እንዲሁም ግዛቱን ለማስፋፋት ስላደረጋቸው አያሌ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ናቸው።

ምንም እንኳ በታሪካችን ውስጥ ጎልተው የሚነሱት እና የሚወሱት ዋና ዋና ነጥቦች እነዚህ ቢሆኑም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች በተጨማሪ እምብዛም ሲገለጽ የማይታይ ነገር ግን በሰው ልጅ ላይ በብዙ መልኩ ተጽዕኖ ሲያሳድር የቆየ እሁንም እያሳደረ ያለ ታላቅ ነገር አለ።

በሽታ!

ከጭቃ ተድበልብሎ፣አልያም ከእንጨት ተቀረጾ ወይንም ደግሞ በዝግም ለውጥ ከዝንጀሮ ተመዝዞ የመጣው የሰው ልጅ እዚህች ምድር ላይ ከመጣበት ግዜ ጀምሮ ከበሽታ ጋር ሲታገል እዚህ እንደደረሰ ይነገርለታል። ምናልባትም በሽታ የሰው ልጅ ፈጥረውኛል ብሎ ወደሚያስባቸው አማልክት እንዲቀርብ እና ከእነርሱ ጋር ያለውን ቁርኝት እንዲያጠብቅ ከሚያደርጉት ዋነኛ ነገሮችም መሃል ነው ብንል ማጋነን አይሆንብንም።

ከጥንት ጀምሮ ምናልባትም እስከዛሬም ድረስ የሰው ልጅ ስለሰራው ክፉ ስራ ወይንም ስለተላለፈው ህግ ከአማልክቱ የሚተላለፍበት ቅጣት ወይንም ደግሞ ክፉ መንፈስ በመኖሪያ አካባቢው ሲሰፍር በሽታ እንደሚከሰት ይታመናል። ለዚህም ማስረጃ ይሆነን ዘንድ የግሪኩን የፓንዶራን ታሪክ እና የሞንጎሊያኖችን ሃተታ ተፈጥሮ እንመልከት።

የፓንዶራ ታሪክ

ብዙ መልክ እና ታሪክ ያለው የግሪኮቹ ሃተታ ተፈጥሮ ስለሰው ልጅ አፈጣጠር ከሚያትታቸው ታሪኮች መሃል አንደኛው የ ፕሮሚቲዩስ እና የመጀመሪያው ሰው የፌይኖን ጉዳይ ነው። ታሪኩም በአጭሩ እንደሚከተለው ነው።

ከቀደምቶቹ አማልክት ከታይታን ጎራ  የሚመደበው ፕሮመቲዩስ ሰው የመፍጠር ሃሳብ በውስጡ ጸነሰ። ጸንሶም አልቀረ ውሃን እና ሸክላን አቀላቅሎ ከሸክላ ጭቃ የመጀመሪያውን ሰው ፈጠረ። ስሙም ፌይኖን ይባል ነበር። የዚውስ ልጅ የሆነችው ሴቷ አምላክ አቴና ደግሞ በፌይኖን ላይ የህያውነትን እስትንፋስ ተነፈሰችበች።

ሰውም ከዚያን ግዜ ጀምሮ ህያው መሆን ቻለ። ፕሮሚትየስ ግን በዚህ ብቻ የሚረካ አምላክ አልነበረም እና ለሰው ሌላ ነገር ሊጨምርለት በልቡ አሰበ። ሰው እንደ አማልክቱ ቀጥ ብሎ ይቆም እና ይራመድ ዘንድ አደረገው። በተጨማሪም እራሱን ከኣደጋ ይጠብቅበት ዘንድ፣ ለብርድ ጊዜ ሙቀት እና ለጨለማም ብርሃን ይሆነው ዘንድ እሳትን ለሰው ልጅ ገጸ፟በረከት አድርጎ ሰጠው።

