በአያ ሙሌና በራቢንድራናት ታጉር (Ravindranath Tagore)
የአፍታ ዳሰሳ
ውብአረገ አድምጥ
ተማኅልሎዓዊነት (Mysticism) አንዳች መለኮታዊ ሃይልን ወይም ታላቁን ፈጣሪ በአርምሞና የስጋ ፍላጎቶችን ችላ በማለት ፈጣሪ ዓለማቱን፣መጋቢ ፍጥረታቱን የማሰስ የነፍስ ህቅታ ነው። ከሃገራችን ገጣሚዎች ውስጥ መንፈሱን በአንዳች መቃተት ውስጥ ያሳለፈ የምድርን ጣዕመ ህይወትም እንደ ኢምንት ቆጥሮ እንዳለፈ የሚነገርለት ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ ነው። በእኔ ትንሽ መረዳት የህንዱ ባለቅኔ ራቢንድራናት ታጉር ( Ravindranath Tagore) ተመሳሳይ መማለሎች እንዳሉት ለማየት እንሞክር እስኪ። ከሁሉ አስቀድሞ ግን ስለሁለቱ ባለቅኔዎች ትንሽ ብለን እንጀምረው እንጂ።
ትውቂያ
ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ)
ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ ሚያዝያ 1946 ዓ፡ም ተወልዶ ሃምሳ ዓመታትን ከተንከራተተ ብሎም ከተመሰጠ በኋላ በነሐሴ 1996 ዓ፡ም ይህቺን ስጋዊ ዓለም ተሰናበተ። እስካሁን ድረስ የታተሙ “የባለቅኔ ምህላ” እና “የነቢያት ጉባኤ” የተሰኙ የግጥም መድብሎች አሉት። በተለያዩ ግለሰብ እጆች ውስጥ የተጠራቀሙና በግምት ከ1000 በላይ ግጥሞች እንዳሉት ጭምጭምታ ይሰማል።የመጀመሪያ ልጁ የሆነው ሼህ አብዱ ሙሉጌታ (ዳንኤል ሙሉጌታ) እና ስንዱ አበበ የባለቅኔው ብዙ ግጥሞች የትም ተበታትነው እንደቀሩና በአንዳንድ ግለሰቦችም እንደተሰረቁ አልደበቁም። በህይወቱ ላይም የተጻፉ “የባለቅኔው ኑዛዜ” እና “ኢትዮጵያዊነት እምነት” የተሰኙ መጻሕፍት አሉ። በ1991 ዓ፡ም ከፈርጥ መጽሔት ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ደራሲ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ “ፍልስምና ዓራት” በሚሰኝ ቅጹ ውስጥ አጠቃሎታል።
ባለቅኔው እጅግ በጣም ብዙ የዘፈን ግጥሞችን ለታዋቂ እና ጀማሪ ድምጻውያን ማበርከቱም አይካድም። ለእነ ጸደንያ ገብረማርቆስ፣ ሃና ሸንቁጤ፣ አበበ ተካ፣ አበበ ብርሃኔ፣ ብጽዓት ስዩም፣ፍቅራዲስ ነቃጥበብ፣ ይሁኔ በላይ፣ ጃን ስዩ ሄኖክና ለሌሎችም ድምጻውያን ያበረከታቸው እልፍ ግጥሞች ዛሬ ድረስ የአድማጭን ስሜት እንደኮረኮሩ ናቸው።
ባለቅኔው በዘመኑ ባለው የህይወት አረዳድ እንደ ኢምንት ተቆጥሮ ያለፈ ነበር። ብዙዎቹ እንደሚንቁት፣ ብዕሩን ሊሸቅሉበት እንደሚፈልጉም በህይወት በነበረበት ወቅት ተናግሯል። የሰው ልጅ ቅዱስም ንጉስም ሊሆን ነውና የተፈጠረው እኔም እንዲያ ነኝ ይል ነበር። አዎ ቃሉ እውነት ነው፣ ቅዱስ ነበር! በሰዎች ህያው ልብም ውስጥ ንጉስ ነው የሚሉ ቋሚ ምስክሮች አሁን ድረስ አሉ። በልብ ላይ የሚነግስ ደግሞ መለኮት ነው። ታዲያ የባለቅኔ መስተካከሉ ከመለኮት ሃገር አይደለምን?
