ከ”ውስጠት” የግጥም መድብል አንጻር!
ውብአረገ አድምጥ
በቃል ድጋም ሲጀመር—–
ዓለም የቆመችው በቃላት ኃይል ነው ይባላል። መጀመሪያ ቃል ነበር እንዲል ታላቁ መጽሐፍም። ቃላት ኃይል አላቸው። ቃላት ሲደጋገሙ አንዳች ጉልበታም መንፈስን ያሰርጻሉ። ለዚህም ነው ሁሉም ነገር በቃል የሚሰራው።
በተለይ በቤተ እምነቶች ዘንድ የቃላት ኃይል በደንብ አጽንኦት ይሰጥበታል። ከጸሎት ይጀምራል። ብዙ ጸሎቶች በቃል ይደረሳሉ። በቃል ከመደረስ ባሻገርም እንዲደጋገሙ ህጋቸው ያዝዛል። ጸሎትስ ተደገመ አይደል የሚባለው።
በኦርቶዶክስ ክርስትና አስተምህሮ በቀን ሰባት ጊዜ ጸሎት ይደገም ዘንድ ይደነግጋል። እያንዳንዱ ሰዓታት የየራሳቸው ትርጉም ቢኖራቸውም ጉዳያችን እሱ ስላልሆነ ከድጋም (Repetition) ጋር የሚያያዘውን እንመልከት።
በቀን ሰባት ጊዜ መጸለዩ በራሱ ድግግሞሽ ነው። በእነዚህ የተወሰኑ ሰዓታት ላይ ደግሞ እንደ መዝሙረ ዳዊት፥ የዘወትር ጸሎት፥ ውዳሴ ማርያም፥ አርጋኖን የመሳሰሉት ጸሎቶች ይደገማሉ። በዚህ መደጋገም ውስጥ ከመለኮት እንደርሳለን፥ ልመናችም ይሰማል ተብሎ ይታመናል።
ምዕመናን አስራ ሁለት ጊዜ እግዚኦ መኃረነ ክርስቶስ ይላሉ። በእንተ እግዝእትነ ማርያም መኃረነ ክርስቶስ ተብሎም ይደገማል። ኪርያላይሶን እየተባለም ድግግሞሹ ይቀጥላል። መነኮሳት በመቁጠሪያቸው ዙር እየተሽከረከሩ ኤሎሄ እያሉ ቃላትንና ስሞችን በመደጋገም ጸሎታቸውን ያደርሳሉ። ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ኪዳኑ ሁሉ የቃላት መደጋገምን ይፈቅዳል።
በእስልምና ሃይማኖት ዘንድም ይሄ መደጋገም አለ።
ቢስሚላሂ አል አረህማን አል ረሂም
አልሀምዱ ሊላሂ ረቢል አለሚን
አል ረህማን አል ረሂም
ማሊክ የውሚዲን
ኢያከ ናእቡዱ ወኢያ ከነስተኢን
ኢህዲነ አል ሲራጠል ሙስተቂም
ሲራጠ አል ለዚነ አንአምተ አለይሂም ገይሪል መግዱቢ አለይሂም ወለ ዳሊን አሚን
እያሉ በቀን አስራ ሰባት ጊዜ ወደ አላህ ጸሎታቸውን ያቀርባሉ። ያውም በዜማ። ደስ በሚል ጥዑም ዜማ!
ከሃይማኖቶች ተሻግረን ወደ አስማትና ድግምት ከሚሰሩት መናፍስት ጠሪዎች ዘንድም ብንሄድ ተመሳሳይ ነገር እናገኛለን። ቃላት በመደጋገም ሃረጋትን ደጋግሞ በማነብነብ አንዳች መንፈሳዊ ኃይልን ይቀዳጃሉ። እርኩስም ይሁን ቅዱስ ድርጊቶችንም ሲፈጽሙ ይታያል።
ለዚህ ነው K. Chandrasekhara Rao እንዲህ የሚለው። Learning anything by heart through repetition gives a sort of command over it. People often repeat phrases that they think important in their conversations or public speeches. Poetry is more akin to magic, prayer, prophecy and myth than a skill to perform mechanical task.
ለዚህ ሁሉ መሰረቶቹ ቃላት ሲሆኑ ድርጊቱ ደግሞ የተመረጡትን መደጋገም ነው። በመደጋገም ውስጥ ውበትን፣ ስሜትን፣ እውነትን ማስረጽ ይቻላል ተብሎ ይታመናል።
ራመድ ወደ ግጥም—–
በግጥም ዘንድም ይሄ ድግግሞሽ አለ። በእንግሊዝኛው Syntactical Repetition ይባላል። እኔም መዝገበ ቃላቶችን አጋለብጬ ስሜቱን ይገልጥልኛል ባልሁት መሰረት አገባባዊ ድጋም ስል ሰይሜዋለሁ።
አገባባዊ ድጋም ማለት በግጥም ውስጥ ድምጸትን፣ ፊደላትን፣ ቃላትን፣ሀረጋትን፥ ስንኞችን ወይም አርኬዎችን በመደጋገም አንድን እውነት ወይም ስሜት የማስረገጥ ሂደት ነው። በእንግሊዝኛ ግጥም ውስጥ ይሄንን ድግግም በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፍሉታል።
እነሱም Repetitions of sounds (የድምጸት ድግግሞሽ) እና Repetition of words, or phrases, lines and stanzas[1] (የቃላት፥ የሃረጋት፥ የስንኞች እንዲሁም የአርኬ ድግግሞሽ) ብለው ይከፍሏቸዋል። በውስጣቸውም ብዙ ክፍፍሎችን እየሰጡ ግጥማቸውን ይተነትናሉ። ለዚህ ጽሑፋችን መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ጠቀስ አድርገን እንለፍ።
በድምጸታቸው ወይም በምታቸው (Rhyme) ድግግሞሽን ከሚያሳዩ ግጥሞች ውስጥ እንደ ምሳሌ ከኢድጋር አለን ፖ (EDGAR ALLAN POE) The Raven ግጥም ውስጥ የመጀመሪያውን ስንኝ ማየት እንችላለን።
Once upon a midnight dreary, while I pondered, weak and weary[2]
ከኮለሪጅ ረጅም ግጥም ውስጥም አንድ ምሳሌ ብንደግምስ።
In mist or cloud or mast or shroud[3]
የቃላት ድግግሞሽ ከሚታይባቸው ግጥሞች ውስጥ ከጆን ሚልተን ግጥም ውስጥ ለቅምሻ እንመልከት።
“For Lycidas is dead, dead ere his prime,
Young Lycidas and hath not left his peer.”[4]
እንዲሁም
The years to come seemed waste of breath, / A waste of breath the years behind”[5]
የሐረግ ድግግሞሽን በምሳሌ ለማየት ያህል ከዊሊያም ሸክስፒር ኦቴሎ ላይ እንምዘዝ።
“Put money in thy purse; follow thou the wars; defeat thy favor with
an usurped beard; I say, put money in thy purse. It
cannot be that Desdemona should long continue her
love to the Moor–put money in thy purse–nor he
his to her:[6]
ለምሳሌ ያህል ከላይ ያሉትን ግጥሞች አየን እንጂ እጅግ ብዙ ገጣሚዎች ይሄን አገባባዊ ድጋም በግጥማቸው ውስጥ ይጠቀሙታል። በዚህም የግጥም ቴክኒክ ማድረስ የሚፈልጉትን ስሜት ማጋባት ይችላሉ።
አገባባዊ ድጋም (Syntactical Repetition)
ለመሆኑ ይሄ አገባባዊ ድጋም (Syntactical Repetition) ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ የተለያዩ የስነ ጽሑፍ ሰዎች በተረዱት ልክ ትርጓሜ ሰጥተውታል።
መምህርና ገጣሚ ቴዎዶር ሮትኪ (Theodore Roethke) “Some Remarks on Rhythm” (1960), በሚለው መጣጥፉ ስለ ድጋም እንዲህ ይላል። “Repetition is in fact “the very essence of poetry.” Arguably, you can write a poem without repeating a single word or rhyme scheme or phrase, and call it a poem, but in that instance, you may find people in fact mistake your poetry for prose”.
