ልዑልሰገድ አስማማው
ለማስታወስ ያህል…
ሰላም ውድ የባይራ ዲጂታል መጽሔት አንባቢያን! በባለፈው እትማችን የሰው ልጅ ከበሽታ ጋር ስለነበረው የግብግብ ጉዞ እንዲሁም በበሽታ ምክንያት ስለደረሰበት በደል እና ግፍ በጥቂቱም ቢሆን ለመዳሰስ መሞከራችን የሚዘነጋ አይደለም። ዛሬ ደግሞ የሰው ልጅ በባህሪው ለውድቀት እጁን የሚሰጥ አይደለምና በሽታን ለመከላከል እና በበሽታ ምክንያት የሚሞቱበትን ወገኖቹን ቢችል ሞታቸውን ለማስቀረት፤ ባይችል ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር ለመቀነስ የሚሄድበትን ርቀት እና የሚያደርገውን እልህ አስጨራሽ ትግል ቃል በገባነው መሰረት ቀንጨብ ቀንጨብ አድርገን ለመዳሰስ እንሞክራለን። አብረን እንጓዝ እንግዲህ።
እንደ መግቢያ
ከቅድመ ታሪክ ጀምሮ የሰው ልጅ ኑሮውን የተቃና ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን በመሞከር-መሳሳት ሂደት ሲያከናውን ቆይቷል። ሂደቱም እስከዛሬ ድረስ እንደቀጠለ ነው። በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከተገኙ ማስረጃዎች ለመገመት እንደተቻለውም በተለያዩ ክፍለዓለማት ተበታትኖ ይኖር የነበረው የሰው ልጅ የቦታ መራራቅ ሳይገድበው ኑሮውን የተቃና ለማድረግ የሄደበት መንገድ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሊባል የሚችል ነው።
ለዚህ ተመሳስሎት መከሰትም ሁለት ንድፈ ሃሳቦች እንደ አስረጂ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
የመጀመሪያው፦ “የሰው ልጅ የተለያየ ጊዜና በተለያየ ቦታ የኖረ ቢሆንም፣ ለሁሉም የሰው ዘር ወጥ እና ተመሳሳይ የአስተሳሰብ መስመር በተፈጥሮ አዳብሯል። በዚህም ምክንያት በአመዛኙ ተመሳሳይ ሊባል የሚችል የአኗኗር ዘይቤ እና ባህል እንዲኖረው አድርጓል።” የሚለው ሲሆን ይህም convergence theory በመባል ይታወቃል። Adolf Bastiyan የተባለው ጀርመናዊ ኢትኖግራፈር በ 1881 እ.ኤ.አ አስተዋውቆታል። ንድፈ ሃሳቡ በታላቁ ሳይኮሎጂስት Carl G. Jung ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረ ይነገርለታል።
ሁለተኛው ንድፈ ሃሳብ ደግሞ convection(diffusion) theory ይባላል። Charles Darwin ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ እንዳሳደረ የሚነገርለትን ይህን ንድፈ ሃሳብ Friedrich Ratzl የተባለው ጀርመናዊ ኢትኖግራፈር በ 1882 እ.ኤ.አ አስተዋውቆታል። በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት “በተለያየ ጊዜ በተለያየ ቦታ ይኖር የነበረው የሰው ልጅ ተመሳሳይ ሊባል የሚችል የኑሮ ዘይቤን ሊያዳብር የቻለው አንድም ከጎረቤት ማህበረሰብ እየተወራረሰ ፤ ሌላም በጊዜ ሂደት ከ አያት፣ ቅድም አያቱ እየተቀባበለ ስለመጣ ነው።” ስለዚህ የሰው ልጅ እራሱን ከበሽታ ለመታደግ እና ለመከላከል የሄደበት መንገድም በብዛት በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቅ ይሆናል ማለት ነው።