ራቢንድራናት ታጉር ( Ravindranath Tagore)
ራቢንድራናት ታጉር ( Ravindranath Tagore) ታላቅ የህንድ ገጣሚ ነው። በተወለደባት ቤንጋል ስሙ ህያው ነው። ከ 1861-1941 እ.አ.አ ለ80 ዓመታት በህይወት ኖሯል። ለመጀመሪያ ጊዜ Gitanjali ተብሎ በተጻፈውና በራሱ በገጣሚው Song of Offerings በሚለው ወደ 106 ግጥሞች በተካተቱበት የግጥም መድብሉ የ 1913 እ.አ.አ የስነ ጽሑፍ ኖብል ሽልማትን (Noble prize in Literature) ወስዷል። በዚህም ግጥም የታላላቅ ገጣሚያንን ቀልብ መሳብ ችሏል። በህይወቱ ከእነ Albert Einstein, Robert frost, Thomas Mann, George Bernard Shaw, H.G Wells ጋር ለመገናኘት ችሏል። በተለይ ከታላቁ የፊዚክስ ሊቅ Albert Einstein ጋር በዘመኑ በነበረው Quantum mechanics ጉዳይ ያደረገው ክርክር አይዘነጋም።
ታጉር ከ1000 በላይ ግጥሞችን በትውልድ ሃገሩ የአፍ መፍቻ ቋንቋው በ ቤንጋሊ ቋንቋ (Bengali Language) ጽፏል። ወደ 2230 የሙዚቃ ግጥሞችን ደርሷል። ዜማዎችንም አቀናብሯል። ስምንት ታላላቅ ልብ ወለዶችን፣ ስምንት የአጭጭር ልብ ወለድ ስብስቦችን፣ ስድስት ኖቬላዎችን(ቤሳ ልብወለዶችን)፣ ከሁለት ደርዘን በላይ ቴአትሮችን ጽፏል። ሙዚቃዎችን በራሱ ተጫውቷል። በተውኔቶች ላይ አብሮ ተውኗል። ብዙ የፍልስፍና ጽሑፎችን እንዲሁም ዲስኩሮችን አዘጋጅቷል። በአምስቱም አህጉራት ከ30 በላይ ሃገራትን በመዞር ትምህርቶችን ሰጥቷል። ታጉር የባንግላዲሽንና የህንድን ብሔራዊ መዝሙር በማዘጋጀት በአንድ ጊዜ ለሁለት ሃገራት ብሔራዊ መዝሙሮችን ማዘጋጀት የቻለ ብቸኛው ሰው ነው።ላበረከተው የስነጽሑፍ አስተዋጽኦ በ1915 እ.አ.አ ከእንግሊዙ ንጉስ ጆርጅ አራተኛ (King George V) ታላቁን የክብር ሽልማት (Knight ship) ተቀብሏል። ነገር ግን የእንግሊዝ ወታደሮች በህንድ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊ ግለሰቦች ላይ በፈጸሙት ግድያ ታጉር የተቀበለውን ማዕረግ በ1919 አውርዷል። በወታደሮች ጥቃት ወደ 400 ንጹህ የህንድ ዜጎች ሲገደሉ ከ400 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለው ነበር ነው።
ተኅማልሎ ወ ተመሳስሎ
የአያ ሙሌና የታጉር ህይወተ ጥበብ ጥቂት የማይባል ተመሳስሎት አለው።
ሁለቱም በዘመናቸው በፖለቲካ ውስጥ የተሳተፉና ከታላላቅ የሃገራቸው ፖለቲከኞች ጋር ግንኑነት ያበጁ መሆናቸው ነው። ታጉር እና ማህተመጋንዲ የቅርብ ጓደኖች ነበሩ። በአንዳንድ ሃገራዊ አረዳዶች ላይ ተቃርኖ ቢኖራቸውም በህንድ ነጻነትና የሰው ልጅ እኩልነት ግን አይደራደሩም ነበር። በህንድ የተደረገውን ጭፍጨፋም አብረው ነበር ያወገዙት። ታጉር ለህንድ ነጻነት የታገለ፣ ከማህተመ ጋንዲ ጋር እኩል ለሃገሩ የተዋደቀ ባለቅኔ ነበር። ሃገሩም ለዚህ ህያው አስተዋጽኦው ክብሯን ከመቸር አልተቆጠበችም።