በዚህ ሁኔታ የተናደደው ዚውስ ደግሞ እሳትን ከሰው ልጅ ነጥቆ ደበቀው። ፕሮሚቲዩስ ግን ለፈጠራቸው የሰው ልጆች ጥልቅ ፍቅር ነበረው እና የተደበቀውን እሳት ከተደበቀበት አውጥቶ መልሶ ለሰው ልጆች ሰጣቸው። ዚውስም የሰው ልጅ እሳትን ሲጠቀምበት በተመለከተ ግዜ እንደተከዳ እና ህጉም እንደተጣሰ አወቀ።

ለዚህም መተላለፍ የሰው ልጅን ሊቀጣ አሰበ እና ብረት ቀጥቃጩ ሄፋስቲየስን አንዲት ውብ ሴት እንዲሰራ አዘዘው። ከሴቷ በተጨማሪም ስጦታ መያዣ የሚሆናትን ሳጥን እንዲሰራም ነገረው። ሴቲቷም ተሰራች ስሟም ፓንዶራ ተባለ። በኦሊምፐስ ተራራ ያሉ እንስት አማልክት ሁላ በውበቷ ተደነቁ።

ዚውስም ይህቺን ውብ እንስት ለፕሮሚቲዩስ ወንድም ኢፒሚትዩስ ስጦታ አሰይዞ ላካት። እንዲህ ሲልም ትዕዛዝን ሰጣት “ሂጂና የፕሮሚትየስ ወንድም የሆነውን ኢፒሚትየስን አግኝው። ከልቡ እና ከቤቱ ይሁኝታን ታገኚ ዘንድ ደግሞ ይሄንን ሳጥን ስጦታ ይሆነው ዘንድ አቅርቢለት። ነገር ግን አንቺ በምንም ተዓምር ይሄንን ሳጥን እንዳትከፍች።”

ፓንዶራም ትዕዛዟን ተቀብላ ወደ ኢፒሜቲየስ ቤት አመራች። ኢፒሜቲየስም ባያት ግዜ በውበቷ ተረታ፤ ወደቤቱም ትገባ ዘንድ ፈቀደላት። ሚስቱ ትሆነው ዘንድም አሰበ። ኢፒሚትየስ ቤት ከገባች በኋላ ፓንዶራ ሳጥኑ ውስጥ ያለውን ነገር የማወቅ ጉጉቷ እያየለ መጥቶ አንድ ቀን ትዕዛዟን አፍርሳ ሳጥኑን ከፈተችው።

ከሳጥኑ ውስጥም ረሃብ፣ በሽታ፣ ህመም፣ ጥላቻ እንዲሁም ሌሎች መጥፎ የተባሉ ነገሮች ሁሉ ወጥተው ከሰው ልጅ መኖሪያ ከተሙ። ከሳጥኑ ውስጥ መጨረሻ ላይ ግን ተስፋ ቀርቶ ነበር።

ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው የሰው ልጅ መጀመሪያ ሲፈጠር ከሃዘን፣ ከመከራ፣ ከችግር፣ ከበሽታ እና ከሌሎችም አስጨናቂ ነገሮች ነጻ ሆኖ ነበር። ነገር ግን አማልክቱ ደስ ባለመሰኘታቸው በሰው ልጅ ላይ ከተላለፈበት ቅጣት መሃል አንደኛው ከበሽታ ጋር መተዋወቅ ሆኖ እናገኘዋለን።

የሞንጎሊያኖች ሃተታ ተፈጥሮ

“በህዋችን ላይ ውሃ እና የሁለት ልጆች አባት ከሆነው የሁሉ ገዢ እና የሰማዩ አምላክ በቀር ማንም አልነበረም።” ብለው ያምናሉ የጥንት ሞንጎላውያን።

የዚህ የሰማይ አምላክ ልጆቹም  ኡልገን እና ኤርለግ ይባላሉ። የሰማዩ ገዢም ለልጆቹ ግዛት ይሆናቸው ዘንድ ከህዋ እኩሌታውን ወደ ላይ ለኡልገን እኩሌታውን ወደ ታች ለ ኤርለግ ሰጣቸው። ኡልገን የራሱን ዓለም ይፈጥር ዘንድ አሰበ።