ጉዞ
ቅድመ ታሪክ የነበረው የሰው ልጅ በሽታን ለመከላከል ምን ያደርግ እንደነበር እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር የሚቻል አይደለም። ሆኖም ግን አንዳንድ የአርኪዎሎጂ ጥናት ውጤቶች ከሚያትቱት በመነሳት በተለያዩ ክፍለ-ዓለማት ይኖሩ የነበሩ የሰው ልጆች በሽታን ለመከላከል ያደርጉ ስለነበረውን ተጋድሎ ግምት ማስቀመጥ ይቻላል። ይህንንም በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች ማጠቃለል ይቻላል።
የመጀመሪያው ዘርፍ የተማህልሎአዊ(mystical) እና አስማታዊውን(magical) መንገድ ሲይዝ ሁለተኛው ደግሞ ዛሬ ላይ ባህላዊ ህክምና የምንለውን ዕፅዋትን መሰረት ያደረገውን(herbal medicine) የህክምና መንገድ ነው። የመጀመሪያውን ዘርፍ በዚህኛው ጽሑፋችን ለመዳሰስ የምንሞክር ሲሆን ሁለተኛውን ደግሞ በቀጣይ ይዘን እንቀርባለን።
ፍለጋ
ጥንታዊው ሰው በሚኖርበት አካባቢ ያሉ ማናቸውም ነገሮች ፦ ግዙፋኑም ሆነ ደቂቃኑ፣ ግዑዙም ተንቀሳቃሹም፣ ህይወት አላቸው ብሎ ያምናል። ህልው መሆን ብቻም ሳይሆን የየራሳቸው የሆነ መንፈስ(spirit) አላቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የነፋሱ ፉጨት፣ የደመናው ጥቁረት፣ የመብረቁ ብልጭታ፣ የነጎድጓድ ተስገምጋሚ ድምጽ፣ እንዲሁም ከተፈጥሮአዊው ኡደት ለየት ለየት ብሎ የሚታይ ወይንም የሚሰማ የተኛውም የተፈጥሮ ሁነት ለአማልክቱ ወይንም ለስውራኑ መናፍስት መኖር (ህያውነት) ሁነኛ ምልክቶቹ ነበሩ። ይህ የአስተሳሰብ መንገድ የሰው ልጅ” የምኖርበት አካባቢ በመናፍስት የተሞላ ነው።” ብሎ እንዲያምን ሳያደርገው እንዳልቀረ ይታሰባል።
እነዚህ የማይታዩ መናፍስት ደግሞ በተቆጡ ሰዓት በሰው ልጅ ላይ በሽታ እንዲከሰት ያደርጋሉ። መናፍስቱ ወደ ሰው ልጅ አካል የሚገቡት በአካሉ ላይ በሚገኙ ቀዳዳዎች ነው። ታዲያ እነዚህ የማይታዩ መናፍስት ወደ አካሉ ውስጥ ገብተው ጥቃት እንዳያደርሱበት በሚንቀሳቀስበት ግዜ አካሉን በአስፈሪ እንስሳት ቆዳ በመሸፈን፣ የተለያዩ አስፈሪ ድምጾችን የሚያወጡ መሳሪያዎችን በመጠቀም እና በማፏጨት መናፍስቱን ለማስፈራራት እና ለማባረር ሙከራ ያደርግ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ መናፍስቱን ለማባረር እና ከአጠገቡ ለማራቅ በልዩ ሁኔታ የተሰሩ እና መናፍስቱን የማባረር ሃይል አላቸው ተብለው የሚታመኑ፣ በልዩ ሁኔታ የተሰሩ የአንገት ሃብሎችን ይጠቀም አንደነበር አንዳንድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።