ግጥምን ያለምንም ድጋም መጻፍ እንደማንችል አስረግጦ ያስገነዝበናል። ቢያንስ ቢያንስ ከግጥም ባህርያት ውስጥ አንደኛው የሆነውን ሙዚቃዊነትን ወይም ዜማዊነትን መልቀቅ እንደማንችል ሲነግረን ነው። በየትኛውም ግጥም ውስጥ የቤት መምታትና ቤት መድፋት እስካለ ድረስ የድምጽ መደጋገም የማይቀር ነው። በእኛ የአማርኛ ግጥም ውስጥም ያለ ምት ወይም ያለ ቤት መምቻና ቤት መድፊያ የተጻፈ ግጥም ግጥም ተብሎ ለመጠራት ይቸግራል።
አያ ሙሌ
እኔን ካበቀለ አፈርና ውሃ
እንዴት ቀለብ ነፍጎ ያደርገናል ድሃ?[7]
ብሎ ሲቀኝ በስንኙ መጨረሻ ላይ ባሉ ተመሳሳይ ሃ ፊደላት ውስጥ አ የሚል ሙዚቃዊ ድምጸት አለ።እነዚህ ሁለት ስንኞች አንዳች ውበትን ለመጎናጸፍና ግጥም ለመሰኘት የቃል ወይም የድምጸት ወይም ደግሞ የፊደላት ተመሳስሎት በቤት መድፊያውና በቤት መምቻው ላይ መኖር አለበት። ለዚህ ነው ከላይ ድግግሞሽ የግድ ነው ማለቱ።
ከላይ የጠቀስነው ቻንድራስካራም Repetition is a rhetorical device. But it should not be studied as only a technique. It has psychological implications[8] ማለቱ።
ምክንያቱን ግጥማዊ ድግግሞሽን እንደ አንድ ቴክኒክ ብቻ የምንማረው ሳይሆን ስነልቦናዊ ተጽእኖም ለማሳደር ሲባል ተግባራዊ የሚደረግ በመሆኑ ነው። በስነጽሑፍ ላይም ተግባራዊ ለማድረግ ከፍ ያለ ምክንያትና ችሎታ የሚጠይቀው ይሄ ጠጣርነቱ ግድ ስለሚለው ነው።
ቻንድራስካራ “Repetition of all kinds necessitates the arrangement of words and lines in a pattern that creates a structure. This structure in turn makes the poem an object of aesthetic appreciation. Repetition draws the attention of the reader to the language itself. It provides ‘literariness’ to the text there by making it different from ordinary speech[9]. ሲልም ያክላል።
[1] The Significance of Repetition in Poetry by K. Chandrasekhara Rao Seminar Paper
[2] Public domain. First published by Wiley and Putnam, 1845, in The Raven and Other Poems by Edgar Allan Poe.
[3] The Ancient Mariner, by S.T Coleridge
[4] (Lycidas, John Milton
[5] William Butler Yeats “An Irish Airman Foresees His Death