ከዚያም ጠላቂ ወፍ ከወደ ጥልቁ ውሃ ገብታ ለፍጥረት መነሻ ይሆነው ዘንድ ጭቃ እንድታመጣለት አዘዘ። ጠላቂ ወፏም ትእዛዙን ትፈጽም ዘንድ አልተቻላትም ነበር።

ከዚያም ኡልገን ድጋሜ ዳክዬን ከጥልቁ ገብታ ጭቃ ታመጣለት ዘንድ አዘዛት። ዳክዬም ከጥልቁ ገብታ ጥቂት የጭቃ ርዝራዥ በአፏ ይዛ ተመለሰች። ኡልገንም ዳክየዋ ካመጣችው ጭቃ ላይ አረፍ አለ። በዚያው እንቅልፍ ወሰደው።

የዚህን ግዜ ወንድሙ ኤርለግ ጭቃውን ሰርቆ የኡልገንን ስራ ያደናቅፍ ዘንድ አሰበ። አስቦም አልቀረ አደረገውም። ጭቃው ግን ከላዩ ላይ ሲቀነስለት መጠኑ ሊያንስ ሲገባ በተቃራኒው  በመጠኑ ይገዝፍ ጀመር። የጭቃው መስፋፋትም ኡልገንን ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው። ኡልገንም ከእንቅልፉ ተነስቶ ከጭቃው ሰውን እና ሌሎች እንሰሳትን ይፈጥር ዘንድ ሃሳብን በልቡ ጸነሳት። ጸንሶም አልቀረ ወለዳት፤ ከጭቃው ሰውን እና ሌሎች እንሰሳትን ፈጠረ እናም አካላቸው እስኪደርቅ ከውጭ አስቀመጣቸው።

ነገር ግን ጊዜው የበረዶ ዝናብ የሚዘንብበት ነበር እና ቶሎ ሊደርቁለት አልተቻላቸውም። ኡልገንም የተፈጠሩትን ፍጥረታት እስኪደርቁ ድረስ እንዲጠብቅ ለውሻ ሃላፊነት ይሰጥ እና ለፍጥረታቱ ነፍስ ይፈጥርላቸው ዘንድ ወደ ሰማይ ይሄዳል። ኡልገን መሄዱን የተመለከተው ኤርለግ አዲስ የተፈጠሩትን ፍጥረታት ለመመልከት ወደ ተቀመጡበት ቦታ ሲሄድ ውሻው አደገኛ ነበር እና ሊያስጠጋው አልቻለም። ኤርለግ ለውሻው ከብርድ መከላከያ እንዲሆንለት ወፍራም እና ጸጉራማ ኮት ይሰጠዋል (ውሾች ቆዳቸው በጸጉር መሸፈን የጀመረው ከዚያን ግዜ ጀምሮ ነው። ከዚያ በፊት መላጣ ነበሩ።) ውሻውም በተሰጠው ስጦታ ተደስቶ ኤርለግ አዳዲሶቹን ፍጥረታት እንዲያይ ይፈቅድለታል።

ኤርለግም ወደ ፍጥረታቱ እንደቀረበ እላያቸው ላይ ተፋባቸው። ከዚያን ግዜ ጀምሮ ሁሉም የፍጥረታት በሽታ እና ህመም እንደተወዳጃቸው ይነገራል።

በዚህኛው ታሪክ ደግሞ የሰው ልጅ ሲፈጠር ንጹህ የነበረ ቢሆንም እኩይ ባህሪን የተላበሰ አምላክ በፈጸመባቸው ድርጊት ከበሽታ እና ህመም ጋር እንደተዋወቀ ማየት እንችላለን። ስለዚህ በሽታ ምንጩ ክፉ መንፈስ ነው ወደሚለው ሃሳብ ያመጣናል ማለት ነው።