ግንኙነት
የሰው ልጅ ከእሱ በላይ ኃይል ያላቸው እንዲሁም ስውራን የሆኑ ልዕለ ኃያላን አማልክት እንዳሉ ማሰብ ከጀመረበት ግዜ አንስቶ ደግሞ የበሽታንም የጤንነትንም ባለቤትነት ለእነርሱው አሳልፎ ሰጥቷል። ከዚህም ባሻገር ለእያንዳንዱ የህይወት ሁነቶች አማልክትን ሰይሞ ጉዳዩን በሞላ ለእነርሱ አሳልፎ ሲሰጥ ለጤንነትም እንዲሁ ለበሽታም ለየብቻ አንዳንዴም በጋርዮሽ አማልክትን ከመሰየም አልተቆጠበም።
ስለዚህ ከወገኖቹ አንዱ በበሽታ ሲያዝ ከበሽታ ይፈወስ ዘንድ፣ በጤንነት ያሉትን ደግሞ ጤንነታቸው ተጠብቆ እንዲቀጥሉ አማልክቱን መለማመን ጀመረ ማለት ነው። ይህም ህክምናን ወደ ተማህልሎአዊ እና አስማታዊ መንገድ እንዲከተል አደረገው። ማለትም አንድ በሽታ መፍትሄ የሚገኝለት ቅዱሳን አማልክቱን በመለማመን፣ ለእነርሱም የደም፣ የዳንስ፣ የዘፈን፣ አልያም የጾም እና ጸሎት መስዋዕት በመሰዋት። ብሎም ሌሎች የቁሳቁስ ገጸ-በረከት ለአማልክቱ በማቅረብ፤ ወይም የቅዱሳን አማልክቱን ስውር ስም እና ሌሎች ሃይል አላቸው ተብለው የሚታመኑ ቃላትን ደጋግሞ በማነብነብ ክፉ መናፍስት ከሰው ልጅ አካል ለቀው እንዲወጡ በማድረግ ራሱን ከበሽታ ለመጠበቅ ሙከራ ያደርግ ነበር ማለት ነው። በዚህም ምክንያት በሰዓቱ የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ከሃይማኖት መሪነታቸው ባሻገር የህክምናውንም ስራ ደርበው እንዲሰሩ አስችሏቸው ነበር።
ግብጽ
የጥንት ግብጻውያን ፈውስ ከአማልክቱ ለሰው ልጆች የሚሰጥ ገጸ-በረከት ነው ብለው ያምኑ ነበር። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ከፈውስ ጋር የተያያዙ የተለያዩ አማልክት ሊኖራቸው የቻለው። እስኪ ለምሳሌ ያህል ብቻ የተወሰኑትን እንጥቀስ።
ቶት
ቶት ባለ ወፍ ጭንቅላት ተደርጎ የሚሳል እና የሚቀረጽ አምላክ ሲሆን ስሙ ከህክምና እውቀት እና ፈውስ ጋር ተደጋግሞ ይነሳል። በቁፋሮ የተገኘ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉሞ እንዲህ የሚል አረፍተ ነገር ያትታል፦ “I’m Toth, the inventor and founder of medicines and letters; come to me, those that are under the earth, rise up to me, thou great spirit.”
ሴኬምት
ሌላኛዋ በጥንት ግብጻውያን ዘንድ እንደ ፈውስ አምላክ ተደርጋ የምትታሰብ የነበረችው ባለ አንበሳ ጭንቅላቷ ሴኬምት የተባለችው የሴት አምላክ ናት። ሴኬምት የ”Ra” ልጅ ስትሆን የፈውስ፣ የበሽታ እና የወረርሺኝ እንዲሁም የጦርነት አምላክ ተደርጋ ትወሰድ ነበር።
ሴኬምት ወዳጆቿን ከበሽታ እና ወረርሺኝ የምትታደግ፣ ጠላቶቿን በበሽታ የምትቀጣ እንደሆነች የጥንት ግብጻውያን ያምኑ ነበር። የሁሉ የበላይ የሆነው “ራ” ባረጀ ጊዜ ማርጀቱን አይተው ለማይታዘዙት እና በእርሱ ላይ ያሴሩ የነበሩትን የሰው ልጆች ትቀጣለት ዘንድ ባዘዛት ግዜ አስደንጋጭ የሆነ እልቂት እንዳስከተለች የሚያትት ታሪክ አለ።