[6] Iago in William Shakespeare’s Othello, Act 1, scene 3
[7] እኔ መዩ
ወርቅ እዮቤልዩ ሙሉጌታ ተስፋዬ- የነቢያት ጉባኤ።
[8] The Significance of Repetition in Poetry by K. Chandrasekhara Rao Seminar Paper
[9] ibid
ውስጠት
ውስጠት ከገጣሚና መምህር እንዲሁም ፎክሎርስት ሠይፉ መታፈሪያ ፍሬው[1] ግጥሞች ውስጥ አንዷ ናት። በሃገራችን ከታተሙ ምርጥ የግጥም መድብሎች ውስጥ አንደኛዋ ናት ቢሉ ማጋነን አይሆንም። በአጻጻፍ ይትባህሏም ይሁን በግጥማዊ ቅርጽ የራሷ የሆኑ ቀለሞች አሏት ።
አገባባዊ ድጋምን ከውስጠት የግጥም መድብል አንጻር በሶስት ዋና ዋና ዘርፎች ከፋፍለን ለማየት እንሞክራለን። ይሄም ማለት ገጣሚው አገባባዊ ድጋምን ለምን ዓላማ ተጠቀመው? ምንን አጽንኦት ለመስጠት መሳሪያ አደረገው የሚለውን ለመፈከር እንሞክራለን።
ከላይ የተጠቀሱት በውስጠት ላይ ተግባራዊ የተደረጉት ሶስቱ የአገባባዊ ድጋም ተልዕኮዎች አንክሮ፤ ውስጠት እና ሂደት ናቸው። አንድ በአንድ እንዴት ከግጥሙ አንጻር እንደተጠቀሟቸው እንይ።
[1] በቀድሞ ተማሪዎቻቸው ዘንድ አብዬ ሰይፉ እየተባሉ ይጠራሉ። ወደ ስድስት የግጥም መድብሎችን ያሳተሙና ወደ ሶስት የሚጠጉ ያልታተሙ የግጥም መድብሎችን አዘጋጅተዋል፣ የቋንቋ ሊቅ፣ ገጣሚ፣ ሃያሲ፣ የፎክሎር ተመራማሪና ለረጅም ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በቋንቋ መምህርነት ያገለገሉ ረዳት ፕሮፌሰር ነበሩ። በካርቱም ዩኒቨርሲቲ የእስያና አፍሪካ ጥናት ተቋም ውስጥ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የፎክሎር ተመራቂ ናቸው፣ የማስተርስ ዲግሪያቸው የሰሩት እዚያው ነው። በኋላም በ1984 ከተባረሩ 42 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ውስጥ አንዱ ናቸው። በስደት በሚኖሩበት አሜሪካ ህይወታቸው ካለፈ ጥቅምት ሁለት ዓመት አለፈው። (ምንጭ- ታናሽ ወንድማቸው ብርጋዴር ጄኔራል መስፍን ኃይሌ፥ የቀድሞ ተማሪያቸውና በጀርመን የሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና ኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል የፎክሎር መምህር ዶ/ር ጌቴ ገላዬ እንዲሁም የቀድሞ ተማሪያቸው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ህዳር 2014 ከዶቼ ቬለ እና ከVOA ጋር ካደረጉት ቃለ መጠይቅ ተቀንጭቦ የተወሰድ)
ሀ/ አንክሮ
