ተገኑ ጸጋዬ
ታህሳስ 15 ቀን 2016 ዓ/ም በእለተ ሰኞ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ድሬዳዋ ለመጓዝ ፉሪ በሚገኘው የበባቡር ጣቢያ ተገኝተን የባቡሩን መነሳት እየጠበቅን ነው፡፡ ህዝቡ ባብላጫው የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል ላይ ለመገኘት የሚጓዝ ህዝብ ነው፡፡ ጥቂቶቻችን እኔን ጨምሮ የባቡር ጉዞ የመጀመሪያችን በመሆኑ ብርቅ ሆኖብናል፡፡ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካበቢ ሲሆን ወደ ባቡሩ ውስጥ ለመግባት ሰልፋችንን ይዘን በቅድም ተከተል እየተፈተሽን ወደ ውስጥ ዘለቅን። እውነት ለመናገር የባቡር ጣቢያው እጅግ ዘመናዊና ምቾት ያለው ነው፡፡ በመጨረሻም የመነሻው ሰዓት ደረሰና በየወንበራችን ተቀምጠን ጉዞ ወደ ድሬዳዋ ፡፡
በባቡር አይሁን እንጂ በተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች ተጉዤ ድሬዳዋን የማየት ዕድል ገጥሞኝ ነበር። ለምን እንደሆነ ባይገባኘም ወደዚያ ስፍራ ስጓዝ ደስ የሚል ስሜት ይሰማኛል። ቅልል ያለ ስሜት። የናፈቁኝን ቤተሰቦቼን የማገኝ ሁሉ ይመስለኝ ነበር። በአሁኑ ጉዞዬ ግን ለምን ደስ እደሚለኝ በደንብ ተረድቻለሁ፡፡ ለምን አትሉኝም? ሁሉም በነጻነት የሚኖርባት፤ ያለ ስጋት የሚንቀሳቀሱባት፤ ከብሔር ፖለቲካ የፀዳች ከተማ ስለሆነች ነዋ፡፡ በዚያ ላይ የከተማው ከንቲባ የአመራር ብቃት የተላበሰ፣ ትሁት፣ ለህዝብ የቆመ መሪ በመሆኑ ከተማይቱን ሰላማዊ አንድትሆን አድርጓታል፡፡ እድለኛ አይደለች ታዲያ ?
ከንቲባውን በምን ቃለት ላመሰግነው እንደምችል አላውቅም። መሪዎች በብሔር ፖለቲካ በተጠመዱበት አገር ላይ እንዲህ ያለ ስብዕና ያለው መሪ ማግኘት የእውነት መታደል ነው፡፡ ማነው ስሙን የዘነጋሁት የራሺያ ደራሲ “ባጣ በገረጣ ፊት ላይ ኪንታሮት እንደውበት ይቆጠራል” ያለው?
ስለ ድሬ በዘፈን፣ በግጥም አያሌ ሰዎች ውዳሴ አቅርበዋል፡፡ ሳስበው በቂ አይመስለኝም። በአሁኑ ሰዓት አላተሚ ፕሮፖጋንዳ በየቦታው በሚነዛበት ሰዓት ከተለያዩ አገሪቱ ክፍል የመጡ ህዝቦች ተቻችለው እና ተፋቅረው የሚኖሩባት ብቸኛዋ ከተማ ድሬ ብቻ ነች ለማለት ይቻላል፡፡
ጉዞው ረጅም ነው። ቢሆንም ባቡር ላይ ወንበር ከምንጋራው ሰው ጋር የረጅም ጊዜ ትውውቅ እንዳለው ሰው የሚበላውን እየተካፈልን ጉዟችንን ቀጠልን። እንዲውም አብዘኛው ተጓዥ የድሬ የፍቅር መንፈስ የተጋባበት ይመስላል። በነጻነት የቆጡን የባጡን እያወራን ከምሽቱ አንድ ሰዓት መልካ ጀብዱ በሚገኘው የባቡር ጣቢያ ደረስን፡፡
ከዛም እቃችንን ሸክፈን ማረፊያችን ወደሆነው መሐል ድሬዳዋ አቀናን።
ቅልል የሚለው ስሜት ከዚህ ይጀምራል፡፡ የምናርፍባቸው ሰዎች ይቅርታ ዘመዶቻችን የሚለው ቃለ ነው የሚገልጻቸው፤ በፈገግታና በደስታ ተቀበሉን። እኔ እንዲውም አቀማጥላ ያሳደገችን አያቴ ጋር ያረፍሁ ነው የሚመስለኝ።