“ራ” ኣራሱ ከመደንገጡ የተነሳ የሚያስቆምበትን መላ ሲያፈላልግ ሴኬምት ደም የምትወድ አምላክ ነበረች። ከዚያም ብዙ መጠን ያለው ቢራ ሌሎች አማልክት እንዲያዘጋጁ እና ቢራውንም ቀይ ቀለም እንዲጨምሩበት አዘዛቸው። ቢራውም ተጠመቀ ቀይ ቀለምም ገባበት ከዚያም በሰፊ ሜዳ ላይ እንዲደፋ ተደረገ አካባቢው የደም ሃይቅ መሰለ።
ሴኬምት በዚያ በኩል ባለፈች ግዜም የተመለከተችው ቀይ ቢራ ደም ስለመሰላት አንድም ሳታስቀር ምጥጥ አድርጋ ጠጣችው። ቢራውም አቅሏን አስቶ ባሰከራት ጊዜ ሁሉን ነገር ረሳች። ሰው መግደሏንም አቆመች። “ራ” ም እፎይታም አገኘ።
በዚህ ምክንያት ሴኬምትን የሚያመልኩ ሰዎች የዓመቱ መጀመሪያ ላይ ክብረ በዓል ባዘጋጁ ግዜ በሴኬምት ስካር እና ራስን መሳት ምክንያት ከመጥፋት መትረፋቸውን ለማስታወስ ከመጠን በላይ ይጠጡ እና ይደንሱ ነበር።
ኢምሆቴፕ
ኢምሆቴፕ በንጉስ ዞረስ ዘመን (ሶስተኛው ዳይናስቲ) ይኖር የነበረ አርክቴክት፣ አስትሮሎጀር፣ እና ሃኪም ነው። ከጥበቡ ልህቀት እና ከችሎታው መራቀቅ የተነሳ ግን ወደ አምላክነት ከፍ የተደረገ ነው። የፕታህ የመንፈስ ልጁ እንደሆነ ይነገርለታል። በመፈወስ ጥበቡ ደግሞ የቶትን መልክ ይዟል እያሉም ያወድሱት ነበር። ለምሳሌ ያህል ሶስቱን አነሳን እንጂ በጥንታዊት ግብጽ ውስጥ እንደ ፈውስ አምላክ ተደረገው የሚቆጠሩት እነዚህ ብቻ አይደሉም አይሲስ፣ ሄካ፣ አኑቄት፣ ሃፒ፣ ቤስ፣ ሃቶር፣ ሆሩስ፣ ፕታህ፣ሰራፒስ የተባሉ እና ሌሎችም ቁጥራቸው በዛ ያለ የፈውስ አማልክት እንደነበሯቸው እና ህዝቡም ወደ ሚያመልኳቸው አማልክት ቤተመቅደስ መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ፣ መስዋዕት በመሰዋት እና ፈውስ እንዲልኩላቸው በመለማመን ጤንነቱን ለመጠበቅ ይተጋ እንደነበር አንዳንድ ጠቋሚ የድንጋይ ላይ እና የፓፒረስ ጽሑፎች ተገኝተዋል።
ግሪክ
ስልጣኔዋንም ሆነ አንዳንድ አማልክቷን ከግብጽ እንደወረሰች በሚነገርላት ግሪክ ውስጥም ልክ እንደ ግብጽ ሁሉ የተለያዩ አማልክት የፈዋሽነትን ሚና ይወጣሉ። እነዚህም ውስጥ በዋነኛነት ይጠቀሱ የነበሩት ፓያን፣ አፖሎ፣ አስከሌፒዩስ፣ ሃይጊያ ሲሆኑ ሌሎችም አርቴሚስ፣ ኢፒዋን፣ ሄራ የመሳሰሉ ተጨማሪ አማልክትም ስማቸው ከፈውስ እና ጤንነት ጋር ይነሳ ነበር።
አስከሌፒየስ
የግብጹ ኢምሆቴፕ እንደሆነ የሚነገርለት አስካሌፒዩስ የ አፖሎ ልጅ ሲሆን በግሪክ ውስጥ ታዋቂ የፈውስ አምላክ ነበረ። ይህን የፈውስ ችሎታውን ሊያገኝ የቻለውም ቼሪዮን የተባለው ግማሽ ሰው ግማሽ ፈረስ ከሆነው አምላክ እንደሆነ ይነገራል። ብዙ ጊዜ ሥዕሉ ሲሳልም ሆነ ሃውልት ሲቀረጽለት እባብ የተጠመጠመበት ዘንግ ይዞ ሲሆን ይህም ዛሬ ድረስ ለዘመናዊ ህክምና ምልክት ሆኖ ግልጋሎት ላይ ይውላል። በጥንታውያን ግሪኮች ዘንድ የህክምና አዋቂ የሆኑ ሰዎች ሁላ የ አስከሌፒዩስ ደቀመዛሙርት ተብለው ይጠሩም ነበር። የዘመናዊ ህክምና አባት የሆነው ሂፖክራተስም ከ አስከሌፒዩስ ደቀመዛሙርት እንደ አንዱ ይቆጠር ነበር።