አንክሮ ማለት አንድን ጉዳይ ከፍ ያለ ትኩረት የመስጠት ተልዕኮ ነው። አጽንኦት የሚሰጠውን ጉዳይም በኪናዊ ድግግሞሽ ከሰዎች ልቦና ውስጥ ለማድረስ የሚደረግ የቃላት መዋደቅ ነው። ገጣሚው ስል መንፈሳቸውን፣ የቃላት ህያው ሃብታቸውን ተጠቅመው፤ የቃላትን የሃረጋትንና የአገባብን ጉልበት ተመርኩዘው ሊያሰርጹት የሚሹትን የሃሳብ ነጥብ በኃይለ ቃል ተረማምደው ከግብ ያደርሳሉ።
“ሰባ ሰማኒያ”[1] በሚሰኝ ግጥማቸው የእድሜን መገስገስና የትናንትናን የውበት ከፍታ ለመግለጽ በመጀመሪያው አርኬ ላይ እንዲህ ሲሉ ይጀምራሉ።
እንዴት—እንዴት—እንዴት[2]–ሙዋሸሸ፥
አበባ
የሁዋሊት ሁዋሊቱን ሸሸ፥
ውስጠትሽ
ሽብሽብ ብሎ ቀረ፥
ቆዳሽ
የፊትሽ
እንዲያ ሙሉ የነበር እንዲያ ሙሉ፥
የልጅነትሽ ጸዳልሽ፤
–
–
–
እያለ ቁልቁል በሚወርደው ግጥም ውስጥ እንዴት፥ ሁዋሊት፥ እንዲያ ሙሉ የሚሉ ቃላትንና ሃረጋትን እየደጋገሙ የትናንትንና የዛሬን ንጽረት በአንክሮ ልዩነቱን ቁልጭ አድርገው ለማሳየት ይሞክራሉ። የሴትነት ውበት ለልጅ በሚከፈል ህያው ወሮታ ውስጥ ሙሽሽ ብሎ እንደሚቀር አጉልቶ ለማሳየት አገባባዊ ድጋምን ከአንክሮ አንጻር ተጠቅመውታል።
ብዙ አገባባዊ ድጋም በሚታይበትና “የህይወት ፍጥርቅታ”[3] የሚል ርዕስ ባለው ግጥማቸው ውስጥ በአምስተኛው አርኬ እንዲህ ይላሉ።
እና የኔውም ይሄ ነው
ይሄው ነው ዶሴዬ ይሄ ነው
ገላጭ ዳኛ እማይገኝለት
ይሄ ነው ክሴ ይሄ ነው፥
የሚሊዮና ሚሊየን ዓመታት ቅርሴ
ሰብአዊ አባዜ
በባዶ ሜዳ ባዶ ሜዳ ትካዜ።
–
–
–
የህይወትን በተቃራኒ ኃይሎች ውስጥ ገብቶ መላተምና መፈጥረቅ ይሄ ነው እያሉ በተደጋጋሚ አስረግጠው ያሳያሉ። ተደራሲም በቃላት ጉልበት ተመክቶ ሊያሳዩት ወደሚሹት የህይወት እውነታ እንዲንጠራራና እንዲደርስላቸው ውብ ቃላትን እየደጋገሙ ይዋደቃሉ።
“ከስፍር ባሻገር”[4] በሚለው ሌላው ግጥማቸውም የውበትን አይሰፈሬነት አደግድገው ያመሰጥራሉ።
ያበቦች ቀለማምነት ያበቦች፥
ችቦ ድምቀት
ውበት
እሱ ውበት ነው እሱ ውበት
በእፍኝ የማይሰፈር፥
እማይመተር
በስንዝር እማይለካ
እማይነካ፤
–
–
–
እያለ በሚወርደው ግጥማቸው የአበቦችን ውበት ከምንም ስፍር ወጥተን እንድናይላቸው ይማጸናሉ። እሱ ውበት ነው እንጂ ሌላ አይደለም እያለ የሚጠቁምን ታላቅ የቅኔ መምህር ይመስላሉ። አፉን እንዳልፈታ ልጅና፥ ልጁን ደግሞ ንግግር እንደሚያስተምር አባት እየደጋገሙ እሱ ውበት ነው ማለታቸው አንድም ከስሜታቸው እንደርስ ዘንድ፤ አንድም ደግሞ ኪኑ በፈጠረላቸው የድግግሞሽ ህግ አስረግጠው እውነቱን እንካችሁ ማለታቸው ነው። የዚህንም ገፊ ምክንያታቸውን ዝቅ ብለው አይሰፈሬነቱን፥ አይመተሬነቱን አጉልተው አሳይተውናል።
[1] (ገጽ 17-18)
[2] አጽንኦት የእኔ
[3] (ገጽ 21-23)
[4] (ገጽ 51)
ለ/ ውስጠት
ውስጠት የግጥም መድብሉ መጠሪያ ስም ነው። ለዚህም መግቢያቸው ላይ “ርዕሱን አስመልክቶ” በሚል ቀዳሚ ቃላቸው ላይ አንዳንድ ነገሮች አንስተዋል። ከዚህም ውስጥ ለዚህ ጽሑፍ የሚያስፈልገንን ጠቅሰን ወደ ዋና ጉዳያችን እንለፍ።
ውስጠት ማለት “ወሰጠ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ነው። ትርጉሙም በውስጥ መሆን፥ ወደ ውስጥ መግባት፥ መክበብ፥መካከል ማለት እንደሆነ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ይነግረናል።
ውስጠትም የአንድ ነገር በአንዱ ውስጥ መሆንን ይወክላል ይላሉ። ለምሳሌ ጠላና አንኮላን ብንወስድ የጠላው በአንኮላው ውስጥ መሆንና፥ አንኮላው ደግሞ ጠላውን በውስጡ መያዝ ውስጠት ይባላል ይላሉ።
ከዚህም በመነሳት የአንዱን በአንዱ ውስጥ ተወሳስጦ መኖርን በግጥማቸው ውስጥ በአገባባዊ ድጋም መልክ እንዴት እንደተጠቀሙበት መፈተሽ እንችላለን።
“ተፈጥሮ ብልጠቱዋ”[1] በሚለው ግጥማቸው የመጀመሪያው አርኬ እንዲህ ይላሉ።
አንዱም፥ አንዱም፥ አንዱም፥ አንዱም
የነጠላዎች ድግምግም
ተዳምሮ
ከምርምር ቃላት አካል ቀምሮ
የተፈጥሮ፥ ተፈጥሮ፥ ተፈጥሮ
–
–
–
እያለ ይወድርዳል።
በዚህ ግጥማቸው ውስጥ “የውስጠትን” ጽንሰ ሃሳብ በተፈጥሮ መካከል እንዴት እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል። አንዱ ነጠላ ዘአካል በራሱ የቆመ ሆኖ ከሌሎች ጋር ያለውን መዛመድና መጋመድ ያመላክታሉ። ከፍ ሲልም የተፈጥሮን ትስስሮሽ ከምላተ አካል ቁመና ጋር እያሰናሰሉ ይቀኛሉ። በዚሁ ግጥም ዝቅ ብለው በሁለተኛው አርኬ እንዲህ ያክላሉ።
ተዳምሮዎቹዋ እና
ተካቶዎቹዋ
የጽንስ፥ ጽንስ፥ ጽንሶችዋ[2]
ይላል።
ታላቁን ተፈጥሮ እንደ አክንባሎ ከላይ ደፍተው የፍጥረታትን ተደማሪነትና ተፈጥሮ ለሚባለው ግዙፍ ሰውነት የእኛን ጽንስነት በውስጥ ለውስጥ እንደ ድር ዘሃ ያያይዙታል። ለዚህም እንደ ዋና መሳሪያ የሚተቀሙት ቃላትንና ሃረጋትን ደጋግሞ መጠቀምን ነው። ተሳክቶላቸዋልም።
[1] (ገጽ 18-25)
[2] ዝኒ ከማሁ
ሐ/ ሂደት
ሌላው በውስጠት የግጥም መድብል ውስጥ አገባባዊ ድጋምን ገጣሚው አጥብቀው የተጠቀሙት ሂደትን ለማመከት ነው። የነገሮችን በጊዜ ሃዲድ ላይ ያለ’ መትመም ለመግለጽ፤ የተፈጥሮን በሰዓት ሰረገላ መነፍላሰስን ለማንጸር፥ የገጠመኞችን ወይም የሁነትን ሂያጅነትና ተራማጅነት ለማንጸር በቃላት ሲጠበቡ ይታያል። እንዲሁም የነገሮችን የቅጥልጥሎሽ አንድምታ ለማጉላት በእጅጉ ተክነውበታል። እንዲያውም አገባባዊ ድጋምን ያዘወተሩት የክዋኔዎችን ሂደት ለመግለጽ ነው ማለት እንችላለን። በብዛትም ይሁን በተደጋጋሚነት ከሌሎች በበለጠ ሂደትን ወካይ ሆኖ ቀርቧል።
“ልጃገረድ”[1] በሚለው ግጥማቸው የልጃገረዷን የእርምጃ ስልት በሙዚቃ ቅኝት መስለው እንዲህ ተቀኝተዋል።
በንጃልሽ እንጃልሽ ጠባቸው፥
ስትሄደው
ድምጻቸው
አለንም—የለንም!
አለንም—የለንም!
አለንም—የለንም!
አለንም—የለንም!