በሚቀጥሉት ቀናት ከተማዋን እየተዘዋወርን ጎብኘናት። ህዝቡ ተመሳሳይ ጸባይ ነው ያለው። ትህትና! ለመጪውም ለነዋሪውም ተመሳሳይ ጸባይ ነው የሚያሳየው። በፀጉረ ልውጥነት የሚደርስብህ አንዳችም ስጋት የለም፡፡
በእለተ አርብ የቅዱስ ገብርኤልን ዓመታዊ የንግስ በዓል አክብረን ስንመለስ ወደ ድሬ የሚሄዱ መኪናዎችን ፍለጋ ጀመርን። ትንሽ የእግር ጉዞ አንዳደረግን አንድ ፒክአፕ መኪና የያዘ የድሬ ሰው መኪናውን አቁሞልን ተጭነን ወደ ድሬ ገባን። አንዱ የጉዞ ጓደኛችን የኔ ዘመዶች የቅዱስ ገብርኤል ዝክር ስላላቸው ጓደኞችህን ይዘህ እንድንመጣ ተብያለሁ አለን። ሁላችንም በአንድ ድምጽ፡ በአንድ አፍ እሺ አልን።
ጉዞ ወደ ድግስ ቤት። በቦታው እንደደረስን ደጋሿ በታላቅ ትህትና እና ደስታ ተቀበሉን። ወዲያውን ምግብና ጠላ ቀርቦልን በደስታ በላን ጠጣን፡፡ ለጓደኞዬ በጆሮው እንዲህ አልሁት። ለመሆኑ ህዝቡ ትህትናና አክብሮት በስልጠና ተሰጥቶት ይሆን ተመሳሳይ የሆነው? ደግሞ እኮ የምር የሆነ ትህትና ነው ያላቸው አልሁት። እሱም መልሶ በጆሮዬ ገና በሁለት ኩባያ መቀባጠር ጀመርህ እንዴ? አለኝ፡፡
በዚህ መሐል ነው ባልንጀራዬ ከአዲስ አበባ ስልክ የደወለልኝ። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ እንደጠፋሁ ነገረኝ። አክሎም የት ሄደህ ነው አለኝ? እኔም ወደ ትንሿ፣ የጥንቷ ኢትዮጵያ እንደሄድሁ ነገርሁት። ምንድነው የምትለው? ብሎ ደግሞ ጠየቀኝ።
አዎ ትንሿ ኢትዮጵያ ድሬ ነው ያለሁት ብዬ መለስሁለት፡፡ ከጎኔ ያለው ልጅ በስልክ የማወራውን ይሰማ ስለነበር በቃ ሞቅ ብሎሀል ጠላው ይቅርብህ አለኝ። ከልቤ ሳቅሁ። ያሳቀኝ ደስታው ነው። ብዙ አልገባውም። አዎ አሁን ያለሁት ከምቀኝነት የፀዳች፣ ከብሔር ፖለቲካ የነጻች፣ ውቧ ድሬ ከተማ ውስጥ ነው። አላጋነንሁም፣ እውነቱ ይሄ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የጋራ አለመግባባቶች መከሰት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዳተኝነት ይሁን የአገርን ታሪክ በቅጡ አለማወቅ ልዩነታችን እየሰፋ መጥቶ ብሔር ላይ ያተኮረ ቀበሌያዊነት እየተበራከተ መጥቷል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ አካበቢዎች ኢትዮጵያዊነት የሚለውን የጋራ ማንነት የሚጠየፍ ትውልድ እየተበራከተ መጥቷል። ኧረ እንዲያውም የአገሪቱን ባንዲራ ባይናችን አንይ የሚሉም አልጠፉም፡፡
አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ። ከሶስት ወር በፊት በእለተ ሰንበት ወንድሜን ለመጠየቅ ኮዬ ፈጬ የሚባል ቦታ ለመሄድ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ተሳፈርሁ። ትንሽ እንደተጓዝን በአጋጣሚ እዚያው አካባቢ የሚገኝ የአንድ ድርጅት የምርቃት ስነ ስርዓት ስለነበር መንገዱ ተዘግቷል፡፡ እንደምንም ደረስንና አደባባዩን አልፈን ትንሽ መንገድ እንደሄድን የሆኑ ወጣቶች መኪናውን አስቆሙትና መታወቂያ እንድናሳይ ተጠየቅን። ሁላችንም ወርደን መታወቂያችንን አሳየን፡፡ ከተሳፋሪው መሃል ታዲያ አንድ ነጠላ የለበሰ ወጣት መታወቂያ ካሳየ በኋላ እኛ መኪናው ውስጥ ስንገባ ልጁን አስቀሩት። ምንም የገባን ነገር አልነበረም፡፡ ሹፌሩን እንድንሄድ ጠየቅነው። ሹፌሩም ፈታሾቹን እኔ ልሂድ ወይ? አላቸው። ከትንሽ ማቅማማት በኋላ ባለ ነጠላውን አስገቡት። ምክንያቱን ስንጠይቅ ልጁ የለበሰው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለት ያለው ነጠላ ስለሆነ ነው። አምላክ ይወቅ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ ይህ እውነት በዓይኔ በብረቱ ያየሁት ነገር ነው፡፡ ድሬዳዋ ቁጭ ብዬ ይሄ ነው ትዝ ያለኝ።
ለመሆኑ በዚህ ህዝብ መካከል ያለ ክፍፍል እና ልዩነት የትና መቼ ተጀመረ? አንድነታችን የሚንዱ እኩይ አመለካከቶችን ያመነጨው ማነው? እያልሁ ማሳብ ጀመርሁ። በተቀመጥሁበት ሆኜ እንዲህ አወጣ አወርድ ጀመር።
በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ ተጨቋኝ ነን የሚሉ ቡድኖች ለገዢዎቻቸው ፈተና የሆኑባቸው ወቅቶች ነበሩ። እንደምሳሌ የቀዳማዊ ወያኔ በ1935 በተንቤን ተንቀሳቅሰው አመጽ፣ በባሌ የተነሳው የገበሬዎች አመጽ እንዲሁም በጎጃም ገበሬ የተቀሰቀሰው አመጽ ዋናው መንስኤ ገዢዎቻቸው በሚጭኑባቸው ከፍተኛ የግብር ጭቆና ምክንያት ጨቋኙን የገዢውን መደብ ተቃውመዋል። ትግል አድርገዋል። ይኸ ሁሉ ሲሆን በአገራቸው ጉዳይ ግን ቅንጣት አይደራደሩም ነበር። ታሪኩን በደንብ ማንበብ ይቻላል፡፡
ታዲያ ይህንን የመከፋፈልና የማባላት እስትራቴጂ ማን ነደፈው? ካልን መልሱ አልገዛም ያልናቸው ቀኝ ገዢዎች መሆናቸውን እንረዳለን፡፡
እስቲ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን አንዳንድ ታሪኮች እየመዘዝን እንይ። በ1835 የካቲት 2 ማኩሊን የሚባል የእንግሊዝ የመሬት ከበርቴ በፓርላማው ላይ የተናገረውን እንመልከት። ማኩሊን በፓርላመው ላይ የተናገረው እንዲህ የሚል ነበር። “ኢትዮጵያን ለማየት ዕድል ገጥሞኝ አይቻታለሁ። በቆየሁባቸው ጊዜያቶች የሚለምን እና የሚሰርቅ ሰው አላየሁም። እነዚህ ህዝቦች የሰብዕና ሀብት እና የአስተሳሰብ ልዕልና ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ የአይበገሬነታቸው ዋናው ሚስጢር መንፈሳዊና ባህላዊ እሴታቸው ነው፡፡ መንግስትንና ህዝብን ያጋመደችው ደግሞ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነች። እኛ ይቺን ሀገር ቅኝ መያዝ ካለብን ይህን እሴታቸውን መናድ አለብን” ብሎ ነበር፡፡
ለዚህም ለቅኝ ግዛት ባለመመቸታችን ምክንያት ይመስላል 1860 ጀነራል ናፒር የእንግሊዝ እስረኞችን ሊያስለቅቅ በመጣበት ጊዜ መይሳው ካሳ እጄን አልሰጥም ብሎ ጥይት ጠጥቶ ሲሞት ጀነራሉ ዜጎቹን ይዞ፤ የያዘውን መሳሪያ ለመንገድ ተቋሚዎቹ ሸልሞ የተመለሰው፡፡