ሃይጊያ
ሃይጊያ የአስከሌፒዩስ ልጅ ስትሆን እሷም እንደ አባቷ የጤንነት እና ፈውስ አምላክ ተደርጋ ስትወሰድ ከጤንነት በተጨማሪ የ ንጽህና አምላክ ተደርጋም ትወሰድ ነበር። hygine የሚለው የእንግሊዘኛ ቃልም ከዝህችው አምላክ ስም እና ግብር የተወሰደ ነው። ሃይጊያ የምትወከለው በ ጎርጓዳ ሳህን ሲሆን ይህም የሃይጊያ ሳህን “the bowel of Hygeia” በመባል ይታወቅ ነበር። ይህም ጎድጓዳ ሳህን በላው ላይ እባብ የተጠመጠመበት ነበር። ዛሬ ላይ መድሃኒት መሸጫ መደብሮች እና መድሃኒት አምራች ድርጅቶች እንደ ምልክትነት ይጠቀሙበታል።
እንደ መውጫ
ውድ የባይራ ዲጂታል መጽሔት አንባቢያን እንግዲህ ጥንታዊው የሰው ልጅ የበሽታን መፍትሄ ለማግኘት ሲሞክር ጅማሮውን ያደረገው ለበሽታ ከሰጠው ትርጓሜ እንደሆነ ከላይ ቀንጨብ ቀንጨብ አድርገን ለማሳየት ሞክረናል።
ምንም እንኳን የሚያመልከው አምላክ እና የሚያመልክበት መንገድ የተለየ ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ የሰው ልጅ ጤንነት የፈጣሪ ስጦታ፣ ፈውስም ከፈጣሪ ፈቃድ የሚገኝ እና በሽታ ደግሞ ክፉ መናፍስት የሰውን ልጅ የሚያጠቁበት መሳሪያ እንደሆነ ያምናል።
ማመንም ብቻ ሳይሆን ሁሉም እንደየ ሃይማኖቱ ይጸልያል፣ ይጾማል ይማጸናልም። ነገር ግን የሰው ልጅ በሽታን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት አማልክቱን በመለማመን ብቻ ተወስኖ የቀረ አይደለም። በጊዜ ሂደት ለምግብ የሚሆኑትን እጽዋት በሚያስስበት ወቅት የሚበሉትን እና የማይበሉትን(መርዛማ የሆኑትን) ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹ ዕጽዋት በተለየ ከተለያዩ ደዌዎች ፈዋሽ የሆኑ እጽዋትንም ለማወቅ እና ለመለየት ችሎ ነበር። ይሄ ደግሞ ዛሬ ላይ ባህላዊ ህክምና እያልን የምንጠራውን መሰረቱን እጽዋት ላይ ያደረገውን የህክምና መንገድ እንዲተዋወቅ አስችሎታል። በቀጣይ ዕትም ባህላዊ ህክምና ላይ ያተኮረ ቅንጭብጫቢ ጽሑፍ ይዘን እስክንመለስ ድረስ ቸር ይቆዩን። ለዛሬ ግን በዚሁ አበቃን።
ማጣቀሻ መጽሐፍት
- Cambridge University, 1996, The Cambridge illustrated history of medicine, Cambridge University Press.
- Fielding h. Garrison, 1929, An Introduction to the history of medicine with medical chronology, suggestions for study and bibliographic data, w. B. Saunders Company.
- Walter Addison Ayne, 1962, The Healing Gods Of Ancient Civilizations, Yale University Press.