——–
ምስኪን ልጃገረድ
ሴት ልጅ ሆኖ መወለድ
–
–
–
ይላሉ።
እዚህ ግጥም ላይ የሰራ አካላቷ እንጃልሽ እንጃልሽ እየተባባሉ የእርምጃዋን ስልተ ምት ተከትለው ሲያረግዱ በዓይነ ህሊናችን መሣሉ አይቀርም።
አለንም የለንም እያሉ የሚወርዱ ስንኞች የልጃገረዷን ቁመናና ተውረግራጊ አረማመድ ቁልጭ አድርገው ያስቀምጣሉ። ይሄ መውረግረግ ደግሞ ሂደትን የተከተለ መሆኑን ለማሳየት አገባባዊ ድጋምን ዋና መሳሪያቸው አድርገው መጠቀማቸው ውስጠ ሃሳባቸውን ግዘፍ ነስቶ ለአንባቢ እንዲደርስ አድርጎላቸዋል።
“የፒያኖ ላይ ምጥ”[2] በሚል ርዕስ በከተቡት ሌላ ግጥማቸው ላይ የፒያኖውን ቁልፎች እየተከተለ የሚነጉደውን ተስረቅራቂ የድምጽ ፍሰት እንዲህ ያመሰጥሩታል።
“ድን” እየመለሰ፣ እየመለሰ “ድን”
“ድን-ድን”፥ ድን እና ድን
አንዲቱዋን ኖታ ብቻ
መባቻ
መጣሁ–መጣሁ ለሚለው ዜማ መክፈቻ”
–
–
–
እያለ ይወርዳል።
ይሄ የድንድንታ ቅጥልጥሎሽ ከከያኒው ምናብ ተተርትሮ ለሚወጣው ዜማ በር መክፈቻ ነው። ሂደቱ እስከ ተቀመረ ዜማ ድረስ-ዜማው እስከ ዘለዓለማዊ የፍጡራን ነፍስ ድረስ መሻገር ነው። በዚህ ድን ድን ውስጥ ዘለዓለምን የሚያህል የድምጸት መንገድ አለ። በእሱ መንገድ ተራምዶ ነው ከተሸመነ የዜማ ልባስ መድረስ የሚቻለው። ድን ድንታውን በድጋም ቀምሮ ሊል የሚሻውን የመንፈስ ፍልቅቅታ ማድረሱ እሙን ነውና አጃይብ ብለን እንሻገር።
“የፍጻሜው ባላደራ”[3] በሚለው የሟችንና የቀባሪን ጉዞ በተቀኑበት ተጓዥ ግጥማቸው የግጥምን አገባባዊ ድጋም እንዲህ ተጠቅመውታል።
ጌታ ሞት እፊት—እፊት–እፊት–እፊት
ሁዋላ ሁዋላው የቀባሪው ትመት
ረመድመድ—ረመድመድ
ረመድመድ—ረመድመድ
–
–
–
እያለ ይወርዳል።
በዚህ ግጥም ላይ አንዳች እንደ ገብረ ጉንዳን ተያይዞ የሚጥመለመልን የሰዎች ጉዞ በምናባችን ቁልጭ አድርጎ እንዲቀረጽ ያደርገዋል። ከዚህ የቀባሪ ረገዳ ሂደትን በድግግሞሽ መግለጽ የሚችል ኪናዊ ውበት መፍጠር መቻል የግጥም መሰጠትን ይጠይቃል።
በተመሳሳይ “ያንድ አቅጣጫ ጩኸት”[4] በሚለው ግጥም ላይም መሰል የሂደት አገባባዊ ድግግሞሽ ይገኛል።
ዝቅ ወደ ታች–ታች–እታች—ዝቅ
ዝቅዝቅ
እኩል ለኩሉን ታጥፎ
እና ካፈር አላክፎ
–
እያለ ይቀጥላል።
ሌላም “እርካታ”[5] በሚሰኝ ግጥም ላይ መሰል ሂደት በግልጽ ይታያል።
እየቀጠነ ሄደ እየቀጠነ
ጭብጥ እየመጠነ
ውፍረቱ
እየተወረደደ ቅርፊቱ
እየሰለለ ክርክራቱ
ግንድ ንጣቱ
ቀቅ–ቀቅ–ቀቅ
እና ው–ድ–ቅ
ዘፍ ግርስስ–ተገረሰሰ
–
–
ይቀጥላል
ይሄ የአንድ እድሜያማ የዛፍ መቆረጥን ሂደት የሚያሳይ የሚመስል ግጥም፤ የዛፉ ግንድ በመጥረቢያ እየተቦደሰ፤ ግንዱም እየቀጠነ መሄዱን ግሩም በሆነ አገባባዊ ድጋም ያሳያል። ይሄ አይዛፍ መቁረጥና የግንድ እየተቀረደደ መሄድ ከተራ ግድን ቆረጣ ባሻገር የቆራጭንና የተቆራጭን እጣ ፋንታ የሚፈክር መሆኑ እሙን ነው። እሱንም ተምሳሌታዊ በሆነ መልኩ እንዲህ ሲገለጽ ደስ ያሰኛል።
እንዲሁም “ምርጫ ያለው ይመስል”[6] በሚለው ግጥም ውስጥ እንዲህ የሚሉ ስንኞች አሉ።
እራሱ –ከራሱ ጋራ-ራሱ ጋራ የያዘ መስሎ
ሙግት
ግራ ቀኝ አያይ ግራ ቀኝ
አይገላመጥ
ውደ ሁዋላው አይመለከት
ወደ ፊት–ፊቱ ብቻ ወደ ፊት ፊቱ
ሁዋላ ሁዋላው ፍየል፤ ፍየል ሁዋላ ሁዋላው
