አይተነው ንጉሤ
ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ እና ከዚያም በላይ ዘመናት ታሪክ ባለቤት ናት ቢባልም፥ በጣት ከሚቆጠሩ ታሪካዊ ከተሞቿ ውስጥ አብዛኞቹ የተመሰረቱት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ነው። ከተሞች የተመሰረቱት ለገዢዎች የግዛት ማስፋፋትና ማስገበር የሚስማሙ ምቹ ቦታዎችን በመምረጥ ነው። የግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች ለሚቆረቁሯቸው ከተሞች ወይም ለሚቀመጡባቸው ነባር ከተሞች ድምቀት የሚሆኑት የሚያሳንጿቸው ቤተ-መንግስቶች ውበትና የሚመርጧቸው ቦታዎች ናቸው ። ከእነዚህ ከተሞች መካከል ራስ ሚካኤል (የኋላው ንጉስ) በ1875 የቀድሞ ዋና መቀመጫቸውን ተንታን ትተው ወደ ቆረቆሯት ከተማ፥ የዛሬዋ የወሎ መዲና ወደ ሆነችው ደሴ አምርቻለሁ። እነሆ የግል ምልከታዬን ላካፍላችሁ።
ደሴ በንግድ የተጨናነቀች ሁለተኛዋ መርካቶ ነች። የሰሜን መተላለፊያ፥ የኡለማዎች መፍለቂያ፥ ለዝየራ የአረብ ገንዳ ማዝገሚያ፥ መርሳ አባ ጌትየን መማፀኛ፥ የግሸን ማዝገሚያ፥ ወደ ፅዮን መቃኛ ልዩ ድባብ ፈጣሪ ናት። የኪነት እምብርት፥ ወደ መቅደላ ማዘቅዘቂያ፥ ወሎ ደሴ የቆንጆ መፍለቂያ፥ የሙሀባዎች መዲና፥ የፍልቅልቅ እናቶች መንደር፥ የልበ ቡቡ አባቶች መስክ ነች።
ደሴ ቀዝቃዛ ነች። ዙሪያዋን የከበቧት ተራሮች በክንፎቻቸው ሸፋፍነው እንደ ሙሽራ አጅበዋታል።
ጀንበር ዘቅዘቅ ስትል ወደ ጄሜ ኮረብታ አቀናሁ። ጄሜ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ በእይታ ቁጥጥር (አልፎ በቅርብ እርቀት ያሉ አካባቢዎችን በግልፅ ለማየት) ስር ለማዋል ሁነኛ ቦታ ነው። የንጉሥ ሚካኤል ቤተመንግሥት “አይጠየፍ አዳራሽ” መገኛም ነው።
ጉልበት ያዝ የምታደርገውን አቀበት መውጣት ስጀምር የከተማዋን ጓዳ ጎርጓዳዋ ቁልቁል እያየሁ አቀበቷን ጨርሸ ከቤተመንግሥቱ በር አረፍ አልሁ። አካባቢው አመሻሽ ላይ ልዩ መስህብ አለው። ከታች ከወደ ባቲ አቅጣጫ በቀስታ ሽው እያለ በስሱ የሚነፍሰው ዳሳሽ ነፍስ ውስጥን ያሞቃል። በከተማዋ ላይ ደልገመን ጥሎ ለእጅ ሰላምታ የቀረበውን የጦሳ ተራራን እስከ አዝዋ ገደል በእልፍ ሸንተረራማ ተፈጥሮ የታጀቡ ሁነቶችን እያስተዋሉ ከራስ ጋር የሚያወጉበት ነው።
ዝቅተኛ ቦታዎች ከታች የአፋር በረሃ፥ የበረሃ ገነት ገመገሞች፤ ከባቲ እስከ ገራዶ መውጫ በጀምበር ግባት ፀአዳ ውብ መስክ የነፍስን ትህፍስት መቃመስን የሚሰጥ ልዩ ቦታ ነው።
አባ ሻንቆን[1] አሰብሁት (በጉዞና ስራ የዛለ ሰውነቱ) እዚህ ቦታ ሲቆም ምን ያህል ውስጣዊ ድባብ እንደሚፈጥርለት ያውም በዛ ጀግንነት ንጉሥነትን ደርቦበት ስለ እሱ እኔ ፈገግሁ።
[1] የንጉስ ሚካኤል የፈረስ ስም
ዙሪያ ገባውን በመስገብገብ እየቃኘሁ ወደ በሩ አመራሁ። ቤተመንግሥቱ ዙሪያውን በነጭ ግንብ ታጥሮ ነጭ ሽቦ ተጨምሮ ቢያዝም ያ በኖራ እና በእንቁላል የተለሰነ (ልስን) ግንብ መደረማመስ ጀምሯል። ከጥበቃ ነፃ ነው። ግርማው ግን አሁንም አልሸሸውም። በሩን ላልፍ ስል ቆምሁ። ሰውነቴን የሚነዝር ስሜት ተሰማኝ… በሀሳቤ ሸማ ጣል ያደረጉና ጦር ከጋሻ ያነገቱ ግራ ቀኝ ቀጥ ብለው የቆሙ ዘቦችን እያሰብሁ ሰፊውን ጉበን ተራምጀ ወደ ውስጥ ገባሁ።
ቤተመንግሥቱ ከተገነባ 140 ዓመታትን ደፍኗል። እድሜ ጠገብነቱና ወናነቱ ወደ እርጅና ቢወስዱትም ግርማ ሞገሱ ግን አልተገፈፈም። የተሰራበት ውብ የስነ-ህንፃ ጥበብ በግርምት እጅን አፍ ላይ ያስጭናል። ከሌሎች በተለየ ሁኔታ የተንጣለለው አይጠየፍ አዳራሽ የግብር ማብያ ሲሆን ከ3000 ሰው በላይ የመያዝ አቅም አለው። በጊዜው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለምርጫ ያስተናግድ ነበር። የአይጠየፍ አዳራሽን ጣራ ጠፈጠፍ መውረጃ ስንመለከት፥ በአንድ ጎኑ ያለው ጠፈጠፍ(ጣራ) ያጠራቀመውን የዝናብ ውሃ ለአዋሽ ገባሪ ወንዞች ሲያዋጣ በሌላኛው ያለው ደግሞ ለአባይ ገባሪዎች ጀባ ይላል።
ቤተመንግስቱን ናፍቀውት እንደሰነበቱ ህፃን ልጅ ሁሉ አይቸም ዳስሸም አልጠግበው አልሁ። የሆነ ጊዜ አብረን የቦረቅን(የቦረቅንበት) ከዚያም ለብዙ ዘመን ተነፋፍቀን እንደቆየን ባልንጀራ ያለ ስሜት …. ። አሳዘነኝ! ብቻውን እንደቀረ ብቸኛ ሰው፥ ወይም በሰው መንጋ መካከል ሁኖ ሰው እንደመራብ (መናፈቅ)…. መሸሸጊያ ጥግ ያጣ መሰለኝ። “እሸሸግበት ጥግ አጣሁ”[1] እንዳለው ሎሬቱ አፍ አውጥቶ ባይናገርም መሸሸጊያ ጥግ ማጣቱን መራቆቱ ይናገራል። አዳራሹ አንድ ፕሮግራም ቀርቦበት ሳይጠረግ የቀረው ጉዝጓዝ አርቲ፣ጠጀ ሳርና ቄጤማ ተዝረክርኮ ወለሉን ሞልቶታል።
አባ ሻንቆ ያንን ዠርጋዳ ሽንጡን ያዝ አድርጎ የተንጎማለለበትን ግቢ ያለ ከልካይ ከታች እስከ ላይ ዋኘሁበት። ከውብ መታጠቢያ ገንዳዎች እስከ ልጅ እያሱ እልፍኝ፥ ከችሎት መሰየሚያ እስከ ጸሎት ቤት፥ ከማድ ቤት(ከምግብ ማብሰያ) እስከ መኝታ ቤቶች፥ከእንግዳ መቀበያ የምድር ቤት እስር ቤት ድረስ….።