እስኪ አሁን ደግሞ ሳይንሱን መሰረት አድርገን ስለበሽታ አመጣጥ እና ምክንያት ጥቂት ነገሮችን እናንሳ።

ኢቮሉሽንን (ዝግመተ ለውጥ) መሰረት ስናደርግ የዛሬ ሁለት ሚሊዮን ዓመታት አካባቢ የጥንት አያቶቻችን ከዛፍ ፍራፍሬውን፣ ቅጠላ ቅጠሉንና ስራስሩን እንዲሁም አንዳንድ አነስ ያሉ እና መጠነኛ እንስሳትን እያደኑ እና እየተመገቡ ከሌሎች ግዙፋን አዳኝ እንስሳት እራሳቸውን እየጠበቁ በታላቅ ፍራቻ ዋሻ ውስጥ ይኖሩ ነበር።

ነገር ግን ይሸሸጉ እና ይደበቁ የነበረው በዓይን ከሚታዩት ጠላቶቻቸው ይሁን እንጂ የእነርሱ እጥቂዎች በዓይን የሚታዩት አውሬዎች ብቻ አልነበሩም። እንዲያውም ለመሸሸግም ሆነ ሮጦ ለማምለጥ አልያም ከድንጋይ ጠርበው በሰሯቸው ስለታም የጦር መሳሪያዎች ለመከላከል የማያመች፤ በየቀኑ የህብረታቸውን አባል ህይወት እየነጠቀ የሚያሳቅቃቸው እና በፍርሃት የሚያር’ዳቸው ስውር ጠላት ነበራቸው ። እሱም መንሴውን እንኳ በቅጡ ሊረዱት ያልቻሉት በሽታ ነበር።

በዚያ ዘመን የነበሩ በሽታዎች አብዛኛዎቹ ከሚያድኗ’ቸው እንስሳት የሚተላለፉ፣ በትላትል የሚከሰቱ፣ ከቅማል የሚተላለፉ፣ ቴታነስ፣ ብላሃርዚያ የመሳሰሉት ሲሆኑ በዘመናቸው የአያሌዎቹ ህይወት ሲቀጥፉ ነበር።

ወደ በኋላ ላይ ግን ከዛሬ 300,000 ዓመት በፊት እንደነበሩ የሚነገርላቸው ኒያንደርታልስ እና ሆሞ ሳፒያንስ የተባሉት የጥንት የሰው ልጅ ዝርያዎች ከላይ ከሰማይ በ መብረቅ ብልጭታ አማካኝነት ወይም ከታች ከምድር ውስጥ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ አማካኝነት ፈልቆ፣ በምድር እጽዋት ነዳጅነት እና በኦክስጅን አጋፋሪነት ተፋፍሞ፣ ከ 400 ሚሊየን ዓመታት በፊት እንደተከሰተ የሚታሰበውን እሳት እንደሌሎች እንስሳት ከመፍራት ተሻግረው መቆጣጠር እና ለግል ፍጆታቸው ማዋል ጀመሩ።

እሳትን መጠቀም መጀመራቸው ከብርድ፣ ከጨለማ እና ከግዙፋን እንስሳት ጥቃት ብቻ አልነበረም የታደጋቸው። ከእሳት በፊት በጥሬው ሲመገቡ የነበረውን የእንስሳት ስጋ አብስለው መብላት በመጀመራቸው በሽታ አምጪ የሆኑትን ትላትል እና በዓይን የማይታዩ ጀርሞችን መግደል ችሎ ነበር።

በዚህም ከበሽታ ጥቂት ፋታ አግኝተው፣ በበሽታ ሳቢያ የሚሞቱባቸውን አባላት ቁጥር መቀነስ ችለው ነበር። ነገር ግን የሰው ልጅ ብዛቱ በአያሌው እየጨመረ መጣ። የምድርም የሙቀት መጠን እየጨመረ፤ ምድርን በበረዶው ዘመን ጊዜ ሸፍኗት የነበረው በረዶም በሙቀቱ ሳቢያ እየቀለጠ የሰው መኖሪያ የነበሩ አያሌ ደሴቶችን እንዲሁም አንዳንድ የየብስ ክፍሎችን ማስመጥ ጀመረ። በሙቀቱ መጨመር ምክንያትም የእንስሳቱ እና የእጽዋቱ ሁኔታ እየተቀያየረ መጣ።

በዚህም የተነሳ የሰው ልጅ ለእለት ጉርስ የሚሆነውን የምግብ ፍጆታ በአደን እና ለቀማ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ለማሟላት የሚቻል አልሆነለትም።