እዚህ ላይ አንድ ግጥምጥሞሽ ልንገራችሁማ። አጼ ቴዎድሮስ ራሱን ያጠፋበት ሽጉጥ በወቅቱ ከነበሩት የእንግሊዝ ንግስት በስጦታ የተበረከተችለት ነች፡፡
ሌላው የባሩድ በርሜል (Abyssinia: The Powder Barrel By Baron Roman Prochazka) በሚባል ወደ አማርኛ የተመለሰ መጽሐፍ ላይ ኢትዮጵያ ጦርነት የማትሸነፍበትን ምክንያት ሲገለጽ አንደኛ ጠንካራ ዘውዳዊ ስርዓት ስላለት፤ ሁለተኛ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያም ህዝቡንና መንግስት ያስተሳሰረች እና ተቀባይነት ያላት ትልቅ ተቋም መሆኗ፤ ሶስተኛ ሀገሪቱ በምትወረር ጊዜ የሚዋጋው ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደወታደር መሆኑ ትልቅ የአሸናፊነት አቅም ስለሆናቸው ነው ይላል። በጦርነት ጊዜ ነገስታቱ ታቦት ይዘው እንደሚዋጉ ልብ በሉልኝ። ህዝብና መንግስት መጋመድ ማለት ይሄ ነው፡፡
ሌለውን የነጮች ሴራ ደግሞ እንመልከት። አሜሪካ ከንጉሱ መውረድ በኋላ ኢትዮጵያን በማጣቷ የጎነጎነችውን ሴራ በእቅድ እንዴት እንደፈፀመችው እንይ፡፡ አሜሪካ በኤርትራ ምድር ነበራትን የጦር ማዘዣ በደርግ መንግስት ተነጥቃለች። በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ልትከተለው የሚገባውን ፖሊሲ በግልጽ አስቀምጣለች፡፡ ይሄ በ1972 በሄነሪ ኪሲንጀር የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ በሆነው ግለሰብ በ Theodore M. Vestal የተጻፈው “The Lion of Judah in the New World: Emperor Haile Selassie of Ethiopia and the Shaping of Americans’ Attitudes toward Africa” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡፡
“ኢትዮጵያ ውስጥ ልንፈጽማቸው ከሚገቡ ነገሮች ውስጥ የመጀመሪያው የእርስ በእርስ ግጭት መፍጠር፤ ሁለተኛው የሀይማኖት ግጭቶች መደገስ” የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ለዚህም መሳካት ብሔር ተኮር የሆኑ ድርጅቶችን ማስታጠቅና መደገፍ ቀዳሚ ተግባራቸው ነው። ለዚህም ነው ብሔር ተኮር የሆኑትን ወያኔን፣ የሻቢያን እና የኦነግን ድርጅቶች በከፍተኛ ደረጃ ስትደግፍ የነበረው፡፡
አሁን ባለንበት የፖለቲካ መመሰቃቀል የውጪ ሴራ እንዳለበት በጥቂቱ ያየን ይመስለኛል።
ቀጥሎ ደግሞ የዘውዳዊ ስርዓትን የገረሰሰውን አብዮትና የአብዮቱ አራማጆቹ ያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ በጥቂቱ እንቃኝ። ኢህአፓ ፣ መኢሰን፣ አዲዩ ወላ ኢጫት ሁሉም ማለት ይችላል በአገራቸው የሚደራደሩ አልነበሩም። ትግላቸው ስርዓቱን ማስወገድ ብቻ እና ብቻ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል ሳይግባቡ ሳይደማመጡ ሲደናቆሩ የወታደሩ ቡድን ትግላቸውንም ድሉንም ቀማቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በሌላ ጽሑፍ እመለሳለሁ፡፡
የተነሳንበትን ነጥብ እንዳትዘነጉ ታዲያ። የብሔር ፖለቲካው የጦዘው እና ላለንበት ደረጃ እንዲደርስ ጅማሬው መቼ ነው? መነሻ ስፍራውስ? ብለን መጠየቅ ይገባል፡፡ ይሄ በሶሻሊስት አገሮች ይቀነቀን የነበረው በተለይ እነ ጆሴፍ ስታሊን ያራምዱት የነበረው የብሔር እኩልነትና የራስን እድለ በራስ ለመወሰን እስከመገንጠል የሚለው ጽንሰ ሀሳብ በአ/አ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መስተጋባት ጀመሮ ነበር፡፡
ለምሳሌ 1962 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሲጀመር ተማሪዎች ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸው መረጋገጥ አለበት ብለው ተቃውሞ አስነሱ። መንግስትም አጻፋዊ ምላሽ መስጠት ጀመረ። በዚህ ተቃውሞና ግጭት ምክንያት ታህሳስ 19 የተማሪዎች መሪ ጥላሁን ግዛው በአደባባይ ተገደለ። በተለይ የብሔር ጭቆና ነበር በሚል ጽኑ ሀሳቡ የሚጠቀሰው ዋለልኝ መኮንን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበረ፡፡
እነዚህ ወጣት አብዮተኞች ትግላቸው ሳይቋጭ ተናጭተው ተነታርከው መግባባት ላይ ሳይደርሱ ወቴው (ወታደር) የወጣቶቹን ሀሳብ የራሱ አድርጎ ዙፋኑን ተቆጣጠረው፡፡ ልብ አድርጉ የብሔር ፖለቲካ ሰርቶ ማሳያ ፕሮጀክት መቼ እንደተጀመረ ለማየት ተቃርበናል። ትንሽ ታገሱ።
ታሪኩ እንዲህ እያለ ይቀጥልና ደርግ በድንገት ያለዝግጅት ያገኘውን ወንበር ለማስጠበቅ ጠበንጃውን መተማመኛ አድርጎ ወሰደ፡፡ ቀጥሎ የተማሪው ሀሳብ የነበረውን የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ለመተግበር ሞከረ። ይሁን እንጂ የውጭ ጫናውን መቋቋም አቅቶት ለ17 ዓመት በጉልበት ቢገዛም ሳይወድ በግዱ ስልጣኑን መልቀቅ ግድ ሆኖበት ለቀቀ፡፡
ይቀጥላል የእኛ ታሪክ——
ደርግን ያስወገደ የኢህአዴግ መንግስት ቤተ መንግስት ገባ። የብሔር ብሔረሰቦች ግጭት ሰርቶ ማሳያው በግልጽ ተጀመረ። መጀመሪያ የኢህአዲግ ከፍተኛ ባለስልጣኖች የአ/አ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ሰብስበው ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ነው ያላት ብለው እርፍ። ይህንን ድፍረት የተናገሩት ግለሰቦች ስም መጥቀስ አስፈላጊ ስላልሆነ ትቼዋለሁ፡፡
ይቀጥላል—-
አንባብያን ከድሬ ተነስቼ እዚህ ደርሻለሁ። ሀሳቤን አላበቃሁም። በሚቀጥለው ጽሑፍ እንገናኝ፡፡
ቸር እንሰንብት! ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!