በየ ጥጋጥጉ ያሉ ቄንጠኛ የዚያ ዘመን ብቻ ሳይሆን አሁንም ታይተው የማይጠገቡ ቤቶች መሰረቶቻቸው እየከዳቸው መደረማመስ ጀምረዋል። ባለ ጥዑም መአዛ ምግቦች እየተሰሩ የሚወጡበት የምግብ ማዘጋጃው አፈር ከድሜ በልቶ ወደ አመድነት ለመቀየር ከአንድ እንቁጣጣሽ የበለጠ እድሜ አያሻውም። ያኔ ለመንካት የሚያሳሱት የመታጠቢያ ገንዳዎች ንጣታቸው አሁንም ለእያሱ እንደተዘጋጁበት ዘመን ቢሆንም፥ ከቦታቸው ተነቃቅለው የውሃ መተላለፊያቸውና መመጠኛቸው ወላልቆ ሸረሪት አድርቶባቸዋል።
ታስሮ ውሎ የተራበ በሬ ተፈቶ ወደ ብዙ ሳር እንደተለቀቀ ዓይን አዋጅ ሁኖብኝ ከላይ ታች እየሮጥሁ የራሴን ዘመን ትውልድ ናቅሁኝ። አቧራቸውን አራግፎና ለቱሪስት ምቹ አድርጎ አገርን ከማስተዋወቅ ባሻገር ገቢ ማስገባት ሲቻል…………….። ግን ለዚያ የሚያበቃ ለስራ የታጠቀ ወኔ አይሸመት ነገር።
በእንደዚህ አይነት ውብ የተፈጥሮ ገጸ-በረከት የታደለ ቦታ ላይ ሰርተው ያወረሱንን ቅርስ ማደስ ባንችል ማፅዳት እንደት ተሳነን? ቢሮ ወንበር ሲያሞቅ የሚውለውን የቱሪዝም ዘርፉን ትተነው፥ እዛው ኮረብታ ስር ከቧንቧ ውሃ እስከ አረብ ገንዳ ድረስ ተደርድሮ የሚውለው ወጣት ባለ ትኩስ ጉልበቱ “ጦሳ ተራራ” ላይ ውብ ቤተመንግሥት መገንባት ቢሳነው እንዴት አይጠየፍን መጥረጊያ ሞራል አጣ?
ከቤተመንግስቱ ጋር ተያይዛ የተሰራችውን ቤተክርስቲያን ለመሳለም ወደ ቦታው የሚመጡ ምዕመናን፥ ከጸሎት በኋላ ወደ ቤተመንግሥቱ ውስጥ ጎራ ይላሉ። ከአድማስ አድማስ በሀሳብና በእይታ እየተጓዙ ለማብሰልሰልም ገብተው አረፍ ይላሉ። ከእዚያ ባሻገርነት ያለውን ጥቅም ግን የተረዳ ያለ አይመስልም። በእጅ የያዙት እንዲሉ……..።
የከተማውን በሰው መከበብ የሸሹ ጥንዶች ወደ ኮረብታው ጎራ ይላሉ። ከታች ከበረሃው ከአፍደራ እየተነሳ በስሱ ሽው እያለ የሚነፍሰውን ውብ ነፍሻ አየር እየማጉ ውብ ውብ የፍቅር ቃላትን ተወራውረው ቁልቁለቷን ያዘግማሉ።
አይጠየፍ ቤተመንግሥት ግን ከቀን ወደ ቀን እንደ አዛውንት ጉልበቱ እየደከመ ወደ ነበር ማዝገሙን ከጀመረ ቆይቷል።
* * *
እየተስለመለመች በመጥፋት ላይ ያለችውን የሚያዝያ ጀንበር ከምህዋሯ ጀምራ እስከ አይጠየፍ ስር የለቀቀችውን ክበቧን እያየሁ፥ ልብን የሚያጠግብ የምህዋሯን ውበት ሳትሰበስብ፥ እንባ እየተናነቀኝ ጉልበቴ ስብር ስብር እያለ ጀሜን ወደ ኋላ ትቼ ቁልቁለቱን መውረድ ጀመርሁ።
አይጠየፍን አይቼ የእኔን ትውልድ በመጠየፍ በቀረችኝ ምሽት የተዘጋ በሩንም ቢሆን ለማየት ወደ ወይዘሮ ስሂን አመራሁ ።
[1] ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን (ሰቆቃዎ ጴጥሮስ)