እንዲህ ለተጋረጠበት የህልውና ተግዳሮት መፍትሄ ይሆነው ዘንድ ጠቢቡ ሰው ከዛሬ 10,000 ዓመታት በፊት እንስሳትን እና የሳር ዝርያ የሆኑ አዝዕርትን በማላመድ ለእለት ጉርሱ ማዋል እንደጀመረ ይነገርለታል።

ያኔ ደግሞ ከእንስሳቱ እና ከሰብሎች በሚተላለፉ አዳዲስ አይነት በሽታዎች ጋር ለመተዋወቅም በቅቷል።William McNeill የተባለው አሜሪካዊ የታሪክ ተመራማሪ እንደሚለው “የሰው ልጅ ከውሾች ጋር 65፣ ከ ቀንድ ከብቶች ጋር 50፣ ከ በግ እና ፍየል ጋር 46፣ ከ አሳማዎች ጋር 42፣ ከፈረስ ጋር 35 እንዲሁም ከዶሮ ዝርያዎች ጋር ደግሞ 26 የበሽታ አይነቶችን ይጋራል።”

በተጨማሪም በግብርና መጀመር ምክንያት የሰው ልጅ ቋሚ የመኖሪያ ቦታ ማቋቋም ችሏል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለወባ ትንኞች ምቹ የመራቢያ ቦታን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ይህም የሰውን ልጅ በከፍተኛ ሁኔታ ለወባ በሽታ ተጋልላጭ አድርጎታል።

የሰው ልጅ ከዋሻ ነዋሪነት ወጥቶ፣ የእለት ጉርስን ለማግኘት ከመባዘን ተሻግሮ፣ ከተሞች መመስረት እና መንግስታት ማቋቋም ከጀመረ በኋላም በሽታ አለ የማይባል አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖውን በሰውልጅ ላይ ሲያሳድር ሰነባብቷል።

ግብጽን የስልጣኔዋ ማማ ላይ እንድትወጣ አድርጓታል ተብሎ የሚታሰበው ፈርኦን አሜንሆቴፕ ሶስተኛ (Amenhotep III ruled Egypt from 1386 to 1349 BC ) በነበረበት ዘመን ምንም አይነት የጦርነት እና የግጭት ምልክት ሳይኖር እንዲሁ የተተዉ እና የተቃጠሉ ከተሞች እና የመኖሪያ መንደሮች በቁፋሮ ተገኝተዋል። እንዲሁም በዚያው ዘመን ምንም አይነት የተመዘገቡ የጦርነት ታሪኮች ሳይገኙ ያለተለምዷቸው በአንድ ቦታ እጅግ ብዙ ሬሳዎችን የያዙ የጅምላ መቃብሮችም በቁፋሮ ተገኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ዘመን አንዳንድ የከፍተኛ ሹማምንት አባላት እና የፈርኦኑ ቤተሰቦችም ሳይቀሩ ከጥንት ግብጻውያን የአቀባበር ባህል በተለየ ሁኔታ ለሹማምንቱ እና ለፈርኦኑ ቤተሰብ በማይመጥን መልኩ መቃብራቸው እንደሌሎቹ ሳይዋብ፣ ከሞት በኋላ ላለው ህይወት የሚገለገሉበት ለክብራቸው የሚመጥን ቁሳቁስም ሳይቀምመጥበት ተቀብረዋል።

ለዚህም እንደ ማስረጃ ተደርጎ የሚሰጠው መላ ምት፡- አንደኛ በዘመኑ ከፍተኛ ህዝብ የጨረሰ የበሽታ ወረርሺኝ በመከሰቱ አያሌ ሰዎችን ስለጨረሰ እና ከሚያልቁት ሰዎች መሃል ደግሞ ቀራጺዎች እና ሌሎች የጥበብ ባለሞያዎችም ስለሚገኙ ያ የፈጠረው ክፍተ ነው የሚል ነው። ሁለተኛው መላ ምት ደግሞ ወረርሺኙ ክፉኛ አስደንጋጭ እና ተላላፊ በመሆኑ ራሳቸውን ለመታደግ ሲሉ ሟቾችን በሰላሙ ግዜ እንደነበረው አይነት አቀባበር መቅበር አልቻሉም የሚለው ነው። በሁለቱም መንገድ ብንሄድ የማይካደው ሃቅ በሽታ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ አድርሶ እንደ ነበር ነው