የሃገራችን ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬም ከኢህአዴግ ጋር ግንኙነት ነበረው። ።”የምደግፈውም የምቃወመውም ኢህአዴግን ነው” ይል ነበር። “ሲያጠፉም አልለቃቸውም!” ማለቱን በአካል የሚያውቁት አጫውተውናል። በተለይ ከበረከት ስምኦን ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበራቸው። እንዲያውም ከበረከት ስምኦን ጋር የሚገርም ገጠመኝ አላቸው።
አያ ሙሌ እንደ የኔ ቢጤ ወደ ጎዳና ሲወጣ ሴት ልጁ 10 ዓመቷ ነበር አሉ። በረከትም የእውቀት አድናቂ ነው ይላሉ። ታዲያ የአያ ሙሌን ወደ ጎዳና እየወጡ ሲንከራተቱ መዋል አልፈለገውም። ሁሌ ወደ ጎዳና እየሄደ ተመለስ ወደ ስራህ ይለው ነበር። ታዲያ አንድ ቀን በረከት አያ ሙሌን ለማሳመን እንዲህ ይለዋል። “ህጻን ልጅህ እንኳን አታሳዝንህም? ትንሽ ልጅ ያለ አሳዳጊ ትተህ መውጣትህ ደግም አይደል” ይለዋል። “ትንሽ ልጅ እኮ አይደለችም። አንተን አንድ ዓመት ትበልጥሃለች።”ብሎ መለሰለት አሉ። ለምን እንዲህ እንዳለው እስካሁን ግልጽ ባይሆንም ቅሉ።
ሁለቱም መንፈሳዊያን ናቸው። አያ ሙሌ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ነበር። ብዙ ግጥሞች ላይ የዚህ ጫና ይታይበታል። ሁሉንም ሃይማኖቶች ለማወቅ እንደሞከረ ራሱም አልካደም። በሚስጥረ ስጋዌ፣ በሚስጥረ ድኅነት እንዲሁም በነገረ መስቀሉ ላይ ትልቅ ተማልሎ ነበረው። ለዚህም እንዲህ ሲል ነገረ ክርስቶስን ይቀኝበታል።
“ቃል”
ካስራ ሁለት ዓመት በላይ ያለን ነገር
ፍቅርና ወሲብ የራሱን ይናገር
ሌላው ሳይጋገር
ውበት ሻተኝና ጦም ጀመርሁ እንደ ቀልድ
ጉልበት እንዳያንሰኝ ሰገድሁ እኔን ልወልድ
ለካስ በጸሎት ውስጥ ቃል ኖሯል አበ ወልድ።
በሌላ ቦታ ላይም
“ቃል ሆኖ ተፈጥሮ
ቃል ሆኖ ሞት ሽሮ
የዘላለም ንጉስ በቃል ተሞሽሮ
ቃልማ ፊርማ ነው የሰለሞን ማህተም
እንደጉም ደመና እንዳሻው የሚተም”……………….
እያለ የቃልን ነገር፣ የአምላክን ሰው መሆን፣ የክርስቶስን ህይወት ሰጪነትና ሚስጥር በተመስጦ ይፈክራል።
በዚያ በኩል ታጉር ደግሞ በባክህቲ (Bhakti) እምነት ወይም ባህል ላይ ተመስርቶ ፈጣሪ ዓለማት ብሎ የሚያምነውን ይለማመናል። Misha Kandhari እንዲህ ትላለች ስለ ጊታንጃሊ የግጥም መድብሉ። “Gitanjali are the reminiscent of a great Indian tradition called the Bhakti tradition.”
በሰባተኛው ክፍለዘመን እንደተስፋፋ ይነገራል ይህ የባክህቲ እምነት። በውስጡም ሁለት ዘርፎች አሉት። አንደኛው Nirguna bhakti ሲባል ሌላኛው ደግሞ Saguna Bhakti።
ታጉር ይከተለዋል ተብሎ የሚታሰበው Nirguna bhakti አምላክ “ቅርጽ የለሽና” በውስጣችን ያለ አንዳች ሃይል ነው ብለው ያምናሉ። በፍቅርና ራስን አሳልፎ በመስጠት ውስጥ ይሄን ህያውና በጽንፈዓለሙ የሞላውን አምላክ ማገልገል እንደሚቻልም አምነው ይተገብሩታል። የገጣሚያንና የሙዚቃ ተልዕኮም ይሄን ሃይል ማገልገል ነው ትላለች ሚሻ።
(Nirguna bhakti, God or the supreme power was a formless energy or force that had to be deeply felt and realized. These poets spoke of everyday activities as a service to God. They believed in love and surrender and in universal religion.
አንተ ብቻ “Only you“የሚል ርዕስ ባለው ቅኔው ታጉር አንተ ብቻ ነህ ሁሉ ነገሬ ይለዋል። ምን አይነት መሰጠት ነው? ምን አይነት ራስን አሳልፎ እንደ አምሃ ማቅረብ ነው? ምን አይነት የጽንፈዓለሙን ቡጥ መሻት ነው?
That I want thee, only thee—-let my heart repeat without end.
All desires that distract me, day and night, are false and empty to the core.
As the night keeps hidden in its gloom the petition for light,
even thus in the depth of my unconsciousness rings the cry
—-`I want thee, only thee’.
ሌላው የዚህ የተማልሎአቸው መገለጫ ደግሞ አምላካቸውን ለመንካት የሚያደርጉት መንጠራራት ነው። የባለቅኔ ከፍታው ከመለኮት መተካከል ነው ቢሉ ማጋነን አይሆንም። ሰብአዓለሙንና ፍጥረታቱን በሙሉ የሚያንቀሳቅሰውን ሃይል ለመጎናጸፍ ስጋን ማጎስቆል የሁለቱም ባለቅኔዎች መንገድ ይመስላል። ለዚህም ነው አያ ሙሌ ነገር ዓለሙን ሁሉ ትቶ እንደማንም በመንከራተት ያሳለፈው። ከአለቤ ሾው ቀርቦም ሳይበላ፣ ሳይጠጣ፣ ወሲብ ሳያደርግ መኖር እንደሚመኝ በአንደበቱ መስክሯል። ግጥሞቹም ያንን ያሳያሉ። ስጋውን ክዶ በመንፈሱ ከመለኮት ለመደራረስ በሚያደርገው ህቅታ ውስጥ የሚከተሉትን የጭንቅ ቃላት አውርዷል።
የባለቅኔው ምህላ በሚል የራሱን ህይወት አዙሮ በፈከረበት ግጥሙ ያሉትን ስንኞች ለአፍታ መመልከት እንችላለን።
“የማይሰፈር ስለካ፣ ከማይቀመስ ስፎካከር
እሰጥ አገባ ስጎሰጥ፣ ጉንጭ አልፋ ስከራከር
እየመሸ እየነጋብኝ፣ ዓይኔ እያየ ዘጋብኝ።
ችዬ አልችልም ብቻዬን፣ አልጸናም ባንድራሴ
ድሃ አደግ ምን ቢተባ ፣ አይደምቅም እንደ እንደራሴ
በእምርታህ በይቅርታህ ማርከኝ፣ እንደ እዝነትህ እንደ ቸርነትህ ባርከኝ
ኤሎሄ ኢላሄ፣ ምሉዕ በኩለሄ
ዕለተ ሞቴን አታስረሳኝ፣ ወንፊት እንጂ እንባ አትንሳኝ’።…………………….
እያሉ የሚዘንቡት የቃላት ቆሎዎች የከያኒውን መንፈስ ፍትጊያ የሚያሳዩ መማለሎች ናቸው። ከህይወቱ ባሻገር ሞቱን እንዳያስረሳው ይለማመናል። እንደ ደቹ impressionist ሰዓሊ ቪንሰንት ቫን ጎህ (Vincent van Gogh) What is certainly true in this reasoning is that while we are alive we cannot go to a star, any more than, once dead, we could catch a train እያለ ሞትን የሚለማመን ይመስላል።
ሌላው የመንፈስ ተንከራታችና ባለቅኔ ታጉርም “Give Me Strength” በሚለው ግጥሙ እንዲህ ይቃትታል። ብርታቱን፣ ጉልበቱን አምጣ ይለዋል። አንተን የምወድበት፣ ከልቤ ሰሌዳ ላይ አይጨበጤ ማንነትህን አውለው ዘንድ ጥንካሬውን ስጠኝ ይለዋል። ከዕለታት መነከላዎስ ባሻገር እመለከት ዘንድ ና ወደ እኔና ጉልበትህን አስርጽብኝ ይለዋል።
Give me the strength to make my love fruitful in service.
Give me the strength never to disown the poor or bend my knees before insolent might.
Give me the strength to raise my mind high above daily trifles.
And give me the strength to surrender my strength to thy will with love.
በምድር ላይ የሚያደርገውን አሰልቺ ህይወት ይታዘበዋል። አያ ሙሌ የስጋን ጉልበት ሊሽር፣ የኑሮን ቀዳዳ ሊሸነቁር ከመለኮት ቤት እንግዳ ሆኖ ሊታደም አንድ በለኝ እያለ ይጎተጉተዋል። በእውነት መንገድ ምራኝ፣ የብርሃናትን መስኮት አመላክተኝ ይለዋል። ብርሃን አይጨበጥም። ብርሃን አይመረመርም። ታዲያ ታላቁን ብርሃናማ መንገድ መሻት የባለቅኔ እጣ ፋንታ አይደለምን?
አንድዬ!
ቤት ለእንግዳ በለኝ፣ በእመ አምላክ
ቤት ለእምቦሳ እንድል፣ በምስራቅ በር
ከጥሬ ዱለት አላለፈም
የእኔ ያልሁት ምላስ ሰንበር…………………
ታጉር Strong Mercy በሚል ልመናው ይቅርታውን፣ እምርታውን ያላብሰው ዘንድ ያን የፍቅር አምላክ በፍርሃት ይለማመነዋል። ወሰራ ዶሮ ሳያርድ፣ ከዛፍ ስር ወድቆ እየተነሳ ሳያለቅስ እንዲሁ በቃላትና በዜማ የምህረትን ዣት ይጠብቃል።
My desires are many and my cry is pitiful, but ever didst thou save me by hard refusals; and this strong mercy has been wrought into my life through and through.
ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ አስምአኒ በሚለው የጸሎትና የምህላ ግጥሙ እንዲህ እያለ ይቃትታል።
አስምአኒ!
ከጌታ ሰማኒ፣
ህያዊት–ለባዊት ነባቢት፣ ነፍሴ ጋር አስታርቀኝ
እኔም ጠፍቼ እንዳልባክን፣ አንተም እንዳትርቀኝ
አንተ ብቻ በውስጤ ከብረህ፣ ስላንተ ብቻ እንድመሰክር
ላክልኝ ጰራቅሊጦስን፣ በመንፈስ ቅዱስ እንድሰክር………….
እንዲህ እያሉ የሚወርዱ የሁለቱ ባለቅኔዎች መማለል በአንክሮ ለተመለከተ አንዳች መመሳሰልና መሳሳብ እንዳለባቸው ያመላክታሉ።
እንደ መሰብሰቢያ
ሃሳባችንን ስንሰበስበው አያ ሙሌና ታጉር አምላካችን ከሚሉት አካል ላይ ሆነው ጽንፈዓለሙን የሚጋተሩ ባለቅኔዎች ነበሩ። ከዚህ ውጪ ሌላ ሃሳብ አልነበራቸውም ማለት አይደለም። ግን ነፍሳቸውን ለአንዳች ሃይል ለማድረስ የሚሳቡ የጥበብ ፈርጦች እንጂ።
በእርግጥ ለታጉር ይሄ መንፈሳዊነቱ የተጫናቸው ግጥሞች የኋላ ኋላ ትችትን አምጥተውበታል። ታላቁ አየርላንዳዊው ገጣሚ፣ ጸሐፊ ተውኔትና ፖለቲከኛ ዊሊያም በትለር የትስ (William Butler Yeats 1865–1939) የቀድሞ ውዳሴውንና አድናቆቱን ረስቶ ብዕሩን ሲያስነሳበት ጥቂት ዓመታት ነው የፈጁበት። እንደሚታወቀው የጊታንጃሊ የግጥም ስብስቦችን መግቢያ የጻፈለት ይሄው የትስ ነበርና ነው። ለዚህ ወቀሳው ደግሞ መነሻው “ብዙ ግጥሞች ህግጋተ ግጥምን ያልተከተሉ ዝርው ስንኞች ሆነው ሳለ ሃሳቡ ከአንድ ሃይማኖታዊ ጉዳይ አልወጣም” የሚል ነበር።
እነዚህን መንፈሳዊ መመሰጥ ወይም ተማልሎ የተጫናቸውን ግጥሞች ለመረዳት አንድም መንፈሳዊነትን ልምምድ ማድረግ ይጠይቃል። የአንድ ቤተ እምነት ምሰሶዎችና ዲበ አካላዊ (metaphysics) የህይወት፣ ሞትና ዘለዓለማዊነት ትርጓሜዎች ማዎቅ ግድ ይላል። ከእነዚህ መሰረቶች ውጭ ሆነን ስናያቸው ግጥማቸው ከአንዳች ልመናና የሃሳብ ድረታ የተሻገረ እውነት እንደያዙ ለመረዳት እንቸገራለን።
የአያ ሙሌ ግጥሞችም ሆኑ የታጉር ቅኔዎች መዳረሻቸው የሰውን ህይወትና አኗኗር ማሰስ ነው። በዚህ ማሰስ ላይ አንዳች ልዕለ ፍጡር ይመራናል ብለው ያስባሉ። እናም ስጋዊ ፍላጎታቸውን ወደ መሸሽ ያዘግማሉ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም አያ ሙሌ ልጅና ትዳሩን በትኖ ወደ ጎዳና የዘመተው።
በአንድ ወቅት ግጥም ለመጻፍ ምን ያስፈልጋል? ተብሎ አልቤ ሾው ላይ ሲጠየቅ የመለሰው መልስ አንድና አንድ ነው። እንባ! የሚል ነበር። “ካለቀሰው ጋር ስታለቅስ፣ እርቦ ነጠላ ለብሶ፣ ንጣይ እንጀራ ቀምሶ ከሚውለው ጋር አብረህ ሆነህ ህመሙን ስትረዳው ገጣሚ መሆን አይከብድህም“ ይላል።
በሌላ ቦታም “ግጥም ለመጻፍ ስትሞክር ብዕርና ወረቀትህን ይዘህ ወደ ቀራንዮ ተመልከት። ወልድ ራሱ ይጽፈዋል “ብሎ እንደነገረው እንዳለጌታ ከበደ (Ph.D) ሲናገር መስማቱን የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ምስክር ነው። ከዚህ የምንረዳው ህይወት በአንዳች ህመም የምታልፍ ከንቱ መብሰክሰክ ናትና በዚህ መቃተት ውስጥ የሰውን ህመም መፈከር የከያኒ አይነተኛ መሳሪያ ነው ማለት ነው።
በዚያው በሃምሌ 1992 ከፈርጥ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ እንዲህ የሚል ሃሳብ አክሏል። “ገጣሚ የሚለውን የሚሰማ መንግስት ብቻ ነዉ በትክክል ማስተዳደር የሚችለዉ። ሰው የሆነ ገጣሚ ካገኜ ነው ታዲያ። መጀመሪያ ገጣሚው ሰው መሆን አለበት። Because the poet is the people ግን he is the people. Because he is the language. Has the best access to many members of the society better than anybody else. አሪፍ አሪፍ wayዎች ካሉ ልናመላክታቸው እንችላለን።” ይላል ቃል በቃል።
ይሄ ነው ባለቅኔ ማለት። በመቃተትና በአንዳች መማለል ውስጥ ሆኖ ሰው የሚባለውን ግዙፍ ፍጡር እንደ አርማ የሚያውለበልብ። በእነዚህ በሁለቱ ገጣሚዎች ውስጥ ያለው መማለል መጨረሻው የሰው ልጅና መለኮት ነው። ነገር ግን እንዲህ አይነት ገጣሚዎችን ሳንረዳቸው ያልፋሉ። ትክክለኛ ገጣሚዎች መለኮት የሚልካቸው ሃዋርያቶቹ ናቸው። እነሱን የሚሰማ ህዝብና ዓለም ይድናል። በብላሽ የሚያያቸውን ግን ታዝበውት ያልፋሉ።
በተለይ በዚህ ሸቀጤ ማህበረሰብ (consumer society) ከስጋ እየሸሹ ወደ ሰው ልጅ ልብ እየጠለቁ የሚማልሉ ገጣሚዎች ተደማጭነታቸው ምንም ነው። ለዚህ አይደል አያ ሙሌ እኒያን ሁሉ ቅኔዎች አንዝቦልን ከአንዳች ብናኝ ካፊያ እኩል የምናየው።
በመጨረሻም በ Misha Kandhari አባባል ሃሳባችንን እንዝጋ።
“When material interests dominate the life of the people the poet is generally undervalued. He is apt or be regard as an unpractical, or even an eccentric and valueless member of the society”
ባለቅኔን የሚያዳምጥ እዝነ ልብ ያድለን እያልን የተማልሎ ዳሰሳችንን አበቃን።