ታብቶበት
በሆነ ስበት
ገመድ
ታች እየነዳለት ዘመድ
በንዲያ-ንዲያ ሄዱ፤ ሄዱ በንዲያ ንዲያ
ተያይዘው
–
–
እያለ ይወርዳል።
ይሄ ግጥም የአንድን ፍየልና የአራጅን ጉዞ ምስል ከሳች በሆነ መልኩ የሚያሳይ ግጥም ነው። ታራጅ መታረዱን ሳያውቅ በገመድ ተይዞ የሚያደርገውን ወደ ሞት ግስጋሴና መፋጠን፣ የአራጅንም የሆዱን በሆዱ ይዞ ፍየሉን በገምድ አስሮ መብከንከን ያስቃኘናል። የግጥሙ ሃሳብ ከፍየልና አራጅ ግንኙነት ባሻገር የሚንጠራራ የፍጥረዓለማትን የህይወት መልክ የሚፈክር አንዳች የሂደት ትዕይንት ነው።
[1] (ገጽ32-34)
[2] (ገጽ-36)
[3] (ገጽ 42-45)
[4] (ገጽ-58)
[5] (ገጽ 60)
[6] (ገጽ 64)
ሲጠቀለል
ከላይ በዘረዘርናቸው ግጥሞች ለማየት እንደሞከርነው ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬ የግጥም አገባባዊ ድጋም በመባል የሚታወቀውን አንድ የአገጣጠም ዘዴ ተጠቅመው ሃሳባቸውን ከዳር አድርሰዋል።
ቃላት እየደረቱ አንዳች ድምጸትን ከመፍጠር ባለፈ ታላቅ ሰዋዊ ብሎም ባለቅኔያዊ ተልዕኮን እንደተሸከመ ባለሟል ጉዟቸውን ከዳር አድርሰዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
እንደ ምሳሌ ውስጠት የግጥም መድብላቸውን ተመለከትን እንጂ በሌሎች የእሳቸው የግጥም መድብሎችም ይሁን በሌሎች የሃገራችን ገጣሚዎች የግጥም ስራዎች ውስጥ መሰል ቴክኒኮችና ተልዕኮዎች እንዳሉ እሙን ነው። እኛም ይሄንን እንደ መንደርደሪያ ተመልክተን ቀሪዎቹን የግጥም ስራዎች በተለያየ አረዳድ እያየን ህያው ስራቸውን እንድንመሰክር እያሳሰብሁ በቻንድራስካራ መደምደሚያ ልሰናበት።
The aura that is created by the usage of repetition cannot be achieved through any other device. It has the ability of making a simple sentence sound like a dramatic one. It enhances the beauty of a sentence and stresses on the point of main significance. Repetition often uses word associations to express the ideas and emotions in an indirect manner.[1]
[1] The Significance of Repetition in Poetry by K. Chandrasekhara Rao Seminar Paper
[1] አገባብ- የቅኔ፥ የሰዋስው፥ አገባብ፤ በስም ላይ በነባር አንቀጽ፤በዘማች አንቀጽ ላይ እየገባ ማሰሪያነት የሚያስለቅቅ አገባብ (መስተዋድድ) ይባላል። (ከሣቴ-ብርሃን ተሰማ፤ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ከተሰማ ሀብተሚካኤል ግጽው ተደርሶ የተጻፈ 2011ዓ/ም፥ ገጽ 811)
[2] ድጋም – በቁሙ መድገም፥ መደጋገም፥ድገማ፥ ድግሚት ፥ ጸሎት። ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወ ግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ 2ኛ እትም 2013 ዓ/ም፣ ገጽ 339)