በሌላ ጎን ደግሞ ከአሜንሆቴፕ ዘመን በፊት ይመለኩ የነበሩ አማልክት የተከታይ ቁጥራቸው ቀንሶ ዝቅተኛ እና ብዙም የማትታወቅ የነበረች፣ ባለ አንበሳ ፊቷ፣ የጦርነት እና የ ወረርሺኝ በሽታዎች አምላክ ተብላ የምትታወቀው ሴኬምት እና ሌሎች የማይታወቁ እና ብዙ ተከታይ ያልነበራቸው ንዑስ የፈውስ አማልክት በዘመኑ ዝናችው ገንኖ ነበር። አሜንሆቴፕም ህዝቡን ከወረርሺኙ ለማትረፍ በሚመስል መልኩ ለሌሎች ዐቢይ አማልክት ወደ 200 የሚጠጉ የድንጋይ ሃውልቶችን ሲያስቀርጽ ለሴኬምት ብቻ ከ 700 በላይ የድንጋይ ሃውልቶችን ስለማስቀረጹ በቁፋሮ የተገኙ ማስረጃዎች ያመላክታሉ። በእሱ ዘመንም ይሰሩ የነበሩ ሃውልቶች በፊት ከነበሩት የጥራት ደረጃቸው ዝቅ ያለ እና በውበትም ሆነ በአቀራረጽ እምብዛም አስደናቂ ያልነበሩ ነበሩ። ይህ ሁሉ የሆነው ግብጽን ለ 8 ዐመታት መትቷታል ተብሎ የሚታሰበው Bubonic Plague የሚባል የበሽታ ወረርሺኝ በተከሰተበት ዘመን ነበር።

ታላላቅ ስልጣኔዎች እንዲሁም ጽህፈት ሳይቀር እንደተወለዱበት የሚነገርለት የነሃስ ዘመን በወረርሺኞች መስፋፋት እና ማየል ምክንያት ሊወድቅ እንደቻለ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። የበሽታ ተጽዕኖ በዚህ ብቻ የተገታ አይደለም። የዓለማችን ታላቁ ንጉስ እስክንድር ሳይቀር ግሪክን ለመቆጣጠር የቻለው የወባ ወረርሺኝ ሃገሪቷን ክፉኛ በመታበት እና ባደከመበት ግዜ ላይ ነበር። እሱ ታላቁ ንጉስ እራሱ ገና በወጣትነት እድሜው፣ ምድርን ሮጦባት ሳይጠግብ west Nile viral encephalitis በሚባል የአንጎል ኢንፌክሽን ሳይሞት እንዳልቀረ  የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

ምናልባትም የሰውን ልጅ እንደ በሽታ ያጠፋ የለም ቢባል እውነታውን ማሳነስ እንጂ ማጋነን ይሆንም። በእርስ በእርስ ጦርነት፣ በድርቅ እና ርሃብ እንዲሁም በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከሞተው የሰው ልጅ ቁጥር ይልቅ በበሽታ ህይወቱን ያጣው የሰው ልጅ ቁጥር ይልቃል። ለማስረጃ ይሆነን ዘንድም በዓለማችን ላይ ከተከሰቱ አያሌ የተላላፊ በሽታ ወረርሺኞች መካከል ሁለቱን እናንሳ።

በ14ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንደተከሰተ የሚነገርለት ጥቁሩ ሞት (Black Death) በመባል የሚታወቀው የበሽታ ወረርሺኝ ብቻውን የ አውሮፓን 40-60% የሚሆነውን ህዝብ ፈጅቷል። እንዲሁም በሰዓቱ እስከ 450 ሚልዮን እንደሚደርስ የሚገመተውን የዓለማችንን የህዝብ ብዛት ወደ 350 እስከ 375 ሚልዮን ድረስ ዝቅ ሳያደርገው እንዳልቀረ ይገመታል። የዓለማችን የህዝብ ቁጥርም እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሊያገግም አልቻለም ነበር።

በሃያኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ስሞል ፖክስ (small pox) እየተባለ የሚጠራው በቫይረስ የሚተላለፍ በሽታ ከመጥፋቱ በፊት እንደ ወረርሺኝ በተከሰተበት ጊዜ ወደ 300 ሚልዮን የሚሆኑ የሰው ልጆችን ህይወት እቀጠፈ ይገመታል። የአሃዙን ግዙፍነት አጥርተን ለመመልከት ያህል በሃያኛው ክፍለ ዘመን በጦርነት ከሞቱት የሰው ልጆች ብዛት ጋር ስናነጻጽረው ሶስት እጥፍ እንደ ማለት ነው።

እንግዲህ በቅንጭብጫቢ መልኩ ለማቃመስ እንደተሞከረው በሽታ በሰው ልጅ ታሪክ ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖውን እንዳሳደረ ለማሳየት ተሞክሯል። ለመጠቅላል ያህል በበሽታ ምክንያት ከተሞች ያለነዋሪ ቀርተዋል፣ ነገስታት ያለክብር ተቀብረዋል፣ አማልክትም ያለ ተከታይ ቀርተዋል። አንዳንድ አማልክትም ደግሞ ስለበሽታው ሲባል ተከታይ በዝቶላቸዋል።

ዓለማችንም በበሽታ ምክንያት ታላላቅ ነገስታትን፣ ጠቢባንን እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎቿን ሳይቀር አጥታለች። በሽታ በእያንዳንዷ የሰው ልጅ የታሪክ ቅንጣት ውስጥ የራሱ የሆነ አሻራ አለው ብንል የማይገባውን ቦታ መስጠት እንዳልሆነ ይህች ቅንጭብጫቢ ጽሑፍ አስረጅ ናት ብለንም እናምናለን።

ነገር ግን የሰው ልጅ በበሽታ ተረትቶ፣ ሽንፈቱን አሜን ብሎ ተቀብሎ፣ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ዘመን ድረስ የበሽታን መንስኤ ለማወቅ፣ መተላለፊያ መንገዶቹን ለመረዳት እና ለበሽታው ፈውስ የሚሆነውን መድሃኒት ለመስራት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎን ሲያደርግ ቆይቷል።

ታዲያ ለዚህ ጠላቱ መፍትሄ የሚሆነውን ያገኝ ዘንድ ከምድር እጽዋት እስከ ባህር ውስጥ ዋቅላሚዎች፣ ከግዙፋን እንስሳት እስከ ደቂቃን ዘአካላት ድረስ ተመራምሯል፤ እየተመራመረም ነው። ለዚህ ዘርፍ ሲባልም አያሌ መጠን ያለውን ገንዘብ ወጪ አድርጓል። ይሄ ተጋድሎውም የሰው ልጅ ህልው ሆኖ እስከቆየ ድረስ የሚቀጥል ነው።

በሚቀጥለው የባይራ እትም የሰው ልጅ ለበሽታ መፍትሄ የሚሆነውን መንገድ ለማግኘት የሄደበትን ርቀት ቀንጨብ ቀንጨብ አድርገን ይዘን እስክንመጣ ድረስ ቸር ይቆዩን። ለዛሬ ግን እዚህ ላይ አበቃን።

(ክፍል ሁለት ይቀጥላል)

ማጣቀሻዎች

1.     Cambridge University, 1996, The Cambridge illustrated history of medicine, Cambridge University Press.

2.     Philip Norrie, 2016, A history of diseases in ancient times; more lethal than war, the University of Washington Press.

3.     Cynthia Stokes Brown, 2008, Big History from the Big Bang to the Present, The New Press.

4.     Stephen J. Pyne, 2001, Fire A Brief History, Springer Nature.

ተያያዥ ልጥፎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *